ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ታላቁን የሥነ-ጽሁፍ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋውን አጥታለች።ይህ ድንገተኛ የሞት ዜና በእሳቸው እጅ ተምረውና ተኮትክተው ካደጉ፤ ትልቅ ደረጃ ከደረሱ ተማሪዎቻቸው ጀምሮ መላውን የኪነ-ጥበብ ማህበረሰብ ልብ የነካ ሆኖ አልፏል። በተለይም ደግሞ እኚህ ሥራ ወዳድ የሥነ-ጽሁፍ ሰው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ለሊት ድረስ በቤታቸው በሥራ ላይ የነበሩ እና ከዚያ በፊት ባሉት ቀናትም ፍፁም ጤነኛ ሆነው መክረማቸውን የሚያውቅ ቤተሰብ፤ የቅርብ ጓደኛና አድናቂያቸው በድንገት ታመው ለሕልፈት የመዳረጋቸውን ጉዳይ ዛሬ ድረስ አምኖ ለመቀበል መቸገሩን በመገለጽ ላይ ይገኛል።
የአንጋፋው መምህር ሥርዓተ ቀብር የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ፣ ምሁራን ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ፣ የስራ ባልደረቦቻቸው ፣ የሥነ-ፁሑፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን ፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ረቡዕ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በታላቅ ክብር ተፈጽሟል። በሥርዓተ ቀብራቸው ላይም የተገኙ ታላላቅ ሰዎች ጋሽ ዘሪሁን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት ባገለገሉባቸው አራት አስርት ዓመታት ሁሉ “ማስተማርን ፈጣሪ በተለየ መንገድ እንደሰጣቸው ፀጋ ተቀብለው ትውልድን ለማነፅ ዋጋ የከፈሉ የትምህርት አባት እንደነበሩ የመሰከሩላቸው ሲሆን ‹‹የሥነ ጽሁፍ ዋርካው ወደቀ›› በማለትም ኀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
በማስተማር ሥራቸው ብቻ ሳይሆን በጥናት እና ምርምር ሥራዎች ላይ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ማከናወንን የሚመርጡ ፤ ሰዓት አክባሪና ሰው ለመርዳት ቀዳሚ የሆኑ ሰው እንደነበሩ የሚነገርላቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ጥቅምት 10 ቀን 1944 ዓ.ም በደሴ ከተማ መወለዳቸውን የታሪክ ማህደራቸው ያስረዳል። የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ አካለወልድ ትምህርት ቤት እና በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።በተለይም በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት በነበራቸው ቆይታ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የትምህርት ቤቱ የኪነ-ጥበብ አባል በመሆን በቲያትር ትወና ፣ በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት የሚሳተፉ ንቁ ተማሪ እንደነበሩ ይጠቀሳል።ይህም ታዲያ በኃለኛው ዘመን እድሜያቸውን ሙሉ ለቆዩበት የሥነ-ጹሑፍ ሕይወታቸው መሰረት ጥሎላቸዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን በ1962 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በልዑል በዕደ-ማርያም የመሰናዶ ትምህርት ቤት መማር ከጀመሩ በኋላ የጥበብ ጥሪውን በመከተል የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል አባል በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ የነበራቸውን ኪነ-ጥበባዊ ጥሪያቸውን ገፍተውበታል።በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ሥነ-ጹሑፍ ትምህርት ክፍል ከ1963 ዓ.ም ገብተው መማር ጀመሩ።በወቅቱ አስፈላጊ በነበረው የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት በመሳተፍ በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በከረን ከተማ ለአንድ አመት ያህል አስተምረው ግዳጃቸውን ተውጥተው ተመልሰዋል።እንዲሁም ደግሞ በ1967 ዓ.ም በታወጀው የእድገት በህብረት የዕውቀትና የስራ ዘመቻ ተሳታፊ በመሆን በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዓድዋና አካባቢው ተመድበው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት መቻላቸው ይነገራል።
በዩኒቨርሲቲ አገልግሎትና በእድገት በህብረት ዘመቻ ምክንያት ለሶስት ዓመታት ያቋረጡትን ትምህርት ለመቀጠል ቢሞክርም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ኃይሎች ትርምስ በቀይና ነጭ ሽብር ምክንያት ተረጋግቶ መማር ባለመቻላቸው በቀድሞው አጠራር አሩሲ ክፍለ ሀገር አሰላ ከተማ በመሄድ አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛና እንግሊዝኛ ትምህርት ለአንድ ዓመት አስተማሩ።ከዚያም ተመልሰው ያቋረጡትን ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል በ1970 ዓ.ም የመጀምሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከዚሁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ተቀብለዋል፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኙ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ስር በነበረው የዓለማያ ግብርና ኮሌጅ በረዳት ምሩቅነት ደረጃ በ1971 ዓ.ም የተቀጠሩ ሲሆን እስከ ዩኒቨርሲቲ መምህርነት ደረጃ ደርሰዋል። በመቀጠልም 1975 ዓ.ም በመምህርነትና በተከ ታታይ ትምህርት አስተባባሪነት ሰርተዋል። ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ድረስ በአዲስ አበባ ዩሚቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋና ፎክሎር ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ውስጥ በተለያዩ ማዕረጎችና ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።
ላለፉት 40 ዓመታት ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በርካታ ተማሪዎችን በማፍራት የሚታወቁት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከማስተማር ጎን ለጎን 143 የመጀመሪያ ዲግሪ 80 የማስተርስ ዲግሪ 20 የዶክቶሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በምርምር ስራዎቻቸው ማመከራቸውን ከግለ- ታሪካቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና እና ምርምሮችን ያካሄዱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ከትምህርቱ ዘርፍ በተጨማሪ ከፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመሆን የተለያዩ የሥነ ሕዝብ ጥናቶችን ሰርተዋል። እንዲሁም ወጣት ደራሲያን እና ተመራማሪዎችን በማማከር እና በመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በጥናት እና ምርምር ሥራዎች ላይ “የኢትዮጵያን ሥነጽሑፍ ታላላቅ የሥነጽሑፍ ስራዎችን የሰነዱ” ታላቅ መምህር የነበሩት ጋሽ ዘሪሁን ከምርምር ስራዎቻቸው በተጨማሪ እነዚህም የሥነ-ጽሁፍ መሠረታውያን ልቦለዳውያን እና የቀደምት ደራስያን አጫጭር ትረካዎች ፣ ሥነ-ጽሑፍ ለማህበራዊ ለውጥ ፣ ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ እንዲሁም በሥነ-ጽሑፍና በፎክሎር የተሰሩ የዲግሪ ማሟያ ጥናቶችና አጠቃሎ ስብስብ የሚሉ አምስት መጽሐፍትን አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የምርምር እና የጥናት ስራዎችን በታወቁ የጥናት መጽሔቶች እና ታላላቅ ጉባዔዎች ላይ የታተሙላቸው ሲሆን አሁንም ድረስ በርካታ ያልታተሙ ስራዎች ያሏቸው መሆኑን ከቅርብ ጓደኞቻቸው ለማወቅ ተችሏል።ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በሀገር ውስጥ ካበረከቷቸው ተሳትፎ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሳታፊ ነበረ።ከእነዚህ መካከልም በአሜሪካ ፣ በጃፓን ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ዛምቢያ ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ እንግሊዝ እና ጀርመን የሚገኙ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በትምህርት ቤት የኪነ-ጥበብ ክበብ የጀመረውን የተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ንቁ ተሳታፊነት ቀስ በቀስ እያሳደገና እያጠናከረ ሕይወታቸውን ድርና ማግ ያደረገ በጥልቅ ተመልካችነት ሥነ-ጽሁፍን የተጠበበ፤ የመረመረ የሄሰ፤ የሀገሪቱን አንጋፋና ወጣት ተመራማሪዎችንም ሆነ ፈጣሪዎች በረቂቁ የአስተሳሰብ መንገድና የአሰራር ብልሃታቸው ያስገኙትን ትሩፋት አንጥሮ በማሳየት ዘወትር የሚተጉ ነበሩ።
ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እንዳስተማሩት ለቢቢሲ የተናገረው ዶክተር አንዱዓለም አባተ በበኩሉ፤ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን “በአስተማሪነቱ ለራሱ፣ ለትምህርት ክፍሉ፣ በትምህርት ክፍሉ ውስጥ ላሉ እና ተማሪው ለሆኑ ሁሉ አርዓያ የሆነ” ሲል ይገልጿቸዋል። ‹‹የኢትዮጵያን ሥነጽሑፍ የሰነዱ›› መሆናቸውን አመልክቶ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስገራሚ የማስታወስ ችሎታ እንደነበራቸውም ያስረዳል። ‹‹በማስተርስ እና በፒኤችዲ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሳይቀር በምን ጉዳይ ጥናታቸውን እንደሰሩ፣ ምን ክፍተት እንደነበረባቸው እና ጥናታቸው፣ ምን ጠንካራ ጎን እንደነበረው ሰንደው የያዙ ነበሩ›› ይላል።
አንዱዓለም ብዙ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የጥናት ርዕስ መደራረብ እንደሚያጋጥም፣ በአንዱ ዩኒቨርሲቲ የተጠናውን ደብቀው አምጥተው ሌላ ዩኒቨርሲቲ የሚያጠኑ መኖራቸውን አስታውሶ “ማን ምን አጠና የሚለው ዝርዝር መረጃ በእኛ የትምህርት ክፍል ያለው እርሱ ጋር ነው” በማለትም ያክላሉ። እኒህን ሰው ማጣት «የተደገፍክበት ወንበር ድንገት ሸርተት ሲልብህ» ያለውን ስሜት የሚፈጥር ነው በማለትም ነው ከያኒ አንዷለም አባተ ለቢቢሲ ዘጋቢ በሞታቸው የተሰማውን ኀዘን የገለጸው።
ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚያውቋቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን በሥራቸው የተመሰገኑ እንደነበሩ ሌላው ለቢቢሲ የተናገሩት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ ናቸው።ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ለዘርፉ እድገት ካበረከቷቸው በርካታ ስራዎች በተጨማሪ የሌሎች ሰዎች ሥራዎችን አርትኦት በማድረግም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ነው የጠቆሙት። ከዚህም ባሻገር ለህትመት ዝግጁ የሆኑ “ሁለት ወይም ሦስት ሥራዎች” እንዳሏቸውም አመልክተዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ካስተማሯቸው ብዙ ደራሲያን መካከል በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሚያገለግሉት እና በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የአጭር ልብ ወለድ አሳታሚ ወይም ጸሐፊት የዝና ወርቁ አንዷ ናቸው።
«ጋሽ ዘሪሁን ትዕግስተኛ ፣ መካሪ ነበር። ኢትዮጵያ እጅግ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር ነው ያጣችው» ብለዋል።
‹‹ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የሚለውን ሥም ከብዙ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ቅዳሜ የኪነ- ጥበባት ምሽት በተባለው ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ስለ የመጀመርያው አጭር ልብ ወለድ ‘የጉለሌው ሰካራም’ ጥናት ሲያቀርብ ነበር የሰማሁት›› በማለት የተናገረው ደግሞ ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ነው። ከዚያ በኋላ ይበልጥ መተዋወቃቸውንና ቅርበታቸውን መጠናከሩን ነው በኀዘን ስሜት የገለጸው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በኢትዮጵያ የሥነ- ጽሑፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ጠቅሶ፤ ከዚህም በላይ በዘርፉ ብዙ የሕይወት ልምዶች እንደነበሯቸው ፣ ነገር ግን «ምን ሠራሁ» የሚል ትህትና የተላበሱ እና በመገናኛ ብዙኃን ብዙም ቀርበው የማይታዩ የማይደመጡ ቁጥብ ሰው እንደነበሩ አስታውሷል።
አድናቂዎቻቸው ‹‹የሥነ-ጽሁፉ ዋርካ›› እያሉ የሚያቆላምጧቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በተወለዱ በ71 ዓመታቸው የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በድንገት ባደረባቸው ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ለ40 ዓመታት በትዳር አብረው ከቆዩዋቸው ባለቤታቸው ከወይዘሮ የትምወርቅ አካሉ አምስት ልጆች አፍርተው እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።
በተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምሮችን በመስራት እንዲሁም በሃያሲነታቸውም ይታወቃሉ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም