ዶክተር ራሄል ባፌ ተወልደው ያደጉት በቀድሞው ከፋ ክፍለ አገር የአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ክልል ዳውሮ ዞን ውስጥ ነው። እድሜያቸውም ለትምህርት ሲደርስ ደግሞ ዋካ ከተማ ውስጥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት ቆይታቸውን አጠናቀዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ከአካባቢያቸው ውጪ ዱራሜ የአሜሪካን ሚሽንና የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ያቋቋሙት አዳሪ ትምህርት ቤት መከታተል ችለዋል።
ዶክተር ራሄል በጣም ጎበዝ የሚባሉ ተማሪ ከመሆናቸው የተነሳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጨርሰው 12ተኛ ክፍል ሲፈተኑም ጥሩ ውጤትን በማምጣት በቀጥታ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ላይ የመመደብ እድልን ያገኙም ናቸው።
“……. በትምህርቴ ጎበዝ ነበርኩ እንደነገርኩሽ ማትሪክ ተፈትኜም ያመጣሁት ውጤት በጣም ጥሩ ስለነበር በቀጥታ ነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት” ይላሉ።
ለቤታቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ዶክተር ራሄል፤ ከአራት ወንድምና ከአራት እህቶቻቸው ጋር በመሆን ጥሩ ቤተሰባዊ ጊዜን ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። በተለይም አባታቸው መምህር መሆናቸው የትምህርትን ጥቅም በውል ስለተረዱት እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ልጆች በትምህርታቸው እንዲጎብዙ መደበኛ ስራቸው አድርገው እንዲይዙት ከማድረግ እስከ ማበረታትና ውድድርን በመካከላቸው እስከመፍጠር የዘለቀ ሚናቸውን ስለመወጣታቸው ያስታውሳሉ።’
እሳቸውን ጨምሮ ልጆቻቸውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የእናታቸውም ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም። በተለይም በወቅቱ እንደ አሁን ዘመን መዋዕለ ህጻናት የሚባል ባይኖርም እናታቸው የፊደል ሰራዊትን ያስተምሩ ስለነበር በልጆቻቸው እድገት እንዲሁም እውቀት ላይ ከፍ ያለ ሚናቸውን ሲወጡም ነበር።
“……..እናቴም ሆነች አባቴ ስለትምህርት ትልቅ ግንዛቤ የነበራቸው በመሆኑ እኛን ለማስተማር ጥረትም አድርገዋል፤ ከአካባቢው ውጪ እንኳን ሄደን እንድንማር ከፍ ያለ እገዛን ያደርጉልን የነበረው ጥቅሙን በመረዳታቸው ነው” በማለት ይናገራሉ።
ዶክተር ራሄል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ይቀላቀሉ እንጂ የትምህርት ሂደቱ ግን ባሰቡት ልክ ጤናማ አልሆነላቸውም ትልቁ ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ነበር፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ፖለቲካው ፈጥሮባቸው የነበረ ችግር በመኖሩ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ባሰቡት ልክ ማስኬድ ሳይችሉ ቀሩ።
“…….አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ትምህርት ክፍል አራት ኪሎ ነበር የገባሁት ነገር ግን ሁለተኛ መንፈቀ ዓመት ላይ የምፈልገውን የትምህርት ዓይነት እንኳን ሳልመርጥ ነው ለማቋረጥ የተገደድኩት፤ በራሴና በቤተሰቤ ችግር ምክንይት ትምህርቴን ባለበት ባቆመውም ራሴን ለማስተዳደር የሚሆን ስራ ግን ለማግኘት አልተቸገርኩም ነበር፡፡ በወቅቱ በትምህርት ሚኒስቴር ስር በነበረ ማስ ሚዲያ ገባሁ፤ ነገር ግን ብዙ ሳልሰራ ለቅቄ ጭነት ማመላለሻ የሚባል ድርጅት ውስጥ ገባሁ” ይላሉ።
ይህም ቢሆን ግን ዶክተር ራሄል የመማር እልሃቸው ውስጣቸው ስለነበር ነገሮች ሲረጋጉና እሳቸውም አረፍ ካሉ በኋላ ዩኒቨርሲቲውን ዳግም ምዝገባ ጠይቀው ፋርማሲ የትምህርት ክፍል በቀን ትምህርታቸውን ለመቀጠል ገቡ። እልሃቸውና ሲማሩም የሚችላቸው ባይገኝም አሁንም ግን በድጋሚ የጀመሩትን መጨረስ ባለመቻላቸው ዳግም ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።
“…….ትምህርቱን አሁንም ለማቋረጥ የተገደድኩት በራሴ የግል ምክንያት ነው፤ ነገር ግን ትምህርቱን ባቋርጥም የራሴን ህይወት መቀጠል ነበረብኝና ስራዬን እየሰራሁ ትዳር መሰረትኩ፤ ልጅም ወለድኩ፡፡ አሁን መረጋጋት እየጀመርኩ ስለሆነ የትምህርት መስኬን ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማህበራዊ ሳይንስ በመቀየር መማር አለብኝ ብዬ ወስኜ ማኔጅመንት ለመማር ገባሁ” ይላሉ።
የማኔጅመንት ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ በሚገባ አጠናቀቁ፤ ከዛም ብዙም ሳይቆዩ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የትምህርት መስክ ለመከታተል ቻሉ። እየሰሩ፣ ቤተሰብ እያስተዳደሩና ልጆች እያሳደጉ በመማርም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአስደሳች ሁኔታ ለማጠናቀቅ ቻሉ።
ከዩኒቨርሲቲ በኋላ በግብረ ሰናይ ድርጅት ወስጥ ስራን የጀመሩት ዶክተር ራሄል፤ በተለይም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲማሩ ከአለቆቻቸው ይደርሳቸው የነበረውን ማበረታታትና ጊዜን የመስጠት ነገር ትልቅ ውለታ እንደሆነ ይናገራሉ ፤ በዚህ አጋጣሚም ያመሰግናሉ።
“…….ማስተርሴን ስጨርስ የሶስተኛ ዲግሪዬን ወይም ዶክትሬቴን ከአሜሪካን አገር ካሊፎርኒያ ከሚገኝ ቪዝን ዩኒቨርሲቲ በሊደር ሺፕ የትምህርት ዘርፍ ለማግኘት ችያለሁ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በቀላሉ የታለፉ አይደሉም ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩበት፡፡ ነገር ግን እኔ ደግሞ ለነገሮች ትኩረት የምሰጥ ለራሴ ግብ አስቀምጬ የምንቀሳቀስ ነበርኩ። ትምህርቴን አቋርጬ ወደትዳር ከገባሁ በኋላም ቢሆን ባለቤቴ በጣም መልካም ሰው ስለነበር ግቤ ጋር እንድደርስ በከፍተኛ ሁኔታ አግዞኛል” በማለት ያሳለፉትን ውጣውረድ ይናገራሉ።
እሳቸውና ባለቤታቸው በከፍተኛ ሁኔታ በመደጋገፍና ፕሮግራም በማውጣት ቤታቸውን ይመራሉ፡፡ በተለይም ለልጆቻቸው ጊዜን ከመስጠት ጀምሮ ትልቅ መስዋዕትነት በመክፈል የተሻለ ትምህርት ያገኙበታል ባሉበት ቦታ አስተምረዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የከፈላቸው ይመስላል፤ ምክንያቱ ደግሞ እሳቸው ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ሲመረቁ የመጨረሻ ልጃቸውም በዶክተርነት ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ስትመረቅ ተገጣጥሟልና፤ ይህ ለዶክተር ራሄል እጅግ በጣም ትልቅ ቦታ ያለውና አስደሳች ሁኔታ ነበር።
ዶክተር ራሄል ‹‹ከልጆቼ ጋር እኩል ነው የተማርነው›› ይላሉ፡፡ በዚህም እሳቸው የእናትነታቸውን እነሱ ደግሞ የልጅነታቸውን እየተረዳዱ ኑሮ ሳይከብዳቸው ኃላፊነት ብቻቸውን ተሸክመው ሳይማረሩ ሁሉም ልጆቻቸው እስከ ሁለተኛና ከዛም በላይ ዲግሪ ተመርቀው በትልልቅ ተቋማት ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ።
ዶክተር ራሄል አገራቸውን በእጅጉ ለማገልገል የሚፈልጉ ከመሆናቸው የተነሳ ልጆቻቸውም ለአገራቸው ፍቅርና ክብር እንዲኖራቸው አድርገው ስለማሳደጋቸው ይናገራሉ ።”……ሁሉም ነገር የሚያምረው በአገር ነው! ከአገር ከወጡ በኋላ ብዙ ችግር አለ፤ ምናልባት ኑሮ ሊመች ይችል ይሆናል፤ ግን ደግሞ ማን እንደ አገር ፤ ልጆቼም የእኔን አይተው ከአገራቸው መውጣት አይፈልጉም ፤ የሚገርምሽ ወንዱ ልጄ የትምህርት መስኩ አርክቴክቸር ነበር፡፡ እናም በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለነበር የኢትዮጵያን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወክሎ በርካታ አገራትን የመዞር እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም አንድም ቀን ግን ወጥቶ ስለመቅረት አስቦ አያውቅም”ይላሉ።
ሴቶች የቤታቸው ራስ ናቸው የሚባለው ያለምክንያት አይደለም፤ የቤቱን የሞላ ጎደለ እንዲሁም የውጪውን ሁኔታ አጣጥመው የመምራቱ ትልቅ ኃላፊነት በጫንቃቸው ስለሚሸከሙ ነው። ዶክተር ራሄልም ቤተሰብን መስርተው ትምህርት እየተማሩ ስራ እየሰሩ ከዚህ ጫና ያመለጡ አልነበሩም ፤ በወቅቱም ብዙ ውጣ ውረድ አጋጥሟቸዋል። ግን ደግም ሴት ነኝ አልችልም ሳይሉ ነገሮችን እንደ አመጣጣቸው እየመለሱ ከባለቤታቸው ጋር እየተጋገዙ ሁሉን አሳልፈዋል።
“……ከልጅነቴም ጀምሮ ሳድግ የተሸናፊነት ስሜት በውስጤ የለም ፤ እንደውም የማይቻል ነገር የለም ብዬ ነው የማምነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ነገር የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለኝ ዝቅ ብዬ ለመስራት የማልሸማቀቅና ችግሩን ለማለፍ የምችል ነኝ፤”ይላሉ።
ዶክተር ራሄል ቀድሞ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፖለቲካን በሩቁ ሲሉ ነው የኖሩት ፤ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ከቤተሰባቸው ጀምሮ በተለይም ሀይማኖትን በተመለከተ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው አባት ስለነበራቸው ፖለቲካና ሀይማኖት አብሮ አይሄድም በሚል ነው ያደጉት። አባታቸውም “ልጆቼ ፖለቲካ ውስጥ አትግቡ ስራችሁን ስሩ አገራችሁንም በሙያችሁ አገልግሉ ” ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ይህም ቢሆን ግን የአገራቸው ፖለቲካዊ ሁኔታ ያሳስባቸው እንደውም እስከ መቼ ነው ሌሎች ሰዎች በእኛ ላይ እንዲወስኑ እያደረግን አገራችንና እኛ የምንፈልገውን ነገር ሳናገኝ የምንኖረው የሚለው ነገር ያሳስባቸው ስለነበር ዶክተር ራሄልም ራሴ ፖለቲካው ውስጥ ገብቼ በመሳተፍ የማመጣውን ለውጥ ማየት አለብኝ ብለው እንደገቡ ይናገራሉ።
“…… በግሌ ሃሳብ ማቅረብ ምክር ቤትም ራሴን ችዬ ተወዳድሬ ቦታ ሊኖረኝ ይችላል ብዬ ማሰብን ጀመርኩ፤ እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው ነገር አባቴ ፖለቲካ ውስጥ እንዳትገቡ ብሎ አሳድጎን አሁን እኔ ደግሞ ፖለቲከኛ ለመሆን ማሰቤ ለራሴ ስላስፈራኝና እሱንም ስለፈራሁት እስኪ በቅድሚያ ላማክረው ብዬ ጠየኩት ፤ ለመጀመሪያ ጊዜም ከእሱ ያልጠበኩት ” እግዚአብሔር ካለው ማን ይከለክላል” የሚል ምላሽ ሰጠኝ፤ በመሆኑም ልብሽ የተሰማውን አድርጊ ሲለኝ በጣም ነበር የተደሰትኩት”በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
“ለመጀመሪያ ጊዜ በ 1983 ዓ.ም መንግስት አደረጃጀቴን በብሔር ብሔረሰብ ነው የማደርገው ሲል የእኛ አካባቢ ወደኋላ እንዳይቀር እንዲመዘገብ ለማድረግ አስችያለሁ፤ በመቀጠልም ወደ ኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ተቀላቀልኩ” ፤ እዚህ ላይ ግን ዶክተር ራሄል ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ይሰሩ ነበርና እነሱ ደግሞ የማንንም የፖለቲካ ድርጀት አባል ስለማይፈልጉ ሁኔታው ቢያስቸግራቸውም ትንሽ ጊዜ በድብቅ የፖለቲካ ስራቸውን ሲሰሩ ቆዩ።
ዶክተር ራሄልን ከፖለቲካው ተሳትፎ የሚያርቃቸው ምክንያት ተፈጠረ በተለይም ባለቤታቸው የኢሰፓ አባል በመሆናቸው ምክንያት ከስራ ሲታገዱ የቤተሰባቸው የመኖር ህልውና በእሳቸው ላይ ወደቀ፤ አሁን የፖለቲካ አባል መሆናቸው ከታወቀ ከስራ ሊሰናበቱ ነው በመሆኑም ለቤተሰባቸው ህልውና መቀጠል ሲሉ ፖለቲካውን አቁመው ስራቸው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግን መረጡ።
“…….ነገሮች ሲስተካከሉና የፖለቲካው ሁኔታ እየባሰ ሄዶ አስገዳጅ የሚሆንበት ሁኔታ ላይ ሲደርስ ሕወሓትም መጥቶ ደርግን እንድንናፍቅ ሲያደርገን ሁላችንም ለአገራችን የድርሻችንን መወጣት አለብን በሚል ውሳኔ ፖለቲካውን ተቀላቀልኩ”ይላሉ።
ፖለቲካ ለሴቶች አስቸጋሪ የሚሆንበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንዱ ባህላችን ሲሆን ሌላው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ አቅማችን ከወንዶቹ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ መሆኑ የቤት እመቤቶች መብዛታቸው ይጠቀሳል፡፡ ከወላጆችና ከባሎች ፍቃድ ውጪ መሆንም ከባድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህን ሁሉ ጫናዎች ተቋቁመው ወደ ፓርቲ ሲመጡ ደግሞ የሚመች ሁኔታ አይፈጠርላቸውም ሞራልም የሚሰጣቸው አያገኙም በዚህ ምክንያት ደግሞ ተሳትፏቸው የወረደ ነው ።
ለምሳሌ ማርች 8 እንቅስቃሴ አሜሪካን አገር ኒዮርክ ከተማ ላይ ነው የተጀመረው፡፡ ይህ ሲጀመርም ሴቶቹ እኩል ስለማይከፈላቸው፣ መብታቸው ስለታፈነ፣ በምክር ቤት መምረጥም መመረጥም አለመቻላቸው የፈጠረው ብሶት ለራሳችን ጉዳይ ራሳችን መነሳት አለብን በማለት እንቅስቃሴ ጀመሩ፤ ይህ እንግዲህ የሚያሳየን ማንኛዋም ሴት ብትሆን መብቷን ለማስከበር ራሷ ካልተነሳች ማንም ስለሷ የሚገደው እንደሌለ ነው።
በመሆኑም ሴቶች በዛን ወቅት ስለ መብታችን ብለው ባይነሱ ኖሮ እውቅናም አያገኙም መብታቸውም አይከበርም ነበር፤ መምረጥም መመረጥም ሳይችሉ ይቀሩ ነበር፤ አሁን ደግሞ በዚህ ዘመን ሴቶች የተከበሩላቸው መብቶች ቢኖሩም አሁንም ብዙ የሚቀር ነገር ስላለ በየዓመቱ ቀኑን ከመዘከር ባለፈ ለመብታችን በመቆም የሚያስፈልገንን መብትና ነጻነት ዋጋ ከፍለን ለማግኘት ዝግጁ ካልሆንን እለቱን ማክበር ብቻውን በስጦታ የሚያሰጠን መብት አይኖርም።
“……..ማርች 8ን ስናከብር እንደ አገር የት ነው ያለነው? የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል። የሴቶች ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሞራላዊ ችግሮች ሁሉ የቱ ጋር ነው ያሉት? ሴቶች ለሚገጥሟት ችግሮች አይሆንም ማለት የምትችልበት አቅም ላይ ናት ወይ ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሴቶች የምትመች አገርስ እየገነባን ነወይ? የሚለው ሊታይ ይገባል” ይላሉ።
ዶክተር ራሄል ባፌ እራሳቸውንና የኢትዮጵያን ሴቶች በመወከል በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ በሰብሳቢነት ለአንድ ዓመት ተኩል አገልግለዋል፤ ሴቶች ወደመሪነት ቢመጡ እንደማያስወቅሱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚችሉ፤ ከእኔ በኋላ ለሚመጡት ይችላሉ የሚለውን ነገር ለማንጸባረቅና የሴቶችን አቅም ለማሳየት ችያለሁም ባይ ናቸው።
‹‹አሁን በጋራ ምክር ቤቱ እንደ ጸሃፊ አያገለገልኩ ነው፤ ይህ ደግሞ አሁንም የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ እንዳለበት የሚያሳይ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም