ስለ ኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና የመደጋገፍ አኩሪ ባህል ብዙ ተብሏል። ይህ አኩሪ ባህል “ድሮ ቀረ” እየተባለም ብዙ ጊዜ ታምቷል። በእርግጥ አሁንም ይታማል። እኔ ግን እየተሸረሸረ መጥቷል እንጂ ከቶውንም አልጠፋም ከሚሉት ወገን ነኝ። የመረዳዳት ባህላችን ጠፋ ሲሉት የሚበራ፣የለም ሲሉትም የሚጎመራ አይነት ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በቦረና የተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሳትን ገድሎ በሰውም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስጋት መፍጠሩ ከተነገረ በኋላ የታየው አስደናቂ ርብርብ ትልቅ ማሳያ ነው።
የቦረናን ሕዝብ ለመታደግ በተለያዩ ደጋግና ቅን ግለሰቦች የተጀመረው እርዳታ የማሰባሰብ ርብርብ እጅግ አስደናቂ ነው። ኢትዮጵያውያን የቱንም ያህል በፖለቲካ፣ታሪክና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ተወጥረን ስንነታረክ ብንከርምም የተቸገረን ለመርዳት፣የተራበን ለማጉረስ፣የተጠማንም ለማጠጣት ዛሬም ትልቅ የሞራል ልእልና እንዳልተለየን አረጋግጧል። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ምን መፍጠር እንደምንችል የጥቂት ግለሰቦች ጥረትና ተነሳሽነት ብቻ ትልቅ አቅም እንዳለን ከወሬ በዘለለ በተግባር አሳይቶናል። ጥቂት ግለሰቦች በጣት በሚቆጠሩ ቀናት እንዲህ ትልቅ አቅም ከፈጠሩ ብዙሃን ምን ሊፈጥሩ ይችላሉ? የሚል ቁጭት ግን አሳድሮብኛል። ይህም የመረዳዳት አኩሪ ባህላችን አንድ ችግር ሲገጥመን ብቻ ለምን ይሆናል? በማለት የምንረዳዳበትና የምንደጋገፍበትን ሁኔታ መለስ ብዬ እንዳጤነው አድርጎኛል።
ችግሮች ሲገጥሙን መረዳዳታችን መልካም ነው። ነገር ግን ለምን ችግር ሲገጥመን ብቻ ይሆናል?፣ ይህን የመረዳዳት አኩሪ ባህል ለምን ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድመን አናደርገውም? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ዘግይቶም ቢሆን በችግር ጊዜ የመረዳዳት ባህሉ ካለን አላሰብንበት ይሆናል እንጂ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት መረዳዳት፣መደጋገፍ አይከብ ደንም። ብዙ ጊዜ እንደምናስተውለው ግን ሰው በቁሙ እያለ ከመርዳትና ከመደገፍ ይልቅ ከወደቀ በኋላ መረባረብ ይቀናናል።
አንድ ሰው በችግር ሲንከላወስ ፈጥነን ችግሩን በመጋራትና ቀዳዳውን ባለን አቅም ለመድፈን ከመጣር ይልቅ ችግሩ አደባባይ እስኪወጣ የመጠበቅ ዝንባሌ እንዳለን መሸሸግ አይቻልም። እርግጥ ነው ሰው ከመቸገሩም አስቀድመው የሚችሉትን ብቻ አይደለም የማይችሉትንም ለማድረግ የሚጥሩ ብዙ ደጋጎች አሉ። ከነዚህ ደጋጎች ይልቅ ግን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለሰዎች ችግር ዳተኛ የምንሆን እንልቃለን። አሁን በቦረና በተከሰተው ድርቅ ብቻ ሳይሆን በጦርነትና ሌሎች ችግሮች በገጠሙን ወቅት የመረዳዳት ባህላችን ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ ደግመን ደጋግመን ታዝበናል። ይህ መልካም ነው። በነዚህ ችግሮች ወቅት ለመረዳዳት ያሳየነው ተነሳሽነትና የፈጠርነው አቅም ግን ብዙ ርቀን እንድናስብ ያደርገናል።
ለምሳሌ ያህል አሁን ለቦረናው ድርቅ በጥቂት ግለሰቦች በጣም በአጭር ቀን ትልቅ ነገር መፍጠር ከቻልን እንደ ቦረና ላሉ አካባቢዎች ችግሮች ባይፈጠሩም ቀደም ብለን ውሃ ማቆር የሚቻልበትን ነገር ተረባርበን መፍጠር ብንችል ብዙ ታሪኮችን መቀየር እንችላለን። ትምህርት ቤት ለሌላቸው ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል ለሌላቸው ሆስፒታል ወዘተ መፍጠር ብንችል ስንት ሸክም ማቅለል እንደሚቻል ማሰብ ነው። እኛ ጋር ያለው ልምድ ግን ተቃራኒ ነው፣ ትምህርት ቤት ወይም ሆስፒታል የምንገነባው ወይ በጦርነት አልያም በሌላ ምክንያት ሲፈርሱ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ችግሮችን ለመቅረፍ ቀድመን የማንገኘው ከመረጃ ማጣት ሊሆን ይችላል። ለዚህም ይመስላል አንድን ማህበረሰብ ለመርዳት የግድ ችግሮች ወደ ሚዲያ እስኪወጡ የምንጠብቀው።
አንዳንዶቻችን ደግሞ ቅን ልቦናና አቅም ኖሮን ለችግሮች ቀድመን ለመድረስ የሚያነሳሳን እንፈልጋለን። በእርግጥ የሚያነሳሳን ካገኘን እንኳን ለችግሮች ለመንግስት የልማት ጥሪዎችም እጃችንን ወደ ኪሳችን ለመስደድ ወደ ኋላ እንደማንል ብዙ ማሳያዎችን መደርደር ይቻላል። በተለይም አገራዊ ለሆኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እጃችንን ለመዘርጋት በቅርብ አመታት ውስጥ እንኳን ታሪክ የማይረሳው አሻራ አኑረናል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚህ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ገበታ ለአገር በሚል ተነሳሽነት በአንድ ምሽት የእራት ፕሮግራም ምን መስራት እንደተቻለም እናውቃለን።
እነዚህ የመንግስት ሰፋፊ ፕሮግራሞች ሊሆኑ ይችላሉና ወደ ጎን እንተዋቸው። ታዋቂ ሰዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች ከዚህ ያልተናነሱ በርካታ የማህበረሰብ ችግሮችን ከተፈጠሩም በኋላ ይሁን ከመፈጠራቸውም በፊት መቅረፍ የሚችሉበት ትልቅ አቅም አላቸው። ችግሩ ማን ተነሳሽነቱን ይውሰድ ነው። ተነሳሽነቱን የሚወስድ ካለ የብዙዎችን ተራራ የሚያህል ችግር በጥቂት ቀናት መናድ ይቻላል። ለአብነት ያህል መቄዶኒያን እንመልከት፣ መቄዶንያ ዛሬ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የበርካታ ዜጎች መከታ የሆነው አንድ ሰው በወሰደው ተነሳሽነት ነው። ምናልባትም ቢኒያም በብሩህና ቅን ልቦናው ይህን ነገር ባይጀምር በርካቶች የእሱን አርአያ ተከትለው ለተቀደሰው ተግባር ባልተረባረቡ ነበር። ልክ እንደ መቄዶንያ ሁሉ የልብና የኩላሊት ሕመምተኞችን ለመርዳት የተደረገው ጥረትም የብዙዎችን ሸክም እንዳቀለለ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል።
ከነዚህ በጎ ተግባራት የምንረዳው ነገር ቀድመን የማሰብ እንጂ እጃችንን የመዘርጋት ችግር እንደሌለብን ነው። ቀድመን የአንድ ሰውንም ይሁን የአንድን ማህበረሰብ ችግሮች ማወቅና ለመፍትሄው መረባረብ የሚጀምረው ደግሞ እያንዳንዳችን በቅርባችን ከምናየው ወይም ከሚገጥመን ነገር ነው። መቼም አይነቱ ይለያይ እንጂ የተቸገረ ሰው በዙሪያችን የለም የምንልበት ሁኔታ ላይ እንደማንገኝ ልቦናችን ያውቀዋል። ስለዚህ ይህን የመረዳዳት ባህላችንን በተሻለ ሁኔታ ለማጎልበት ቅድሚያ ከራሳችን እንጀምር። ቅንነት ለዘላለም ይኑር!!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም