በ1960ዎቹ ከታተሙ የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ላይ ለንባብ ከበቁ አንዳንድ ዘገባዎች መካከል ለዛሬ የተወሰኑትን ለማስታወስ መርጠናል፡፡ከመረጥናቸው ዘገባዎች መካከል አብዛኞቹ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ዛሬ ላይ ስንመለከታቸው ግርምት ይፈጥራሉ ብለን ያሰብናቸውን ዘገባዎችም ቀነጫጭበን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፡፡
ዝንጀሮዎች ሰው ገደሉ
ጐፋ፤ (ኢ-ወ-ም) በገሙ ጐፋ ጠቅላይ ግዛት በጐፋ አውራጃ በጐፋ ወረዳ ኮስቲ በተባለው ቀበሌ ሺበሺ ሴንሣ የተባለው የ፲፪ ዓመት ልጅ የበቆሎ ሰብል ሲጠብቅ ዝንጀሮዎች በቆሎውን ለመብላት መጥተው ሊያባርራቸው ቢሞክር ተሰብስበው በመያዝ እየጐተቱ የገደሉት መሆኑን የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ በጽሑፍ መግለጣቸውን ዋናው ጸሐፊ አቶ ታደሰ ለገሠ አስታወቁ፡፡(መስከረም 9 ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ባለ የ158 ዓመት ዕድሜ ሰው በኬንያ ተገኙ
ከናይሮቢ ፤(ኤ-ኤፍ-ፒ) ዕድሜዬ ፩፻፶፰ ዓመታት ነው፡፡እ/ኤ/አ/ በ፲፰፻፶፱ ዓ/ም/ ወደ አፍሪካ ከመጡት ከሊቪንግስተን ከሌሎችም ተጓዦች ጋር ተገናኝቻለሁ የሚሉ አንድ ኬንያዊ ገበሬ በአሁኑ ጊዜ ባላቸው አሥር ጋሻ መሬት ላይ የተለመደ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ይገኛሉ፡፡
በናይሮቢ አቅራቢያ የሚገኙት ሳምሶን ሻኰራጎ፤ በአሁኑ ጊዜ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከሚገኙት ብዙ ዓመታት የኖሩ ሰዎች ሁሉ የሚበልጡ አንጋፋ ናቸው፡፡
በታንዛኒያ ውስጥ ዓይናቸውን ተቀድደው ሕክምና ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ በቅርቡ የተደረገላቸው ምርመራ እንደሚያመለክተው ዓይናቸው ድኗል፡፡
የርሳቸውም አባት የናስላንድ ጐሣ ባላባት ነበሩ፡፡ከነበሩዋቸው ፴፱ ሚስቶች ፩፻፵፭ ሴት ልጆችና ፶፰ ወንዶች አስወልደዋል፡፡ከእነዚህ መካከል ፩፻፶፰ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሻኰራጎ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው፡፡
ሻኰራጎ እ/ኤ/አ/ በ፲፰፻፺፮ ዓ/ም/ ተጠምቀው ፕሮቴስታንት እስከሆኑ ድረስ ሦስት ሚስቶች እና 16 ልጆች ነበራቸው፡፡ነገር ግን ፕሮቴስታንት ከሆኑ በኋላ ሁለቱን ሚስቶቻቸውን ፈተው በአንድ ተወስነው ሲኖሩ እ/ኤ/አ/ በ፲፱፻፳ ዓ/ም/ ሚስታቸው በመሞታቸው እ/ኤ/አ/ በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም በ፩፻፳፭ ዓመታቸው አራተኛ ሚስት አግብተው አራት ሕፃናት አስወልደዋል፡፡አራተኛዋ ሚስታቸውም በወሊስ ሞተዋል፡፡
(መስከረም 17 ቀን 19 60 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ልጅዋን በሆስፒታል ጥላ ጠፋች
አዲስ አበባ ፤(ኢ-ዜ-አ) ፤ አንዲት ሴት የሶስት ወር ሕፃን ከፓርላሜንት አካባቢ ይዛ ወደ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ከወሰደች በኋላ ፤ርዳታ ያደረገላትን የቀን ሠራተኛ ‹‹ሕፃኗን የማሳክምበት ካርድ እስካወጣ ይዘህልኝ ጠብቀኝ ›› በማለት ሕፃኗን ጥላ መሔዷን የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አስታወቀ፡፡
ሴትየዋ ይህቺን የሦስት ወር ሕፃን ወደ ሆስፒታሉ የወሰደችው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ነው፡፡በዚህ ጊዜ ርዳታ ያደረገላት አቶ ታምራት በላይ የተባለ የቀን ሠራተኛ ሲሆን ፤ሁኔታውን ለማወቅ የተቻለው እርሱ በሰጠው ቃል መሰረት መሆኑን የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ሹም ጥላሁን ዓሊ አስረድተዋል፡፡ሕፃንዋ ለመጀመሪያ ጊዜ አስፈላጊው ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ፤ የሆስፒታሉ አላፊዎች ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንድትወሰድ ያደረጉ መሆናቸውን የዚሁ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ሹም በተጨማሪ ገልጠዋል፡፡
(መስከረም 27 ቀን 19 60 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ፍየሏ፤ በግና ፍየል በአንድ ጊዜ ወለደች
ጐንደር፤(ኢ-ዜ-አ) በቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት በጐንደር አውራጃ ዘንጋጅ ምክትል ወረዳ ግዛት ውስጥ አንዲት ፍየል አንድ በግና አንዲት ሴት ፍየል ባንድነት ወለደች፡፡
በአንድነት የተወለዱት በግና ፍየል ግልገሎች ሁለቱም የሚገኙ መሆናቸውን የጐንደር አውራጃ ገዢ ፊታውራሪ ተስፋ አስናቀ ገለጡ፡፡
ፍየሊቱ በዘንጋጅ ምክትል ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የአቶ ጫሉ ገሠሠ መሆናቸው ታውቋል፡፡
(መስከረም 27 ቀን 19 60 ከታተመው አዲስ ዘመን)
የዓቢያታና ሻላ ሐይቆች ለዓሣ ማጥመድ ሥራ ተከለከሉ
አዲስ አበባ ፤(ኢ.ዜ.አ) በስምጥ ሸለቆ (ሪፍጥ ቫሌይ) ውስጥ በሚገኘው ብሔራዊ ክልል ያሉት የዓቢታና ሻላ ሐይቆች ለዓሣ ማጥመድ ተግባር የተከለከሉ መሆናቸውን የዱር አራዊት ጥበቃ ትናንት አስታወቀ፡፡
በተጠቀሱት ሐይቆች አካባቢ በዓለም ውስጥ ሊጠፉ የተቃረቡ ፤እንዲሁም በዓለም የማይገኙ ፤ቱሪስትን ለመሳብ የሚችሉ ልዩ ልዩ ብርቅ አእዋፋት አካባቢ በዓለም ውስጥ ሊጠፉ የተቃረቡ ፤እንዲሁም በዓለም የማይገኙ፤ ቱሪስትን ለመሳብ የሚችሉ ልዩ ልዩ ብርቅ አእዋፋት እነዚህኑ አእዋፋት ለማየትና ጥናት ለማድረግ ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ፊልም አንሺዎችና የተፈጥሮ ጥናት ተመራማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሔዱን ድርጅቱ ጠቅሶ ፤አእዋፋቱ ሁለቱ ሐይቆች የሚያፈሩትን ዓሣዎች በመመገብ የማይኖሩ በመሆናቸው ዓሣ ማጥመድ የተከለከለ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በዚህም ምክንያት የስምጥ ሸለቆ ብሔራዊ ክልል ሆነው በሚገኙት ዓቢታና ሻላ ሐይቆች ውስጥ ገብቶ ዓሣ ማጥመድ እንደማይፈቀድና በሁለቱ ሐይቆች ውስጥ የሚገኘው የዓሣ ምርት ‹‹የተፈጥሮ ፀጋ›› ለሆኑት አእዋፋት መኖ መሰጠቱን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በተጠቀሱት ሐይቆች ማኛውም ሰው የዓሣ ማጥመድ ሕግን በመጣስ እንዳያከናውን ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
(የካቲት 23 ቀን 1965 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም