ጉርሻ ወይም ‹‹ቲፕ›› እንግዶች/ተገልጋዮች በሆቴል ወይም በማንኛው የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ መልካም አገልግሎት(መስተንግዶ) የቀረበላቸው እንደሆነ በፈቃደኝነት የሚሰጡት የማትጊያ ጉርሻ ነው። ቲፕ በስፋት እንደሚስተዋለው በጥሬ ገንዘብ የሚሰጥ ነው፡፡ ቲፕ በሆቴል አገልግሎት ሰጪ ከሆኑ ሰራተኞች መካከል በስፋትና በተለመደው መልኩ ለምግብ ቤት አስተናጋጆችና ለእንግዳ መቀበያ ክፍል ሰራተኞች( እንግዳ ተቀባዮች) ይሰጣል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት፣ እንግዶች (ደንበኞች) የምግብ ቤት አስተናጋጆችን በፊት ለፊት ስለሚያገኙያቸውና ቀጥተኛ መስተንግዶ ከእነርሱ ስለሚያገኙ ነው፡፡ በተለይ ደንበኞች ወደ ሆቴል የሚሄዱት የማደሪያ አገልግሎት ለማግኘት ከሆነ በቅድሚያ የሆቴሉን ገፅታ የሚያገኙት ከእንግዳ ተቀባዮች ነው፣ በመቀጠልም የቆይታቸውን ረጅም ጊዜ የሚያሳልፉት በምግብ ቤት አካባቢ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የስራ ክፍሎች በተደጋጋሚ እንግዶችን የማግኘትና የመርዳት አጋጣሚያቸው በጣም ከፍተኛና የስራቸው ዋና አላማ ነው፡፡
ቲፕ ለአሰሪ ድርጅቶችና ለተቀጣሪ ሰራተኞች ሰፊ ጠቀሜታ አለው፡፡ ቲፕ በቀጥታ የሚያገኘው ግለሰብ የገንዘብ አቅሙን ከፍተኛ ያደርግለታል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም ቲፕ የሚያገኙ አስተናጋጆች በተለየ ሁኔታ ፈጣንና ታዛዥ ናቸው ተብሎ ይታመናል። በሌላ መልኩም ቲፕ የሰራተኞችን የመስራት መንፈስ ያነቃቃል፣ ያወዳድራል፣ የህብረት ስራዎችን ያቀጣጥላል፣ በሰራተኞች መካከል የመተጋገዝ መንፈስ ይፈጥራል ይባላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መልኩ ግን ቲፕ በአግባቡ ያልተያዘና ወጥ ስርዓት የሌለው እንደሆነ ለሰራተኞች ከሚያስገኘው የገንዘብ ጠቀሜታ በዘለለ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፣ እንደውም የፉክክር ባህሪያት፣ ያለመተማመን፣ የአድሎት፣ የልግመኝነት፣ የስራ መርጫ ሁኔታዎችን ያስፋፋል፡፡ ቲፕ ለሁለቱም ወገኖች ተቀሜታ እንዲኖረው ለማድረግ በአንዳንድ ሆቴሎችና ማግብ ቤቶች የሚደረጉ ልማዶች አሉ፡፡ እነዚህ ልማዶች ለሃገራችን የሆቴል ተጠቃሚና ሰራተኞች ያልተለመዱ ይሁኑ እንጂ በሌሎች አለማት መደበኛ አሰራር ናቸው፡፡
ለምሳሌ ያህል ቲፕ ለሁሉም በሚል መርህ አሰሪዎች (ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች) የቲፕ መሰብሰቢያ አንድ ሳጥን በማዘጋጀት ለደንበኞች መስተንግዶ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሰራተኞች እንዲከፋፈሉት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ቲፕ የተሰበሰበው በምግብ አዳራሽ ከሆነ፣ የምግብ ዝግጅት ሰራተኞች፣ የምግብ ቤት ፅዳት ሰራተኞች፣ ዕቃ አጣቢዎች፣ አስተናጋጆች፣ ባር ሰራተኛ፣ ካሸር እና ሌሎች ለምግብ መጠጥ መስተንግዶ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን ሰራተኞች በተለያየ ኮታ መሰረት እንዲከፋፈሉ ይደረጋል፡፡ ይህን አሰራር በውጪ አለም በጣም የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ቲፕ ከመስጠታቸው በፊት ይህንን ሳጥን ይጠይቃሉ፡፡
በኢትዮጵያ በቲፕ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይነሳሉ፡፡ ቲፕ የሚሰጠው ለትላላቅ ሆቴሎች ሰራተኞች ብቻ ነው፣ የቲፕ መጠን ስንት ነው፣ ቲፕ መስጠት ግዴታ ነው የሚሉና ሌሎችም ናቸው፡፡ ቲፕ የእንግዶች በጎ ፈቃድ ነው፡፡ ቲፕ እንግዶች ለተደረገላቸው መልካም መስተንግዶ የማበረታቻ ስጦታ ነው፣ ቲፕ በእንግዶች አቅም መሰረት መሰጠት ያለበት ስጦታ መሆን አለበት፡፡ ለውጭ ሃገር ዜጎች በሚታተሙ የጉዞ መጠቆሚያ ሰነዶች ላይ (GUIDE BOOK) ቲፕ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ግምት ያለው መሆኑንና የቲፕ አሰጣጥ በሆቴሎች ውስጥ ሊሰጥ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም የቲፕ መጠን በሆቴሎች ደረጃ ሊለያይ እንደሚችልም ያስረዳል፡፡ እኛ ጋር ግን ጉዳዩ ተቃራኒ ሆኖ ይታያል። በቲፕ ተቀባይ ሰራተኞች የቲፕ ጠባቂነት (ለቲፕ መቁለጭለጭ) አንዱ ነው፡፡ በብዛት ሰራተኞች እንግዶችን የሚያስተናግዱት ቲፕ እንዲሰጣቸው ነው፡፡ እንግዶችን የሚያስተናግዱት ድርጅቱ በገንዘብ በቀጠራቸው ደሞዝ መሆኑን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ ያው የሚከፈላቸው ደመወዝ ትንሽ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል፡፡ ቲፕ የመልካም መስተንግዶ ማበረታቻ መሆኑን ያለመረዳት ችግርም በስፋት ይታያል፡፡
የደንበኞች የክፍያ ቀሪ ገንዘብ ማረሳሳት፣ ደንበኞች ከመስተንግዶ በኃላ ክፍያ ፈፅመው ተመላሽ ገንዘብ ሊኖራቸው ችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የደንበኞችን ገንዘብ በፍጥነት ባለመመለስ ወይም ዝርዝር የለም በማለት የእንግዶችን መልስ ለማስቀረት መሞከር ሌላው ችግር ነው፡፡ መልስ የግድ መመለስ ካለባቸውም ለቲፕ እንዲመች በማድረግ ዝርዝር ሳንቲም መስጠት የተለመደ ነው፡፡ አድሎ ማድረግ ሌላው ጉድለት ነው፡፡ ሰራተኞች በተደጋጋሚ ቲፕ የሚሰጣቸውንና የማይሰጣቸውን ተገልጋይ በመለየት አድልዎ ማድረግ ከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ሲፈፅሙ ያልገጠመው አለ?፡፡ አድሎ በዚህ ብቻ አይገለፅም ቲፕ የሚሰጡና የማይሰጡ ብሎ እንግዶችን በቅድሚያ መገመትና መጠበቅ ባህሪም ይስተዋላል፡፡
ቲፕ ግዴታ ነው ብሎ ማሰብ፣ እንግዶች ቲፕ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም፡፡ ቲፕ የሚሰጡት በፈቃደኝነት ነው፣ በመሆኑም እንግዶች ቲፕ እንዲሰጡ መገፋፋትና አስገዳጅ ሁኔታዎችን መደርደር ተገቢ አይደለም፡፡ ቲፕ የሚሰጣቸው ሰራተኞች ለእንግዶች በሰጡት መስተንግዶ የራሳቸው ብቻ ጥረት አይደለም፣ ሌሎች ለእንግዶች ያልታዩ ነገር ግን ለምግብ መጠጥ ይሁን ለሌላ መስተንግዶ የሚለፉ ሰራተኞች ከጀርባ አሉ፣ እነዚህን ሰራተኞች ለማካፈልና ለማበረታት ማድረግ የሚችል ቲፕ ተቀባይ አይስተዋልም፡፡
ቲፕ ተቀባዮች ዛሬ ላይ ቲፕ ከሚያገኙበት የስራ ዘርፍ ላይ ወደ ሌላ የስራ መስመር ለመሄድ ፍላጎት ያለማሳየትም አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቲፕ ተቀባዮች ሊያስቡት የሚገባ ጉዳይ መጪው ዘመን ለቲፕ የተመቸ አለመሆኑን ነው፡፡ ቴክኖሎጂ በተስፋፋ ጊዜ የክፍያ ስርዓት እጅግ በተራቀቀና ካሽ በሌለበት መሆኑ አይቀሬ ሲሆን በመመልከት ላይ ነን፡፡ ለምሳሌ ቲፕ በቻይና ክልክል ነው፤ እንደውም ሆቴሎች “ቲፕ ክልክል ነው” ብለው ማስታወቂያ በምግብ ቤታቸው የሚለጥፉም አሉ፡፡ ቲፕ ማግኘቱ ጥሩ ነው፡፡ ቲፕ መልመዱ ግን በጣም አደገኛ ልማድ ነው፡፡ የቲፕ ሱስ የሚመስል ልማድ ያለባቸው ሰራተኞች ዛሬም ቲፕ በማሳደድ ከፍተኛ የስራ ሃላፊነትን የሚሸሹ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ቲፕ ዘወርት ጠባቂነትን መንፈስ ይፈጥራል፣ ገንዘብ በቀላሉ የማግኘት አባዜን ያዳብራል፡፡ የቲፕ ሱስ አደገኛ ነው፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም