«ችግር ብልሃትን ይወልዳል» እንዲሉ የዘንድሮ የሴቶች ቀን አርያችን ከ15 ዓመታት በፊት በድንገት ያጋጠማቸው የልብ ህመም ዛሬ ላይ ከሁለት መቶ ለማያንሱ አረጋውያን ከመሬት አንስቶ የሚንከባከብ ትልቅ የበጎ አድራጎት ድርጅት መከፈት ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ የጥንካሬ አብነት የሆኑት እኚህ ሴት ከሞት አፋፍ መንጭቆ በህይወት ያቆማቸውን ፈጣሪ ጥሪ ተቀብለው እንደ ቀልድ የጀመሯት የበጎ አድራጎት ድርጅት ጧሪ ቀባሪ አጥተው ጎዳና የወደቁ የአገር ባለውለታ አረጋውያን ከመንከባከብ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድም ተምሳሌትነቱን በማስመስከር ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣም የክብረ አረጋውያን መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ወርቅነሽ ሙንኤ በዚህ ስራ ውስጥ ያሳለፉት ውጣ ውረድ ለሌሎች ሴቶች መልካም ተሞክሮ ይሆናል ብሎ በማሰብ እንግዳ አድርጎ ይዞላችሁ ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ በጎ አድራጎት ስራ የገቡበትን አጋጣሚ በማንሳት ውይይታችንን ብንጀምር ?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- ይህንን ራዕይ የጀመርኩት ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ነው። ራዕዩን ግን የተቀበልኩት ከእግዚአብሔር ነው። ይሁንና ራዕዩን እግዚአብሔር ሲሰጠኝ ዝም ብሎ አልሰጠኝም፤ ወይም ሽማግሌዎችን ስለምወድ ብቻ አልሰጠኝም። ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ድንገተኛ የልብ ህመም አጋጥሞኝ ሁለት ጊዜ ሞት አፋፍ ላይ ደርሼ ነው የተመለስኩት። እዚህ አገር ለመታከም ስለማይችል ሐኪሞች ሳይቀሩ እኔ እንደማልተርፍ ደምድመው ነበር። ግን እግዚአብሔር ዕድሜ ቀጥሎልኝ ደቡብ አፍሪካ የመሄድ ዕድል አጋጠመኝና ታከምኩኝ። አራት ቀን ሆስፒታል ቆየሁና በማርፍበት ሆቴል ውስጥ የተለየ ድምፅ ሰማሁ። በነገራችን ላይ ከፈጣሪዬ ጋር ያለኝ ግንኙነት ጠንካራ ነው፤ ደግሞ ሐኪሞች ተስፋ የቆረጡበትን ህመሜን ፈውሶ ዳግም ያቆመኝ በመሆኑ ከምንም በላይ የሱን ፈቃድ ለማድረግ ነው ሁሌም የምተጋው።
በመኝታ ክፍሌ ውስጥ ሆኜ ‹‹ምድሪቷን እየረገሙ የሚሄዱ አረጋውያንን ታነሻለሽ እንጂ አትሞችም! በህይወት ትኖሪያለሽ›› የሚል ድምፅ ሰማሁ። የሚገርመው በዚያ ወቅት በዊልቸር ነበር የምንቀሳቀሰው፤ አይደለም ሌሎችን ከወደቁበት ላነሳ እኔ ራሴ በህይወት ቆይቼ መሄድ እችላለሁ ወይ? የሚለው ነገር አስግቶኝ ነበር። በነገራችን ላይ አረጋውያን የሚለውን ቃል የሰማሁት ያኔ ነው፤ ከዚያ በፊት ሽማግሌ ወይም አዛውንት የሚሉትን መጠሪያዎች ብቻ ነበር የማውቀው። እናም በመጀመሪያ ያደረኩት የቃሉን ትርጓሜ ማወቅ ነው። በተጨማሪም እኔ ብዙ እድሜዬን ውጭ በመቆየቴ እዚህ ስመጣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ባይም በዚህ ደረጃ አረጋውያን ጧሪ ቀባሪ አጥተው መንገድ ላይ ወድቀዋል የሚል መረጃም አልበረኝም።
እናም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አረጋውያን ለአገራቸው ብዙ ዋጋ ከፍለው ሳለ በመጣላቸው ምክንያት ምድሪቷን እየረገሙ ስለመሄዳቸው ማሰብ ጀመርኩኝ፤ የኢትዮጵያ አለመባረክ ምክንያት ይህ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩኝ። በዚህ ጉዳይ ላይ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችን አማካርኩኝ። ግን ደግሞ ብዙዎቼ ባለቤቴ አምባሳደር በመሆኑ ምክንያት ከመንግስት ስራ ጋር አብሮ አይሄድም የሚል ጥርጣሬ አደረባቸው። ሁሉም ሰው ተቃወመኝ። ደግሞም በዚያ ጊዜ የበጎ አድራጎት ስራ ሲባል ሁሉም ሌባ ነው ስለሚባል ከባለቤቴ የፖለቲካ ስራ ጋር አብሮ ማስኬድ በጣም አስቸጋሪ ነው። በሌላ በኩል ከእኔ ቀጥተኛ ተናጋሪነትና ባህሪ አንፃር አይሄድም የሚልም ስጋት አጭረውብኝ ነበር። በዚህ ምክንያት ትንሽ ጥርጣሬ ስላደረብኝ በመጀመሪያ ቤት ለቤት እየዞርኩኝ ለመርዳት ወሰንኩኝና ጀመርኩኝ።
እናም መገናኛ አካባቢ አምስት አረጋውያንን መረጥኩና ቤታቸውን ሰራንና የተለያዩ ድጋፎችን አደረኩላቸው።
በወቅቱ በዚያ ጊዜ ካየሁት ችግር አንፃር አረጋውያን ምድራቸውን እየረገሙ ነው የሚሙት የሚለውን ነገር ትክክል እንደሆነ ለማየት ችያለሁ። በየቤቱ ጓዳ ውስጥ ገብተሽ ስታይ የሚኖሩበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪና አሳዛኝ ነው። ለእነዚያ ሰዎች እየከፈልኩኝ ቁርስ ምሳ እራት ማብላት ቀጠልኩኝ። ወጣቶችን በማስተባበር የአረጋውያኑን ቤት ሳይቀር እናፀዳ ነበር። ይሁንና በጤናዬ ምክንያት በየሶስት ወሩ ደቡብ አፍሪካ ለክትትል እመላለስ ነበር። አንድ ጊዜ ከሄድኩበት ስመለስ እኛ የምንረዳቸው አንድ የቀድሞ ሰራዊት አባል የነበሩ ሰው የሚያያቸው ሰው አጥተው ሞተው ደረስኩኝ። በዚህ ጊዜ በጣም አዘንኩኝ፤ እናም የአምላኬን ትዕዛዝ ማሰብ ጀመርኩኝ። እግዚአብሄር ሰብሳቢ እንጂ ቤት ለቤት እየዞርሽ አግዣቸው እንዳለለኝ ስረዳ የቤት ለቤቱን ድጋፍ አቁሜ በአንድ ላይ ሰብስቤ ለማኖር ወሰንኩኝ።
ይሁንና በወቅቱ ምንም አይነት ገንዘብ ስላልነበረኝ እንዴት ብዬ እንደምጀምር አላውቅም ነበር። በተጨማሪም ሕጋዊ ለመሆን አስቀድሞ የፕሮጀክቱን ፕላን መስራት እንዳለብኝ አንዳንድ ሰዎች ነገሩኝ። ያኔ ደግሞ ፈቃድ የሚሰጠው ፍትሕ ሚኒስቴር ነበር። አጠቃላይ ፈቃድ የማግኘት ሁኔታ በጣም ፈታኝ ነበር። እነሱ እንዳሟላ የጠየቁኝ ጥያቄ ሕጉን መሰረት አድርገው ነው፤ እኔ ደግሞ ራዕይ እንጂ ምንም የሌለኝ በመሆኑ እነሱ የሚጠይቁትን መስፈርት ማሟላት አልቻልኩም። በብዙ መከራ ግን ፈቃዱን ተሰጠኝ፤ ግን ቶሎ አልጀመርኩም። ምክንያቱም ቤት መከራየት ነበረብኝ፤ አረጋውያንን ከየት እና እንዴት እንደምሰበስብ አላውቅም ነበር። ማነውስ ለእኛ የሚሰበስብልን? የተቸገሩ መሆናቸውንስ እንዴት ነው የምናውቀው? የሚሉት አሳስበውኝ ነበር።
‹‹ክብረ አረጋውያን›› የተባለ ድርጅት ከአቋቋምኩኝ በኋላ የመጀመሪያ ስራ ያደረጉት ስለአረጋውያኑ ጥናት ማድረግ ነበር። ከባለቤቴ ጋር በመሆን ያለችንን ትንሽ ብር አሰባስበን ቤት ተከራየሁ፤ ሁለት ሰራተኞችን ቀጠርኩኝ። ግን ቤቱ ምንም ዕቃ አልነበረውም፤ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወሳኝ የሚባሉ አልጋና ሌሎች እቃዎች ማሟላት አልቻልንም ነበር። አንድ ቀን አንድ ሰው ልጄን ትምህርት ቤት ያገኘውና መልኩ ከአባቱ ጋር ስለሚመሳሰል ‹‹የአምባሳደር ተሾመ ቶጋ ልጅ ነህ?›› ብሎ ይጠይቀዋል። ልጄም መሆኑን አረጋገጠለትና ስልክ ቁጥሬን ወስዶ ደወለልኝ። መቼም እግዚአብሔር አመጣጡና መንገዱ አይታወቅም። በዚያ ሰው አማካኝነት ሌሎች ሰዎች ተዋወኩኝና ስለጀመርኩት ስራ አጫወትኳቸው፤ የሚገርመው ግን ልመና እንኳን አልችልበትም ነበር።
እነዚያ ሰዎች ድርጅቴን ሊጎበኙ ሲመጡ ባዶ ቤት ሆነው ሲያዩት የሚያስፈልገውን ጠየቁኝ። እኔም ፈጠን ብዬ አልጋ፤ ፍራሽ፤ አንሶላ፤ ብርድልብስ እንደሚያስፈልግ
ነገርኳቸው። የተወሰነው ሰው አልጋልብስ፤ ሌላው ብርድልብስና አንሶላ አመጣለሁ ብሎ ቃል ገቡልኝ። ከዚያ 20 አልጋ እንደሚገዙልኝ ነገሩኝ። የሚገርምሽ ያንጊዜ 250 ብር የተገዛው አልጋ አሁንም ድረስ ነው እየተጠቀምንበት ያለው። ቃል በገቡት መሰረት 20 አልጋ፤ ፍራሽ ገዙልኝ፤ አንሶላና በረድ ልብሱንም አመጡልኝ። በዚያ መነሻ አድርገን አንዲት አረጋዊት ተቀብለን መንከባከብን ጀምረን፤ ከዚያ በኋላ ቁጥራቸው እያደገ መጣ።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ማህረሰብ አቀፍ ስራም እንሰራ ነበር፤ በተለይም አቅም የሌላቸውን ሴቶችን ወፍጮ ቤት፤ ሻወርና መፀዳጃ ቤት ገንብተን አከራይተው እንዲጠቀሙ አድርገናል። አሁን ድረስ በብዙ በመልሶ ግንባታ ፈረሰባቸው እንጂ በወቅቱ ቤቶቻቸው በጣም ያረጁ ሴት አረጋውያንን ቤት አፍርሰን ገንብተናል። እነዚያ ሰዎች ስናገኛቸው አይደለም ሰው እንስሳ እንኳን ይኖርበታል ተብሎ የማይጠበቅ ነበር፤ ሰው በሕይወት እያለ በተኛበት ትልና ነፍሳት ሲበላው ያየሁት ያኔ ነው። እኔ ራሱ እነሱን ስረዳ የዚያ እጣ ፈንታ ተካፋይ የሆንኩባቸው ገጠመኞች ብዙ ናቸው። ጉንዳን ይዞኝ መንገድ ላይ ልብሴን አውልቄ ያራገፍኩበት ቀንም አለ። ከዚያ በኋላ ነው ሰዎች መክረውኝ ተባይ የማይዝ ቆዳ ልብስና ቦት ጫማ እየለበስኩኝ አረጋውያኑን ማንሳት የጀመርኩት።
አዲስ ዘመን፡- አረጋውያኑን በምን መስፈርት ነው የምትመርጧቸው?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- በአብዛኛው የሚመርጡልና በትክክል ችግረኛ መሆናቸውን ለይተው የሚሰጡን የከተማዋ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሰዎች ናቸው። ይሁንና እኛም ብንሆን ስራውን የጀመርነው እነዚህ አረጋውያን አዲስ አበባ መጥተው ጎዳና ላይ የወደቁበትን ምክንያት በማጥናት ነው። ብዙዎች ልጆቻው በጦርነትና በተለያየ መንገድ ሞተውባቸው ረዳት አጥተው ጎዳና የወጡ ናቸው። አንዳንዱ ደግሞ በሱስ ምክንያት እንደሆነ ተረዳን። ሌሎች ደግሞ በተፈጥሮ መውለድ ባለመቻላቸው ጧሪ ቀባሪ አጥተው ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸውን በጥናታችን ለይተናል። አንዳንዱ ግን ለጠበል መጥተው ‹‹የአዲስ አበባ ህዝብ ደግ ነው›› በሚል ልመና ውስጥ የገቡም አሉ። በዚያ መሰረት ነው እነዚህን አረጋውያን መሰብሰብ የጀመርነው።
አረጋውያኑን ሰብስቤ ምደግፍበት ቤት የአንድ የሐይማኖት ቤት አይደለም። እኔ የፕሮቴስታንት ክርስቲያን እምነት ተከታይ ብሆንም በአብዛኛው የአርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ያሉበት እዲሁም ጥቂት ሙስሊም አረጋውያን የሚኖሩበት የሁሉም ቤት ነው። የኦርቶዶክስ ተከታይ የሆኑ መመልኮስ ሲፈልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ አደርግላቸዋል፤ ለሙስሊሞቹም በፆም ጊዜ ቤታቸው የሚደረግላቸውን ሁሉ እንክብካቤ አደርጋለሁ፤ ሌላው ይቅርና የሙስሊም አልባሳትን መስኪድ ድረስ ሄጄ ለምኜ አመጣላቸዋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በጎ አድራጊነት ስነልቦና ከየት ነው ያዳበሩት መነሻውስ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- በመሰረቱ ያደኩበት ቤተሰብም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ በቸርነትና ለሰዎች በጎ በማድረግ የሚያምን ነበር። በተለይ አባቴ የራሱ ፋርማሲ ያለው በአካባቢው የታወቀ ሐኪም ነበርና ሰዎችን ይረዳ ሲረዳ ነው የኖረው። እኔን ፋርማሲ እንድጠብቅ ሲያደርገኝ ለመጣሁ ሁሉ መድሐኒት በነፃ መስጠት ያስደስተኝ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ሰዎች ተርበው ስመለከት የራሴን ምግብና ውሃ ሳይቀር እሰጥ ነበር። አሁንም ድረስ ሰዎችን መርዳት፤ ያለኝን ሁሉ ማካፋል እጅግ ያስደስተኛል። ካገባሁ በኋላም ከባለቤቴ ጋር ለስራ በምንዞርባቸው አገራት ሳይቀር ለተቸገሩ ሰዎች እንረዳ ነበር። ለምሳሌ ኬኒያ በነበርንበት ወቅት በመጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን እንደግፍ ነበር፤ እርግጥ ደመወዛችን ብዙ የሚያወላዳን ባይሆንም እቤት ያለውን ትርፍ ምግብም ቢሆን መጥተው እንዲወስዱ እናደርግ ነበር። እኔ ቤት ምግብ ኖሮ ሰዎች ተርበው ማየት አልፈልግም።
አሁንም ቢሆን አብሮ መብላትና መካፈል የእኔ የህይወት መርህ ነው። የተከፋ፣ የተቸገረና በህይወት ተስፋ የቆረጠ ሰው በእኔ ትንሽ እርዳታ ቀና ማለትና ዳግሞ ተስፋ ሲያደርግ ማየትን የመሰለ ሌላ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። በመሰረቱ ይሄ ደስታ አንድም የፈጣሪን ትዕዛዝ መፈፀም ነው፤ ምክንያቱም ቃሉ እንደሚለው ለድሀ የሚሰጥ ለእግዚአብሄር ያበድራልና ነው። ደግሞም በዓለም ላይ ሁሉ ነገር ያልፋል፤ ውበት ይረግፋል፤ ሃብት ንብረት ይጠፋል፤ ቁም ነገር ሰርቶ ማለፍ ነገር ትልቅ መታደል ነው። ስለዚህ ለሚያልፍ ዓለም የማያልፈውን ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ትልቅነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ስራ እጅግ ፈታኝና የማይረሱትን ገጠመኝ ያጫውቱን?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- ዱቄት አልቆብን የቤቴን ሁሉ እስከ ማምጣትና ቤተሰቤን ሳይቀር ችግር ላይ እስከመጣል የደረስኩበትን አጋጣሚ መቼም አረሳውም። አንድ ወቅት ላይ 20 አረጋውያን ስንረዳ በነበረበት ጊዜ እንጀራ ጋጋሪዋ ጠርታኝ ስምንት እንጀራ ብቻ መኖሩንና ለእነዚያ ሁሉ ሰዎች እንዴት እንደምትመግባቸው ግራ መጋባቷን ነገረችኝ። እኔ ግን የመለስኩላት መልስ‹‹ እግዚአብሄር የመስዋቱን በግ ያዘጋጃል›› የሚል ምላሽ ብቻ ነበር። ግን ለእሷ እንዲህ ብልም ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ በውስጤ መጨነቄን አላቆምኩም ነበር። ከፈጣሪዬም ጋር ሙግት ውስጥ ገብቼ ነበር። ሕክምናም ያስፈልጋቸው ነበር። በባንክ አካውንቴ ላይ የነበረው ደግሞ 1ሺ 250 ብር ብቻ ነበር። ያ ደግሞ ምንም ሊያደርግ አይችልም ነበር። ምክንያቱም ለአንድ ሰራተኛ ሶስት ሺ ብር ነው የሚከፈለው፤ የቤት ኪራይ 6ሺ 500 ብር መክፈል ይጠበቅብኝ ነበር። ሁሉም ችግር የእኔን ምላሽ ይጠብቅ ነበር፤ ግን ደግሞ ምንም አልነበረኝም ነበር።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ እግዚአብሄር መምጫው ሁሉ የተለየ ነው። አንድ ኬኒያ የምናውቀው ሰው በአጋጣሚ ይደውላል። መታመሜን ሰምቶ ስለነበር ካላየሁሽ አለኝ። በዚህ ጊዜ ይሄ ሰውዬ ከመጣ የሆነ ነገር ሊያደርግልኝ ነው ብዬ አሰብኩኝ። ሰውየው እንዳለሁ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ድርጅቱ ድረስ መጣና አረጋውያኑን ጎበኘ፤ ስለስራዬ ሁኔታ እየተወያየን እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ቆየን። በጣም የሚገርምሽ ይህ ሰው እጁን ወደ ኪሱ በከተተ ቁጥር የሆነ ነገር የሚሰጠኝ እየመሰለኝ አይኔ ከእጁ ላይ መነሳት አቅቶት ነበር። ጊዜው እየመሸ ሲሄድ ሰውየው ዝም ሲለኝ ተናድጄና ተስፋ ቆርጬ በቀልድ ዝም ብሎ በወሬ ከሚያደርቀኝ መኪና ስለያዘ ቤቴ እንዲያደርሰኝ ጠየኩት።
ሰውየው ቤቴ አድርሶኝ እንደተመለሰ በጣም ከፍቶኝ ስለነበር ምርር ብዬ አለቀስኩኝ። እምባ የእሳት ያህል እንደሚፋጅ ያየሁት ያኔ ነው። እነዚህን ሰዎች ምን ላበላቸው ነው? የሚለው ነገር እጅግ አስጨነቀኝ። ልጆቼ በሁኔታዬ ተደናግጠው አሟታል ብለው ለአባታቸው ደወሉለት፤ በወቅቱ ደግሞ ባለቤቴ አጣዳፊ ስራ ስለነበረው ለሌላ ሰው ነገሮ ሐኪም ቤት ሊወስደኝ መጣ፤ የተላከው ሰው ተጣድፎ ሲመጣ እኔ የተለመደውን ስራ ማዕድ ቤት ገብቼ እየሰራሁኝ ነው። ሰላም መሆኔን ነገርኩት። ሌሊት ተነስቼ ግን በአምላኬ ፊት ተንበርክኬ መጮህ ጀመርኩኝ፤ እነዚህን ሰዎች እንድሰበስብ የነገረኝ ራሱ ሆኖ እንዴት እንደዚህ ያደርገኛል? ብዬ ከፈጣሪዬ ጋር ሙግት ያዝኩኝ። እነዚህ ሰዎች ለመደገፍ ዕድሜ ቢቀጥልልኝም፤ እነሱን እንደሚገባ ማኖር ካልቻልኩኝ የእኔንም ህይወት እንዲወስደው ተማጸንኩት። ምክንያቱም ደግሞ የነበረው ሁኔታ እጅግ ተስፋ አስቆርጦኝ ነበር። ‹‹ጀምራ ተወች›› የሚባለውም ነገር አሳስቦኝ ስለነበር በሌሊት እያለቀስኩኝ ከፈጣሪ ጋር ተከራከርኩኝ።
በማግስቱ ጠዋት ያው ሰውዬ ሲደውልልኝ ብዙ ሬስቶራንቶች ስላሉት ትርፍራፊ እንጀራ ሊሰጠኝ እንደሆነ አሰብኩኝ። ያም ቢሆን ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ ለመቀበል ወሰንኩኝ። ጠዋት ቢሮ ስገባ ላንድሮቨር ፒካፕ መኪና ተከትሎኝ መጣ፤ ወጥቼ ስመለከት በመኪናው ሙሉ የተጫነ እህል የያዘ መኪና ነው። ልክ ያንን ሳይ ማንም ይላከው ማን ብቻ ፈጣሪ ጥያቄዬን ሳይዘገይ ስለመለሰልኝ በደስታ ብዛት ዘለልኩኝ። ጎበዝ ዘላይ መሆኔን ያወቅሁት የዚያን ቀን ነው። በኋላ አንዲት ሴት ከመኪናው ወረዱና የማታው ሰው እንደላካቸው ነገሩኝ። እኔ ትርፍራፊ ስጠብቅ እግዚአብሔር ግን አስር ኩንታል ጤፍና ሶስት ኩንታል የስንዴ ዱቄት ነው የተሰጠኝ። የሚገርመው ያንን ያህል እህል የማስቀምጥበት እቃም ሆነ ቦታ እንኳን አልነበረኝም። ሴትየዋን ችግሬን ነገርኳቸውና እሳቸው ጋር ተቀምጦ እኔ በየወሩ እንዳመጣ ተስማማን። በዚህ ብቻ አላበቃም ሴትየዋ ባዩት ነገር እጅግ በመደሰታቸው ምክንያት ሶስት ተጨማሪ ኩንታል ጤፍ፤ ፍሪጅ፤ አልጋ፤ ክራንች፤ የማዕድ ቤት ዕቃዎችና የህክምና መሳሪያዎች በሙሉ ሰጡኝ። ጤፉ የጠፋው ለካ ብዙ ሊያመጣ ነው ብዬ አሰብኩኝ።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ ያለበትን ቦታ ያገኙበት አጋጣሚ ለየት እንደሚል ሰምቻለሁ፤ እስቲ ስለዚህ ሁኔታ ይንገሩን?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- ይህንን ቦታ የሰጠኝ መንግስት ነው፤ ከዚያ በፊት ግን በኪራይ ቤት በጣም ብዙ ዋጋ ከፍለናል። በቤት ኪራይ ብዙ ተጎላልተናል፤ ያም ቢሆን ግን አንድም ቀን ጊዜ አሳልፌ ከፍዬ አላውቅም። አንድ ወቅት ላይ ቀኑ እስከሚደርስ ድረስ ምንም አይነት ገንዘብ አልነበረንም። ደግም የስድስት ወር በአንዴ 35 ሺ ብር ስለሚከፈል ገንዘብ ማጣቴና የቀኑ መድረስ እጅግ አስጨንቆኝ ነበር። በአጋጣሚ ልጄን ከትምህርት ቤት ላመጣ ስሄድ አንድ ሰው ደወለልኝ እንደሚፈልገኝና እዛው ቆሜ እንድጠብቀው ነገረኝ። ሰውየው ምንም ሳልነግረው በቃ ውስጤ አሳስቦኝ ነው ብሎ በካኪ ፖስታ የታሸገ 30 ሺ ብር ሰጠኝ። በዚህ አይነት የእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት በዝቶልን ቀን ከሌለት የሱን ክንድ እያየን እስካሁን አለን።
ወደ ጥያቄሽ ስመለስ አዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራ ጉዳይ ጋር ስንፈራረም በፕሮጀክቱ ከተቀረፀው ሶስት ሚሊዮን ብር ውስጥ 10 በመቶ የሚሆን ገንዘብ አካውንት ላይ መኖር አለበት የሚል ነገር ነገሩኝ። እኔ ግን አካውንት ከከፈትኩበት 50 ብር ውጪ ምንም አልነበረኝም። ያለብኝን ችግር ለኃላፊው አጫወትኳቸው፤ ይሁንና የተቀመጠ ሕግ በመሆኑ እሳቸው ምንም ሊያደርጉልኝ አልቻሉም። አዝኜ ከቢሯቸው ስወጣ አንዲት የተቋሙ ሰራተኛ ምን እንደሆንኩኝ ጠየቀችኝና ሁኔታውን አጫወትኳት፤ ከዚያ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እንድሄድ መከረችኝ። አሁን ላይ ሳስበው ይህችን ሴት እግዚአብሔር የላከልኝ መልዕክተኛ እንደሆነች ነው የምረዳው።
ሴትየዋ እንዳለችኝ በዚያው በኩል ሄድኩኝና ከሰዓት በኋላ ፀሐፊዋ ለ15 ቀን ቀጠሮ እንደተሰጠኝ ነገረችኝ። በዚያ ቀጠሮ መሰረት ከቦርድ አባላት ጋር በመሆን ከንቲባው ቢሮ ሄድኩኝ፤ በአጋጣሚ ሆኖ እኛ የከለከሉኝ የማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እዛው አገኘኋቸው። ከንቲባው ኃላፊውንና እኛን አብረን እንድንገባ አደረጉ። ወቅቱ ደግሞ የአዲስ አበባ ባላደራ ቦርድ አማካኝነት የተሾሙት ከንቲባ ብርሃኑ ደሬሳ ጉዳዮን ከመሰረቱ ጀምሮ ሳጫውታቸው አይናቸውን ለሰከንድ ሳይነቅሉ በተመስጦ ነው ያዳመጡኝ። አሁን ያለብኝን ችግር ሲጠይቁኝ ወደ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ሰውዬ እያመለከትኩኝ ችግሬ እሳቸው ናቸው ብዬ በድፍረት ተናገርኩኝ። እሳቸውም ቢሆኑ ሕግና ደንብ ማክበር ስለሚገባቸው እንጂ ለክፋት ነው ብዬ እንደማላምን አከልኩበት። ግን ደግሞ አረጋውያን ምድራችን ባርከው እንዲሄዱ ከተፈለገ ለአሰራር ማነቆ የሆኑ እነዚህ ህጎች እንዲስተካከሉልኝ ጠየኳቸው። እሳቸው ሁኔታዬን በሚገባ ተረድተው ስለነበር እያመመኝ ለአረጋውያንን ያለኝን ጉልበትና አቅም ሁሉ ሳልሰስት መሰጠቴ በራሱ እንደገንዘብ ተለውጦ በአስቸኳይ ችግሩ እንዲፈታልኝ ማስጠንቀቂያ ሰጡልኝ።
በዚህ ብቻ ሳይወሰን ቤት እንዳሌለኝ ስነግራቸው አዲስ አበባ ውስጥ የቀበሌ ቤት ካለ ፈልገሽ ጠቁሚኝ አሉኝ። በደላላ አማካኝነት እየዞርኩኝ የቀበሌ ቤት ባይኖርም ለመኖር አስቸጋሪ ሆነብኝ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለው ቤቱ ካልሆነልሽ ቦታ ትፈልጊያለሽ? ብለው ጠየቁኝና ሶስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሲኤምሲ አካባቢ 10 ሺ ካሬ የሚሆን መሬት ተሰጥቶኝ ውል ፈረምኩኝ። የሚገርመው ከአራት ቀን በኋላ የባላደራው አስተዳደር ቀርቶ ሌላ ከንቲባ መጣ። ያንን ተከትሎ የተሰጠ መሬት እንዲሁም መስጠት እንዲታገድ ተደረገ። ትንሽ ቆይቶ ወደ መሬት ባንክ እንደሚገባ ሰማን። እኛ ግን ይህንን ሁሉ ከመስማታችን በፊት የህንፃ ፕላን አሰርተንና መስሪያ ገንዘብ ፈጣሪ እንዲሰጠኝ እየጸለይን ነበር። በኋላ ግን አዋጁ ሲታወጅ ባንክ የገባ መሬት ማንም አያወጣውም ብለን ሁሉንም እርግፍ አድርገን ተውነው።
አንድ ወቅት ላይ ፈረንሳይ አገር ሔጄ እንደተመለስኩ ውስጤ ማዘጋጃ ቤት እንድሄድ ተሞላና ቀጥብዬ መሬት አስተዳደር ሄድኩኝ፤ ግን ለምን እንደምሄድ ምንም አላውቅም ነበር። ዝም ብዬ ወደፎቁ እየወጣሁኝ ሳለ አንድ ከረጅም ጊዜ በፊት የማውቀው ሰው አገኘሁና ዝም ብዬ ጉዳዬን አጫወትኩት። ይህንን ሲሰማ ተመልሶ አብሮኝ ኃላፊው ቢሮ ገባንና በአዲስ መልክ ስለድርጅታችንና ለዚህም ስራ በቀድሞው ከንቲባ ተሰጥቶኝ ስለነበረው መሬት ሁኔታ ለኃላፊው አስረዳሁት። ኃላፊው በጣም መልካም ሰው ስለነበር በትዕግስት አዳመጠኝ። የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለነበረው ለአንድ አረጋውያን ድርጅት መሬት መሰጠቱን ግን ደግሞ የትኛው ድርጅት እንደሆነ በውል እንደማያውቅ፤ አጣርቶ እንደሚነግረን እየተናገረ ሳለ የሚመለከተው ሰው በአጋጣሚ ስለዚያው ጉዳይ ከኃላፊው ጋር ለመወያየት ነበር የመጣው። እሱም ያንኑ ነገር አረጋገጠልንና መሬት የተሰጠው ድርጅት ማንነት ለማጣራት መዝገብ ቤት ሄድኩኝ። የመዝገብ ቤቱ ሰራኞች ለካ በቴሌቪዥን ያውቁኝ ኖሮ ገና ሲያዩኝ መሬቱ የተወሰነው ለእኔ ድርጅት መሆኑን አበሰሩኝ። እናም በዚያ መሰረት ነው አሁን ቦሌ ቡልቡላ ያለውን ይህንን መሬት ያገኘሁት። በተጨማሪም የእኔን ስራ በቴሌቪዥን ያዩ ሴት ቤታቸውን ሽጠው ገንዘቡን ለእኛ ሰጡን፤ ከሌሎችም ሰዎች ገንዘብ ፈልገን አሁን በምታይው ቦታ ላይ በርካታ መኝታ ክፍሎችና ቢሮዎችን ሰራን። በዚያ አልተወሰንም ከአራት ዓመት ወዲህ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ህንፃ መገንባት ጀምረን በገንዘብ እጥረት ማጠናቀቅ ሳንችል ቀርተናል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ድርጅት ምንያህል ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል? ለስንት ሰዎችስ ነው የስራ እድል የተፈጠረው?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- ድርጅታችን አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ ወፍጮ ቤት፤ ዳቦ ቤት፤ መፀዳጃ ቤትና ሻወር ከፍቶ ለአንድ ሺ 500 እናቶችና አባቶችን ተጠቃሚ አድርጓል። በድርጅታችን ውስጥ ተቀጥረው በቋሚነት የሚሰሩት 15 ናቸው። በሌላ በኩል እዚህ በድርጅታችን ውስጥ ያሉትንም አረጋውያን ዘንቢል፤ ሽመና እንዲሁም ባልትና እየሰሩ ራሳቸውን የሚደጉሙበት ሁኔታ ፈጥረን ነበር። ሆኖም ኮቪድ ከተከሰተ በኋላ ስራው ቆሟል። ምክንያቱም አረጋውያኑ ተይዘውብን ስለነበር፤ ከስራው በላይ አደጋው የከፋ በመሆኑ ነው በውስጥ የምንሰራውን ስራ ያቆምነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የጓሮ አትክልት እየተከልን ራሳችንን ምንመግብበት ስርዓት ዘርግተናል፤ ሆኖም በአካባቢው ከፍተኛ የውሀ እጥረት በመኖሩ የምንፈልገውን ያህል ማስፋት አልቻልንም። ከዚህ ችግር የተነሳ የራሳችንን የውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር በዝግጅት ላይ ነን ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ስራ ስትጀምሩ ብዙ ሰዎችና ሁኔታዎቹ ተስፋ ቢያስቆርጥም፤ ራዕዮን ተስፋ ሳይቆርጡ ለስኬት በቅተዋል፤ ለመሆኑ እንደርእርሶ ራዕይና ህልም ኖሯቸው ግን በሁኔታዎች ተስፋ ቆርጠው ለተቀመጡ ሴቶች ምን ይመክራሉ?
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- በነገራችን ላይ ባለቤቴን ጨምሮ አንዳንድ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ከነበረኝ ጤና አንፃር ስጋት አድሮባቸው እንጂ እኔን ተስፋ ለማስቆረጥ ብለው አይደለም። ልብ ደግሞ የሰውነታችን ሞተር ነው፤ ድንገት ልብ ከታመመ ህይወት ሙሉ ለሙሉ ሊቋረጥበት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። እናም እኔ የምረዳው ከዚያ አንፃር ለእኔ ከመሳሳት እንደሆነ ነው። በመሰረቱ ባለቤቴ ለዚህ ስራ እዚህ መድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። የሚገርምሽ ይህንን ስራ ከጀመርን ጀምሮ በዓል ቤታችን አክብረን አናውቅም፤ ያለንን ይዘን አብሮኝ ከአረጋውያኑ ጋር ነው የሚያከብረው። እሱ ለፍቶ የሚያገኛትን ገንዘብ ሳይቀር ሳይሰስት ነው ለድርጅት የሚሰጠኝ። እኔ እዚህ ቀን ከሌሊት ስዳክር ልጆቼን ተንከባክቦ ያሳደገው እሱ ብቻውን ነው። አንድ ቀን ገንዘብ አውጥተን ውጪ ሻይ ቡና ብለን አናውቅም፤ በጋራ ተጋግዘን ቤታችን ውስጥ ነው የምንዝናናው።
በአጠቃላይ የባለቤቴን ውለታም ሆነ መረዳት እንዲሁ በቀላሉ የምገልፀው አይደለም፤ በጥቅሉ ፈጣሪ ይክፈለው ነው ማለት የምችለው። በዚህ አጋጣሚ ግን በጣም እንደምወደው ልገልፅለት እፈልጋለሁ። ሌሎቹም ሰዎች ቢሆኑ ከእኔ ባህሪ አኳያ አይሆንላትም ብለው በቀናነት ከማሰብ ይመስለኛል። ምክንያቱም ደግሞ እኔ ፊት ለፊት የማምንበትን የምናገርና የማደርግ በመሆኔ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተግባብታ መስራት ይከብዳል በሚል ስጋት እንጂ በክፋት አልነበረም።
እንደ እኔ ራዕይ ይዘው በስጋት ለተቀመጡ ሴቶች ግን ከእኔ ሁኔታ በመነሳት ልመክራቸው የምፈልገው ነገር አንድን ነገር ለመስራት ካሰቡ የማንም አፍራሽ ሀሳብ መስማት እንደሌለባቸው ነው። የቱንም ያህል ሁኔታዎች ተስፋ የሚያስቆርጡ ቢሆኑም ወድቆ መነሳት እንዳለ ተገንዝበው ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማለት የለባቸውም። በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋ የሚሰጥ እግዚአብሔር የታመነ መሆኑን ማመን አለባቸው። እንዲህ አይነት ስራ ደግሞ በዋናነነት የሚፈልገው ንፁህ ልብና ቁርጠኝነት ነው። ገንዘብ ብቻውን የሚሰራ ነገር የለም። ‹‹እችላለሁ!›› የሚል ልብ ካለ ሁሉንም ማሳካት ይቻላል። ይህንን ስል ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለቴ አይደለም፤ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለማለፍ ዝግጁ መሆን አለባቸው። እንደተባለው ሴቶች ብዙ እውቀትና አቅም ቢኖራቸውም ካደጉበት ማህበረሰብ አስተሳሰብ አኳያ ራሳቸውን እንደደካማ ይቆጥራሉ። ግን ይህ እውነት አይደለም ሁላችንም የተሰጠኝ እምቅ አቅምና እውቀት አለን፤ ልዩነታችን አቅማችን ለመጠቀመ በቆራጥነት መወሰናችን ላይ ነው። እኔ ይህንን አስተሳሰብ ፈፅሞ አልቀበለውም፤ በየቀኑ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስቼ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ሁሉ ብቻዬን ሰርቼ፤ ልጆቼን አብልቼ ትምህርት ቤት አድርሼ ደግሞ ቢሮዬ በሰዓቴ ደርሼ አረጋውያኑን አጥቤ፤ ቁርስ አብልቼ ሌሎች የሚሰሩ ስራችን ሁሉ በተገቢው ጊዜና ሁኔታ ከውኜ ለስኬት በቅቻለሁ። ሌላዋም ሴት እንዲሁ ብቃቷን ማስመስከር ትችላለች ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ ራሳቸውን ማሳነስ የለባቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ስላካፈሉን ተሞክሮ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ወርቅነሽ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን
“እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ!”
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም