ትዝብት አንድን ነገር መተቸትና አቃቂር እያወጡ ማብጠልጠል ብቻ አይደለም። የሚተቹ ነገሮች በራሱ ዝም ብሎ ለመተቸት ሳይሆን ነገ ተሻሽለው ወደ ጥሩ መስመር እንዲገቡ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር አንድን መልካም ነገር የማድነቅና የማበረታታት ባህላችን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ብዙ ጊዜ ትችታችንም የተሻለ ነገር ለመፍጠር ወይም ዛሬ የተጣመመው ነገር ነገ እንዲቃና ሳይሆን ይበልጥ እንዲሰበር የሚያደርግ መሆኑን በብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል።
እኛ ለእኛ ብሎ የሚለፋልንን ማጀገን እና ሌላ ጀግና እንዲወለድ ማድረግ አለመደብንም። ሁሉንም መልካም ነገሮች ከሃይማኖት፣ፖለቲካ፣ብሔርና ሌሎች ነገሮች ጋር እያገናኘን መተቸትና ማድነቅን ባህላችን እስኪመስል እየተለማመድነው መጥተናል። አድናቆታችንም ይሁን ትችታችን በነዚህ ጉዳዮች ተፅእኖ ስር ወድቀዋል ወይም በነዚህ ጉዳዮች የተቃኙ ሆነዋል ብለን ደፍረን መናገር የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።
አንዳንድ ነገሮች ግን አሉ፣ ሳይደነቁ የማይታለፉ። መልካም ነገር ሁሌም ሊበረታታና ሊደነቅ ይገባልና የዛሬው ትዝብታችንም በአድናቆት የተሞላ ነው። ልናደንቀው የመረጥነው ጉዳይም አድናቆት ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም።
በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ አንድ ትልቅ ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይህም ከሰባት ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን በውስጡ በመያዝ አገልግሎት እየሰጠ ለሚገኘው መቄዶኒያ አዲስ ላስገነባው ህንጻ በርና መስኮት ለማሟላት የተካሄደው የቀጥታ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር የታሰበውን አሳክቶ ተጠናቋል። መቄዶኒያ ያስጀመረው ባለ 12 ወለል ሕንፃ ከሁለት ነጥብ
ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን፤ በርና መስኮት ለመግጠም 151 ሚሊየን ብር ያስፈልግ ነበር።
በኮሜዲያን እሸቱ መለሰ አስተባባሪነት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ታዋቂ ግለሰቦች በተሳተፉበት የዩቲዩብ የቀጥታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ አድርገዋል። በተደረገው የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብርም ለ888 በሮች እና ለ739 መስኮቶች የሚውል ገንዝብ የተገኘ ሲሆን፤ የአንድ በር ዋጋ 106 ሺህ ብር የአንድ መስኮት ዋጋ ደግሞ 80 ሺህ ብር መሆኑ ተገልጿል። መቄዶንያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን ለመመገብ ብቻ በቀን አንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያለበት እንደመሆኑ በራሱ አቅም ይህን ለማሳካት አይችልምና ሌላ መፍትሄ የግድ ይላል። ግን እንዴት? የሚለው አሳሳቢ ነበር። ኢትዮጵያ በእንዲህ አይነት ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ይዞ የሚመጣ ጀግና ሁሌም አታጣም። ይሆናል ብሎ ለመገመት በሚከብድ ሁኔታ ነገሮችን የሚያስተካክል ጀግና በዚህኛው ትውልድም አልጠፋም።
በኮሜድያን እሸቱ መለስ ዶንኪ ቲዩብ አስተባባሪነት ለመቄዶኒያ የበርና መስኮት ማሰሪያ እሁድ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት የተጀመረው የ1 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ማሰባሰብ መርሐግብር 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በማግስቱ ሰኞ ለሊቱን ዕቅዱን አሳክቷል።
ይህ የደጋግ ኢትዮጵያውያን የዘመናችን ትልቅ ገድል ነው። ከዚህ በላይ ጀግንነት የለም። ከዚያም አልፎ “ሰውነት አልሞተም” ብለን እንድንደመድም በቂ ምሳሌ ነው። በዚህ ጊዜ እኛ ኢትዮጵያውያን ብሎም በዓለም ላይ የሚታየው የሚሰማው ሁሉ ሰው ሰውነቱን በቃ አጣ? ዓለም ለመኖር አስፈሪ እየሆነች ይሆን? የሚያስብሉ ሰው የሰው ስጋት እየሆነ የመጣበት አስከፊ ነገሮች ተከስተዋል እየተከሰቱም ነው፣ ሰብዓዊነትም እየተሸረሸረ የመጣበት ጊዜ ነው።
ነገር ግን አሁንም በጨለማ ውስጥ ብርሃን የሆኑ እና ለመኖር እንድንጓጓ የሚያደርጉን ጥቂት የማይባሉ ለነብሳቸው ያደሩ ልበ ብሩሃን መልካም ሰዎች ዛሬም አሉ። በልበ ብሩሁ ቢኒያም አማካኝነት ለተቋቋመው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የማስፋፊያ ህንፃ ግንባታው ተጠናቆ ነገር ግን ያላለቁ የበር እና የመስኮት እንዲሁም አንዳንድ የፊኒሺንግ ስራዎች ለማጠናቀቅ የሚውል ገንዘብ አሰባስቤ ሳልጨርስ ከዚች ወንበር ንቅንቅ አልልም ብሎ ራሱን ለመልካምነት አሳልፎ የሰጠውን በበጎ ስራዎቹ የምናውቀው ኮሜድያን እሸቱ መለሰን አለማድነቅ አይቻልም። እንደዚህ ያሉ መልካም ሰዎች ቢያንስ በተግባራቸው ማድነቅና ማበረታታት መለመድ አለበት። እነዚህን ሰዎች ብንችል ሸልመንና እውቅና ሰጥተን ልናበረታታቸው ይገባል።
ይህን የበጎነት ጥግ የሆነ ተግባር የትኛውም ሃይማኖት፣ የትኛውም የፖለቲካ አቋም፣ የትኛውም ብሔር አባል ነኝ የሚል ሰው ላለማድነቅ ምክንያት የለውም። ለእንደዚህ አይነት መልካምነት አድናቆት ከሌለን ነገ ሌሎች በጎ ሰዎችን መፍጠር አንችልም። ዛሬ የምናየውን ጀግና ማድነቅ ካልቻልን ነገ ሌላ ጀግና አይወለድልንም።
ዛሬ ላይ የምንኖረው ምስጋና የለሽ በሆነ ዓለም ውስጥ ቢሆንም ሁላችንም ብንሆን ባንናገረውም ሌሎች በመልካም ተግባራችን እንዲያመሰግኑን መፈለጋችን ተፈጥሯዊ ነው። ሌሎችን ከልብ በመነጨ ስሜት ስናመሰግናቸው እንዲበረታቱና መንፈሳቸው እንዲታደስ እናደርጋለን። ከልብ የመነጨ ምስጋና፣ ሰዎች አቅማቸው የሚፈቅደውን ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ያነሳሳቸዋልና ማመስገንና ማድነቅ ይልመድብን።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም