የመነሻ ወግ፤
“የአንድ ትውልድ የዘመን ስሌት ምን ያህል ነው? መለያ ድንበሩስ” – ጠያቂዎችንና መላሾቹን ሊያግባባ ያልቻለ የዓለማችን ምሁራን የጋራ ጥያቄ ነው። ሞጋቹ ጥያቄ ምላሽ የተነፈገው በዛሬ ጀንበር ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም እየተጠየቀ መሰንበቱ ስለማይቀር፤ ጊዜው ደርሶ ቁርጥ ያለ መልስ እስክናገኝ ድረስ “አጉራህ ጠናኝ” በማለት “የእንደመሰለን ሃሳባችንን” እያነሳሳን መወያየቱን እንቀጥልበታለን።
እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ዘመን ይሠራል፤ በራሱም ዘመን የራሱን አሻራ አትሞ ያልፋል። ይህ እውነታ በሁሉም ያገባኝ ባይ የእውቀት ዘርፍ ተዋንያን ዘንድ አሜንታን ያተረፈ ስለሆነ እጅግም ለክርክር በር አይከፍትም። “ትውልድ በራሱ ዘመን ይሰለጥናል ወይንም ካስፈለገ ይሰየጥናል”። ይህ ማለት ግን አዲስ መጭው ትውልድ መንበሩን የሚቆጣጠረው ከባዶ ተነስቶ ሳይሆን በነባር ትውልዶች መሠረት ላይ የራሱን ጡብ እያስቀመጠ መሆኑም አይዘነጋም።
የግብጾች የቤተሰባዊ ትውልድ ቅብብሎሽ ተሞክሮ በአብነት ቢነሳ ይጠቅም ስለመሰለን ምሳሌነቱን ለማሳያነት እንጠቀምበት። ሌሎች ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው አገራትም ሊኖሩ እንደሚችሉ ልብ ይሏል። ግብጾች ለቤተሰብ መኖሪያ የድርብ (ፎቅ) ሕንጻዎችን ወደ ላይ ሲያንጹ ለቀጣዩ ትውልድም የድርሻውን እየተውለት ነው። ለምሳሌ፡- ወላጆች የታችኛውን የምድር ቤት ወለል ለራሳቸው ሲሰሩ በቀጣዮቹ ወለሎች ላይ ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው የራሳቸውን መኖሪያ ቤት እንዲገነቡ ጭምር ኮንክሪቱንና ቀጣዩ ወለል የሚያያዝበትን መቀጠያ ብረት ጫፉን አዘጋጅተው ይተውታል።
እነዚህ ብልህ የግብጽ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት ነባሩና መጻኢው የቤተሰብ አባላት የጋራ ሕንጻ እንዲጋሩ ስለፈለጉ ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊ ቁርኝቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲቀጥል ስለሚፈልጉም ጭምር ነው። ይህ ቤተሰባዊ ትሥሥራቸው ለኅብረተሰባቸው ጥንካሬ የዘመናት ተሞክሮ ስለሆነ ዛሬም ባህሉ አልደበዘዘም። ይህ ጸሐፊ በቦታው ተገኝቶ ተሞክሯቸውን ተሞክሮ ትምህርት ቀስሟል።
የትውልድ ሰንሰለት ሳይበጠስ ሊቀጥል የሚችለው ከላይ እንደተጠቀሰው ምሳሌ በቤተሰባዊ መስተጋብር ብቻ ሳይሆን በጋራ አገራዊ ጉዳዮችም መቀባባል፣ መደጋገፍ፣ መከባበር፣ መረዳዳትና መደናነቅ ሲቻልና ሲሰራበት እንጂ ከሥር የተሸከመውን የትናንት መሠረት በማናጋትና ምሰሶውን ለመንቀል በመታገል ሊሆን አይገባም።
እርግጥ ነው ትውልዶች የታነጹባቸው የሥር መሠረቶችና ታሪኮች በሙሉ ሁሉም እንደሚፈልገውና እንደሚመኘው የሰመረና የተዋበ ላይሆን ይችላል። የኋለኛው መሠረት አንዳንዴ ስንጥቅም ሆነ ክፍተት ሊኖርበት ይችል ይሆናል። ቢሆንም ግን ተቃውሞን ለመግለጽ በመፈለግ ብቻ የታችኛውን መሠረት ሙሉ ለሙሉ በመናድ ሽቅብ የተንጠለጠሉበት ምሰሶ ብቻውን እንዲቆም መሞከር ትርፉ ተያይዞ መውደቅን ማስከተሉ አይቀርም።
የነገረ ትውልድ የወግ መንደርደሪያችን ይህንን ያህል ለመነሻ ሃሳባችን ጉዝጓዝ ከሆነን ዘንድ ወደ አገራዊ ጉዳያችን ቅኝት ከማለፋችን አስቀድሞ ዓይን ከፋች የሆነ አንድ የአሜሪካኖችን “ትውልድ ነክ” ጥናት ለመደላድል እንዲረዳን ዘርዘር አድርገን እንመልከት። “ብልህ ሰው ከሌሎች እውቀትን ይሸምታል፤ ከራስ ድካም አሸናፊነት ይማራል” እንዲሉ መሆኑን ልብ ይሏል።
“የአያት ቅድመ አያቶቻችን የሩጫ ፍጥነት ቀጣዩን ትወልድ ተረጋግቶ እንዲራመድ ረድቶታል።” ይህ ድንቅ አባባል በብዙ ሕዝቦች ቋንቋዎች ውስጥ ይነገራል። የአባባሉ ሁለተኛው ክፍልም እንዲህ ይላል፡- “በፈጣን ሩጫዎቻቸው መካከል ከስህተት ነፃ እንዳልሆኑም ስለምናምን ጥፋታቸውን በአክብሮት፣ በጥበብና በተሻለ ተግባር ለማረም እንሞክራለን እንጂ አጽማቸውን ቀስቅሰን ይግባኝ በማይባልበት የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቁመን የዳግመኛ ሞት ፍርድ እንዲፈረድባቸው አንጨክንም ” ድንቅ ብሂል ነው።
በአመራር ጥበብና በኮሚዩኒኬሽን የእውቀት ዘርፍ በአሰልጣኝነታቸው፣ በአስተማሪነታቸውና በተጠቀሱት ሁለት ዲሲፕሊኖች ላይ በጻፏቸው መጻሕፍት የሚታወቁት ጆን ካልቪን ማክስዌልና አራት የሥራ ባልደረቦቻቸው በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ አማካይነት የሰጡትን ድንቅ ሥልጠና ይህ አምደኛ ለመከታተል እድል ገጥሞት ነበር። ዘመን ወለዱን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከእነዚህ የዓለማችን ጉምቱና በሳል ምሁራን ጋር በማገናኘት ትምህርት እውቀት እንድንቀስም መድረኩን ያመቻቹት የራይዝ ኤንድ ሻይን ኢንተርናሽናል ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወዳጄ ዶ/ር ዳንኤል ጣሰው ነበሩ። ልባዊ ምሥጋናችን ይድረሳ ቸው።
ከማክስዌል ባልደረቦች መካከል ፓትሪክ ሌንሲዎኒ የተባሉት ምሁር በራሳቸው የሥልጠና ክፍለ ጊዜ ያስተማሩት የአገራቸውን የአሜሪካንን የቅርብ ዘመናት የትውልዶች የዘመን ሥሪት አወቃቀር ከፈጠራ፣ ከሥራ ባህልና ከበርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች አንጻር በምሳሌነት በመተንተን ነበር። ትምህርቱንም በራሳችን ዐውድ የአገራችንን የትውልድ ፍሰት እንድንፈትሽ አበረታተውናል።
ፓትሪክ ለመሸፈን የሞከሩት እ.ኤ.አ ከ1925 እስከ 2020 ያሉትን የዘጠና አምስት ዓመታት የአሜሪካዊውን ትውልዶች በአምስት ዘመናት በመከፋፈል ነበር። ከ1925 እስከ 1946 የነበረው ትውልድ የተሰየመው ለአገር ግንባታ የጨከነና የለሆሳስ ትውልድ (Builders/Silent Generation) እንደነበረ ገልጸው ብዙ ከመፎከር ይልቅ ለአገሩ ብዙ መሥራት የትውልዱ ዋና መገለጫ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። ለባህሉና ለሥርዓቱም “ወግ አጥባቂ” ተብሎ የሚፈረጅ ዓይነት ሲሆን ለሥራና ለፈጠራ የነበረው ተነሳሽነትም በዋነኛነት መሠረታዊ ቁሳዊ ፍላጎቶቹን ለማርካት ይተጋ እንደነበርም በዝርዝር አመላክተዋል።
በሁለተኝነት የጠቀሱት ትውልድ ከ1946 እስከ 1964 ዓመታት የኖረውንና የመታወቂያና የመለያ ስያሜውም እንደ “እንጉዳይ የፈላ ትውልድ” (Baby Boomers) የሚባል ነበር። ይህ ትውልድ ይህንን ስያሜ ሊያገኝ የቻለው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የውልደት መጠኑ (Birth Rate) በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ብዙ ሕጻናት (እስከ 78 ሚሊዮን ይገመታሉ) በአሜሪካ ምድር ብቻ መወለዳቸውን ለመግለጽ ነው።
የትውልዱ ባህርይ የተገለጸውም “የተሻለው ሁሉ የሚገባው ለእኔ ነው” ባይ ተድርጎ ነው። በዚህ ትውልድ ዘመን የከለር ቴሌቪዥን የተዋወቀበት፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት የተስተዋለበት፣ ወደ ጨረቃ ጉዞ ዝግጅት የተጧጧፈበት፣ አሜሪካ ከቪዬትንም ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችበት፣ የክሬዲት ካርድ በስፋት የሁሉም ሰው መገልገያ መሆን የጀመረበት፣ ኤልቪስ ፕሪስሊን የመሳሰሉ የሙዚቃ ከዋክብት የደመቁበት፣ ቢትልስና ሮሊንግ ስቶን የተሰኙ ባንዶች የገነኑበት ትውልዱም አብሮ ማበድ የጀመረበት ዘመን ነበር። በትውልዱ ዘንድ ከኢንዱስትሪ ምርቶች ይልቅ በዋነኛነት አገልግሎቶች (Services) ተመራጭ ነበሩ።
ሦስተኛው ትውልድ ጄኔሬሽን X (Generation X or Busters) በመባል የሚታወቅ ሲሆን የሚሸፍነው ዘመንም ከ1965 እስከ 1982 ያሉትን አስራ ሰባት ዓመታት ነው። ይህ ዘመን በራሷ በአሜሪካ ውስጥም ሆነ በሌላው የዓለም ክፍል ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች የተስተዋሉበት ዘመን ነበር። ኒል አርምስትሮንግ በአፖሎ 11 ጨረቃ ላይ ያረፈው፣ ቻሌንጀር የተባለችው መንኮራኩር አየር ላይ ጋይታ የተሳቀቁበት፣ አገራቸው በቪዬትናም ጦርነት የሽንፈት ዋንጫ የጨለጠችበት፣ የሃሊ ኮሜት ኮከብ ተከስታ ዓለም የተደመመበት፣ የስቶክ ገበያ አደጋ ላይ የወደቀበት፣ የቴሌቪዥን የመዝናኛ ቻናሎች እንደ አሸን የፈሉበት፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመንን የለየው የበርሊን ግንብ የፈረሰበት ወዘተ. ዓመታት ነበሩ። የሥራ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የተነቃቃበትና የባለሙያዎች የሥራና የዕውቀት ልምድ ከበሬታ ያገኘበት ዘመንም ነበር።
አራተኛው ትውልድ የእሥራ ምዕቱ ትውልድ (Millennias/Generation Y) በመባል የሚታወቅ ሲሆን የሚሸፍነው ዘመንም ከ1983 እስከ 2000 ያሉትን ዓመታት ነው። ይህ ትውልድ የሥራና የሕይወት ፍልስፍናው ትራንስፎርሜሽን (ሥር ነቀል ለውጥ) የሚል ሲሆን “ሕይወትን በካፊቴሪያ እንደምናገኘው አገልግሎት ያህል አቅልለን ማየት ይኖርብናል” የሚል
ፍልስፍና የነበረው ትውልድ ነበር።
በእነዚህ የዓመታት ክልል ውስጥ ዓለም አዲሱን የእሥራ ምዕት (ሚሊኒዬም) በዓል በስጋትና በተስፋ ያከበረችበት፣ አሸባሪነት ለአሜሪካ ከፍተኛ ስጋት የሆነበት፣ ትውልዱም ከፍርሃትና ከውጥረት ለመላቀቅ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፊልሞችን በመመልከት የተጠመደበት፣ የክሬዲትና የዱቤ የንግድ ልውውጦች የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት የተቆጣጠሩበት ዘመን ነበር።
አምስተኛውና የመጨረሻው ዘመን “የX” ትውልድ (Generation X) በመባል ሲታወቅ የሚሸፍነውም ከ2001 እስከ 2015 ያሉትን ዓመታት ነው። የዚህ ትውልድ ዋነኛ መገለጫ በቴክኖሎጂ ፈጠራ መራቀቅ የጀመረበትና የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነቱን እንደ ጣኦት ያመለከበት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ሕይወቱን ማቆራኘት የጀመረበት ዘመን ነበር። በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገራት ልዩ ልዩ አሉታዊና አወንታዊ ክስተቶች መስተዋላቸውም አልቀረም።
ለምሳሌ፡- አሜሪካ አፍጋኒስታንን መውረሯ፣ አብዛኞቹ የእስያ አገራት በሱናሚ አውሎ ነፋስ የደቀቁበት፣ የየአገራቱ ምሥጢሮችና ጠንከር ያሉ የውስጥ ገመናዎች በዊኪ ሊክስ (Wiki Leaks) የመረጃ መረብ እያፈተለኩ በግላጭ አደባባይ የተነዙበት፣ የተራቀቁ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች (3D Movies, Smart TV) የመሳሰሉ የተዋወቁበት፣ ወጣቱ ክሬዲት ካርዱን ለአልባሌ ጉዳዮች እየተጠቀመ ራሱን በዱቤ እዳ ውስጥ የዘፈቀበት፣ የተቦጫጨቀ ጂንስ በመልበስ የሥልጣኔና የፋሽን ምልክት አድርጎ እንዲቆጠርለት ያስተዋወቀበት ዘመን ነበር።
የእኛስ ትውልዶች?፤
የአገሬን ቀዳሚ ትውልዶች በተመለከተ በተለየ ሁኔታ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሥራ ባህል፣ ከሕይወት መርህ ፍልስፍና፣ ከዕውቀት ኀሠሣ ትጋት፣ ከአኗኗር ዘይቤ፣ ከሥርዓተ መንግሥታትና የአገዛዝ ዘይቤና ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች አንጻር እየተነተኑ የሚያሳዩ ጥናቶችን ይህ ጸሐፊ ተሰንዶ ስለማንበቡ እርግጠኛ አይደለም። ጥናቶች ተሰርተው ከሆነም በግላጭ ቀርበው ውይይት ሲደረግባቸው እጅግም አይስተዋልም። አልፎ አልፎ መነካካታቸውን መካድ ግን አይቻልም።
የራስን የመዋጮ ጠጠር መወርወሩ መልካም መስሎ ስለታየኝም “በወፍ በረር ቅኝት” እንዲሉ ለውይይት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ግርድፍና ከዚህም ከዚያም የተቃረሙ ምልከታዎችን ከንባቤ፣ ከታላላቆች ያደመጥኩትን፣ በግሌም የዐይን እማኝ የሆንኩባቸውን ልምድና እውቀቶች በማሰባሰብ የአገሬን የትውልድ ፍሰት በተመለከተ እነሆ የድኅረ ኢጣሊያ ወረራን (1934 ዓ.ም) ማግሥት መነሻ በማድረግ እስከ 2014 ዓ.ም ያሉትን ስምንት አሥርት ዓመታት እንደሚከተለው “በአምስት የትውልድ ዘመናት ከፋፍዬ” የጥናት መነሻ ቅኝት ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ይህ የጸሐፊው የግሉ ምልከታ መሆኑንም ቀድሜ አሳውቃለሁ።
የመጀመሪያው ትውልድ፡- ከ1934 እስከ 1953 ዓ.ም ያለውን የአገር ገንቢዎች ትውልድ (Nation Builders) ይሸፍናል። ይህ ዘመን አገሪቱ ከፋሸስት ኢጣሊያ ወረራ በአሸናፊነት የተወጣችበት፣ የተለያዩ የድል ማግሥት የመብት ጥያቄዎችና የይገባናል ሙግቶች በዋናዎቹ አርበኞች፣ በስደተኞች፣ በውስጥ አርበኞችና በባንዳዎች መካከል የተፋፋመበት፣ በወረራው ምክንያት መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የፈራረሰበትና የተሰነጣጠቀበት ዘመን ነበር።
የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ለመወሰን በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች ግብግብ የፈጠሩበት፣ ኢትዮጵያ በኮሪያና በኮንጎ ጦርነቶች የተሳተፈችበት፣ ወጣቱ ትውልድ አገሩን ለመገንባት ቁርጠኝነት ያሳየበት፣ ለከፍተኛ ትምህርት ውጭ አገራት የተላኩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በጨረሱ ማግሥት አገራቸውን ለማገልገል እየተጣደፉ የመጡበትና መንግሥት በሚመድባቸው የትኞቹም የሥራ መስኮች ሳያመነቱ ለማገልገል የጨከኑበት ዘመን ነበር።
የኢጣሊያ ወራሪዎች ተክለዋቸው የሄዱት አንዳንድ አይረቤ ልምምዶች ሥር መስደድ የጀመሩበት፣ አገሪቱ በዋነኛነት ለትምህርትና ለግብርና ትኩረት የሰጠችበት፣ ፊውዳላዊው የመሬት ቅርምት የተጧጧፈበት፣ የውጭ ዲፕሎማሲው በአንጻራዊ መልኩ በተሻለ አቋም የተጠናከረበት፣ የንግዱ ዘርፍ በዋነኛነት በውጭ አገራት ዜጎች የተያዘበት፣ በወታደራዊ ክፍሎች መካከል መቆራቆስ በግልጥ የተስተዋለበትና በክብር ዘበኛው ጄኔራል በመንግሥቱ ነዋይና በወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ ፊት ቀደምትነት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎ የከሸፈበት ወቅት ነበር። ይህ ጸሐፊ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ከሦስት አሥርት ተኩል ዓመታት በፊት የሠራው የመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ጽሑፍ ዝርዝር ጉዳዮችን በስፋት ዳሷል።
ሁለተኛውን የትውልድ ዘመን “የነውጠኛው ትውልድ ዘመን” (Revo Generation) ብዬ ሰይሜዋለሁ። ዘመኑም ከ1954 እስከ 1966 ያሉትን ያጠቃልላል። ትውልዱ ትምህርትና ለውጥን እኩል ያፈቅር የነበረበት፣ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቁ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በስኮላር ሺፕ የመጡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን “የመሬት ላራሹን” ትግል በአብሮነት የደገፉበት፣ በእውቀታቸው፣ በንባብ ችሎታቸውና በድርሰት ሥራዎቻቸው ከፍታ ላይ የነበሩ ወጣቶች የታዩበት፣ ብሔረተኛ የፖለቲካ ቡድኖች ያቆጠቆጡበት፣ ኢኮኖሚው የተሻለ መነቃቃት ያሳየበት፣ ወታደራዊ መዋቅሩ የተጠናከረበት፣ የድርቅና የርሃብ በላ የተከሰተበት፣ የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን በከፍተኛ ሁኔታ መነቃነቅ የታየበትና የሕዝብ አመጽ ከቁጥጥር በላይ የወጣበት የጋለ የትውልዱ አብዮታዊ ዘመን ነበር።
ሦስተኛው ትውልድ፡- የወታደራዊ አገዛዝ ዘመን (ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም) ትውልድ ሲሆን “የጠፋ ትውልድ” (Lost Generation) ቢባል ተገቢ ስያሜ ይመስለናል። ወታደራዊው ደርግ የንጉሡን ዙፋን የገለበጠበትና ንጉሡን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና የሃይማኖት መሪዎች በገፍ የተጨፈጨፉበት። “ሶሻሊዝም” የፖለቲካው መርህ መሆኑ፣ የእድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ትግበራ፣ የገጠር መሬት አዋጅ፣ የከተማ ትርፍ ቦታና ቤት መውረስ፣ የኢንዱስትሪዎች ወደ መንግሥት ንብረትነት መዛወር፣ እለት በእለት በአዋጆችና መመሪዎች እንደጎርፍ መጥለቅለቅ የታየበት።
የቀይና የነጭ ሽብሮች ፍጅት፣ ድርቅና ርሃብ፣ የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት፣ የሱማሊያ ጦርነት በድል መቋጨት፣ “ከገንጣይ አስገንጣይ” ቡድኖች ጋር የማያባራ ጦርነት፣ ለጦርነት የወጣቶች አፈሳ መጧጧፍ፣ የኢሠፓ መመሥረትና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ ዓለም አቀፉ የሶሻሊስት ሥርዓት መፈራረስ፣ የደርግ መንግስት መሰነጣጠቅና መፈረካከስ ከብዙ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹና የትውልዱን ዘመን የሚወክሉ ናቸው። “ወዛደራዊ አምባገነንነት” የዘመኑ ዋነኛ የፍልስፍና መንፈስ ነበር።
አራተኛው ትውልድ፡- ከ1984 እስከ 1997 ዓ.ም ያሉትን ዓመታት ይወክላል። የትውልዱን ዘመን “የግፈኞች ሰለባ” (The Victimized Generation) ብለን ልንሰይመው እንችላለን። የበረኸኞቹ ጦረኞች ሥልጣን ተቆጣጥረው በትውልዱ ዘመን ላይ የፋነኑበት፣ ዘርና ብሔር ተበታትኖ በየመደቡና በየጓዳው እንደ
ችግኝ የፈላበት፣ የፖለቲካ ቡድኖች እንደ እንጉዳይ ያበቡበት፣ “ነፃ” በሚል ስያሜ የህትመት ውጤቶች እንደ መና የዘነቡበት፣ አድሎና ዘረኝነት ጥግ የደረሰበት፣ ዘረፋ፣ የአየር በአየርና የኮንትሮባንድ ንግድ የተስፋፋበት ዘመን ነበር።
የሀብት ሽሚያ ወደ ባህል ደረጃ ያደገበት፣ የልማት ጅምሮች እዚህም እዚያም የሚስተዋሉበት፣ የእውቀት መስፋፋት ሳይሆን የተዝረከረከ የትምህርት ተቋማት ግንባታ የተስተዋለበት፣ ከኤርትራ ጋር የጦርነት ፍልሚያ የተደረገበት፣ “አንጻራዊ” የሃይማኖት ነፃነት የታየበት፣ የወረቀት ገንዘብ ለውጥ የተደረገበት፣ የሰብዓዊ መብት በአደባባይ እየተጣሰ መከራና ግፍ የናኘበት፣ አገራዊ አንድነት አደጋ ላይ የወደቀበትና አምባገነንነት የደመቀበት ዘመን ነበር። ወጣቶች ሥርዓቱን ለመለወጥ ከፍተኛ ትግል ለማድረግ የጨከኑበት፣ ኢህአዴጋዊ ፖለቲካና የሀብት ቅርምት የተጣመሩበት ዘመንም ነበር።
አምስተኛው ትውልድ (?)፡- ከ1998 እስከ 2014 ያለውን ዘመን የሚወክል ሲሆነ ግራ ገብ ትውልድ (Confused Generation) በማለት ሰይሜዋለሁ። ከ97 ምርጫ በኋላ ፖለቲካውንና ሥርዓተ መንግሥቱን በዋነኛነት የሚመራው የሕወሓት ቡድን ከውስጥና ከውጭ የውጥር ተይዞ የሚይዝ የሚጨብጠው የጠፋበት። የጋዜጠኝነት ዋጋ የረከሰበትና ብዙ ባለሙያዎችም የተሰደዱበት፣ መንግሥታዊ እልህና እብሪት በግላጭ የተስተዋሉበት ዘመን ነበር።
እብሪቱም ገዢውን መንግሥት ለውድቀት የዳረገበት፣ ቴክኖሎጂውና ማሕበራዊ ሚዲያው ለትውልዱ “የእስትንፋስ” ያህል የቀረበበት፣ የሥራ ተነሳሽነት መንፈስ በአያሌው እየተዳከመ በአቋራጭ መክበር እንደ ስኬት የሚታይበት፣ የብሔረተኝነት መንፈስ “ከአበባ ወደ ምርት” ፈጥኖ የተሸጋገረበትና ሽበርተኝነት፣ መፈናቀልና ግድያ የተለመደ የዕለት ተዕለት ክስተትና ዜና የሆነበት ዘመን ነበር።
የኖቤል ሽልማት ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተበረከተበት፣ ሳተላይቶች የመጠቁበት፣ የሰሜኑ ጦርነት ትውልዱን እምሽክ አድርጎ የበላበት። ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ፊት የተነሳችበት፣ ግዙፍ አገራዊ የልማት ሥራዎች የተስተዋሉበት፣ የሥርዓተ መንግሥቱ ርዕይና አካሄድ ጥርትና ኩልል ብሎ ስለመፍሰሱ ግራ ያጋባበት፣ ዓለም አቀፉ የኮረና ወረርሽኝ ደጃፍ ያዘጋበት፣ የኑሮ ጫና እንደ ወስከንባይ በሕዝቡ ላይ የተጫነበት፣ እና የሕዝብ ጥያቄ የበረከተበት ሲሆን የአራተኛው ትውልድ ቅጥያና በክፍል ሁለት ገቢርነት ሊታይ የሚችል ነው። ብዙም ማለት ገና ያልጠለሉ ብዙ ጉዳዮች ስላሉ ይህንን የትውልድ ዘመን በይደር ማቆየቱ ይበጃል።
በሰማንያ ዓመት ውስጥ ልክ እንደኛ ከፊውዳሊዝም ወደ “ሶሻሊስት ነኝ ባይ” አምባገነናዊ ወታደራዊ አገዛዝ፣ ብሎም ወደ ብሔር ፖለቲካ፣ እናም “ዲሞክራሲን” አቀነቅናለሁ ወደሚል ሥርዓት የተሸጋገሩ ሌሎች አገራት ስለመኖራቸው ወደፊት ጥናት አድርገን እንመለስበታለን። በአምስቱም ዘመናት ውስጥ በጋራ አገር ከመገንባት ይልቅ በየግል አገር ለማፍረስ የተለያዩ ሙከራዎች የተደረጉባቸው ታሪኮቻችን መልካቸውም ብዛታቸውም የትዬለሌ ሊባል የሚችል ነው።
ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው፡- “አንድ ትውልድ የሚሸፍነው ስንት ዓመት ነው? ከትውልድ ትውልድ የመሸጋገሪያ መለያ ድንበሩስ ምንድን ነው?” – ቁርጥ ያለ መልስ ያልተሰጣቸውን እነዚህን ሁለት ዋና ጥያቄዎች ለመመለስ አዳጋችም ከባድም ነው። ወደፊት ብዙ ጥናትና ምርምር እንደሚጠይቁም ጠቁመን እናልፋለን። በነጥቦቹ ላይ ደፈር ብለን ብንወያይባቸው ይጠቅመናል። ሰላም ለአገሬ፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም