ወንድ ልጅ እንደሴት ልጅ ምን ጌጥ አለው? እግዜር እንደሴት የተዋበ ምን ፈጥሯል? ከትላንት እስከዛሬ ዓለም በሁለት ኃይሎች ስር ናት እላለው..በሴትና በውበት፡፡ ዓለም የሴትን ውበት ተደግፋ እንደቆመች የገባኝን ያክል ምንም አልገባኝም፡፡ ምድር ላይ እንደ ሴት ልጅ ቀምሼው የጣመኝ ጣፋጭም የለኝም፡፡
እነ ስምረት ግቢ ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ ግቢው ውስጥ ሰባት የሚከራይ ክፍል አለ..ከሰባቱ ክፍል ስድስቱ የተያዘው በሴቶች ነው..በላጤ ሴቶች፡፡ እዛ ግቢ ስገባ ገነት የገባሁ ነበር የመሰለኝ፡፡ በህይወቴ መቼም ከማላገኘው እድል ጋር የተገናኘሁ ያክል ነበር የተሰማኝ፡፡ ገነት ምን ትመስላለች ላለኝ የነስምረት ግቢ እለዋለው፡፡ ገነት ምን ትመስላለች ላለኝ ሌላም የምመልሰው አንድ መልስ አለኝ..በተዋቡና በቆነጁ ሴቶች መሀል መገኘት የሚል፡፡ ምድር ላይ ደጋግሜ ብፈጠርም ይሄን እውነቴን የሚሽር እውቀት እንደማይኖር አምናለው፡፡ ሴት የወንድ ገነት ናት..ወደምድር የመጣባት..ባዝኖና ተንከራቶ ከምድር የሚሄድባት፡፡ ሴት የወንድ ልጅ አዲስ ነገሩ ናት..ሴት በወንድ ነፍስ ውስጥ አሮጌ ሆና አታውቅም፡፡
ስድስት ሴቶች ወዳሉበት ግቢ በተከራይነት ገባሁ፡፡ መቼም እንደዛ ቀን ያለ የሙላት መንፈስ ጎብኝቶኝ አያውቅም፡፡ ደስታዬ በሴቶች መኖር ላይ መንጠልጠሉ ብዙ ቀን መከፋትን ቢፈጥርብኝም ግን ከዛ እውነት መሸሽ አልቻልኩም፡፡ ዓለም ላይ ወንዶች ጠፍተው እኔና እልፍ ሴቶች ብንቀር የምመኝ አይነት ወንድ ነኝ፡፡ ከአምስቱ ጋር ተግባባሁ..ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ የሚመስል ትውውቅ ፈጠርን፡፡ እጅግ ሲበዛ መልካምና ተጫዋች የሆኑ ሴቶች ናቸው፡፡ በተለይ ሩታና ሳሮን የውስጥ ሸሚዜን ያክል የቀረብኳቸው ሴቶች ሆኑ፡፡ አደይና ኤማንዳም ህይወት የሚያጣፍጡ ቅመሞች ሆነው ወደህይወቴ መጡ፡፡ ማክዳ ጭምትነት ቢይዛትም ባለሁበት ሁሉ ነበረች፡፡ ቤቴ የበላሁበት ጊዜ ትዝ አይለኝም..ዛሬ አንዷጋ ነገ አንዷጋ እያልኩ የገነት ህይወቴን ተያያዝኩት፡፡ ምግብ ማብሰል እንደምችልና ጎበዝ እንደሆንኩ ስነግራቸው ባላማመን ከመወድስ በቀር ሁሉም የሰራሁትን ቀምሰውታል፡፡
ከጎኔ ካለችው መወድስ ጋር ግን ምንም አናወራም፡፡ እኔን ስታይ ሴይጣኗ ይመጣል መሰለኝ..የዝምታ ጋኔኗ የሚነሳው ያኔ ነው፡፡ ስቃና ተጫውታ እኔጋ ስትደርስ ዝም የሚያሰኝ የሆነ ጋኔን አለባት፡፡ ዝምታዋን ግን እወደዋለው፡፡ ዝምታዋን ስለምወደው ዝም እንድትል ያደረጋትን ጋኔን እካድመው ጀመር፡፡ ጋኔን ስወድ..ጋኔን ሳፈቅር መወድስ የመጀመሪያዬ ናት፡፡ ከእሷ ውጪ ማንም የማይችለው ደስ የሚል ዝምታ አላት፡፡ ዝምታዋ ውስጥ ካልሆነ ወሬዋ ውስጥ ብርቅ ሆናብኝ አታውቅም፡፡ በሳቋ ውስጥ ያን ያክል ናት፡፡ ከዚህም በላይ ዝም እንድትል ፈጣሪ ልሳኗን እንዲዘጋው ተመኝቼ አውቃለው፡፡ ሁሉም ቀርቶብኝ ለምን እንደምትጠላኝ ብቻ ባውቀው እላለው፡፡ እሷን አልፌ ሩቅ ካሉት ሳሮንና ሩታ ጋር ድንበር አልፌ ሳወራ በር ላይ እቃ እያጠበች ዝም ትለኛለች፡፡ እሷን አልፌ የሚቀጥለው ክፍል ካሉት ኤማንዳና አደይ ጋር በርበሬና ጨው ስዋዋስ የጆሮ ማዳመጫዋን ሰክታ ልብስ እያጠበች ትዘጋኛለች፡፡ ይቺን ሴት ጎኔ ስላደረጋት ፈጣሪን ወቅሼው አላውቅም፡፡ እንኳንም ጎረቤቴ ሆነች ስል ሰማይ አይቼ አውቃለው፡፡ ስወጣና ስገባ ዝም ያለ ፊት እጣ ክፍሌ ሆኖ ህይወት ቀጠለ፡፡
ጠዋት ወደ ስራ ልሄድ በሬን ስከፍት ጥርሷን እየፋቀች ከነዝምታዋ አገኛታለው፡፡ ዝም ባለው ንጋት ውስጥ ዝም ብላ ሳያት ገና ያልነጋ መዐልት ትመስለኛለች፡፡ ከለሊቱ አስራ አንድ ሰዐት የሚመስል ፊት አላት..ሊነጋ ያለ ቀይዳማ ፊት፡፡ ዝምታዋ ይጥመኛል፡፡ የትም ሰምቼው ከማላውቀው ከሳሮንና ከኤማንዳ ሳቅና ድምጽ በላይ የእሷ ዝምታ ደስታዬ ነው፡፡ ኩራቷ ይስበኛል..የትም ጠርኖኝ ከማያቀው ከአደይና ከሩታ ሽቶ በላይ ኩራቷ ይማርከኛል፡፡ ከመወድስ ዝምታ ተነስቼ ሴት ሲኦልም ናት ስል እንዳስብ አደረገኝ፡፡ አንዲት ውብ ሴት ጎንህ ሆና ዝም ስትልህና እንዳልተፈጠረ ስትቆጥርህ ከዚህ በላይ ምን ሲኦል አለ? ለመላዕክትነት የቀረበች አንዲት አማላይ ሴት አንተን አልፋ ከሌሎች ጋር ስታወራና ስትሳሳቅ እንደማየት ምን ገሀነም አለ? በመወድስ ዝምታ የደረስኩበት የመጨረሻው ግኝቴ ሴት ልጅ ሁሉንም መሆን እንደምትችል ነው፡፡
ከሴቶች ጋር መገልፈጤ ያላማራቸው የስምረት አባት አንድ ቀን ጠርተውኝ ‹ምንህም ደስ አላለኝ..ሴት አውል ነገር ነህ መሰለኝ..ቆፍጠን በል› ሲሉ ገረመሙኝ፡፡ ግቢው ውስጥ በተከራይ ላይ የተጣለ አንድ ማዕቀብ እንዳለ በገባሁ በመጀመሪያዋ ሰከንድ ተነግሮኛል..እርሱም የትኛዋም ሴት ተከራይ ግቢው ውስጥ ወንድ ይዛ ማምጣት እንደማትችል ነው፡፡ የነስምረት ግቢ ወንድ የማይገባበት ግቢ ነው፡፡ እኔ ራሱ የገባሁት እህቴ ውጪ አገር ለመሄድ በወጣችበት ተተክቼ ነው፡፡ እኔን ከዛ ግቢ ለማስወጣት የስምረት አባት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ በቤት ኪራይ ተማሮ ይወጣል ሲሉ በወር ሁለት ጊዜ ቤት ኪራይ ጨምረውብኝ ያውቃሉ፡፡ በዚህ አልሳካ ሲላቸው ‹አንተ ከገባህ ወዲህ የውሀና የመብራት ኪራይ ጨምሮብኛል ወይ ቤቱን ልቀቅ ወይ ክፍያ ጨምር› ሲሉ በሌላ ዘዴ መጡብኝ ይሄንንም ስቄ አለፍኩት፡፡ እዛ ግቢ እኔ ብቻ ነኝ ያልተገባ የቤት ኪራይ የምከፍለው፡፡ ወሩ ደርሶ የቤት ኪራይ ልሰጣቸው ወደቤታቸው ስሄድ ከብዙ ማስጠንቀቂያ ጋር ነው የሚሸኙኝ፡፡ ባለፈው ወር የገናን በአል አስመልክቼ አንኳን አደረሳችሁ ልላቸው በዛውም የኪራይ ብር ልሰጣቸው ስሄድ ‹የማልወዳቸውን አንድና ሁለት ነገር ስታደርግ ካየሁ ከቤት አስወጣሀለው› አሉኝ፡፡
‹የማይወዱት ምንድነው? ስል ካህን ፊት እንደቆመ መዕምን እጄን ወደ ኋላ አጣጥፌ ጠየኩ፡፡
‹እሱ ምንም አያደርግልህም..ያልኩህን ላለማድረግ ተጣጣር› ብለውኝ ብሩን ከእጄ ላይ የመቀማት ያክል ወስደው ዘጉብኝ፡፡ ምንድነው የማይወዱት እያልኩ ራሴን እየጠየኩ ወደቤቴ ተመለስኩ፡፡ ቆይቼ ስሰማ የስምረት አባት ወንድ ልጅ ቤታቸው እንዲገባ የማይፈልጉት ለልጃቸው ሲሉ እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ ግቢው ውስጥ ከስምረት ጋር ላለመገናኘት የማላደርገው ጥረት አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለምን እንደፈለገችኝ ሳላውቅ በሬ ላይ ቆማ ስትጠራኝም ሆነ በሬን ስታንኳኳ እየሰማሁ ዝም የምልበት ጊዜ ነበር፡፡
የመወድስ ዝምታ የጣመኝን ያክል ይጎመዝዘኝ ጀመር፡፡ ገነት ነው ያልኩት ግቢ በመወድስ ዝምታ ጸለመብኝ፡፡ የአምስቱ ሴቶች ውበትና ቁንጅና ሳቅና ወሬ በመወድስ ዝምታ የደበዘዘ አለሜን ማንጻት አልቻለም፡፡ እየቆየሁ እኔም ዝም ማለት ጀመርኩ..የሚስቁልኝን ደጋግ ፊቶች እያለፍኩ በዝምታ ቤቴ ገብቼ መውጣት ጀመርኩ፡፡ እነ ሩታ ቤቴ ሲመጡ በዝምታ ነበር የማደምጣቸው..ምን እንደሆንኩ ሲጠይቁኝ ምንም እንዳልሆንኩ ከመመለስ ባለፈ የምላቸው አልነበረም፡፡ በኔ ነውር ራሳቸውን ጥፋተኛ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በህይወቴ ያየሁት ሌላው ገነት..ቆንጆ ሴት ምንም ባላጠፋችው ጥፋት ወንድን ልጅ ይቅርታ ስጠይቅ ሆኖ ልቤ ተቀመጠ፡፡ አስቀይሜያቸው ሳበቃ ያስቀየሙኝ መስሏቸው እነዛ ደጋግ ልቦች ሸሹኝ፡፡ በአንዲት ዝምተኛ ነፍስ ግቢው ሙሉ ዝምታ ወደቀበት፡፡ ግቢው እንዳይሰማ በሚጠነቀቁ ሹክሹክታዎች ተዋጠ፡፡ የማውቀው የሳሮን ሳቅ..መቼም የሚረሳኝ የማይመስለኝ የኤማንዳ ድምጽ ከጆሮዬም ከልቤም እየደበዘዘ መጣ፡፡
እየቆየሁ ስመጣ በውስጤ የሆነ ስሜት እየተፈጠረ መጣ። ‹አይ ሰው! አልኩ ለራሴ፡፡ በፍቅርና በደግነት የከበቡኝን ነፍሶች ትቼ ፊት የነሳችኝን አንዲት ሴት እከጅል ገባሁ፡፡ በማላውቀው ስበት መወድስን አስብ ጀመር፡፡ ያቺን የተረገመች ነፍስ አፈቀርኳት፡፡ ጊዜ ሲጥል ማለት ይሄ አይደል? በዛ ዝምታዋ ውስጥ እንዴት ፍቅሬን መግለጽ እንዳለብኝ የተጠበብኩትን ጥበብ መቼም አረሳውም፡፡ የወንድ ታሪክ በሴት ጀምሮ በሴት ያበቃ ነው ስል እርግጠኛ ሆንኩ፡፡
አንድ ምሽት ቤቴ ተንኳኳ በሩን ስከፍት የስምረት አባት የደርግ መለዮአቸውን አጥልቀው በሬ ላይ ቆመዋል፡፡ ‹እንዴት አመሹ ጋሽ ትዕግስቱ! ከማለቴ..
‹ትዕግስቴ አልቋል! ነገ ጠዋት ቤቱን ለቀህ እንድትወጣ..› ብለውኝ መልስ ሳይጠብቁ ትተውኝ ሄዱ፡፡
ህይወቴ እዛጋ የቆመ መሰለኝ..ከዚያ ቀን በኋላ መኖር የሌለ መሰለኝ፡፡ የስምረትን አባት አየኋቸው ቀጥ ብሎ የተስተካከለ አዛውንት ቁመናቸው ቃሌ ከሚያልፍ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል የሚል መሰለኝ፡፡ በጅነና ርምጃ ለአንዴም ሳይዛነፉ ከመጡበት ደረሱ፡፡ የበረንዳውን መወጣጫ በእጃቸው ተደግፈው ሰባት የሚሆነውን ደረጃ ወደላይ ተያያዙት፡፡ የመጨረሻው ወለል ላይ እስኪደርሱ ድረስ እንዲያዩኝ በመሻት ቆሜ ሳያቸው ነበር፡፡ ግን አላዩኝም፡፡ ጀርባቸው አይን ቢኖረው ፊቴ ላይ ያለውን የስቃይ አዘቅት ያየው ነበር..ጀርባቸው አይን ቢኖረው ስል ተመኘው፡፡ ከግቢዬ ውጣ ብለው ሳይሆን ገለውኝ አስከሬኔን ወደመቃብር ስፍራ የሚሸኙ ነበር የመሰለኝ፡፡
በህይወቴ ሁሌም በምረግማት የእሮብ ማለዳ ላይ ከቤት ወጣሁ..ከእኔ መውጣት በኋላ እዛ ቤትና በእዛች ዝምተኛ ነፍስ ውስጥ ያለውን ታሪክ አላውቀውም..ግን ሁሌም ይናፍቀኛል፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም