ቀዳሚ የምሥጋና ቃል፤
ከየካቲት 11 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ያህል በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ሲመክር የሰነበተው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ በሰላም ተጠናቆ የደርሶ መልስ አሸኛኘቱም በስኬት መከናወኑ በይፋ ተገልጾልናል። የመሪዎቹ መርሃ ግብር የተከናወነባቸውን ሁለት ቀናት በዋነኛነት ጠቀስን እንጂ “ዝግጅቱና ምጡ” የጀመረው ከዓመት በፊት መሆኑ ጠፍቶን አይደለም።
በተለይም የኅብረቱ ዋና ጽ/ቤት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማችን ለመሪዎቹና ለልዑካን ቡድኖቹ፤ “እንግዳ፡- ፊት ወርቅ፣ ኋላ ብር፣ ኋላ ጨርቅ” ሆኖ እንዳያስገምታት በመጠንቀቅ ለመስተንግዶውና ለደህንነታቸው ጉዳይ እንቅልፍ አጥታ ስትጨነቅ እንደሰነበተች ከማናችንም የሚሰወር አይደለም።
የጉባኤው ዝግጅት እንዲሰምርና በስኬት እንዲጠናቀቅ ለደከሙትና ዋጋ ለከፈሉት ባለድርሻ አካላት፣ ለፀጥታው ክፍል ባልደረቦችና ለሚዲያ ባለሙያዎች በሙሉ በስምሪት ሰጭ ተቋሞቻቸው አማካይነት ብቻ ሳይሆን በእኛ በተራ ዜጎች “ተራ አንደበት” ጭምር እየተጨበጨበ ቢመሰገኑ ለቀጣዩ አገልግሎታቸው ብርታትና ስንቅ እንደሚሆናቸው ስለምናምን እነሆ ምሥጋናችን ይድረሳቸው እንላለን። ኢትዮጵያ ሆይ እንኳን ደስ አለሽ! ለአፍሪካ ኅብረት ጽ/ ቤት ዋነኛ ሹሞችና ባልደረቦችም በሙሉ ገለቶማ! ብለን አክብሮታችንን እንገልጽላቸዋለን።
የጋራ ቤት የጋራ ድምቀት፤
የሚዲያ ሠራዊት ተሰለፎ፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች ተደርድረው ከሚከናወነው የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን “ለአፍሪካ ትንሣኤ” የሚበጁ እጅግ በርካታ መርሃ ግብሮች ሲከናወኑ ከርመዋል። ለአብነት ያህልም ይህ አምደኛ ከአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ በርካታ ወንድም እህቶቹ ጋር ለአንድ ሣምንት ያህል በአህጉራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በቀረቡ ትምህርቶችና ሴሚናሮች አማካይነት እውቀት፣ ጥበብና የየሀገሩን መልካም ተሞክሮዎች ሲቀስም ከርሟል። የእግረ መንገድ አጋጣሚዎች ሲመቻቹለትም ስለ ሀገሩ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን ለመመለስና ለማብራራት መሞከሩ አልቀረም።
ይህንን ታላቅ የአፍሪካውያን ጉባዔ በራስ ተነሳሽነት በማዘጋጀት እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ የከፈለው ቤዛ ኢንተርናሽናል የተባለ ቤተ እምነት መሆኑን ቀደም ባለው ጽሑፌ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። ይህ አህጉራዊ ፕሮግራም በሀገራችን እንዲካሄድ ራእዩን ጸንሶ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ቀዳሚውን ድርሻ የወሰዱት የቤተ እምነቱ መሪዎች ዶ/ር ቤተ መንግሥቱና ልጃቸው መጋቢ ዘሩባቤል መንግስቱ ከፍ ያለ የአክብሮ ት ምሥጋና ይገባቸዋል ።
“አፍሪካ ተነሽ” – “Africa Arise” በሚል መሪ ርዕስ ከአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና መሪዎች ጉባዔዎች ጎን ለጎን ፕሮግራሙ መካሄድ ከጀመረ ከአሥር ዓመት በላይ አስቆጥሯል። የፕሮግራሙ አንድ አካል የሆነውና “The African Union Prayer Breakfast” በሚል ዓላማ መሪዎቹ ጉባዔያቸውን በሚጀምሩበት ዕለት የሚከናወነው መርሃ ግብር ሲመራ የቆየው በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት በክቡር ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የበላይ ጠባቂነት ነው። የካቲት 11 ቀን 2015 በዚያው በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ማለዳ ላይ የተከናወነው ይህ መርሃ ግብር የተከፈተውም በእኚሁ ታላቅ አፍሪካዊ አባት መሳጭ ንግግር አማካይነት ነበር።
ፓፓ ኦባሳንጆ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሕይወት እልፈት፣ እጅግ ለሚበዙትም መፈናቀልና የንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ ንግግርና ውይይት እንዲቋጭ አማጺውን የሕወሓት ቡድንና የፌዴራል መንግሥቱን በማቀራረብ የከፈሉት ዋጋም በታሪካችን ውስጥ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው።
በማለዳው የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ለሰላም ንግግሩ የተሄደበትን እጅግ ፈታኝ መንገድ በማስታወስ ለስኬት ላበቃቸው ለፈጣሪ ተገቢው ምሥጋና እንዲቀርብ ጉባዔተኞችን ጠይቀዋል። እኚሁ ታላቅ የአፍሪካ አባት ለኢትዮጵያ ሰላም መስፈን ስላደረጉት በጎነት እጅግ ከፍ ያለ ምሥጋና የቀረበላቸው ሲሆን ለዕድሜ ልክ ትዝታቸውና ለበጎነታቸው መታሰቢያ እንዲሆንም “በዕድሜዬ ዘመን ሁሉ እንዲህ ዓይነት የከበረ ሽልማት አላገኘሁም” በማለት የመሰከሩለትን ሽልማት ከፕሮግራሙ ባለ ራእዮች እጅ ተቀብለዋል።
ከእርሳቸው በማስከተልም ጉባዔውን በጸሎት የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ነበሩ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት በዚህ የማለዳ የጸሎት መርሃ ግብር ላይ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም የተዳሙ ሲሆን የማሳረጊያውን የቡራኬ ጸሎት የመሩት ደግሞ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹእ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ነበሩ።
የአፍሪካን ተስፋ የሚያነቃቃ እጅግ መሳጭ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ማሙሻ ፈንታ ሲሆኑ መልእክቱም ጉባዔተኛውን ያነቃቃና በይዘቱም ወቅታዊ ነበር። አፍሪካዊያኑ ወንድም እህቶቻችን ይህን እጅግ የሰመረ “የአፍሪካ ተነሽ!” ጉባኤና የማለዳ መርሃ ግብር ልብ ተቀልብ ሆነው ከተከታተሉ በኋላ በማጠቃለያው መርሃ ግብር ላይ የሰጧቸው ተመሳሳይ አስተያየቶች ሲጨመቁ “ኢትዮጵያ ለአፍሪካ መጻኢ ትንሣኤ በርግጥም ተስፋ መሆኗን አረጋግጠናል” የሚል ነበር። እንደ ምኞታቸው እንዲሁ ይሁንልን።
ስንፍና የቅርቡን አርቆ የሩቁን ያስመኛል፤
አፍሪካን ለዘመናት የተጫናት አዚም ፈውስና መፍትሔ እንዲያገኝ ብዙ መሠራት እንደሚገባ በየመርሃ ግብሩ ላይ በስፋትና በዝርዝር ተወስቷል። መሪዎቿ በአደባባይ ሲመካከሩ እየዋሉ በየጓዳቸው የጠብ እሳት መጫር የተለመደ ባህርያቸው እስኪመስል ድረስ የአህጉሪቱ እንቆቅልሽ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲወሳሰብ እንጂ ሲቀል አለመስተዋሉም በምሁራኑ አቅርቦት ላይ ተንጸባርቋል።
የእርስ በእርስ ጦርነት በረደ ሲባል ርሃብና ድርቅ መከሰቱ፤ አበረታች የልማት ጅምሮች መስተዋል ሲጀምሩ የአሸባሪዎች እኩይ ጥፋት ገንኖ መውጣቱ፤ አንዱ የችግር ቀዳዳ ሲደፈን በሌላ በኩል ማፈትለኩ፤ በጥናት የተደገፉ ማስረጃዎች እየተጠቀሱ ዋና ዋና የአህጉራችን ችግሮች በሚገባ ተዝርዝረው ቀርበዋል። በበሳል የአህጉሪቱ ምሁራን ሲንቆረቆር የሰነበተው ይህን መሰሉ “የቤት ልጆች የመማማር ጉባዔ” የሚዘነጋ ብቻ ሳይሆን ለተግባር እርምጃም የሚያስጨክን ነበር።
የአፍሪካ ህመሟ ጠንክሮ ፈውሷ ሊርቅ የቻለው ሰበበ ምክንያት እጅግ ብዙና የተወሳሰበ ቢሆንም የአፍሪካ መሪዎችና ምሁራን በአንድነት ተባብረው ለመደጋገፍ ከበረቱና ከጨከኑ ግን አህጉራችን “የዳቦ ቅርጫት፣ የሰላም ርግቦች ጎጆ፣ የእውቀት መፍለቂያ ምንጭ” ሆና ከፍታ እንደምትጨምር ማረጋገጫዎች ተሰጥተዋል።
ከሌሎች ሀገራትና አህጉራት ከመማር ይልቅ በሌሎች ማሳበብ የብዙ አፍሪካዊያን ባህልና ተግባር መሆኑም በድፍረት ተብራርቷል። የአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ዘመን ያከተመው አፍሪካ ራሷን የራሷ ቅኝ ግዢና ተገዢ እንድትሆን ተደርጎ በተዋቀረ ስትራቴጂ እንደነበርም በብዙ ማሳያዎች ለማመላከት ተሞክሯል።
እርግጥ ነው፡- የምድር በረከት ሳይጎል፣ ከሰማይ ደመና ሳይጠፋ ስለምን አፍሪካ በርሃብ ልትጠቃና ልትታወቅ እንደበቃች ማሰላሰሉ በራሱ ጤና ይነሳል። ጦርነትን ባህሏ አድርጋ፤ መገዳደልን እንደ ጀብድ ቆጥራ፤ በድርቅና በርሃብ እየተፈተነች እስከ መቼ እንደምትዘልቅም አዋቂው አንድዬ ብቻ ነው።
ከሴሚናሮቹና ከንግግሮቹ መካከል የሦስት ያህሉን ተናጋሪዎች መርጠን ለአብነት እናስታውስ። ዲዬዶኔ ናሂመና ‹Dieudonnè Nahimana› በብሩንዲ ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበሩና አንቱታን ያተረፉ የአፍሪካ ልጅ ናቸው። በጎዳና ወጣቶች ሕይወት ዙሪያ የሚሠራ አንድ ውጤታማ ተቋም በስማቸው በማቋቋም ዓለም አቀፍ እውቅና እስከ ማግኘትም የደረሱ ናቸው።
እኚህ የተከበሩ ሰው “የግል ምስክርነቴ” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1993 በቡሩንዲ ውስጥ በተፈጸመው የዘር እልቂት ምክንያት ከአካባቢያቸው ሸሽተው ለጎዳና ሕይወት መዳረጋቸውና አባታቸው፣ በርካታ የቤተሰባቸው አባላትና የማሕበረሰቡ ነዋሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፋቸውን ሲተርኩ በእውነቱ የሰብዓዊነት ትርጉም ግራ እስኪያጋባ ድረስ ታዳሚው ያደምጣቸው የነበረው “እኛም እኮ!…” በሚል ቁጭት እምባውን እያፈሰሰ ነበር።
እጅግ የሚያስገርመው ግን የአባታቸውን ደም ጨምሮ የብዙ ዜጎቻቸውን ሕይወት በግፍ ለቀጠፉት አንድ ግለሰብ ቀዬአቸው ደረስ በመሄድ ይቅርታ ማድረጋቸውና ወዳጃቸው እንጂ ጠላታቸው ያለመሆናቸው አቅፈው በመሳም ያሳዩትን ርህራሄ ማድመጥ “በውኑ ዓለም በርግጡ ሊደረግ ይችላል ወይ?” እስከ ማለት አድርሶ ነበር።
ይቅርታ ማድረግ ብቻም ሳይሆን የልጆቻቸውን ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ጭምር እስከ መጨረሻው አስተምረው ለቁም ነገር ለማብቃት መወሰናቸውንም ያረጋገጡላቸው በፍቅር በተነካ ልብ ነበር። ከተናገሯቸው ኃይለ ቃላት መካከል ጥቂቱን እንጥቀስ፡- “There is no future for Africa without forgiveness and reconciliation… Our Heads of States are sitting together but don’t love each other… We have to take every opportunity to be agents of peace and reconciliation.”
ሁለተኛው ተናጋሪ የግብጽ የልዑካን ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ሳሜህ ናቸው። እኚህ ታላቅ ሰው ያስተማሩት ስለ አንድነትና ተቀራርቦ አብሮ ስለመሥራት ነው። እጅግ በሚመሰጥ ንግግር መልእክታቸውን ያስተላለፉት “የዓባይን ውሃ እንደሚጋራ” የሩቅ ሀገር ሰው ሳይሆን እንደ አንድ የቤተሰብ አባል አድርገው ራሳቸውን በመቁጠር ነበር። አብሮ በመደጋገፍ ተራራው ደልደላ ሜዳ፣ ሸለቆው በበረከት ውሃ እንደሚሞላም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ሦስተኛው ተናጋሪ ከደቡብ ሱዳን የመጡት ቢሾፕ ፖል ዴንግ ጆሹዋ ሊክ ነበሩ። በአነቃቂ ንግግሮቻቸው፣ ስለ ሀገራቸው የነፃነት ትግል በዓይን ምስክርነት በሚያጋሩትና በማይሰለቹ የታሪክ ነገራ ችሎታቸው የሚታወቁት እኚህ ሰው “The Spirit of Politics” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ በአፍሪካ ዙሪያ ተወዶ እየተነበበላቸው ነው።
እኚህ ሰው የተናገሩበት ርዕስ “Breaking the Horns of Limitations” በሚል ርዕስ ሲሆን “አፍሪካን ከላይ ወደ ታች የተጫኗት አራት ቀንዶች ናቸው። እነዚህ አራት ቀንዶች በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በሰላምና በምህረት እስካልተሰባበሩና ተሸንፈው እስካልተነቃቀሉ ድረስ አፍሪካ ከህመሟ ልትፈወስ አትችልም”፤ ዋና የንግግራቸው አንኳር ሃሳብ ነበር።
በአራት ተዋጊ ቀንዶች የወከሏቸውና የአፍሪካ ቀዳሚ ችግሮች ያሏቸው፡- “The horns that are raised up in this continent are greed, tribalism, poverty and shame. We need ask ourselves why we struggle with all these failures and poverty in the midst of such fertile ground and good weather; why we are so divided. These horns of limitations have scattered us.” በማለት ነበር።
እናጠቃለው፡- ሥልጡኖቹ የአውሮፓ ሀገራት 27 ሆነው በመሰባሰብ (Supranational Political and Economic Union) በሚል የበላይነት መርህ ከእርስ በእርሳቸው መደጋገፍ አልፈው ዓለምን ለመቆጣጠር እያለሙ ነው። በፓርላማ፣ በካውንስል፣ በኮሚሽን፣ በፍትሕ፣ በመረጃ ደህንነትና ጥበቃ፣ በእምባ አባሽነት ወዘተ. ባዋቀሯቸው በርካታ ተቋማት እየተመሩ ለየሀገራቸውና ለቡድናቸው ከፍታ ሲጨምሩ አፍሪካ ግን ገና ከእንቅልፏ ለመባነን ብርታት ያለማግኘቷ ለመሪዎቿ ብቻ ሳይሆን ለምሁራኗና ለዜጎቿም ጭምር በእኩል ደረጃ አሳሳቢ ተግዳሮቶች ናቸው።
እ.አ.አ በ1945 የተመሠረተው የአረብ ሀገራት ሊግ በ22 አባል ሀገራት ተደራጅቶ ተፈጥሮ በለገሰቻቸው በነዳጅና በከርሰ ምድር ሀብታቸው ሲቀናጡ የእኛይቱ አህጉር ግን “ርሃቧን” እንደ ምክንያት እየጠቀሰች የተጋገረ ዳቦ ትለምናቸዋለች። መጨራረሻዋን የጦር መሣሪያ እንዲያቀርቡላትም ትማጸናቸዋለች፤ ልጆቿንም “በቤት ሠራተኝነት” እየላከች ኑሯቸውን ታዳምቅላቸዋለች።
አሜሪካና ካናዳን ጨምሮ ሌሎች አምስት የአውሮፓ ሀገራትን ያሰባሰበው የG-7 ቡድን ዋነኛ ትኩረት በፖለቲካና በሴኪዩሪቲ ዙሪያ ዓለማችንን ለመቆጣጠር መሆኑ ፖለቲካቸውን ለሚከታተል ለማንም ሰው ግልጽ ነው። G-8 እና G-20 በሚል ስያሜ የሚሰባሰቡት ታላላቅ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካኖቹ ሁለቱ ኃያላን ሀገራት ምን ተልእኮ ለማስፈጸም እንደተቋቋሙ ከማንም የተሰወረ አይደለም። የአፍሪካንና የእስያ አህጉራትን ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር በዝብዞና አግዞ የብልጽግናቸውን ከፍታ ለማተለቅ እንደሆነም በግልጽ ይታወቃል።
“ምድራችሁን፣ ጠፈራችሁንና የባሕር ዳርቻዎቻችሁን ‹የጦር ቤዝ› እንድንመሰርት ዝግጁ አድርጉልን” ጥያቄያቸውም ፋታ የሚሰጥ አይደለም። ማስፈራሪያቸው ደግሞ ርዳታና ብድር መሆኑ የታወቀ ነው። “ወንድ ወደሽ፤ ጢም ጠልተሸ” እንዲሉ አፍሪካ በሥልጡኖች ሀገራትና በኅብረታቸው አማካይነት የውጥር ተይዛ ልትቀሰፍ የቻለችው ዓለም አቀፉን የፖለቲካ አዙሪት በኅብረት ለመቋቋም ገና ጉልበቷ ስላልጸና ነው።
የአውሮፓ ሀገራት በቪዛና በንግድ ሥርዓታቸው ተደጋግፈውና ተናበው ሲሰሩ የአህጉራችን መሪዎች ግን ዛሬም ድረስ ስለ “ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ስለ ጋራ የቪዛ አገልግሎት” ተስማምተው መወሰን ተስኗቸው “እባብ ለእባብ ይተያያሉ ካብ ለካብ” እንዲሉ ከእርስ በእርስ መጠራጠር ስሜታቸውን ሊያነጹና ሊያጠሩ አልቻሉም።
“አፍሪካ ተነሺ!” የሚለው ዓመታዊ ጉባዔ ለተዘረዘሩት ዘመን ጠገብ ችግሮች በሙሉ መፍትሔ ያመጣል ባይባልም የምሁራኑ ዓይን ከፋች ትምህርቶች፣ የጋራ ምክክሮቹና፣ ልባዊ የአብሮነት ጸሎቱ ግን ውጤት አምጥቶ የአፍሪካን የራስ ከራስ እርቅና ትንሣኤ ሊያፋጥን እንደሚችል ይታመናል። ሰላም ለሀገራችን፤ ለሕዝባችንም በጎ ፈቃድ።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም