የ13 ወራት ፀጋ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ወራቶቿም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ የሀገር ፍቅር ስሜት በመፍጠር በባህል፣በእምነት፣ በታሪክ፣ የተከፋፈለ እሴት ያላቸውና የሚተነተኑ የሌላውንም ዓለም ቀልብ የሚስቡ ናቸው። በዚህ ረገድ በዋናነት ከሚጠቀሱት ወራቶች ያሳለፍነው ጥር እና የያዝነው የካቲት ወራቶች ይጠቀሳሉ።
በማይዳሰስ ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የተከበረው የጥምቀት በዓል ከአንዱ ነው፣ በዓሉ ያለው መንፈሳዊ፣ በማህበራዊ ፋይዳ ከመላው ዓለም ጎብኚዎችን በመሳብ ለሀገር ምጣኔ ሀብት አቅም በመሆን ላይ ይገኛል።
የያዝነው የካቲት ወር ደግሞ ከባለታሪኳ ኢትዮጵያ አልፎ በጥቁሮች ልብ ውስጥ የተጻፈና የሁሉም መኩሪያ የሆነ፣ ዓለምም በአድናቆት እንዲያያት ያስቻለ ገድል የተፈፀመበት ነው። በዚህም ወሩ የአፍሪካውያን ወር እስከ መባልም ደርሷል። የአፍሪካውያን ወር ያሰኘው ብቸኛው ምክንያትም ደግሞ የዓድዋ ድል ነው።
የዓድዋ ድልም እንዲሁ በተመሳሳይ በአኩሪ ታሪክ ተምሳሌትነቱ ከመወሳት ባለፈ የቱሪስት መስህብ ቢሆን የላቀ ድርሻ እንዳለው ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ ነው። ወራቶቹ በታሪክ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ሀገር የም ታተርፍባቸው ናቸው።
በትውልድ ቅብብሎሽ ታሪክ እያስታወሰው፣ በተለያየ ዝግጅት የሚከበረው የካቲት 23 ቀን / የዓድዋ ድል በዓል እነሆ ዘንድሮም ለ127ኛ ጊዜ ይከበራል። እኔም በዚህ አጭር ጽሁፍ የዓድዋ ድል ለመዘከር /አንድ ለማለት ሞከርኩ እንጂ ጉዳዩ በዚህ ጽሁፍ ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› እንደሚባለው ሊሆንብኝ እንደሚችል አምናለሁ።
እነዛ በልማት ጊዜ ገበሬ፣ ሀገራቸው ስትደፈር ደግሞ ዳር ድንበሯን ለማስከበር ሞፈርና ቀንበራቸውን ሰቅለው ማቄን፣ጨርቄን፣ ልጄን፣ ሚስቴን ሳይሉ ሊያውም ዘመናዊ መሣሪያ ሳይታጠቁ በወኔ ከጠላት ጋር ተፋልመው ድል ስለተቀዳጁት፤ይህን ትውልድ አንገት ስላስቀኑ ወገኖች ጥቂት ማለት ፈለኩ።
ከዚህም ጎን ለጎን ዘመናዊ ኢትዮጵያን በመፍጠር፣ የአፍሪካና የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ እንደሆኑ የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክርላቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክን፣ ወቅቱንም ማስታወስ ወደደኩ።
ኢትዮጵያ ነፃነቷ ተከብሮ፣ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ጉልህ ስፍራ የነበራቸው አፄ ምኒልክ ብቻ አልነበሩም ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱም ነበሩ። ጦሩን ሰብቆ ኢትዮጵያን በኃይል ሊወር የመጣው ፋሽስት ጣሊያን በውጫሌ የውል ስምምነት ላይ ኢትዮጵያን ከጨዋታ ውጭ ሊያደርጋት የነበረውን ሴራውን በማክሸፍ እቴጌ ጣይቱ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ታሪክ ያስታውሳል።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 የኢጣሊያንኛው ‹‹ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በጣሊያን መንግሥት በኩል ማድረግ አለባት›› የሚል ሲሆን፣ በአማርኛው ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በጣሊያን መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች››
በሁለቱ ቋንቋዎች በውሉ ላይ የተገለፀው ሰፊ የትርጉም ልዩነት እንዳለውና የጣሊያንኛው ትርጉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ብቻ ሳይሆን፣ ብሄራዊ ክብሯን የሚያስደፍርና ጥቅሟንም አሳልፎ የሚሰጥ እንደሆነ የተገነዘቡት የኢትዮጵያ መሪ፣ውሉ የኢትዮጵያን ክብር በሚያስከብርና ጥቅሟንም አሳልፎ በማይሰጥ መልኩ መልሶ እንዲስተካከል በተደጋጋሚ ቢያቀርብም ስምምነት ላይ አለመደረሱን ታሪክ ያስረዳል።
ይሄኔ ነገሩ ያላማራቸው ብልህዋ እቴጌ ጣይቱ በአንቀጹ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ አደገኛነትና ከወራሪው ጋር ጦርነት መግጠም እንደሚያስፈለግ ለአፄ ምኒልክ እንደነገሯቸው ታሪክ ያመለክታል። ሀገራዊ ክብርና ጥቅም ሲነካ፣ ክብሯን ማስጠበቅ ከአንድ ሀገር መሪ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ኃላፊነትና ግዴታም በመሆኑ ወራሪውን ፋሽስት ጣሊያንን በመጣበት መክቶ ለመመለስ ህዝቡ ለዘመቻ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል።
የክብር ጉዳይ ነውና የክተት ዘመቻ ጥሪውን ለመቀላቀል ወደኋላ ያለ እንዳልነበር ጦርነቱና የተገኘው ድል ምስክር ነው። ከታሪክ ድርሳናት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ዓድዋ ላይ የተደረገው ጦርነት ከአራትና አምስት ሰዓታት በላይ አልዘለቀም። በአየርና በየብስ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ ኃይል ሙትና ቁስለኛ ከማድረግ ባለፈም የጦር አዛዦችን፣ ቁጥር ስፍር የሌለው መሣሪያዎችንና መድፎችን በመማረክ ጀብድ በመፈጸም በጠላት ላይ ድል የተቀዳጀው ኢትዮጵያዊ የማረካቸውን የጦር መሣሪያዎች በአጋሰስ ጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስም ውሎ አላደረም።
ለጦርነቱ መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል ስምምነት ፋሽስት ጣሊያንን ዋጋ ያስከፈለና ለውርደትም የዳረገ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ዳር ድንበሯን አናስደፍርም ብለው ከቀፎው እንደወጣ የንብ መንጋ በአንድ ሆነው ባደረጉት ተጋድሎ ያስመዘገቡት ድል በመላው ዓለም ስሟ እንዲጠራ አድርጓል።
በባዶ እግር፣ በመድፍ ታግዞ ዘመናዊ መሣሪያ ከታጠቀ ኃይል ጋር ተዋግቶ ያሸነፈ እስካሁን በታሪክ አልተሰማም። ለዚህም ነው የዓድዋ የድል በዓል በየአመቱ እንደ አዲስ የሚወሳው፣ ታሪኩም ገኖ የሚነገረውና አይረሴ የሆነው። ድሉና ታሪኩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ጸሐፍትንም አነሳስቷል።
በዓድዋ ድል ማግሥት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፣ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ ብለው የዘገቡትን የእንግሊዝ ጋዜጦች በታሪክ እናገኛለን። ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል (ዓድዋ ድል)በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ለውጥ በማምጣትም ሚናው የጎላ እንደሆነም ታላላቅ ፀሐፍት በብእራቸው ማስፈራቸው ይታወቃል።
ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ የኢጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦርነት በሚለው መጽሐፉ ላይ እንደገለጸው የዓድዋ ድል በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በ1895 ዓ.ም ሲሆን፣ በዓሉም አሁን በሚከበርበት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ምኒልክ አደባባይ ነው። በወቅቱም በነቂስ ከወጣው ኢትዮጵያዊ በተጨማሪ ዲፕሎማቶች ታድመዋል። የፈረሰኞቹ ብዛትም ልክ አልነበረውም።
የዓድዋ ድል የአንድ ወቅት ብቻ አይደለም። ጽናት፣ አንድነት፣ መከባበር፣ የሀገር ፍቅር ስሜት የምንማርበት ተምሳሌት ነው። በመሆኑም አኩሪ ድሉን ስናጣጥም ያለብንንም ኃላፊነት ሳንዘነጋ መሆን ይኖርበታል። በጀግኖች አባቶች አጥንትና ደም ታፍራና ተከብራ የቆየችውን ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ጠብቆ፣ በውስጥም አንድነትን፣ አብሮነትን፣ መከባበርን አጠናክሮ በጋራ የመኖር እሴትን ማቆየትና ለተተኪ ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነት የዚህ ትውልድ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ይህን ማድረግ ካልቻልን የውጭ ጠላቶች በቀላሉ በተከፈተላቸው በር ገብተው አንድነታችንን እንዲንዱ እድል ይመቻችላቸዋል። በዚህ ደግሞ የምናጣው ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን እስከዛሬ አንገታችንን አቅንተን የምንጓዝበትን ነፃነታችንን ጭምር ነው ፤ መልካም የዓድዋ ድል በዓል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም