የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነት የተንጸባረቀበት ከመሆኑም ባሻገር የአንድ አገር ሕዝብ ያለምንም ልዩነት በአንድነት መቆም ከቻለ ማንኛውንም ዓይነት የችግር ዳገት በቀላሉ መውጣት እንደሚችል ለዓለም ሕዝብ ማሳየት የተቻለበት ነው።
ዛሬ ላይ የአንድነትን እና የመተባበርን ጥቅም ከዓድዋ ድል የተማሩ እና የተገነዘቡ በርካታ አገራት አገራቸውን ከቅኝ ግዛት ከማላቀቅም ባለፈ ተባብረው በመሥራት ኢኮኖሚያቸውን ከፍታ ማማ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል።
ስለ ዓድዋ ድል ሲነሳ ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ድል ማድረግ እንዲችሉ የረዳቸውን አብይ ምክንያት ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል። ኢትዮጵያውያን የዓድዋ ጦርነት ድል እንዲያደርጉ ያስቻሉ በርካታ አስቻይ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱና ዋነኛው ምክንያት ግን የአባቶቻችን የአመራር ጥበብ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም።
ምን ዓይነት ጥበብ? ብሎ ለሚጠይቅ መልሱ ይኸው ነው… ከጦርነቱ በፊት ጣሊያን የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለመሸርሸር በማሰብ የተለያዩ የአውራጃ ገዥዎችን በጥቅም እና በስልጣን በመደለል የውስጥ አንድነትን ለማዳከም ከፍተኛ ሥራ ሠርታለች። አልተሳካም የንጉሡ የቀኝ እጅ የሆኑትን ራስ መኮንን ሳይቀር በስልጣን እና በጥቅም እስከማባበል የደረሰ ሙከራ አድርጋ ነበር።
ከተለያዩ የታሪክ ድርሳናት የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከጦርነቱ በፊት የጣሊያን ሰላዮች በንግድ እና በፖለቲካ ወኪልነት፣ በሐኪምነት እና በመሐንዲስነት በየአውራጃዎች በመሰማራት እና ለመሳፍንቱ የቅርብ ሰው በመሆን በወቅቱ በኢትዮጵያውያን መሳፍንቶች እንደ ብርቅ የሚቆጠሩትን ጠመንጃ፣ ሽጉጥ ፣ ስጋጃ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ሽቶ መሰል የመደለያ ዕቃዎችን ከጣሊያን እና ከአውሮፓ በማምጣት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስለላ እና የመከፋፈል ሥራ ይሠሩ ነበር።
ይህንን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል መሳፍንቶች እና መኳንንቶች ለጣሊያን አድረው ነበር። የአፄ ምኒልክ የአመራር ጥበብ የተፈተነውም በዚህ ነበር። አፄ ምኒልክ እና በዙሪያቸው የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች በአንድ በኩል በወቅቱ የአገራቸውን ጥቅም በስልጣን እና በነዋይ አሳልፈው የሰጡ የስልጣን እና የነዋይ ሴሰኛ መሳፍንቶችን እና ሹመኞችን ጥበብ በተሞላበት አኳኋን ከአገሪቱ የፖለቲካ ድግስ እንዳይሳተፉ በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ አገራቸውን በነዋይ ያልቀየሩ አገር ወዳድ መሳፍንቶች እና መኳንንቶችን ደግሞ በፖለቲካው ድግስ ከመታደም አልፈው በአገሪቱ የፖለቲካ ድግስ ላይ ዋና አጋፋሪ መሆን እንዲችሉ አድርገዋል።
በዙሪያቸው የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ከነዋይ ይልቅ አገራቸውን ያስቀደሙ፤ በጥበብ የታሹ መሪዎችን በፖለቲካው ድግስ ዋና አድራጊ ፈጣሪ ማድረጋቸው እና በነዋይ ተገዝተው እኩይ ተግባር ያረገዙ ባንዳዎችን ደግሞ በጥበብ ከአገሪቱ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ገሸሽ ማድረግ መቻላቸው የዓለምን ሕዝብ በአድናቆት «አጃይብ» አስብሎ እጅን በጉንጭ ላይ የሚያስጭን ድልን እንዲያስመዘግቡ ረድቷቸዋል። የዓድዋ ድል!
የአሁን መሪዎችም ይህንን የአባቶቻችንን ጥበብ እንደ ትምህርት ወስደው በወቅታዊ የአገራችን ፖለቲካ ሜዳ ላይ የሚታዩ ደንቃራ የሆኑ የጽንፈኛነት አስተሳሰቦችን በጥበብ ከፖለቲካው ሜዳ ማስወጣት ይገባቸዋል ባይነኝ።
«የእሳት ልጅ አመድ» እንዲሉ አሁን ላይ የዓድዋን ድል ተባብረው ያስመዘገቡ አባቶች የሆንን ልጆች የተሳፈርንበት ባቡር እና እየሄድንበት ያለው የባቡር ሃዲድ ኢትዮጵያውያን መድረስ ከሚፈልጉት የእድገት ማማ ላይ እንዲያደርስ እንቅፋቶቹ ሊወገዱለት ይገባል። የአገራችንን ሁለተናዊ እንቅስቃሴ የሚመለከት ማንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እውነት እኛ የዓድዋን ድል ያስመዘገቡ ልጆች ነን ? ብሎ ራሱን መጠየቁ ግድ ነው።
በተለይም በአገራችን ፖለቲከኞች መካከል የሚታየው ጤነኛ ያልሆነ እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም በሚል የሚደረግ ሩጫ እና የእርስ በርስ መጠላለፍ ስንመለከት ወራሪው ፋሽስት ጣሊያን እና አባት አርበኞች የሚያደርጉት ጦርነት እንጂ ምናችንም የዓድዋን ድል ያስመዘገቡ አባቶች ልጆች አንመስልም የሚለውን ለመጠየቅ መገደዳችን የማይቀር ነው።
አሁን ላይ ለራሳቸው የፖለቲከኛ ካባ ያለበሱ አንዳንድ ፅንፈኛ (የሃይማኖትን እና የብሔር) ፖለቲከኞች ግለሰቦች እና ቡድኖች የተለያዩ ተልካሻ ምክንያቶችን እየወለዱ እና እያዋለዱ ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድነት ከመውሰድ ይልቅ መለያየትን መርጠው በሰፈር እና በሃይማኖት አቧድነው ወደ ከፋ ችግር ሊወስዱን እየሞከሩ ነው።
እነኝህ በጥፋት እና በጀብደኝነት የተካኑ አፅንፈኞች ይህንን እኩይ ተግባራቸውን እንደ ፖለቲካ እውቀት በመቁጠር ራሳቸውን ከስህተት ከመመልስ ይልቅ በጥፋቱ ባቡር ተሳፍረው እና ተከታዮቻቸውንም አሳፍረው በጥፋቱ ጎዳና መሸምጠጡን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል። የሚገርመው ደግሞ የአገሪቱን ችግር ማወሳስብን እንደ ትልቅ የፖለቲካ እውቀት መቁጠራቸው ነው።
እነኝህ አካላት የፖለቲካ አዋቂ በመምሰል በየአደባባዩ ይደስኩሩ እንጂ አገራችን ችግር ገጥሟት ፖለቲካዊ የአመራር ጥበብ በፈለገችባቸው ወቅቶች አንድም ጊዜ የመፍትሔ ሃሳብ ሲያዋጡ አላየናቸውም። ሕዝብ በረሃብ እና በጦርነት አይሆኑ ሆኖ ሲፈተን እና ሲጎሳቆል እንኳን የነዋይ ሴሰኝነታቸውን ጥም ከማርካት እና የራሳቸውን ጥቅም ለማግበስበስ ከመራኮት ውጪ ለሕዝቡ ምንም ሲያደርጉ አልተስተዋሉም።
ፈላስፎች «ነፍስ ስጋን ካሸነፈቻት ስጋ የነፍስ መቃብር ትሆናለች » ያሉት እንደእነዚህ ዓይነት ፖለቲከኞችን ለማመላከት አስበው ይመስለኛል። የሚገርመው እነኝህ ፖለቲከኛ ነን ባይ ግለሰቦች ለሕዝባቸው አብዝተው እንደሚጨነቁ እና እንደሚያስቡ በየአደባባዩ ለመደስኮር የሚቀድማቸው ኃይል አለመኖሩ ነው። ለዲስኩር ሲሽቀዳደሙ ከብርሃን ፍጥነት በላይ ናቸው። እጅጉንም አታላይ እና አስመሳዮች ናቸው።
ከማስመሰል እና ከማታለል ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በአገራችን ያሉ ፖለቲከኞችን ስመለከት የውጫሌን ውል ያጭበረበረውን አንቶኖሊን ያስታውሰኛል። ብዙዎቹ እንደ አንቶኖሊ አስመሳይ እና አታላይ ናቸው የሚሉት ሌላ የሚያደርጉት ሌላ። እንደእነዚህ ዓይነት አስመሳይ እና የአንድነትን ምስጢር መረዳት የተሳናቸውን ጽንፈኛ ፖለቲከኞችን መታገል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።
የውጫሌን ውል መጭበርበር እንዳጋለጠው እንደ ቀኝአዝማች ዮሴፍ ዓይነት በአመራርነት ደረጃ የሚገኙ ከመንግሥት አካላት ብዙ እንጠብቃለን። እደግመዋለሁ ! እነኝህን የፖለቲካ ካባ በለበሱ ፅንፈኞች አገራችን እንዳይሆኑ ሆና ሳያበላሿት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አምርሮ ሊታገላቸው ይገባል።
ይህ መሆን ያለበት ዛሬውኑ ሳይረፍድ ነው። ነገር ግን ከረፈደ በኋላ በአስመሳዮች የሚፈጠርን ችግር መመለስ ዳሽን ተራራን የመውጣት ያህል እንዳያስቸግረን ያሰጋኛል። መራር ዋጋ እንዳያንከፍለንም ያስፈራኛል። ሰላም!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም