አዲስ አበባ እንደ ‹ሊቃ ዱለቻ›› አልሆነላትም። ኑሮ ከብዷታል፣ ህይወት ፈትኗታል። ታደርገው፣ ብታጣ አንገቷን ደፍታ ማልቀስ ይዛለች። እየጨነቃት ነው። ዘወትር ሀዘን ከቁጭት፣ ሲያስተክዛት ይውላል። አቀርቅራ ታስባለች፣ በየሰበቡ ሆድ ይብሳታል። ቤተሰቦቿ በዓይኗ ውል ሲሉ ናፍቆቱን አትችልም። ትዝታው ያንገላታታል። ፈጥና ወደቀዬዋ አትመለስ፣ ካገሯ ወለጋ ርቃ መጥታለች። ሁሌም በዕንባዋ ጭጋግ ‹‹ሊቃ ዱለቻ›› ትውስ ይላታል።
‹‹ሊቃ ዱለቻ›› ተወልዳ ያደገችበት መንደር ነው። አካባቢው ክረምት ከበጋ ያመርታል። የገጠሯ ጉብል ሌሊሴ ቀጀላ ወላጆቿ አራሽ ገበሬዎች ናቸው። ዕድሜዋ ከፍ ሲል ከግብርናው ንግድን መረጠች። ለእሷ ሥራውን መልመዱ፣ መሸጥ መግዛቱ አልከበዳትም።
ሌሊሴ የቤተሰቦቿን ኑሮ ታውቃለች። ችግረኞች ናቸው። ልጅ ብትሆንም በእሷ ሰበብ ህይወታቸው ቢቀየር፣ ኑራቸው ቢለወጥ ትወዳለች። ይህ ህልሟ በየቀኑ ከተማ አውሎ ይመልሳታል።
ሌሊሴ በሥራዋ ከቤተሰብ መራቋ ለገንዘብ ብቻ አልሆነም። ድንገት ከአንድ ሰው በፍቅር ወደቀች። ስሜቱን ወደደችው። አፍላነቷ እሱን፣ እሱን ብቻ ይላት ያዘ። እንዲህ መሆኑን አልጠላችም። አጋጣሚው ልቧን ክፉኛ ቢያሸፍት ሌላውን መንገድ አሰበች። ከምትወደው ሰው መራቅ፣ መለየት አልፈለገችም። ይህ ሰው ደግሞ ከአካባቢው ሊሄድ እግሩ ተነስቷል፣ ጓዙን ሸክፏል።
ሌሊሴ ይህን ስታውቅ አብራው ልትሄድ ወሰነች። ፍቅረኛዋ ሀሳቧን አልተጋፋም። ወጣቷ ‹‹ቤተሰቤን›› አላለችም። ፈጥና የእጇን ጣለች፣ ንግዷን ተወች ‹‹ ሊቃ ዱለቻ››ን ርቃ ወላጆቿን ትታ ስትወጣ ደስ እያላት ሆነ።
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ለሌሊሴ አዲስ ዓለም ነው። ከዚህ ቀድሞ አታውቀውም። ትጠጋበት፣ ታርፍበት ዘመድ የለም። አሁን ባለቤቷ ከጎኗ ነው። እንዲያም ሆኖ የተመቻት አይመስልም። ለጊዜው ከእሱ ወንድም በቀር ተቀባይ ዘመድ አላገኙም።
ውሎ አድሮ ባልና ሚስት ራሳቸውን ቻሉ። አዲስ አበባ እንደአገራቸው አልሆነም። ኑሮ ይከብዳል፤ የቤት ኪራይ፣ የዕለት ወጪው አይገፋም። እሱ ውሎውን በጉልበት ሥራ መግፋት ያዘ። ህይወት እንዳሰቡት አልሆነም። በእሱ ትከሻ ብቻ ጎዶሎው አልሞላም፣ ሀሳብ አልተሳካም። ጥብ፣ ጭንቅ ሆነ።
ባለቤቷ እንደ ትናንቱ ፈገግታ የለውም። በየሰበቡ ይናደዳል፣ ይበሳጫል፣ ሌሊሴ ሁኔታው እያሳሰባት ውስጧን ታዳምጣለች። ጤና ይሉት የላትም። ደርሶ የሚረብሻት ስሜት እየደጋገማት ነው። እውነቱ አልጠፋትም። መፀነሷን አውቃለች። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ እርግዝናዋ ዕንቅልፍ ነስቷታል።
የእሷ ማርገዝ ለባሏ ጫና ሆኖ መነጫነጩ ቀጥሏል። መሀላቸው ሰላም ጠፍቷል፣ ፍቅር ርቋል። ሌሊሴ እየከፋት ነው። በቸገራት ጊዜ ክፉኛ ታዝናለች፣ ትተክዛለች። ኑሮ እንደትናንቱ ቀጥሏል። ህይወት አልተቀየረም፣ ችግር አልራቀም።
አዲስ እንግዳ
ሌሊሴና ባሏ ህይወትን በአንድ ጎጆ እየመሩ ነው። ኑሮ ባይደላም፣ ቤት ባይሟላም እንደነገሩ ጊዜያት ተቆጥረዋል። አሁን ደግሞ በቤታቸው አዲስ እንግዳ ተቀብለዋል። የምታምር ትንሽ ህጻን ከህይወታቸው ገብታለች። ከሁለት ሶስት የሆኑት ጥንዶች ስጦታቸውን በደስታ ተቀብለዋል።
ሌሊሴ የልጅ እናት ከሆነች ወዲህ ኑሮ ይበልጥ አሳስቧታል። ከዚህ በኋላ የእሷን ጨምሮ ለህፃኗ ብዙ ያስፈልጋል። ዛሬም ኑሮ አልተለወጠም፣ አሁንም ባሏን ለማገዝ፣ ሸክሙን ለማቅለል አቅሟ አልበረታም። ይህ እውነት የጥንዶቹን ሰላም ይሸረሽር ይዟል።
አሁን ትንሽዋ ልጅ ‹‹ድክ ድክ ›› ማለት ጀምራለች። የምታምር፣ ለዓይን የምታጓጓ ቆንጆ ነች። ‹‹ሴና›› በድህነት ጎጆ የተገኘች የጥንዶቹ ፍሬ የዓይን ማረፊያ ናት። ያያትን ሁሉ ትቀርባለች፣ የቀረባትን ትወዳለች። አላፊ አግዳሚው ሴናን አይቶ አያልፍም። እየሳመ ያጫውታታል፣ እያጫወተ ይስማታል።
ሴና የአንድ ዓመት ልደቷን እንዳከበረች በቤቱ አዲስ ነገር ሆነ። አባወራው ለሥራ እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ። ሌሊሴ ባሏ ትቷት መሄዱን ስታውቅ ሰማይ የተደፋባት ያህል ከበዳት። የእሷንና የልጇን ዕጣ ፋንታ እያሰበች በትካዜ ቆዘመች። ብቸኝነት፣ ከባይተዋርነት ተዳምሮ ሆድ ያስብስ፣ ያስለቅሳት ጀመር።
ሌሊሴ ችግሮቿ በረከቱ። አፍ የፈታችበት የኦሮምኛ ቋንቋ የልቧን በወጉ እንዳትናገር ምክንያት ሆነ። ለጠየቋት ሁሉ ምላሽዋ በዝምታ ተዋጠ። ትንሽዋን ሴና ይዛ በዕንባ ከመታጠብ ሌላ ምርጫ አልነበራትም። አሁን ለልጇና ለእሷ ቀለብ፣ ለቤቷም የወር ኪራይ ያስፈልጋል። በእጅጉ ጨነቃት። ‹‹የኔ›› ትለው ወዳጅ ዘመድ ቅርቧ የለም።
ሌሊሴ ቁርጠኛው የችግር ቀን መድረሱን አወቀች። ከሁሉም ህጻኗ በርሀብ ልትቀጣ ነው። የወደፊቱ ክፉ ችግር እየታያት ተብሰለሰለች። የሰው እጅ ለማየት ልምድና ድፍረት ይጠይቃል። ‹‹ቸገረኝ›› ብሎ ለመጠየቅ ብልሀት ያስፈልጋል። ሌሊሴ ይህን ለመሞከር ወኔ ከእሷ ርቋል።
ቆም ብላ ማሰብ፣ ማብሰልሰል ያዘች። አዎ! ‹‹ከመሞት መሰንበት›› ይሻላል። የአዲስ አበባ ሰው እንኳን ልጅ ለያዘች ለሌላውም አይሰሰትም። ያለውን ይሰጣል። ደግማ፣ ደጋግማ ከራሷ ሞገተች፣ ቤት ኪራይ ደርሷል። እየራባት፣ እየጠማት ነው።
ሀሳቧን ዓይምሮዋ በዋዛ አልተቀበለውም። ለቀናት ከርሀብና ከውስጠቷ ስትታገል ቆየች። ሌሊሴ ወደአገሯ መመለስ ፈለገች። ብቻዋን ወጥታ ልጅ ይዛ መመለሱ ከበዳት። ሰው ቤት ሰራተኛ ለመሆንም አሰበቸ። ከነልጇ ለመቀጠር ፈተናው ከባድ ነው። እሱንም ተወችው።
የወዳጅ ምክር
ቀናት ከነችግራቸው እየነጎዱ ነው። ሌሊሴ በዝምታ ያለፈቻቸው ጊዜያት መፍትሄ አላመጡም። አሁንም ጨንቋታል፣ ችግሯን በየቀኑ የምታይ አንዲት ባልንጀራዋ ግን ይበጃል ያለችውን መላ ማመላከት ይዛለች። ሴትዬዋ ጠዋት ወጥታ ማታ የምትመለስ ጎረቤቷ ነች። መንገድ ላይና ቤተክርስቲያን ደጃፍ እንደምትለምን ታውቃለች።
ጎረቤቷ ሌሊሴን ካለችበት መከራ ያሻግራል ያለችው የልመናውን ሥራ ነው። ራሷን ምሳሌ አድርጋ እንድትሞክረው ስትገፋፋት ቆይታለች። ሌሊሴ ይህን በሰማች የመጀመሪያ ቀን ሀሳቧን ስትኮንነው፣ ድርጊቷን ስትቃወመው ውላለች። ልመና አስነዋሪ መሆኑን ነጋሪ አያሻትም። ደጋግማ ባሰበችው ቁጥር በጎረቤቷ ምክር አፍራለች፣ ተሸማቃለች።
አሁን የቤቷ ችግር ብሷል። ልጇን እያጠባች፣ ስታለቅስ ትውላለች እስከዛሬ ጎረቤቷ ያለቻትን ለመቀበል ስትወላውል ነበር። አሁን ግን ሀሳቧን ከመቀበል ሌላ ምርጫው የላትም። ሌሊሴ ሁኔታው ቢከብዳትም ልመናውን ልትሞክረው ወሰነች። ቤት ተቀምጣ ልጇን በርሀብ ከመግደል፣ ራሷም ከመሞት የተባለችውን መፈጸም ግድ መሆኑን አመነች።
የሰው ፊት እሳቱ
አንድ ቀን ማለዳ ሌሊሴ ትንሽዋን ልጅ ይዛ ከመንገድ ዳር ተቀመጠች። ውስጧ ፈርቷል፣ ሰውነቷ ይንቀጠቀጣል። የሰው ፊት እሳት ሆኖ እየፈጃት ነው። ሙሉ አካል ይዞ እጅን ለልመና መዘርጋት እጅግ ይከብዳል። ሌሊሴ ይህን ተቋቁማ መለመኑን ይዛለች። የመጀመሪያው ቀን በቁም የሞተች ያህል ተሰማት። ቀና ብላ የሰው ዓይን ማየት እስኪከብዳት አፈረች፣ ተሸማቀቀች።
በሚቀጥለው ቀን እንደ መጀመሪያው አልሆነችም። ፍርሀቱ ባይለቃትም ጥቂት ለመደችው። ትንሽዋ ሴና ባህሪዋ ይለያል። ያየችውን ትለምዳለች፣ አላፊ አግዳሚው አያልፋትም። የመልኳን፣ ማማር፣ የልጅነቷን ለዛ ያዩ ሁሉ እያቀፉ ይስሟታል። ሴና ፍቅር የሰጧትን ተከትላ ትሄዳለች። ስትመለስ እጇ ባዶ አይሆንም። የተጠቀለለ ብር ታመጣለች።
መሀል አራት ኪሎ ሌሊሴንና ልጇን የሚያዩ ሁሉ ከልብ ያዝናሉ። አብዛኞቹ የምሳ ዕቃቸውን ያካፍሏቸዋል። አንዳንዶች ያልተጎዳ ፊታቸውን እያዩ በሀዘኔታ ያልፋሉ። ጥቂቶች ደግሞ እናት ሌሊሴ ሰርታ እንድትበላ ይመክራሉ። ትንሽዋ ልጅ በየተራ ፀሐይና ብርድ ያገኛታል። ቀን ውላ ማታ ስትመለስ የጠዋት ገጽታዋ ይጠቁራል። እያደገች ቢሆንም ተጎሳቁላለች፣ የዕለት ጉርስ ባታጣም የአካሏ ጉዳት ኑሮዋን ያሳብቃል።
የጎዳናው ላይ ውሎ ቀጥሏል። ሌሊሴ ውስጧ ቢጨነቅም ልመናውን አልተወችም። ወደ ቤት ስትገባ የእጇን ገቢ ትቆጥራለች፣ ሲጠራቀም የቤት ኪራይዋን ይችላል። ቀለባቸውን ይሸፍናል። ከወጪዋ የሚተርፋትን ለይታ ለነገ ታስቀምጣለች። እንዲያም ሆኖ ውስጧ ሰላም ያጣል።
አንድ ቀን የሚያውቋትን ብታገኝ ሊሆን የሚችለውን ታስብና ራሷን ትረግማለች። ካገሯ ወጥታ ለልመና መዳረጓ ደጋግሞ ያሳፍራታል። ሌሊሴ ከልመና ይልቅ ሥራን ትመርጣለች። ካለችበት ሕይወት የሚያወጣትን እያሰበች ነው። አጋጣሚ ሆኖ አንድቀን ጆሮዎቿ መልካም ነገር አቀበሏት። አንድ ድርጅት ሥራን ለሚሹ ሰዎች ራስን እንደሚያስችል ሰማች።
ከተባለችው ስፍራ ስትሮጥ ደረሰች። ድርጅቱ ተገቢውን ጥያቄ አቅርቦ፣ በስልጠና መክሮ ጥቂት መቋቋሚያና ለጀብሎ ንግድ የሚሆኑትን አሟልቶ ሰጣት። ውላ አላደረችም። የያዘችውን ይዛ ማስቲካና ብስኩት መሸጥ ጀመረች። ትናንት በልመና የሚያውቋት መንገደኞች ሌሊሴን ቢያዩ አመሰገኗት። ጥቂት ነገሮች በሳንቲም እየገዙ ብዙ ገንዘብ ይተውላት ያዙ።
የሌሊሴ ገጽታ በፈገግታ ፈካ። ቀድሞ በልመና ከምታገኘው ብር የአሁኑ ጥቂት ገቢ ከልብ አስደሰታት። አንገቷን ቀና አድርጋ የእጇን መሸጥ ልምዷ ሆነ። ከማስቲካና ብስኩት ትርፍ ተነስታ የሞባይል ካርድ ሽያጭ ጀመረች። አዋጣት። አሁን የሠው እጅ እያየች አይደለም። ደስ እያላት ቤቷ ትገባለች።
ከቀናት በአንዱ
ሌሊሴ ልመናን ከሥራ ባየችበት ጎዳና ብዙ ወዳጆችን አፍርታለች። እስከዛሬ እሷንና ልጇን የሚያውቁ ‹‹አይዞሽ፣›› ሲሏት ቆይተዋል። የአንዲት ሴት አቀራረብ ግን ከሁሉም ይለያል። ሄለን የባንክ ሰራተኛ ነች። ለትንሽዋ ሴና ልዩ ፍቅር አላትና አይታት አታልፍም። በየቀኑ የተጠቀለለ ብር ከእጇ ታኖራለች። በፍቅር ራሷን ዳብሳ አቅፋ ትስማታለች።
አንድ ቀን ይህች ወጣት ሌሊሴ ዘንድ ቀርባ ስለእሷ ነገ ያሰበችውን ነገረቻት። የችፕስ ማሽን ከነሙሉ ወጪው ልትገዛላት ማቀዷን ስትሰማ ጆሮዋን ማመን ተሳነው። ከውስጧ እየተሟገተች ጥቂት ቀናት ቆየች። ፈገግታና ዕንባ ፈተኗት፣ ተስፋ ከድንጋጤ ከበቧት። ህልም እንጂ እውነት ያልመሰላት ሀቅ ጊዜው ደረሰ።
ወዳጇ ቃሏን አላጠፈችም። ማሽኑን ገዝታ፣ አስፈላጊውን አሟልታ የኢትዮጵያን ፕሬስ ድርጅት በራፍ አንኳኳች። ፊት ያዞረባት፣ በር የዘጋባት የለም። ሀሳብ ዕቅዷን የተረዱት የድርጅቱ ዋና ሥራአስኪያጅ ሌሊሴን በሚፈለገው መጠን ለማገዝ ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋገጡላት። ይህን የምስራች ለእናት ሌሊሴ ያበሰረችው ሴት ሙሉ የኤሌክትሪክና የውሀ ፍጆታ በነፃ መጠቀም እንድትችል አመቻችታ ሥራውን አስጀመረቻት።
ፈገግታ ያበራው ፊት
እነሆ! ሌሊሴ ታሪኳ ተቀይሯል፣ ትናንት ለልመና የተዘረጉ እጆቿ ዛሬ ለሥራ መጣደፍ ይዘዋል። አሁን የእሷ ጎዳና የልመና አይደለም፣ ፈጽሞ አትፈራም፣ አትሸማቀቅም። እጆቿ ድንች እየጠበሱ ብር ይቀበላሉ። ብር እየወሰዱ ሥራ ይፈጥራሉ። ዛሬ ዕንባዋ ታብሷል። ሀዘኗ ጠፍቷል ። ታሪኳ ተቀይሯል።
ሌሊሴ ደግማ ደጋግማ ፈጣሪዋን ስታመሰግን በጎ የዋሉላትን አትረሳም። ስለማንነታቸው ልዩ አክብሮት አላት። እነሱ ስሟን ለውጠዋል። ህልሟን ፈተዋልና ምስጋናዋ ከልብ ነው። የሌሊሴ ለውጥ በእሷ ብቻ አልቆመም። ልጇ ሴናም ታሪኳ ተለውጧል። አሁን እንደትናንቱ የጎዳና ብርድና ፀሐይ አያገኛትም። እንደቀድሞው የመንገደኛውን ዓይን አታይም።
ዛሬ ሴና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሕፃናት ማቆያ ከሚጠቀሙ ባለመብት ልጆች አንዷ ሆናለች። እናቷ በሥራ ስትውል እሷ በተመቸ ስፍራ ታርፋለች። በዕድሜዋ የሚገባትን፣ ለማግኘት ድርጅቱ ያሻትን አሟልቷል። ጥሩ ለብሳ፣ ጥሩ ተመግባ የእፎይታ ዕንቅልፍ ትተኛለች። አሁን ጥቁረት ክሳቷ ጠፍቷል፣ ቁመቷ አድጓል። ፈገግታዋ ደምቋል።
ሌሊሴ ዛሬ
እናት ሌሊሴ በቀን ከምታገኘው ገቢ ቆጥባ የሳምንት ዕቁብ ትጥላች። ነገ ስለሕፃን ልጇ የሰነቀችው ተስፋም ብሩህ ነው። አስተምራ፣ በወጉ አሳድጋ ዩኒቨርሲቲ የማድረስ ህልም አላት። ወደፊት ሥራዋን አስፍታ ከፍ ያለ ደረጃ ለመድረስ ዛሬ ብርታቷን ልታሳይ ቆርጣለች።
ሌሊሴ የትናንት ህይወቷ ለዛሬ ማንነቷ መሰረት ሆኗል። የዛኔ ሳትወድ የገባችበትን የልመና ታሪክ በጥንካሬዋ ዘግታዋለች። እንደዋዛ ልመናን ልምድ ለሚያደርጉት ደግሞ ከልብ ታዝናለች።
እሷን ወደጎዳና የገፋቻት ባልንጀራዋ ዛሬም ድረሰ ሥራ ይሉትን አታውቅም። የሰውን እጅ ተማምናለችና ልመና ህይወቷ ሆኗል። እሷ ግን ዛሬ በለውጥ መስመር ቆማለች፣ ትናንትን ረስታ፣ ዛሬን አክብራ፣ ነገን ተስፋ ታደርጋለች። ብርቱዋ፣ ጠንካራዋ ፣ የሊቃ ዱለቻ ጉብል ሌሊሴ ቀጄላ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም