የመነሻ ሀሳብ
ከሀገራዊ ብሂሎቻችን መካከል ስለ ሹመትና ሹም የሚናገሩት አባባሎች በርከት ያለ ቁጥር እንዳላቸው በሚገባ የተረዳሁት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ዝግጅት ሳደርግ ነበር። “ሹመት ላወቀው ይከብደዋል፤ ላላወቀበት ደግሞ ያሳብደዋል” የሚለው አንዱ ዘለላ አባባል ፈገግ ያስደረገኝን ያህል “ሹምና ጥጥ እያደር ይከብዳል” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገርም “እውነትም!” አሰኝቶ ውስጤን እንዳነዘረኝ መደበቅ አልሻም።
ሹመት ከጥጥ ጋር ተነጻጽሮ ይከብዳል መባሉ፤ ውሎ ሲያድር የሹሙ አመራርም እንዲሁ “ውሃ እንደነካው ጥጥ” እየከበደና የተመሪውን ጫንቃ ቁልቁል እየተጫነ ለምሬት እንደሚዳርግ ለመግለጽ ነው። ይህንን የመንደርደሪያ አንቀጽ ለመነሻ እንዲያግዝ ካስታወስን ዘንድ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ምክንያት ወደ ሆነኝ የግል ገጠመኝ ልሸጋገር።
እ.ኤ.አ ……በአሜሪካዋ የሐዋይ ክፍለ ግዛት በተለይም በፓስፊክ ውቅያኖስ መካከል ከሚገኙት ውብ ደሴቶች መካከል ማዊ በመባል በምትታወቀው በአንደኛዋ ደሴት እምብርት ላይ በሚገኝ አንድ ዓለም አቀፍ የሥልጠና ማዕከል ለመገኘት ዕድል አጋጥሞኝ ነበር። የሥልጠናው ዋና ትኩረት በዋነኛነት በከፍተኛ የአመራር ጥበብና በኮሙዩኒኬሽን የዕውቀት ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ከሃያ ሰባት ያህል ሀገራት የተውጣጡና በተለያዩ ደረጃዎች ሀገራቸውን የሚያገለግሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ነበሩ።
ትምህርቱን ይሰጡ የነበሩት መምህራንም እንዲሁ በየተሰጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ መጽሐፍትን የጻፉ፣ በተለያዩ የዓለማችን ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩና አንቱታን ያተረፉ ታላላቅ ምሑራን ነበሩ። እነዚያን ከመሳሰሉ “የቀለም ቀንድ” ሊቃውንት ዕውቀታቸውንና የግላቸውን ተሞክሮ መቅሰም በግል እድለኝነት ቢመስልም ሰፋ ተደርጎ ሲታሰብ ግን “ወይ ሀገሬ!” አሰኝቶ ቁጭት ላይ የሚጥሉ ብዙ ትምህርቶችን ለመማር ችያለሁ።
ጸሐፊው ሥልጠናውን አጠናቆ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላም “የአመራር ጥበብ” በሚል ርዕስ ተደጋግማ ለሕትመት የበቃች አንዲት መለስተኛ መጽሐፍ ለንባብ ለማብቃት ሞክሯል። ለመጽሐፏ መታተም ሁለት ዋና ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። አንድም፡- ጸሐፊው ያገኘውን እውቀት “የጋን ውስጥ መብራት” አድርጎ ለራሱ ብቻ ከማስቀረት ይልቅ ለወገኖቹ የማካፈል ጉጉት ስለነበረው፤ ሁለትም፡- በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ እያንዳንዱ ሠልጣኝ ያገኘውን እውቀት የሀገሩን ዐውድ በሚመጥን አቀራረብ ሌሎችን እንዲያሰለጥንና የተማረውን እንዲያካፍል “የቃል ኪዳን ያህል” አደራ ገብቶ ስለነበርም ነው።
እጅግ የተከበረና ጠቃሚ እውቀት የገበየንበትን ያንን ዓለም አቀፍ ሥልጠና በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት እንዲተገበር ለማስተባበር የተመረጡት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ነበሩ። ብርጋዲዬር ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ዕድሉን አግኝተው ምርጫውን ያሸነፉት ሀገራቸውን ባገለገሉበት ዘመን ባተረፉት መልካም ዝናና አክብሮት ይሁንታ በማግኘታቸው ነበር። ጄኔራል ታዬ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ዘመን ድረስ በአየር ኃይልና በባሕር ኃይል ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ እርከን አገልግለዋል።
በመቀጥልም በሀገር አስተዳደርና በመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ውስጥ በሚኒስትርነት ማዕረግ ከፍተኛ የአገልግሎት ወንበር ላይ የተቀመጡ ሲሆን በመጨረሻም በውጭ ሀገራት አምባሳደርነት በሚያገለግሉበት ወቅት የወታደራዊው ደርግ አገዛዝ ስላላስደሰታቸው ሥልጣናቸውን በመተው ስደትን መርጠው በአሜሪካ ይኖሩ ነበር። የሥልጠና ማዕከሉ ኃላፊዎች “በመብራት አፈላልገው” የማስተባበሩን ኃላፊነት የሰጧቸው በአገ ልግሎታቸውና በተሞክሯቸው ግዝፈት ተማርከው እንደሆነ ለመገመት አይከብድም።
ዓለም ባከበራቸውና ይህ ጸሐፊም በርቀት ሲያከብራቸው የኖረው እኚህ ታላቅ ሰብዕና የተላበሱ ኢትዮጵያዊ በሚያስተባብሩት ሥልጠና ላይ መገኘት ማለት ግጥምጥሞሽ ተብሎ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን መባረክም ጭምር እንደሆነ በጽኑ ያምናል። ከጄኔራሉ ጋር ስለ ሀገር ጉዳይ ስንወያይ ያነሳናቸውን እጅግ ጠቃሚ ነጥቦች በተመለከተ ጊዜው ሲፈቅድ በዝርዝር ለማካፈል እሞክራለሁ። ስለ ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ይበልጥ ለማወቅ ካስፈለገ፤ “የሕይወቴ ጉዞ” በሚል ርዕስ በወንድዬ ዓሊ አሰናጅነት በ2010 ዓ.ም የታተመውን ግለ ታሪክ መጽሐፋቸውን ማንበብ ይቻላል።
የዐይን ከፋቹ ሥልጠና ትሩፋት፤
ከላይ በተጠቀሰው የሥልጠና መርሐ ግብርና በተለይም በቡድን ውይይቶች መካከል ተነስተው ከነበሩ በርካታ ሃሳቦች መካከል ከዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ጋር የሚጎዳኙትን አንዳንድ ነጥቦች ልጠቃቅስ። “የየሀገራችሁ መንግሥታት በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ለሚሾሟቸው ባለስልጣናት የሚሰጧው የሹመት ደብዳቤዎች ይዘት ምን ይመስላል?” በኮሙዩኒኬሽን አሠልጣኛችን አማካይነት ለቡድን ውይይት ከተሰጡን ጥያቄዎች መካከል አንዱ ነበር። ይገርማል! ይህ አነስተኛ የሚመስል ርዕሰ ጉዳይ ለካንስ ብዙ የሚተነተኑ ሃሳቦችን የያዘ ኖሯል።
እውነቱን ለመመስከር ከዚያ ዕለት በፊት አንድም ቀን ስለ ሹመት ደብዳቤዎች የይዘት ምንነት አስቤ አላውቅም ነበር። በቡድን ውይይቱም ላይ እንደ ሌሎች ተሳታፊዎች ንቁ ነበርኩ ለማለት አይቻልም። በተለይም በአፍሪካ ወንድሞቻችን ይሰጡ የነበሩት በሳል አስተያየቶች ይህንን ጸሐፊ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ውጭ የመጡ የሌሎች ሀገራትን ተሳታፊያን ጭምር ማስደመሙ አልቀረም።
ከናይጄሪያ የመጣው አንዱ ሠልጣኝ የሰጠው ሃሳብ ረዥም ሰዓታት አወያይቶን እንደነበርም አስታውሳለሁ። እንዲህ ነበር ያለው፡- “በአፍሪካውያን የሹመት ደብዳቤዎች ውስጥ ‹የተመደበልዎትን ጥቅማ ጥቅም እያገኙ› የሚል ሐረግ ካልታከለበት በስተቀር የሚሾሙት ግለሰቦች ደስተኛ ላይሆኑ ይችላሉ። ለሹመት የቀረቡ ዕጩዎችም በደብዳቤያቸው ውስጥ ፈጥነው ለማንበብ የሚጣደፉት “ጥቅማ ጥቅም” አመልካቿ ሀረግ በደማቁ መጻፏን እንጂ ለዝርዝር የሥራ መመሪያቸው ደንታ ያላቸው አይመስልም። እንዲያውም እጅግ የሚያስገርመው ነገር ከብዙ የሹመት ደብዳቤዎች ጋር ዝርዝር የሥራ መመሪያ መስጠት የተለመደ አይደለም። ምናልባትም መመሪያው በአለቃቸው ቢሮ በኩል በቃል ተነግሯቸው ይሆናል ወይንም ‹ዋኝታችሁ ተወጡት› ተብሎም ሊሆን ይችላል”
ናይጄሪያዊው ሠልጣኝ ጓደኛችን ሃሳቡን በአጭሩ ለመቋጨት የፈለገ አይመስልም፡- “የአፍሪካ መሪዎች ለሚሾሟቸው ባለሥልጣናት የሚጽፉት የሹመት ደብዳቤ ርዝመት በአንድ ዐረፍተ ነገር የተጠቃለለ መሆኑም እጅግ ያስገርማል። ‹ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥቅማ ጥቅምዎ ተከብሮ የ……. ሚኒስትር/ኃላፊ/ኮሚሽነር… ሆነው የተሾሙ መሆንዎን አስታውቃለሁ። ይኼው ነው።”
ከዚህ አስተያየት በኋላ ውይይቱ ተጋግሎ በመቀጠል እያንዳንዱ ሠልጣኝ የየሀገሩን ተሞክሮ እየተሽቀዳደመ ይተርክ ጀመር። “በእኔ ሀገር…” አለ አንዱ የእስያ ሀገር ሠልጣኝ፡- “ማንም የመንግሥት ሹመኛ ሥልጣን በተሰጠው ዕለት በቀጥታ በሚተላለፍ የሚዲያ መርሐ ግብር ስለተሾመበት የኃላፊነት ቦታ ምን ራዕይ ኖሮት ምን ለማስፈጸም እንዲሚተጋ ለሕዝቡ በይፋ ያስታውቃል። ከሚዲያ ባለሙያዎች ለሚቀርቡለት ዝርዝር ጥያቄዎችም ተገቢውን መልስና ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ አለበት። ቃል የገባውን ውጤት ማሳካት ካልቻለም ኃላፊነቱን በፈቃዱ እንደሚለቅ በግልጽ ያስታውቃል።”
ይህ እስያዊ ሠልጣኝ ከልቡ ይህንን አስተያየት ሲሰጥ ከአፍሪካ ሀገራት የተጋበዝነው ተሳታፊዎች “ወይ ነዶ! አይ እምዬ አፍሪካ!” በሚል ዓይነት ቁጭት እየተጠቃቀስን እርስ በእርስ መተያየታችንን አስታውሳለሁ። ምክንያቱም የእኛይቱ አፍሪካ ለዚህን መሰሉ ግልጸኝነት ስላልታደለች ወይንም መሪዎቻችን ስላላደሉን መሆኑን ልብ ይሏል።
“ኢትዮጵያ ሆይ! ተጠየቂ!?”
ይህ ጸሐፊ ከዚያ ሥልጠና በኋላ የበርካታ የሹመት ደብዳቤዎችን ናሙና ለመመልከት ሞክሯል። መነሻ ያደረገውም የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ዘመን ነው። በደብዳቤ አጻጻፍ ወግና ሥርዓት ይህ የምኒልክ ዘመን የተለየ ባህርይ አለው። በአጠቃላይ ሲፈተሽ ንጉሠ ነገሥቱ በጻፏቸው አብዛኞቹ የሹመት ደብዳቤዎች ውስጥ የተጠቀሱት ቃላት ትሕትና የሚስተዋልባቸው፣ በርህራሄ የታጀቡና እንደ ሀገር መሪ ሳይሆን በአንድ ደረጃ ላይ የሚገኝ የሥራ ባልደረባ የሚጽፈውን ዓይነት ይዘት ያላቸው ናቸው።
አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የተጻጻፏቸውንና በጳውሎስ ኞኞ አማካይነት የተሰባሰቡትን ዳጎስ ያሉ ባለሁለት ጥራዝ መጽሐፍት የአርትኦቱን ሥራ የሠራው ይህ ጸሐፊ ስለሆነ የደብዳቤ ባሕርያቱን በሚገባ ለመረዳት እድል አጋጥሞታል። ዘርዘር በሚሉት የሹመት ደብዳቤዎቹ ማጠቃለያ ላይ ባለስልጣናቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጭምር ጠበቅ ያለ የአደራ ቃል ይጠቀሙ ነበር።
በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ቢሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ይጻፉ የነበሩት የሹመት ደብዳቤዎች የአደራ ቃሉ ጠንከር ይል ካልሆነ በስተቀር “የጥቅማ ጥቅም” ጉዳይ የተገለጸባቸውን ደብዳቤዎች በግሌ ፈልጌ ለማንበብ አልቻልኩም። ንጉሡ ሹመት ከሰጡም በኋላ ሳይውል ሳያድር የተሾሙት ባለሥልጣናት ቤተ መንግሥት እየተጠሩ የአደራውን ቃል ያጠናክሩ እንደነበር ከክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም ግለ ታሪክ መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ አንብቤያለሁ።
“በግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድና ትዕዛዝ የትምህርትና ሥነ ጥበብ ዋና ዳሬክተር መሆኔን ጸሐፌ ትዕዛዙ ነገሩኝና ንጉሠ ነገሥቱን እጅ ነስተን ወደየቤታችን ተመለስን። ከጥቂት ቀናት በኋላ ከጃንሆይ ፊት ለጉዳይ ቀረብሁና “የተሰጠህ ትልቅ ሥራ ነው አሉ።” እኔም “አዎን ጃንሆይ! ካሁኑ ከባድነቱ እየተሰማን ነው” አልኋቸውና በፈገግታ ተለያየን” (የሕይወቴ ትዝታ – ገጽ 43)።
የዘመነ ደርጉ ሥርዓት ብዙ ያነጋግራል፤ ያወያያልም። ርግጠኛ መሆን የሚቻለው ግን “አብዮቱን በመስዋዕትነት ጭምር ከግብ እንድታደርሱ” ከሚል መመሪያ በዘለለ “ተገቢው ጥቅማ ጥቅም ተጠብቅዎሎት…” የሚል ሐረግ እድል ገጥሞኝ ለማየት በቻልኳቸው የሹመት ደብዳቤዎች ውስጥ ለማንበብ አልቻልኩም። ምንም እንኳን ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይሄ “የጥቅማ ጥቅም አጽንኦት” ጉዳይ በሹመት ደብዳቤዎች ላይ መጠቀስ የጀመረው ከዘመነ ሕወሓት/ ኢሕአዴግ ዘመን ጀምሮ ይሆንን የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል። ወደፊት ጊዜው ሲፈቅድ ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረግ እንደሚገባኝ ተረድቻለሁ።
በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት ወደ ተንደረደርኩባቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ልመለስ። ማንኛውም የኃላፊነት ወንበር የራሱ የሆነና ሹመቱን የሚመጥን በዝርዝር የተወሰነ ጥቅማ ጥቅም እንዳለው ይታወቃል። ይህ አሠራር አዲስ ሳይሆን በየትኞቹም ሀገራት ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ የነበረና ዛሬም እየተተገበረ ያለ ደንብ ነው። ከሁለትም ሦስት መኪና፣ የሚያዝናና መኖሪያ ቤት፣ ልዩ ጥበቃና እጀባ ወዘተ. እንደ ሥልጣናቸው ክብደትና ቅለት መሰጠቱ የተለመደና የታወቀ ነው።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ በየሹመት ደብዳቤዎቹ ውስጥ ለታወቀ ባህልና ልማድ “የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ” ከአገልግሎት አደራ ቀድሞ ለመጠቀስ ስለምን ያስፈልጋል? በዚህ ጸሐፊ መረዳት “የአዋጁን በጓዳ” እንዲሉ “ፀሐይ የምትወጣው በምሥራቅ በኩል ነው” የሚለውን ተፈጥሯዊ እውነታ ካልተረዳችሁ የማለት ያህል ያስገምታል። ለነገሩስ የጥቅማ ጥቅሙ ጉዳይ በደብዳቤው ውስጥ ባይገለጽስ ሊቀር የሚችል ጉዳይ ነው?
ደግ ደጉን እንመኝና እንደ እስያው ሠልጣኝ ጓደኛችን ገለጻ አንድ ባለ ሥልጣን በሀገራችን ከተሾመ በኋላ ከብዙኃን መገናኛ ባልደረቦችና አስፈላጊ ከሆነም እርሱ/ እርሷ በተሾሙበት ዘርፍ ከሰለጠኑ ባለሙያዎችና ዜጎች ተሹዋሚው ለማሳካት ስለሚያቅደው/ስለምታቅደው የሥራ ፕሮግራም ከዜጎች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች መድረክ ተመቻችቶ ውይይት ማድረግ ቢቻል ለሀገር እድገት አይበጅም? መቼም “እኛ ዜጎች እንደምናምነው፤ ባለስልጣኖቻችንም አሌ ሊሉ እንደማችሉት” የምርጫ ካርዳችንን ተጠቅመን “እንደራሴያችን” እንዲሆኑ ለወንበራቸው ክብር ያበቃናቸው አንዲያገለግሉን እንጂ ለራሳቸው “እንደ ራሳቸው” ሆነው ጥቅማ ጥቅም ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አይደለም።
እንደ ድፍረት ካልተቆጠረብን በስተቀር በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያስተዋልናቸው ያሉትን ሀገራዊ ቀውሶችና ተግዳሮቶች ማርገብና በጥበብ ማስከን የተሳናቸው አንዳንድ የመንግሥት ሹመኞች “የተሰጠኝን ኃላፊነት መወጣት ስላልቻልኩ ኃላፊነቴን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ” ሲሉ ማድመጥ የምንመኘው ብቻ ሳይሆን ሆኖ ብናየው በእጅጉ እንደምንናፍቅ ለሚመለከታቸው መሪዎቻችን ይድረስ ብንል ያስወቅሰን ይሆን? አይመስለኝም።
“ሹመት ናፋቂ ውሎው ወንዝ ዳር ነው” ይባላል፤ ለምን ቢሉ፡- “የውኃውና የድንጋዩ ቻቻታ የሕዝብ አቤቱታ ይመስለዋል” እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር “ሹመት ሺህ ሞት ነው” በማለት እንደ ብሂሉ ደፍረን ባንናገርም እንኳን፤ “ሕዝብን ማገልገል ከጥቅማ ጥቅም በላይ የሆነ ምድራዊና ሰማያዊ አደራ” መሆኑን ባለሥልጣኖቻችን በተግባራቸው ቢያረጋግጡልን እያከበርናቸው እንመራላቸዋለን። “ከግላዊ ጥቅማ ጥቅሙ ባሻገር ምን ያህሉ ሹም ሕዝብን ለማገልገል ራሱን ለሕዝብ ጥቅም አድርጎ እንደሚሰጥ” ቢፈተሽ ብዙ ገመና ይገለጥ ነበር።
“ጥቅማ ጥቅሙ ብቻ እያማለላቸው” ፍሬያቸው ሲጎመዝዝና አደራ በል ሆነው ስናስተውል በየጓዳችን ከማማትና ከመታዘብ አልፈን ተርፈን እንደየሃይማኖታችን በየቤተ እምነቶቻችን ታዛ ሥር ስንሰባሰብ በፈጣሪ ፊት ምን ብለን እንደምንጸልይባቸው ይጠፋቸዋል ማለት አይቻልም። ከአሁን ቀደም ባስነበብኩት ጽሑፌ ውስጥ የጠቀስኩትን አንድ አባባል አስታውሼ ርዕሰ ጉዳዬን ልደምድም። “ሹመኞቹ የሀገሬ የሕዝብ ባላደራዎች ሆይ! እንደምትኖሩ ሆናችሁ ሥሩ፤ እንደምትሞቱ ሆናችሁ ኑሩ!”። ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም