ወይዘሮ እንግዳ ካሳ ስድስት ኪሎ በአካባቢ መኖር ከጀመሩ አራት ዓመታቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ አራት ዓመታት ወስጥ ሁለቱን ዓመት ውሃ ሙሉ ቀን ሳይቆራረጥ ያገኙም እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ውሃ ከመቆራረጡም በላይ ሳይመጣ ሳምንታት ይቆጠራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች መዳረጋቸውን ያብራራሉ፡፡
ውሃ መጣች ብለው ስራ መስራት ሲጀምሩ ወዲያው ትቋረጣለች፡፡ ከዚህ በኋላ ትመጣለች ተብሎ 10 እና 15 ቀን ሲጠበቅ ማሽን ውስጥ ሊታጠብ የገባው ልብስ ሳይቀር ይበላሻል፡፡ ይህ ከሚሆን እያሉ አሁን አሁን ውሃ እያስገዙ ማሳጠብ ጀምረዋል፡፡
ውሃን ትመጣ ይሆናል በሚል ተስፋ በቤት ውስጠ የሚጠራቀመውን ልብስ በእሳቸው ጉልበት የሚታጠብ አለመሆኑን የምትናገረው ልጃቸው ችግሩ በጣም የከፋ በመሆኑ እሷም ሥራ ለብሳ የምትሄደው ልብስ እስከማጣት የምትደርስበት ጊዜ መኖሩን ትናገራለች፡፡ እኛም ባገኘናት ጊዜ በቤት ውስጥ የተከማቸውን ልብስ ለማጠብ ከስራ ቀርታ ውሃ ከሩቅ መንደር እያስገዛች በማጠብ ከላይ ነበረች፡፡ የወይዘሮ እንግዳ ልጅ አክላም ልብስን በዚህ መልክ አጠብን ነገር ግን የግል ንጽህናችንንስ አንዴት እንጠብቅ የት ሄደን ገላችንን እንታጠብ ስትልም ትጠይቃለች፡፡
እዛው ስድስት ኪሎ አካባባቢ የሚኖሩት ሌላዋ ወይዘሮ ውብዓለም ደምሴ ይባላሉ እሳቸውም በውሃ እጦት እየተሰቃዩ ካሉት የአካባቢው ነዋሪዎች አንዷ ናቸው፡፡ እሳቸው አንደሚሉትም ነዋሪው አብዛኛው ጡረተኛ ነው ፣ የመንግስት ሠራተኛም የሆነና በልጆቹም እየተረዳ የሚኖር አለ፡፡ እያንዳንዱ ቤት ውስጥ ቢያንስ ስድስት ቢበዛ እስከ 15 ልጆችና ቤተሰብ ይኖራሉ ፡፡ አሁን ላይ ኑሮ እየከበደ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በየቤቱ ቤተሰብ ማስተዳደር የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ቀለብ ትራንስፖርት በጠቅላላው ብዙ ወጪዎች አሉ ፤ በእነዚህ ላይ የውሃ ወጪ ሲጨመር በእጅጉ እንደሚያማርርም ያብራራሉ፡፡
“እኔ ሥራ የለኝም፡፡ ወጪዎቻችንን በሙሉ የሚሸፍነው ባለቤቴ ነው፡፡ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ውሃ በ25 ብር እንገዛለን ፤ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ደግሞ ባለቤቴን በየቀኑ መጠየቅ ያሰለቻል ፡፡ እኛ በባሎቻችን ሥር ነው የምንተዳደረው፡፡ ባሎቻችን ሴቶች ለብዙ ነገር ውሃ እንደሚያስፈልገን ግንዛቤ ስለሌላቸው ደጋግሞ ገንዘብ መጠየቁ አያሳቀቀን ነው” ብለዋል፡፡ አራት ህፃናት ልጆች እንዳላቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ በተለይ ሦስቱ ትምህርት ቤት የገቡ በመሆናቸው ዩኒፎርማቸውን ለማጠብ ውሃ በየጊዜው ቢያስፈልግም ባለመገኘቱ የቆሸሸ ለብሰው ለመሄድ ተገደዋል፡፡ እንዳንዴም ለእጅ መታጠቢያ የሚሆን ውሃ እያጣን እጃቸውን ሳይታጠቡ የሚበሉበትም ጊዜ መኖሩን ይናገራሉ፡፡
በሰፈሩ ካለው ነዋሪ በተለይ የሴቶች ፤ ከሴቶችም የደረሱ ልጃገረዶች ይበዛሉ የሚሉት ወይዘሮ ውብዓለም ለነዚህ ልጃገረዶቹ ንጽሕና መጠበቂያ ውሃ ያስፈልጋል፡፡ እኔም በቅርቡ የወለድኩ አራስ በመሆኔ ለእኔና ለህጻኑ ልጄ ጽዳት መጠበቂያ ውሃ የግድ ነው፡፡ ነገር ግን ውሃ የለችም፡፡ ውሃ ገዝቶ ሁሉን ለማድረግ ደግሞ ወጪው ኢኮኖሚን የሚፈታተን እየሆነ መጥቷል ይላሉ፡፡
በሌላ በኩልም ሌሊት እየተነሱ ውሃ የሚቀዱት ነዋሪዎች የጀርባ አጥንትና ሌላ የአጥንት ህመም ያላቸው ፤ የእግርና እጅ እንዲሁም የአስም ህመም ታማሚዎች ናቸው፡፡ ከሌሊቱ ስምንት፤ ዘጠኝና 10 ሰዓት ውሃ መጣች ፤አልመጣች በሚል ቁጭ ብለው ያድራሉ? ቀን ሳይተኛ ሌሊት ሳይተኛ እንዴት ይቻላል? መንግሥት ቢሮዎቹን መፈተሽ አለበት፡፡ የውሃ አቅርቦት የሙስና ጉዳይ ሊሆን ይችላልና ሲሉም ወይዘሮ ውብዓለም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ወይዘሮ አፀደ ዓለሙም የዛው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ እንደሚናገሩትም በአካባቢው ከ50 ዓመት በላይ ኖረዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ በመሆናቸው ሌሊት እየተነሱ ውሃ መቅዳቱ በሥራ ገበታቸው ላይ ጭምር ጫና እየፈጠረባቸው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መጣች አልመጣች እያሉ ሌሊት የምትመጣዋን ውሃ በመጠባበቅ ነው የእንቅልፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት፡፡ እንደዚህም ተጠባብቀው ሳትመጣ የምትቀርበትና መጥታም የተደቀነው ባሊ ግማሽ ሳይደርስ የምትቋረጥበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
እያንዳንዱ ቤተሰብ በሥሩ ስምንትና 10 ሰው አለው ዘጠኝ ቤተሰብ ያለው ሊጥ አቡክቶና እንጀራ ጋግሮ፤ ወጥ ሰርቶ፤ ልብስ አጥቦና ጽዳቱን ጠብቆ ማስተዳደር ስለማይቻልም ማልደው ውሃ ፍለጋ መቅጃዎቻቸውን በማሰባሰብ ከሰፈር ውስጥ መኪና ያላቸውን ለምነው ከቤላና ምኒሊክ ሆስፒታል አካባቢ ሊቀዱ ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዴ ታዲያ ረፍዶባቸው ከሥራ የሚቀሩበት ጊዜ አለ፡፡ ቢሄዱም ሌሊት እንቅልፍ አጥተው ስለሚያድሩ ሥራ በአግባቡ ሳይሰሩ ሲያንቀላፉ ውለው ነው የሚመለሱት፡፡
አቶ ጌታቸው በሪሁን እንደሰጡን አስተያየት በተለይ ሴቶች በውሃ እጦት እየተቸገሩ ነው ፤ የሚመለከተው አካል ስለችግሩ ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ ውሃው ከቁልቁለት ወደ ዳገት አይወጣም ነው፡፡ ሆኖም ድሮም ያለነው መድኃኒዓለምና ውሃ ክፍል ፊት ለፊት ዳገት ላይ ነው ፡፡ ቀድሞ 24 ሰዓት ሳምንቱን ሙሉ ውሃ ይኖረን የነበረው በዚሁ ዳገት ተቀምጠን ነው ፡፡ ያኔ ዳገቱ ለምን አልከለከለም ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ በመሆኑም ነዋሪዎች መስመሩ ተለውጧል ወይም የሙስና ሥራ እየተሰራበት ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ውሃ የሚሸጡ ሰዎች እንደ እነሱ ሁሉ ዳገት ላይ መኖራቸውንና 24 ሰዓት ውሃ የሚያገኙበት የነበረ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡ ውሃ ከሱቅ ለሚያመላልሱላቸው ሰዎች 25 ብር ይከፍላሉ፡፡ ልብስ ሲታጠብ በትንሹ 10 ጀሪካን ስለሚገዙ 250 ብር ያወጣሉ። ሆኖም እነሱ ጀሪካን ስለሌላቸውና የሱቁ ጀሪካን ስለማይታጠብ ውሃው ዘይቱ የሚንሳፈፍ በመሆኑ ንጹህና ለምግብ መስርያ የሚያገለግል አይደለም፡፡
“ይሄም ብቻ ሳይሆን አምስት ዓመት አልጋ ላይ የተኛች ልጅ አለችኝ” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ መንግሥቴ ላቀው ይህች ልጅ ወጣት እንደመሆኗ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን መቀየር ብቻ ሳይሆን መንቀሳቀስ ባለመቻሏ ሁሉን ነገር መኝታዋ ላይ ሆና ነው የምትገለገለው፡፡ ለዚህ አገልግሎት ታዲያ በየቀኑ ብቻም ሳይሆን 24 ሰዓት እርዳታ ትፈልጋለች ፤ሌሊት ውሃ ለመቅዳት ደግሞ እጠብቃለሁ“ ሲሉ በምሬት ይህ ችግር ግን የተፈጠረው በአሰራር ዝንፈት ነው ይላሉ፡፡
የሎዛን ሁቴል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል በቀለ ወደ ድርጅቱ ከመጡ ሦስት ዓመታቸው ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን በውሃ እጥረት ምክንያት ድርጅታቸው ሥራ ለመሥራት በእጅጉ ሲቸገር መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ይሄንኑም ምስካይ ሕዙናን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አጠገብ ለሚገኘው ውሃ ልማት አሳውቀዋል፡፡ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸውም ችግሩ በተለይ በሴት ነዋሪዎች ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ከሚገልጽ ማሳሳቢያ ጋር የነዋሪውን ፊርማ አሰባስበው አስገብተዋል፡፡ ሁሌም መልሳቸው መስመሩ ወደ ላይ ወደ ዳገት አይወጣምና ፤ እጥረት አለ እንጂ ይመጣል ነው፡፡
ድርጅቱ በየዓመቱ ከ 100 ሺህ ብር በላይ ለመንግሥት ግብር የሚከፍልና ከስምንት ድርጅቶች በላይ ቢያስተዳድርም የነዚህን ወጪዎች መሸፈን አልቻለም፡፡ ሆቴሉ 17 አልጋ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሳሙኤል ውሃ ለአንሶላ ማጠቢያ ፤ ለሻወር ፤ለቤት ጽዳትና ለብዙ ነገሮች እንደሚያስፈልጋቸው ያነሳሉ፡፡ በየአራት ቀኑ በቦቴ ለማስገልበጥ ሦስት ሺህ ብር እንደሚከፍሉም ነግረውናል፡፡
ይሄን የነዋሪዎቹን ቅሬታ ይዘን ፊት ለፊታቸው ወደሚገኘው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጎራ አልን፡፡ የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ አቶ አምባዬ አሰፋ እንደሚሉት ፤ ” የውሃ ችግር አለብን” ነዋሪዎቹ ከዚህ በፊት ወደ እሳቸው መጥተው ቅሬታቸውን አላቀረቡላቸውም፡፡
የሕብረተሰቡ ቅሬታም ሆነ አራዳን ጨምሮ ለሦስት ክፍለ ከተማ የውሃ ስርጭት መስጠቱን አስታውሰው የሕብረተሰቡ ቅሬታ የቀረበበት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ላይ ውሃን የተመለከተ ሪፖርት ከዚህ ቀደም እንዳልደረሳቸው ተናግረው ቅርንጫፍ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ በፈረቃ እየተሰጠ መገኘቱ የሚታወቅ እንጂ አዲስ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ የውሃ ስርጭት ከኤሌትሪክ ኃይል ጋር የተገናኘ ስለሆነ በተለያዩ ምክንያቶችም የውሃ መቆራረጥ ሊኖር መቻሉንም እውነት ነው ብለዋል፡፡ ፈረቃው በሳምንት አንድ ቀን መሆኑና በዚህ ወቅት መብራት ቢቋረጥ ውሃው ላይደርስ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ የነዋሪዎችን ቅሬታ የተመለከተ ሪፖርትም ደርሷቸው እንደማይውቅ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንደሚናገሩት የነዋሪዎቹ መስመር ነባር ነው፡፡ ሆኖም በባለሥልጣኑ በኩል ይሄን መስመር ለመዝጋትም ሆነ ለመክፈት የተካሄደ ሥራ የለም፡፡ ነገር ግን ችግሩ በተጨባጭ አለ የሚባል ከሆነ ቅርባችን በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ወርዶ ማየት ስለሚገባን ወርደን አይተን እናስተካክላለን›› ብለዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ቅርንጫፉ የካና አራዳን ጨምሮ ለሦስት ክፍለ ከተማ የውሃ ስርጭት ይሰጣል፡፡ የሕብረተሰቡ ቅሬታ የቀረበበት ጉለሌ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ላይ ከአካባቢው መሬት አቀማመጥ ጋር በተያያዘ ውሃ በፈረቃ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ይሄ ውሃ በፈረቃ የሚሰጥበት ፕሮግራም እንደ አገር እየተሰራበት የሚገኝ እንጂ አዲስ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ የውሃ ስርጭት ከኤሌትሪክ ኃይል ጋር የተገናኘ ስለሆነ በተለያዩ ምክንያቶችም የውሃ መቆራረጥ ሊኖር የመቻሉንም ዕውነት ሥራ አስኪያጁ አምነዋል፡፡ ፈረቃው በሳምንት አንድ ቀን መሆኑና በዚህ ወቅት መብራት ቢቋረጥ ውሃው ሊደርስ ማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር መቻሉንም አውስተዋል፡፡
ችግሩ መኖሩን ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ይሄም ችግሩ ለመኖሩ አንድ ማረጋገጫ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዚሁ ቅርንጫፍ አንድ የሥራ ሂደት ኃላፊ ነዋሪዎቹ ያቀረቡትን ቅሬታ ቀደም ብለው ሰምተው የነበረ መሆኑን ነግረውናል፡፡ በመሆኑም በተለይ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት ሩቅ ቦታ ከመሄድ ጀምሮ በይበልጥ ተጎጂ የሆኑበትን የውሃ ችግር ወርዶ በማየት መፍታቱ አግባብ ነው በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም