ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዘመናትን ተሻግራ የቆመችና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የገነባች ነች። ለዚህ ስኬት አስተዋፅዖ ያበረከቱት የጋራ እሴቶች፣ የደመቁ ታሪኮች፣ ዘመናትን የተሻገሩ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ዕውቀቶቹ ያፈሯቸው ሊቃውንቶች ባቆዩልን ጥበብ ነው። ከሁሉም በላይ ከሺህ ዘመናት በላይ ያስተሳሰራት፤ እህል የሞላውን ጆንያ እንደሚቋጥር ገመድ ዘመንን ከዘመን አሰናስሎ ያሻገራት ዋናው ሰንሰለት በሕዝቦቿ መካከል ያለው መተማመንና ቅንነት ነው።
ሀገር ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ስላላት ብቻ አትፀናም። የተከለለ ድንበር፣ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ስለሆነችም አትቀጥል። ሀገር በእድገትና በአንድነት ወደ ፍፁማዊነት በተጠጋ አብሮነት ወደፊት እንድትራመድ በአንድ ጣሪያ ስር የሚኖሩ ማኅበረሰቦች እርስ በእርስ ከፍፁም ቅንነት የመነጨ መተማመን ሊኖራቸው ይገባል።
ከዘመን ወደ ዘመን ስንሸጋገር አብሮነታችንን፣ መተማመንና አንድነታችንን ፈተና ውስጥ የከተቱ እክሎች የነበሩበት ወቅት እንዳለ የታሪክ ድርሳኖቻችን ቢያስታውሱንም ሰፊውን ድርሻ የሚወስደው ክፍል ግን ታላቅና ባለታሪክ ሀገር መገንባታችንን አስረግጦ የሚነግረን ነው። ለዚህ ነው ካለፉት ስንጥቆቻቸን እየተማርን የዛሬውን ክፍተት መድፈን የብልህ አካሄድ ነው የምንለው።
መተማመን ራዕይን ያፀናል። እርስ በእርስ የሚኖረን መተማመን ወደፊት እንድንራመድና በተስፋ እንድንሞላ የሚረዳን ታላቅ አቅም ነው። ለዚህ ነው በአብሮነታችን ግዜ፤ የጋራ በሆነችው ኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ መግባባትና መተማመን ላይ መድረስ የሚኖርብን።
ባለፉት የፖለቲካ እጥፋቶቻችን ውስጥ ባለመደማመጣችንና ባለመተማመናችን ብዙ ጠባሳና ቁስሎችን አትርፈናል። በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬን ያነገሱ፣ ፍቅርን ያቀዘቀዙና ጭካኔን ያሰፈኑ አያሌ ችግሮች ገጥመውናል። ከእነዚህ ስብራቶቻችን ትምህርት መውሰድ ይጠበቅብናል።
በአንደኛው የታሪክ ክፍላችን 60 እና 70 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ የንጉሡ ሥርዓት ላይ እምነት ያጡ ቡድኖች እንደነበሩ እናስታውሳለን። እነዚህ አዲስ አስተዳደር ለማፅናት ያቀዱ ግለሰቦች እና ሥርዓቱን ሲመራ የነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት በመካከላቸው መተማመን ባለመፍጠራቸውና ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የሚያስችል ባሕል ባለመኖሩ ምክንያት ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል ።
በተለምዶ የታኅሣሥ ግርግር እያልን የምንጠራው ክስተት ኢትዮጵያን ማገልገል የሚችሉና ወደፊት የማራመድ አቅም ያላቸው ግለሰቦችን ከመቅጠፉም ባሻገር መተማመናችን እና ለአንድ አገር በጋራ የመሥራት ባሕላችን ደካማ እንደነበር ማሳያ ሆኖ አልፏል።
በደርግ ዘመነ መንግሥት አዲሱ ሥርዓት መንበረ ሥልጣኑን ሲያፀና በቀድሞው የንጉሡ ሥርዓት ሲያገለግሉ የነበሩ በርካታ ምሑራን ወደ ሞት ተሸኝተዋል። ገሚሶቹም ወደ ከርቸሌ ገብተው እድሜያቸውን ጨርሰዋል። በዚህ ሀገር ዋጋ ከፍላለች። ከዚያ በላይ ግን በአንድነት ለምንኖርባት ሀገራችን በኅብረትና በፍፁም እምነት በውይይት ላይ ተመሥርተን አዲስ መንገድ ለመቀየስ እንደሚተናነቀን ይህ የታሪክ ክፍላችን አንድ ነገር ሹክ ይለናል።
ለምን ይሆን ታላላቅ የሚባሉ ለውጦችን በፍፁም አንድነትና ቅንነት ለሀገር ግንባታና ሽግግር ልንጠቀምባቸው ያልቻልነው? ለምንስ ነው ፍፁም መተማመንን ምግባራችን አድርገን ምቹ የፖለቲካ ባህል መገንባት ያቃተን? እነዚህን ጥያቄዎች አዲሱ ትውልድ መልስ ሊያገኝላቸው ይገባል።
ኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በፈጣን የፖለቲካ ለውጥ ውስጥ ትገኛለች። ከ30 እና 40 ዓመት በፊት የነበረው ሥርዓት ዘመኑን ባለመዋጀቱ ለውጡን ጎትቶ ይዞት እንደመጣ ይታመናል። በዚህ ሂደት ታዲያ አሮጌው ሐዲድ ላይ የነበሩት በአቋማቸው በመፅናታቸው ምክንያት ወደ አዲሱ ለመግባት ከሚታገሉት ጋር ሰፊ ተቃርኖና ልዩነት እንዲፈጠር ሆኗል።
ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመግባባት፣ ጦርነት፣ የሴራ ፖለቲካ በመከሰቱ ምክንያት በርካቶች ሞተዋል። ሕፃናት፣ ሴቶች አዛውንት እና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል። በኢኮኖሚያችን ላይ ከባድ ስብራት ደርሶ ነበር። አሁንም ይህ ከድብታ ውስጥ አልወጣንም።
በሕዝቦች መካከል የነበረውን መተማመን የሚሸረሽሩ አያሌ እኩይ ተግባሮች ነበሩ። ከእዚህ መረዳት የምንችለው ቁጭ ብሎ ለመነጋገር፣ ለችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ከመጣር ይልቅ አጥፊውንና ከባዱን መንገድ መምረጣችንን ነው። ይህን የጥፋት መንገድ እንድንከተል ያደረገን እርስ በእርስ የነበረን መተማመን በመሸርሸሩና በምትኩ መጠራጠር በመንገሡ ምክንያት ነው። ለዚህ ደግሞ ዋጋ ከፍለንበታል። ፖለቲካችን ታምሞ እንዲድህ ሆኗል።
ዛሬ አጥፊውን መንገድ መከተላችን ተገቢ አለመሆኑ የገባን ይመስላል። ችግሮችን ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት ወኔውን አግኝተናል። የጠፋ ሕይወት፣ ንብረትና የደረሰ የሰብዓዊ ጥሰት ከባድ ኪሳራ ውስጥ ከትቶን ቢሆንም ከዚህ እኩይ መንገድ ብዙ ሳንርቅ እና የበለጠ ጥፋት ሳይደርስ መመለሳችን እራሱ የሚያበረታታ ነው። ለዚህ ነው ፖለቲከኞቻችን፣ ማኅበረሰቡ፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ ሰዎች በመካከላቸው ፍፁም መተማመንና ቅንነት ሊኖራቸው ይገባል የምንለው።
ባለፉት ወራት በሰሜኑ ክፍል ተከስቶ የነበረውና ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታትና ለመቀራረብ እየተወሰደ የሚገኘው አበረታች እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው። በውጪ ኃይሎች አጋዥነት ከኢትዮጵያ ውጪ የተደረገው ስምምነትም ወደ ሀገር ውስጥ ዘልቆ ተደጋጋሚ ውይይቶች፣ መተማመንን የሚያመጡ መቀራረቦች መፈጠራቸው ለሕዝቡ እፎይታን የሚሰጥ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
ከሁሉ በላይ ግን አዲስ የፖለቲካ ባህል የሚፈጥር በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ለሚከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተመሳሳይ መፍትሔ ለመፈለግ እድሉን የሚከፍት እንደሆነ ይሰማናል። ማንኛውም ግለሰብ ሃሳብ ካለውና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማገዝ ከፈለገ መንገዱ ሰላምና ሰላማዊ መሆን ይገባዋል።
ከሁሉ በላይ ከባላጋራውና ከተቀናቃኙ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥና ሀሳብ ለማፋጨት ጫንቃውን ሊያደነድን የግድ ይላል። ይህ ለዘመናት ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ያኖራት የሕዝቦች አንድነት፣ መተማመንና ፍፁማዊ ቅንነት የፖለቲካ እጥፋት በገጠመን ቁጥር ስጋት ላይ እንዳይወድቅ ያግዘናል።
ውዷ ፀሐይ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም