የጥቁር ሕዝቦች ምድር ያፈራቸው የምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ልጆች «እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ» ሆነው ዘመን የማይሽረው ታሪክ ከሰሩ ይኸው ዘንድሮ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሞላቸው – ዓድዋ። ዓድዋ በስሙ የጥቁር ሕዝቦች ድል ይባል እንጂ የተሰራው ስራ የተጀገነው ጀግንነት የተገኘው ውጤት በጥቅሉ በተገዢነት ቀንበር ውስጥ ለነበሩት ሁሉ የድል ብስራትን ያበሰረ ነው። በርካታ ሕዝቦች ለአንድ አላማ የተሰለፉበትና አኩሪ ገድል ያስመዘገቡበት የታሪክ ክስተትም ነው።
ድሉ የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ቀና ያደረገ ፤ የስልጣኔ ማማ ላይ ተቀምጠናል ያሉትን ደግሞ የሰው አምሳል ይሉት ስለነበረው የጥቁር ሕዝብ ደግመው ደጋግመው እንዲያስቡ ያደረገም ነበር። ይህ በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ብስራት ከተከወነ ምእተ አመት ቢያልፈውም የድሉ ትኩሳት ዛሬም በልብ ውስጥ ስሜት ይፈጠራል። ዘመን የማይሽረው የዓድዋ ድል በትውልድ ቅብብሎሽ እየተወሳ እንደ አዲስ መጽሐፍ እየተገለጠ ብዙዎችን እያስተማረ ዛሬ ላይ ደርሷል።
የዓድዋ ድል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቅድም አያቶች የተጋድሎ ውጤት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ የሚያወሳው የማይዳሰስ ቅርሱ ነው። የዓድዋ ድል ዛሬ ላለው ከመቶ ሚሊየን በላይ ለሚገመት ኢትዮጵያዊ ትምህርት ቤቱም ቤተ መጻሐፍቱም ነው። ለዚያውም የህብረትን የአንድነትን ምንነት የሚገነዘብበት፤ ነጻነት የሚለውን ቃል አፉን ሞልቶ የሚተረጉምበት የጀግኖች አባቶቹ ዘመን የማመይሽረው ውድም ክቡርም ስጦታ።
እንደ ዛሬው የህዳሴ ግድብ ሁሉ የዓድዋ ድል ላይ አሻራ የሌለው ደሙ ያልፈሰሰ አጥንቱ ያልተከሰከሰ የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም። በዘመኑ የነበረውን ሕዝብ ያሰባሰበውም የነጋሪቱ መጎሰም የአዋጁ መነገር ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ልብ የነበረው የሀገርና የሕዝብ ፍቅር፤ የባርነትና የተገዢነት ጥላቻ ነበር። ይህ ነበር የቀጠሮ ቦታና ጊዜ ሳያዛንፍ በጎርፍ የሚመሰል ሕዝብ በአንድ የተከሰተው – ለአደራ እናቱ ለኢትዮጵያ። ይህ ጀግና ሕዝብ ያኔ ነበር ከዘመናት በፊት እያንዳንዱ ሰው ተወልዶ የሚኖርበት የሚሞትበት የሚሞትለት ሀገር ሊኖረው እንደሚገባ የተረዳው።
ኢትዮጵያ ባህር አቋርጦ ስምና ክብሯን ገፎ ልጆቿን ከፋፍሎ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ሊያውል ለመጣው ጠላቷ ተገቢውን ምላሽ የሰጠችው በሁሉም ልጆቿ ተሳትፎም ነበር። የክተት አዋጁ ከተነገረበት ቅጽበት አንስቶ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ወደዓድዋ መዝመት ጀምሮም ነበር። የሚዘምተው ጥይትና ዝናሩን አቅሙ የፈቀደውም ለጭነት ይሆን ዘንድ ፈረስ፤ በቅሎና አህያውን ሲያዘጋጅ ነበር። እናቶችና ሚስቶችም የጣይቱ ብጡልን አርአያነት በመከተል ከስንቅ ዝግጅት ከወንድ እኩል ወደ ጦር ግንባር እስከ መዝመት የሚጠበቅባቸውን ሳይሆን ከሚጠበቅባቸው በላይ ከፍለዋል። አገር ከሌለች ምንም እንደማይኖር ሃይማኖትም አደጋ ላይ እንደምትወድቅ የተረዱ የሃይማኖት አባቶችም ለክተት አዋጁ ያላቸውን ህብረት የገለጹት ውለው ሳያድሩ ነበር።
የኪነ ጥበብ ሰዎችም የነበራቸው አብርክቶ ከድሉ ዋዜማ የጀመረ ነበር። እንኳን በዛ ዘመን ዛሬም ኢትዮጵያ ጠርታው ጆሮ ዳባ ልበስ የሚል ባይኖርም ሁሉም ሞቶ ሀገር ለማዳን መነሳት እንዳለበት ያዜሙት ሁሉ ሰርቶላቸው በልበ ሙሉነት ለማዋጋት በቅተዋል። የአዝማሪዎች ተሳትፎ ግን በዚህ ያበቃም አልነበረም ተአምር የተሰኘው ድል ከተገኘም በኋላ ታሪክ እየተወሳ እንዲኖር ብዙ ሰርተዋል።
እኛ የዚህ ትንግርት ጀግና የሆነ ሕዝብ ልጆች ነን። ዛሬ ወንድሞቻችንን አፍሪካውያን በየአመቱ የሚያከብሯቸው ብሔራዊ ቀናት የሚባሉት ከባርነት ቀንበር ከዘመናት ግዞት ነጻ የወጡበትን ነው። እነሱ ለዘመናት ያሳለፉትን የስጋና የህሊና ባርነት በሚገባ ስለሚገነዘቡት የነጻነት ቀናቸውን የሚያከብሩት በፍጹም ደስታ በአዲስ የሕይወት ምእራፍ ነው።
በየአደባባዮቻቸው የሚያዩዋቸው ነገሮች ሁሉ ከትላንት ማንነታቸውና ምንነታቸው ጋር የሰቀቀን ጥምረትን ያዘሉ ናቸው። እነዚህ ወንድሞቻችን በኢትዮጵያውያን ጀግኖች የተፈጸመው ገድል ምን ያህል እንደሚያስደስታቸው አይተናል። የድሉ ቀጥታ ተሳታፊ እነሱ ቢሆኑ ደግሞ ምን እንደሚሰማቸው መገመቱ የሚከብድ አይመስለኝም። ለዚህ ነው በርእሴ ዓድዋን ድል የመላው ኢትዮጵያውያን የማይዳሰስ ቅርስ ለማለት የወደድኩት።
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ዛሬስ እኛ ከዓድዋ ምን እንማር ? የዓድዋ ድልስ ምን አስተማረን ? የዓድዋ ድልንስ ከዓመት ክብር በዘለለ ረቂቅ ሀብትነቱን፤ እሴትነቱን ተጠቅመንበታል ወይ የሚለው ይመስለኛል። አያቶቻችን የሰሩትን አኩሪ ተጋድሎ እንዳንረሳ አባቶቻችን በየአመቱ እያዘከሩልን ዛሬ ላይ ደርሰናል። የዚህ ታላቅ የነጻነት ጎህ ማሳያ ሕዝባዊ ክብረ በዓል መከበር ያለው ፋይዳ ሁሉም የሚገነዘበው ነው።
ከዚህ ባሻገር ሀገራችንም ሕዝባችንም ከዓመት ዓመት የሚፈልገው የዓድዋ አይነት ተጋድሎዎችን የሚፈልጉ በርካታ ጥያቄዎች አሉበት። ችግሮቹ ደግሞ ጀግና ሆነን… ጀግና ፈጥረን…. ከዓመት እስከ ዓመት እየሰራን ካልተሻገርናቸው ብዙ የሚያስከፍሉን ብሎም ከቅኝ ግዛት ዘመን ባልተናነሰ የሚያዋርዱንና ከሰውነት የውሃ ልክ የሚያወርዱን ናቸው።
የዓድዋ ድል በህብረት ከቆምን በአንድ ከመከርን የማንሻገረው ገደል አለመኖሩን የራሳችን ታሪክ ሆኖ የሚያስተምረን ነው። ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ዛሬ የተጋረጡብን ችግርችም ደግሞ ህብረታችን ከጠነከረ ሳንነካቸው ሳንገፋቸው በነው የሚጠፉ ናቸው።
ለዚህ ከትናንቱ የዓድዋ ድላችን አብዝተን ልንማርበትና ከዛሬው ስህተታችን ልንታረም ይገባል። እለቱንም ስናስብ በዓመት አንድ ቀን አክብረንው ዓመት ሙሉ የምንኖረው የምንሆነው ብሎም በልቦናችን የሚቀመጥ የማይዳሰስ ቅርሳችን ሊሆን ይገባል የእለቱ መልእክቴ ነው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም