(የመጀመሪያ ክፍል)
አሁን አሁን በፖለቲካው ተወስደን/obsessed/ ሆነን ፤ ሁላችንም ፖለቲከኛና ተንታኝ ሆነን አረፍነው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ኪነ ጥበባዊ ጉዳዩን እርግፍ አድርገን ትተነዋል። አየሩንና መልካውን የሴራ ትንተናና የደባ ስለቃ ተቆጣጥሮታል። ለዛሬ ለለውጥ ያህል ሳይንስ ላይ ጫጭሬያለሁ። ወደፊትም ከአገራዊ ጉዳዮች መሳ ለመሳ ወቅታዊ ዓለምአቀፍ ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ። አበው እመው ሰማይን ያለ ባላ፣ ምድርን ያለ ካስማ ያቆምህ የሚል ይትበሀል አላቸው። የፈጣሪን ጥበብና ሁሉን ቻይነት ሲገልጹ።
በአጽናፍ ዓለም /ዩኒቨርስ/ከ200 እስከ 300 ቢሊዮን የሚደርሱ ከዋክብት፤ 2 ትሪሊየን ጋላክሲዎች የሚኖሩ ሲሆን፤ ህላዌአቸው ለምድራችንና ለፍጥረት እንዲመቹ ተደርገው ነው የተፈጠሩት። በፔሬዲክ ቴብል የሚገኙ 118 ንጥረ ነገሮች መጠን እንኳ በተፈጥሮ የተመጠነ ነው ይላሉ በዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በፈጣሪ ህላዌ የሚያምኑ የስነ ፈለግ ወይም የስነ ጠፈር ተመራማሪዎች። የ21ኛው መክዘ ክስተት የሆነው የ«ጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ» /አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር/ይሄን ተአምር ነው ገላልጦ ያሳየን ይላሉ ተመራማሪዎች።
የጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ በሰው ልጆች ታሪክ የአጽናፈ ዓለምን/universe/ወይም የህዋን/space/ ጓዳ ጎድጓዳ ፤ በርብሮና አብጠርጥሮ ጥርት አድርጎ ለዚያውም 13.8 ቢሊዮን አመት ወደኋላ ተመልሶ ያስመለከተ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የ21ኛው መክዘ ክስተት ነው። ለግንባታው 10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የወጣበት ሲሆን፤ ለማጠናቀቅ ደግሞ 30 ዓመታትን ወስዷል።
ከቴሌስኮፑ ግንባታ ጀርባ ያሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ የጠፈር ምርምር (ናሳ) ፣ የአውሮፓና የካናዳ የጠፈር ሊቃውንት ተሳትፈዋል። ሊቃውንቱ ይሄን በዓይነቱ ልዩ ፣ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ቴሌስኮፕ ሠርተው ለማጠናቀቅ አምላካቸው፤ ትዕግስቱን ፣ ጊዜውን እና ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ሲለማመኑ ነበር ይለናል TIME መጽሔት በስላቅ። ይኸው ልመናቸው ተሰምቶ በትዕግስት በጽናት ሦስት አስርት አመታትን ወስዶና ቢሊዮን ዶላሮቹን ፈጅቶ ለስኬት በቅቷል።
ነገሩ ወዲህ ነው በ1996 ዓ.ም የናሳ የስነ ፈለክ/astronomers/ሊቃውንት ኮሚቴ የመጪውን ትውልድ ግዙፍ የህዋ ቴሌስኮፕ ለመገንባት ወሰነ። 13.8 ቢሊዮን አመታትን ወደ ኋላ ተጉዞ ጠፈርን የሚመለከት ቴሌስኮፕ በስምንት አመት ማለትም እስከ 2007 ዓ.ም ለማጠናቀቅ አቅዶ ፣ ሆኖም ከእቅዱ በ22 አመታት ዘግይቶ፤ ከተያዘለት የ500 ሚሊዮን ዶላር በጀት 20 እጥፍ 10 ቢሊዮን ዶላር ጨርሶ በወርሀ ታኅሣሥ 2021 ዓ.ም ተጠናቀቀ። የጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ የጊዜንና የህዋን ርቀት አጥፍቶ ነው ህዋን የሰው ልጆች ዓይን ስር አቅርቦ እያሳየ ዓለምን ዳር እስከዳር ጉድ እያሰኘ ያለው።
ሊቃውንት አጽናፈ ዓለም ከ13.8 ቢሊዮን አመታት በፊት በተከሰተ ትልቅ ፍንዳታ/Big Bang/ ነው የተፈጠረው ብለው ያምናሉ። በአግራሞትና በአድናቆት እጅን በአፍ እያስጫነ ያለው ይህ ቴሌስኮፕ ከዛ ሩቅ ዘመን አንስቶ ነው እንግዲህ፤ በሙቀት ብርሃን ጨረር ታግዞ የሰው ልጅ እስከዛሬ ተመልክቷቸው የማያውቁ አስደናቂ የህዋን ገጽታዎች እያስመለከተ ያለው። ባለፈው ሐምሌ ሜሪላንድ በሚገኘው የናሳ ማዕከል ፤ በጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ የተነሱ አራት ምስሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ፤ ለብዙኃን መገናኛዎች ይፋ ሲሆኑ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ መነጋገሪያ ሆነው ነበር ሲል የTIME መጽሔት ያወሳል ።
የሚያንጸባርቅ በሕብረ ቀለም የተንቆጠቆጠ የአቧራ መሰል ወይም የጭስ ዳመና /nebulae/ ፤ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ልብን በሀሴት የሚሞሉ የከዋክብት ክምችት/galactic clusters/፤ በአጽናፈ ዓለም ከዚህ ቀደም ተደርሶባቸው የማያውቁ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የከዋክብት ክምችትን/SMACS 0723/ የሚያሳዩ ምስሎች ፤ በናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን አማካኝነት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ በተገኙበት በኋይትሀውስ ይፋ ሆነዋል።
ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ፕሬዚዳንት ባይደን ባደረጉት ንግግር፣«እነዚህ አስገራሚ ምስሎች አሜሪካ ዛሬም ፋና ወጊና ትላልቅ ፈጠራዎችን ማከናወን እንደምትችል ለዓለም ያረጋገጡ ናቸው ።» ብለዋል፤ በማስከተለም፣ «ይህ እኛ አሜሪካውያን ማሳካት የማንችለው ምንም ራእይ እንደሌለ ያሳያል። የዌብ ቴሌስኮፕ ደግሞ ፤ የአሜሪካውያንን የማያቋርጥ አስተዋይነት የተሞላበትን የፈጠራ ችሎታ ያረጋግጣል።» በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የዌብ ቴሌስኮፕ እስካሁን እያነሳ የላካቸው የህዋ ምስሎች በራሳቸው ስኬት ከመሆናቸው ባሻገር፤ ከዚህ ቀደም እንደዚህ ያለ ቴሌስኮፕ ተገንብቶ እንደማያውቅም አረጋግጧል። በ1990 ዓ.ም ወደ ህዋ ከመጠቀው ሀበል ቴሌስኮፕ እጅግ የረቀቀ ነው። የዌብ ቴሌስኮፕ ከመሬት 1.6 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቆ ህዋ ላይ የተቀመጠ ስለሆን፤ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ይሠራል። ምህንድስናውና በህዋ ላይ የተቀመጠበት ስፍራ ከሀበል የተለየ ያደርገዋል።
የሀበል ቴሌስኮፕ ከምድራችን 547 ኪሎ ሜትሮችን ርቆ በሚገኝ ምህዋር ላይ ተቀምጦ መሬት በመዞር ህዋን ያስመለክታል። ሀብል በብረት በቱቦ ቅርጽ የተሰራ/ሲሊንደር/ ሲሆን ውስጡ ደግሞ ከአንድ አቅጣጫ የሚገባ ብርሃንን የሚቀበል ኦፕቲክስ አለው። ሀብል ምስሎችን የሚያነሳው በተለመደው አግባብ ማለትም በዓይን የሚታይ ሕብረ ቀለምን/spectrum/ በመጠቀም ነው።
ይህ ማለት መስታወቶች ከፀሐይ፣ ከመሬትና ከሌሎች አካላት ከሚመነጭ አዋኪ ብርሃን መከለል አለባቸው። የሀብል ቴሌስኮፕ የምናየውን ብርሃን ጨረር ሲጠቀም የጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ደግሞ በሙቀት ጨረር የሚመነጨውን ብርሃን /infrared spectrum/፤ በመጠቀም እስከ ዛሬ ተደርሶባቸው የማያውቁ አጽናፍ ዓለማትን ማለትም፤ 13.8 ቢሊዮን አመታትን ወደ ኋላ ተመልሶ ያሳያል። ሀብል ቴሌስኮፕ ግን የምናየውን ብርሃን ስለሚጠቀም የምናየው ብርሃን ደግሞ በህዋ ውስጥ ባለ አቧራና ጭስ መሰል አየር ስለሚጋረድ የዌብን ያህል የማሳየት አቅም የለውም።
የጄምስ ዌብ የህዋ ቴሌስኮፕ 6000 ኪሎ ግራም ሲመዝን፤ ዋናው መስታወቱ ደግሞ 6.5 ሜትር ይረዝማል። ባለ ሰባት ጎን ማዕዘን 18 ክፍሎች ያሉት ቴሌስኮፕ ስለሆነ የጸጉርን አንድ ስልሳ ሺህኛ ወይም የሜትርን አንድ ቢሊየነኛ አቅርቦ የማሳየት አቅም አለው ይላል TIME መጽሔት። የሀብል የህዋ ቴሌስኮፕ ህዋን የሚዞር ፤ የመስታወቱ መጠንም 2.5 ሜትር ስለሆነ የሚያነሳው ምስል ጥራት ከዌብ በ100 እጅ ያንሳል። የዌብን የህዋ ቴሌስኮፕ ከፀሐይ ፣ ከመሬትና ከጨረቃ ሙቀት ለመከላከል የመስታወቱ ማህደር የፀሐይ መከላከያ መሣሪያ ተገጥሞለታል።
የካይት ዓይነት ቅርጽ ያለው ይህ የፀሐይ መከላከያ አምስት ንብርብር ያለው እጅግ ስስ ማለትም ከጸጉር አምስት እጥፍ ብቻ የሚበልጥ መሆኑን መጽሔቱ ያብራራል። ውጫዊ የፀሐይ መከላከያው እስከ 230 ዲግሪ ፋራናይት ወይም 110 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት መከላከል በመቻሉ፤ የቴሌስኮፑን ውስጣዊ ክፍል ከዜሮ በታች በ394 ዲግሪ ፋራናይት ወይም 237 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቀዝቃዛ አድርጎታል። ይህ እጅግ ቀዝቃዛ የሆነው የቴሌስኮፑ ውስጣዊ ክፍል በጠፈር ውስጥ ያለውን ዝቅተኛ የሙቀት ጨረር ተጠቅሞ ፤ እስከ የህዋ ውስጠኛ አካል በመዝለቅ በቴሌስኮፑ መስታወት በመመዝገብ ወደ ሚታይ ምስል ይቀይረዋል።
የዌብ ቴሌስኮፕ ጠረፍን አቅርቦ ማሳያ ብቻ ሳይሆን ሩቅ የሆነ ጊዜንም ወደ ኋላ ተመልሶ የሚያስመለክት የጊዜ ማሽን ነው ይለዋል የTIME መጽሔት። ዛሬ በቴሌስኮፑ የምናየው የ13.8 ቢሊዮን አመት የከዋክብት ክምችት የዛሬውን ሳይሆን በሚያስገርም ሁኔታ ከ13.8 ቢሊዮን አመት በፊት የነበረውን ነው። በመላው ዓለም የሚገኙ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ሳይቀር በቴሌስኮፑ በመገረምና በመደነቅ ላይ ናቸው። ዌብን ተጠቅመው ምርምር ለማድረግ ካላቸው ጉጉት የተነሳ መነሻ ሀሳባቸውን በማቅረብ ወረፋ እየያዙ ነው። የጠፈሩ ዓለም ለዘመናት ከእይታችን ሸሽጎ ያኖረውን አስገራሚና አስደናቂ ምስጢርና ውበት የዌብ የህዋ ቴሌስኮፕ እያስመለከተ ነው።
በነገራችን ላይ የዌብ የመጀመሪያው መስታወት በስሱ በወርቅ የተለበጠ መሆኑ ብርሃንን በቀላሉ እንዲያንጸባርቅ አስችሎታል። የዌብ ቴሌስኮፕ ዛሬ የሚገኝበት የጠፈር አካል ላይ ለመድረስ ከመሬት ከመጠቀ በኋላ አንድ ወር ወስዶበታል። በዓለማችን እጅግ ውድ ፣ ዘመናዊና የመጀመሪያ የሆነውን የዌብ ቴሌስኮፕ ለመገንባት ለአመታት ሌት ተቀን ሲታትሩ የኖሩ ፤ 20ሺህ ሊቃውንት የድካማቸው ፍሬ የሆነውን የዌብ ቴሌስኮፕ ሲመጥቅ ለማየት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፤ ትለናለች ታሪካዊ ቀኑን የእናት ምድርና የአጽናፈ ዓለም የልብ ወዳጅ የሆነው “NATIONAL GEOGRAPHIC” መጽሔት ጸሐፊ ናዲያ ድራኬ።
30 አመታትን ከፈጀ እልህ አስጨራሽ ፤ ዕቅድ፣ ንድፍ ፣ ግንባታ ፣ ጥበቃና ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ ውስብስብ የሆነው የዌብ ቴሌስኮ ለመምጠቅ ተዘጋጅቷል። የማምጠቁ ሒደት በስኬት ይጠናቀቅ ወይስ አንዳች ያልተጠበቀ እክል ገጥሞት ይስተጓጎል የሚለው ጥያቄ በሁሉም አእምሮ ውስጥ እየተመላለሰ ነበር በማለት ታስታውሰናለች። የሚንቀለቀለው ሮኬት ውስብስቡን የዌብን ቴሌስኮፕ ያለ እንከን ከታቀደለት በማድረስ ለአጽናፈ ዓለም አዲስ ብስራት ይዞ ይመጣ ፤ ወይስ እንደ ቻሌንጀር ፈንድቶ ያን ሁሉ ድካም ጊዜና ገንዘብ ከንቱ አድርጎ ለናሳም ለአሜሪካም ሌላ የሀፍረት ከል ያከናንብ ስትል ጸሐፊዋ በወቅቱ ስጋቷን ገልጻ ነበር።
በመጨረሻም በግንባታው የተሳተፉ ሳይንቲ ስቶች ፣ ሒደቱን በቅርብ የሚከታተለው ኋይት ሀውስ ፤ ለአመታት እንደ ነፍሰ ጡር ቀን ሲቆጥሩለት የኖሩት የሳተላይቱ ማምጠቂያ ቀን ታኅሣሥ 25 2021 ዓ.ም ሆኖ ተቆረጠ። ቀኑ ደረሰና ቴሌስኮፑ በደቡብ አሜሪካ ሰሜናዊ ምሥራቅ የባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው የፍሬንች ጉያና የጠፈር ወደብ ወደ ህዋ መጠቀ። በዕለቱም በተሳካ ሁኔታ በመምጠቅ ለ30 ቀናት የሚያካሂደውን የ1.6 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የህዋ ጉዞ ጀመረ። በወሩ ቀድሞ በታቀደለት የጠፈር አካል መድረሱ ተረጋገጠ። ቀጣዩ ሥራ ቴሌስኮፑ በተገጠመለት ፕሮግራም መሠረት፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውስብስብ የሆነ ሒደት አልፎ ለምልከታ ዝግጁ የመሆኑን ነገር ማረጋገጥ ለሳይንቲስቶች ሌላ ጭንቅ ጥብ ነበር ስትል ታስታውሰናለች።
አንዲት ሒደት ከተዛነፈች አጠቃላይ የጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ተልዕኮ ይጨናገፋል ትለናለች ናዲያ። ቴሌስኮፑ ከሰው ልጅ ንክኪ ርቆ ራሱን በራሱ ለተልዕኮው ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ለዚህ ነው የናሳው ምክትል አስተዳዳሪ ፓሜላ ሜልሮይ ተልዕኮውን፤ «ለአደጋ የተጋለጠ፣ ከተሳካ ደግሞ የህዋን ምርምር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ፤» ስትል የገለጸችው። ሆኖም ትላለች የ”NATIONAL GEOGRAPHIC” መጽሔት ጸሐፊ ናዲያ ድራኬ፤ በዘርፉ ከሚፈጥረው ተአምር አንጻር፤ የተሆነለት ነገር ሁሉ ይገባዋል። የሰው ልጅ ለዚህ መርሀ ግብር የቱንም ያህል ዋጋ ቢከፍል ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም ትለናለች።
የጄምስ ዌብ የህዋ ቴሌስኮፕ ወርቃማውንና 6.4 ሜትር የሚሰፋውን ዓይኑን ከፍቶ እያሳየን ያለው ትዕይንተ ዓለም/cosmos/፤ አይደለም ለተራው ሕዝብ ለስነ ፈለክ ሊቃውንትም በአግራሞትና በአድናቆት እጅን በአፍ የሚያስጭንና የማወቅ ጉጉትን የሚጨምር ነው። የጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ህዋን ብቻ ሳይሆን ጊዜንም አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር ነው ይላሉ የአውሮፓ የስፔስ ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ ማርክ ማክካውግሬን፤ ቴሌስኮፑ አጽናፈ ዓለም ተፈጥሮበታል ተብሎ በሳይንቲስቶች ከሚታመንበት 13.8 ቢሊዮን አመት ወደ ኋላ ተመልሶ የሚያስመለክት ነው ይሉናል አማካሪው። ቀጣዩንና የመጨረሻ ክፍል በነገው ዕትም ይዤ እመለሳለሁ።
ሻሎም !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም