በአገራችን የነፃ ገበያ ሲመጣ፤ ከአጸደ ህፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የግል ትምህርት ተቋማት በየቦታው መስፋፋታቸው ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። በአዲስ አበባ ለግለሰብ መኖሪያ ቤትነት የተዘጋጁ በብዛት አፀደ ህፃናት ሲሆኑ አይተናል።
ፈረንጆቹ ‹kindergarten› የሚሉት አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በመከፈታቸው ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ወላጆችም ለልጆቻቸው የተሻለ ትምህርት ቤት በመሻት እነዚህን ትምህርት ቤቶች ምርጫቸው ሲያደርጉ ይስተዋላል። ሆኖም የግል ትምህርት ቤቶች ሁሉ ግን የተሻለ፣ ተመራጭ እና ተወዳጅ ናቸው ማለት አይቻልም።
አንዳንዶቹ የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች እጅግ በጣም የተጋነነ ክፍያ ያስከፍላሉ፤ ወላጆች ለልጆቻቸው የላቀ ስለከፈሉ የሞቀ የደመቀ ትምህርት ቤት ሁሉ ያስገቡ ይመስላቸዋል። አንዳንዶቹ ህፃናት የተወሰነ እንግሊዝኛ ሰባብረው ሲናገሩ በግንዛቤ ማነስ ወላጆች ልጄን ጥሩ ትምህርት ቤት አስገባሁት ብለው ይረካሉ፣ ይኮራሉ።
ከመዋዕለ ህፃናት መካከል በትምህርት ቢሮ የሚታተሙ መፃሕፍትን ወደ ጎን ትትው የራሳቸውን መፃህፍት አሳትመው ለህፃናቱ የሚማሩበት በሚል ለወላጆች በግዴታ የሚሸጡ አሉ። ይህም የትምህርት ቢሮዎች ክትትል ማነስ ውጤት ነው። ሌላው በሰበብ አስባብ የትምህርት ክፍያ የሚጨምሩ ይገኙበታል፤ በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የግል ትምህርት ቤቶች በመጪው አዲስ ዓመት ምንም ዓይነት የትምህርት ክፍያ መጨመር እንደማይችሉ ማሳሰባቸውም በኑሮ ውድነት ለሚንገላቱት ወላጆች አንድ ፋታ እና እፎይታ ነው።
መምህራኑ ምን ያህል ብቃት አላቸው የሚለውም ያጠያይቃል። አንዳንዶቹ ተማሪዎቹን ለማስተማር ሳይሆን ለማጫወትም ብቃት ያላቸው አይመስሉም፤ ለህፃናቱ የሚጠይቁት ጥያቄ አንዳንዴ አዋቂዎችንም ግራ ያጋባል። ስለልጅዎ ትምህርት በትምህርት መጽሐፉ ላይ ጽፈው አስተያየት ሲሰጡ እንግሊዝኛውን ሰዋሰዋዊ ሥርዓት የማያውቁ አይቻለሁ። ለወንድ ህፃን (she was a good student) ጥሩ ተማሪ ነበረች፤ ብለው ለወላጅ አስተያየት ሲጽፉ አያስገርምም? አስተማሪው ራሱ ስለሚያስተምርበት ቋንቋ ሳያውቅ ሲያስተምር ተማሪውን ከማደናገር እና ከማደናቆር በቀር ፋይዳ የለውም።
በተለይም በአዲስ አበባ የሚያስተምሩበት ግቢ በብዛት ለሰው መኖሪያ ቤት የተዘጋጀ እና ለአፀደ ህፃናት ታስቦ የተሠራ ስላልሆነ ህፃናቱ እንደልብ የሚጫወቱበት ሠፋ ያለ ቦታ የላቸውም። ከመቶ በላይ ተማሪ በጠባብ ግቢ ሰብስቦ ማስተማር ህፃናቱን ማጨናነቅ ነው። ህፃናት ማስተማር የሚቻለው በጨዋታ፣ በውዝዋዜ፣ በዘፈን፣ በተረት፣ በስዕል በመሳሰሉት ነው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት በአጸደ ህፃናት የሚማሩት ለዋናው ትምህርት ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ልብ የሚቦርቁበት ሠፋ ያለ ግቢና መጫወቻዎች ለህፃናቱ ማስፈለጉ ግድ ነው። ጨዋታና ብላቴና አይነጣጠሉምና።
ወደ ግል ኮሌጆች ስንመጣም አንዳንድ እንከኖች ሊኖሩባቸው እንደሚችሉ ማሰቡ ጥሩ ነው። ትምህርታቸውን በለብለብ መልኩ የሚሰጡ ብዙ ኮሌጆች አሉ። አንዳንዶቹ በዲግሪ ተመርቀው ስማቸውን እንኳ በቅጡ መፃፍ አይችሉም። ይህ ለነገሩ የመንግሥት ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችንም ይመለከታል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የታጠፈው የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ሚኒስቴር ዓላማው በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ላይ ክትትል ቁጥጥር ማድረግ ነበር። በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያደረገው ቁጥጥርና ክትትል ብዙም ሳይሰማ ነው የታጠፈው። በትምህርት ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ጉዳዮች ነቃ ያለ ክትትል ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል።
ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የተጀመረውም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነው። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣኑ በአራት ዙር ባደረገው ድንገተኛ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፍተሻ 332 ካምፓሶችና ቅርንጫፎች ላይ እርምጃ ወስዷል።
ባለሥልጣኑ ባጠቃላይ በ2014 ዓ.ም በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በአንደኛው ዙር በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች 106፣ በ2ኛው ዙር 95፣ በ3ኛው ዙር 104 እና በ4ኛው ዙር 27 ካምፓሶችና ቅርንጫፎች ላይ እርምጃ ወስዷል። እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል፤ ግብአቶች ያጓደሉ፣ የዕውቅና ፈቃድ ሳያሳድሱ ተማሪ የመዘገቡ፣ የዕውቅና ፈቃድ ባልተሰጠበት የርቀት ቅርንጫፍ ማዕከል ከፍተው ተማሪዎች መዝግበው ያስተማሩ፣ ያለባለሥልጣኑ ዕውቅና የህንፃ ለውጥ ያደረጉ ያልተሰጣቸውን የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ ስያሜ የተጠቀሙ ይገኙበታል።
ሌላው የግል ኮሌጅ ተማሪ የዲግሪ ዲፕሎማ ትምህርት ማስረጃው ቢጠፋ እና በአጋጣሚ የተማረበት ኮሌጅ ቢዘጋ ችግሮች መፈጠራቸው የማይቀር መሆኑ ነው። የትምህርት ማስረጃውን ቢጠፋ ከየት ያገኘዋል? በእኔ ግምት ተምሮ እንዳልተማረ የሚሆንበት ዕድሉ ሠፊ ነው።
ያም ሆነ ይህ ትምህርት ሚኒስቴር በዜጎች ትምህርት ውጤትና ምረቃ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ የመረጃ ቋት ማዘጋጀት አለበት። የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለተማሪዎቻቸው ትምህርትና ውጤት ምረቃን ሁሉ በየጊዜው ማስረጃ ነክ ዝርዝር ጉዳዮችን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲልኩ መደረግ ያለበት ይመስለኛል። ትምህርት ሚኒስቴርም፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ተማሪዎች፣ ትምህርት፣ ውጤትና ምረቃን ሁሉ በየዓመቱ መሰነድን ሊመለከተው ይገባል። የተማሪዎችንም ሆነ የትምህርት ቤቶችን ማስረጃዎችን ሁሉ ለመያዝ ደግሞ ዘመኑ የፈጠረው በይነ መረብ ለዚህ የተመቸ ነው። የኮሌጆችና የዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የተማሪዎቻቸውን ሁኔታ የትምህርት ውጤቶቻቸውንና ነጥቦቻቸውን በመረጃ ቋት ሥርዓት ሰብስቦ የሚይዝ ቡድን መፍጠር አለበት።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ትምህርታቸውን ትተው ሸሽተው መጥተዋል። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም ትምህርታቸውን ካቋረጡበት ቀጠሉ፤ ሊመረቁ ሲሉ ግን ዩኒቨርሲቲዎቹ የተማራችሁበትን የትምህርት ማስረጃ እንሰጣለን እንጂ አናስመርቅም አሉ። ተማሪዎቹም ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ችግሩ ሊከሰት የቻለው በአገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ተማሪዎች ዙሪያ በየጊዜው በድረግብር (network) የሚጠናከር የመረጃ ቋት ሥርዓት ባለመኖሩ ነው።
የግልና የመንግሥት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ እስኪያጠናቅቁ ድረስ የትምህርት መረጃዎቻቸው የትምህርቱ ዓይነቱና ውጤቱ ሁሉ በአንድ የመረጃ ቋት ቢሰበሰብ፤ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃዎቻቸው ቢጠፉ በቀላሉ መረጃውን ሊያገኙ ይችላሉ። የግድ የተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ድረስ የማይሄዱበትሥርዓት ይኖራል። ሳይማሩ ተምረናል የሚሉ አይኖሩም። ቢተገበር እና ቢጀመር ተማሪዎችና ተመራቂዎች መረጃ ፍለጋ እንዳይንከራተቱ ይረዳል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም