ጊዜው ሩቅ አይደለም ።ጉዳዩን ብዙዎች እንደሚያስታውሱት እገምታለሁ።ባልሳሳት ቦታው ‹‹ሰሚት›› ከሚባለው ሰፈር መንገድ ዳር ያለ አካባቢ ነው።ይህ ስፍራ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ በፍጥነት ይካሄድበታል።ወዳጆቼ! ‹‹በፍጥነት›› የምትለውን ቃል የተጠቀምኩት በምክንያት ነው።
በአካባቢው ከሚታዩ ፈጣን ግንባታዎች መካከል በየቀኑ ዕድገቱ የሚጨምር አንድ መለሎ ሕንፃ ‹‹አጀብ›› እያሰኘ ነው።ህንፃው ሸንጡ እየሰፋ፣ አንገቱ እየረዘመ ሽቅብ መገስገሱን ይዟል።ወዳጆቼ አሁንም ‹‹ፍጥነት›› ይሉትን ጨዋታ እንዳትዘነጉብኝ ።
እሁን በየዕለቱ የሚለወጠው ህንፃ ሌላ ዕቅድ ያለው ይመስላል።የታችኞቹ ወለሎች በተለየ መልክ ተቀይረዋል።ክፍሎቹ በማራኪ ቀለም አምረውና ተውበው በርና መስኮታቸው ተገጥሟል ።ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ የታችኞቹ ክፍሎች ግንባር ላይ የባንኮችን ስያሜ የያዙ አርማዎች ተለጥፎባቸዋል ።ልብ በሉልኝ ይህ ሁሉ የሚሆነው የህንፃው ሙሉ ግንባታ በወጉ ሳይጠናቀቅ ነው።ይህን ስነግራችሁ ‹‹እንዲህ መከራየቱ ብርቅ ነው እንዴ?›› ትሉኝ ይሆናል ።እውነት ነው ።ህንፃዎች በወጉ ሳያልቁ ግማሽ አካላቸው ለቅርጫ መቅረቡ ፈጽሞ ብርቅ አይደለም።ደግሞስ ፍጥነትና ሩጫው ለምን ሆነና ከዚሁ ግብ ለመድረስም አይደል?
ወደቀደመው ጉዳዬ ልመለስ ወደ ታላቁ ህንጻ ግንባታ ።ህንፃው ከወገቡ በታች እንዳማረበት ቀጥሏል ።የተከራዩት ባንኮች በወጉ ስራ ጀምረዋል፤ ሌሎችም ቦታውን ይዘው ደንበኞችን እያማተሩ ነው።የታችኛው ወለል ስራ ሲጀምር የላይኛው ክፍል ግንባታ አልተገታም ።ሁሌም የቀን ሰራተኞች ባሬላ ተሸክመው በእንጨት መወጣጫዎቹ ከላይ ታች ሲራወጡ ይውላሉ ።
የተከራዩት አካላት አናታቸው ላይ የግንባታ ማሽኖች እየተራወጡ፣ አቧራና የሲሚንቶ በረከት ሲቅሙ መዋልን ለምደዋል።ሁኔታው ‹‹ወደሽ ከተደፋሽ››ይሉት አይነት ነው።ደግሞስ ሁለት ወዶ ይሆናል እንዴ ? አይሆንም።
ወዳጆቼ! እኛ እኮ የላዩን ሳያጋምሱ የታቹን አስውቦ ስራ ማስጀመር ልክ አስኪመስለን ለምደነዋል።እንዲህ ሲደረግ የግንባታው ጥራት፣የጊዜው ቆይታ ፈጽሞ አይታሰብም።ለሚከሰተው ችግርም ተጠያቂ ይሉት አካል የለም።እንደውም ህንፃው ሊጀመር ገና ጉድጓዱ ሲቆፈር አንስቶ ለወደፊቱ የንግድ ኪራይ የሚሯሯጡ በርካቶች ይመስሉኛል።
የቀደመው ጉዳዬን አልዘነጋሁም ።አሁንም ሰሚት አካባቢ ካለው ህንፃ ላይ ነኝ ።ይህ ህንፃ ዛሬ ከምን እንደደረሰ መረጃው የለኝም።ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነበትን እውነት ግን አሁንም ድረሰ አስታውሳለሁ።ግንባታውንና የንግድ ሂደቱን የጎንዮሽ ሲያጣድፈው የሚውለው ጅምሩ ፎቅ ውሎው በምሽት ሲተካ ለደህንነቱ ጥበቃዎች ሲዞሩት ያመሻሉ።
ጥበቃዎቹ አንድም በኪራይ ላሉት ድርጅቶች ፣ሌላም ደግሞ ለሙሉው የህንፃ ንብረት ቅኝት የሚያደርጉ ናቸው።ከዕለታት በአንዱ ቀን ተረኞቹ በስራ ላይ ሳሉ የተለየ ድምጽ ከጆሯቸው ገባ ።ድምጹ ቆየት፣ ዝግ እያለ የሚያቃስት ነበር።ዘቦቹ የጣር ያህል የሚሰማቸውን አስደንጋጭ ድምጽ ለይተው አስኪያውቁት በእጅጉ ተጨነቁ።
የምሽት ተረኞቹ እያረፈ ወደጆሯቸው የሚደርሰውን ድምጽ ንቀው መተው አልቻሉም።በስጋት እየተያዩ በጥንቃቄ ማዳመጥ ያዙ ።ድምጹ አሁንም ውሉን አልሳተም።በቆይታ እያቃሰተ ወደእነሱ ይደርስል።አስጨናቂው ለሊት እንደምንም ተጋምሶ ንጋቱ ተቃረበ።ጥበቃዎቹ እፎይ ያሉ መሰሉ።
በድንገት ግን አስደንጋጩ ጉዳይ ሁኔታዎችን ቀያየረ ።እንደደራሽ ወንዝ ግልብጥ ያለው ክስተት በሀይለኛ ነጎድጓድ ድምጽ ታጅቦ ስፍራውን በከባድ አቧራ ሸፈነው።ምድር ከሰማይ የተደበላቀ አስኪመስል ፍንድታው ርቆ አስተጋባ።ጅምሩ ህንጻ በራሱ ጊዜ እየፈረሰ፣ እየተናደ ነበር።ደግነቱ ጠርጣራዎቹ ጥበቃዎቹ አስቀድመው ከስፍራው ርቀዋል።
ጠዋት ላይ ጉዳዩ ሲታይና ሲሰማ አንዳንዶች በንብረቱ መውደም እያዘኑ ሁኔታውን በቁጭት አጤኑት።በርካቶች ደግሞ በስፍራው ሰዎች ቢኖሩና የስራ ሰአት ቢሆን ሊፈጠር የሚችለውን ገምተው ተሳቀቁ።በወቅቱ ንብረትም ይውደም፣ ሰዎችም ይሙቱ፣ ዜናው የአንድ ሰሞን ወሬ ሆኖ እንደዋዛ ተረሳ።
በእርግጠኝነት አሁን ላይ መናገር የሚቻለው የወደቀው ተነስቶ፣ የወደመው ተገንብቶ ዳግም ስራው ሊጠናከር እንደሚችል ነው።ይህ አይነቱ አጋጣሚ በአንድም በሌላም በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱን እናውቃለን።ከንብረት መውደም ባሻገር የሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣አካል መጎዳቱን ጭምር ሰምተናል።ሁሌም ግን ከችግሩ በፊት ሳይሆን ከጉዳቱ በኋላ እሳት አጥፊዎች መበራከታቸው የሚያስገርም፣የሚያስተዛዝብ ነው ።
ከሰሞኑ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሆነውን እናስታውስ።በአንድ ህንጻ ግንባታ ላይ የነበሩ ሶስት ወጣቶች በተመሳሳይ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል።ከስፍራው ሲባል እንደተሰማው አደጋው የደረሰው በግንባታው የጥራት ደረጃ ማነስ ምክንያት ነው።ይህ ጉዳይ አስቀድሞ ሊደርስ እንደሚችል ቢገመትም ለሰው ልጆች ትኩረት አልተሰጠምና ህይወት ሊጠፋ ግድ ብሏል።በጣም የሚያስገርመው ጉዳይ ከአደጋው በኋላ ተወሰደ የተባለው ፈጣን ርምጃ ነው።የወጣቶቹን ህይወት ይመልሥ ይመስል የህንጻው ግንባታ ፈቃድ እንዲታገድ ተደርጓል።
እንዲህ መደረጉ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ይሉትን ምሳሌ የሚቃረን ይመስላል።ችግር ከመድረሱ አስቀድሞ ርምጃ መውሰድ ሲቻል ህይወት ከጠፋ ወዲህ የሚደረግ ውሳኔ የይምሰል ጨዋታውን ያደምቃል።አንድን ጉድጓድ ከፍቶ አግርን ከሰበሩ በኋላ ወጌሻ ማፈላለጉ አይጠቅምም።ይልቅስ ከጉዳት በፊት ሜዳውን መደልደልና ለእርምጃ ምቹ ማድረጉ ይበጃል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት ተፈጥሯዊ አደጋ ቢሆንም መሰል ርምጃዎች ተወስደዋል።ለአደጋው መከሰት ምክንያት ናቸው የተባሉና ጥራት የጎዳላቸው ህንፃዎች እየተለዩ እንዲፈርሱ ሆነዋል።ይህ አይነቱን ርምጃ መውሰዱ መልካም ነው ቢባልም ጉዳዩ የዘገየ ነውና ሲቃጠል በቅጠል ከማድረግ አይዘልም።ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ እነዚህ ህንጻዎች ፈርሰው ቢሆን የአደጋውን መጠን መቀነስ ይቻል ነበር።
አንዳንዴ የእኛም ጉዳይ እንዲሁ ነው።ከመሆኑ በፊት ከመጠንቀቅ ይልቅ ከሆነ በኋላ የፈሰሰን ልናፍስ፣ የወደመን ልናቀና ፣ እንሮጣለን ።ይህ እውነት ደግሞ ለማንም፣ ለምንም አይበጅም።ጉዳዩን እንደነበልባሉ ከማድረግ በቀር ።
እሳት ከመቀጣጠሉ፣ ከመንደዱ በፊት በቅጠል ቢያዳፍኑት ፈጥኖ ይጠፋል።ስር ከሰደደ፣ ከፋመ በኋላ ሊቀርቡት ቢሹ ግን ትርፉ ቅጠሉን አያይዞ ራስን ማቀጣጠል ብቻ ይሆናል።ሁሌም ‹‹ሲቃጠል በቅጠል›› ከማጥፋት፣ ሳይቃጠል በቅጠል ማዳፈኑ መልካም ነው።ይህ መልዕክት እንዲህ አይነቱን ድርጊት ለምትደጋግሙ አካላት ‹‹ይድረሰ›› ብለናል።‹‹ሲቃጠል በቅጠል›› ለማጥፋት ለምትጣደፉ ፈጣን ሯጮች ሁሉ።አበቃሁ!
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም