በዛሬው የባለውለታችን አምድ ይዘን የቀረብናላችሁ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ፤ መንፈሳዊና ታሪካዊ መፅሐፍት እንዲሁም ለትርጉም ስራዎች መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን ብላታ መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስን ነው፡፡ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የተወለዱት መጋቢት 17 ቀን 1891 ዓ.ም ሸዋ ጅሩ ውስጥ እምቧጮ መግደላዊት በተባለ ስፍራ ነው። መርስዔ ኀዘን እድሜያቸው አራት ዓመት ሲሞላ እምቧጮ ላይ ከንባብ አስተማሪው ከደብተራ እንደ ብልሃቱ ፊደል መቁጠር ጀመሩ፤ በ1896 ዓ.ም ደግሞ ወደ እንጦጦ መጥተው ከአባታቸው ዘንድ ንባብ ተማሩና በሰባት ዓመታቸው ዳዊት ደገሙ። በመቀጠልም የዜማ ትምህርት ጀምረው ጾመ ድጓን ተምረዋል።
ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ ጅሩ ሄደው ጅሑር ላይ ሲያስተምሩ ከነበሩት ከአለቃ ወልደ ማርያም ቅኔ መቁጠር የጀመሩ ሲሆን ከሦስት ወር በኋላም ወደ ደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ ተላልፈው በአለቃ ወልደ አብ ቅኔ ተምረዋል። በዓመቱም ወደ እንጦጦ ተመልሰው ከታላቁ የቅኔ መምህር ከአለቃ አወቀ ተማሩና ቅኔ ተቀኙ። በ1904 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ወርደው ከግራ ጌታ ገብረ መድኅን የቅኔ አገባብ ተማሩ።
መርስዔ ኀዘን የሥራ መያዝ ፍላጎት ስላደረባቸው በወምበሩ ቀኛዝማች ናቄ ዘንድ የጸሐፊነት ሥራ ያዙና አንድ ዓመት ከአራት ወር በጸሐፊነት አገልግለዋል። በኋላም በአባታቸው ወዳጅ በአቶ ሕለተ ወርቅ እሸቴ ምክር የጸሐፊነቱን ሥራ ትተው ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ። እዚያም ሳሉ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ በመማር በዘርፉ ያላቸውን እውቀት አዳበሩ፡፡
በዚህም ሳይወሰኑ ወደ ሐረር ወርደው በአደሬ ጢቆ ሥላሴ ከአለቃ ገብረ ክርስቶስ ወልደ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ትርጓሜ የተማሩ ሲሆን ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ከቀድሞ አስተማሪያቸው ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ሐዲሳቱን በመከለስ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
በመንፈሳዊ ትምህርት ተኮትኩተው ያደጉት እኚህ የሀገር ባለውለታ በ1912 ዓ.ም በጽሕፈት ሥራ ተቀጥረው የመንግሥት ሥራ የጀመሩ ሲሆን የመንፈሳዊ ፅሁፍ ትርጓሜ ረቂቅ ማውጣትና፤ በባለሙያው ሊቅ አረጋግጠው ንባቡን ከነትርጉሙ ለኅትመት በማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ከእነዚህም ስራዎች መካከል ‘አረጋዊ መንፈሳዊ’ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን በ1920 ዓ.ም. ድሬዳዋ ላይ ያሳተሙት ተጠቃሽ ነው። መርስዔ ኀዘን ከዚህም ባሻገር ሌሎችን የትርጓሜ ሥራዎች አዘጋጅተው አቅርበዋል። በተለይም ከአለቃ ኃይለ ሥላሴ ጋር ሆነው የሠሩት የሲራክና የደቂቀ ነቢያት ትርጓሜ በስፋት ይታወቃል።
መንፈሳዊ ትምህርትና ቅኔ መማር ብቻ ብዙ ወንዝ እንደማያሻግር ቀድመው የተገነዘቡት እኚህ ሰው የውጭ አገር ቋንቋን ለመማር ተመኙ፡፡ ተመኝተው ብቻ ግን አልቀሩም፤ ከዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ቤት ገብተው እንግሊዝኛ መማር ጀመሩ። ይሁንና ከሦስት ወር በኋላም የትርጓሜ ሥራቸውን ብቻ እንዲከታተሉ የሚያደርግ አንድ ምክንያት ስላጋጠማቸው የቋንቋ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። መርስዔ ኀዘን ስለዚህ ሁኔታም “ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው” በሚል ርዕስ በ2005 ዓ. ም ላይ ታትሞ በወጣው የግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ ‹‹የቋንቋ ትምህርት መጀመሬንም እንዳይሰሙብኝ ለማድረግ ተጣጣርሁ። ዳሩ ግን ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ ወሬውን ሰምተው ጠሩኝና እያዘኑ ክፉኛ ገሠጹኝ። ዳግመኛ ወደዚያ ስፍራ እንዳትመለስ ብለውም አስጠነቀቁኝ። እንግዲህ የተፈሪ መኰንን ተማሪ ቤት እስከ ተከፈተ ድረስ የቋንቋ ትምህርቴን አቋርጬ ተቀመጥሁ። ጌታ አለቃ ገብረ መድኅን ይህን ማድረጋቸው በእርሳቸው አስተያየት እኔን ለመጥቀም እንጂ ለክፋት እንዳላደረጉት ሕሊናዬ ስላወቀ አላዘንሁባቸውም›› ሲሉ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ብርሃንና ሰላም ብለው የሰየሙት አንድ አዲስ ጋዜጣ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም. በማተሚያ ቤቱ ዳሬክተር በአቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሃይማኖት መሪነት ሲመሠረት መርስዔ ኀዘን ወደ ጋዜጠኛነት ተዛውረው በዋና ጸሐፊነት ይሠሩ ጀመር። ከአራት ወር በኋላም የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ሲከፈት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ ሆነው ወደ ትምህርት ቤቱ ተዛወሩ። በዚህ ጊዜ ያሰናዱት “ትምሕርተ ሕፃናት” የተባለች መጽሐፍ ግንቦት 1 ቀን 1917 ዓ. ም ታትማ ወጣችና የግብረ ገብ ትምህርት ማስተማሪያ ሆነች። እሳቸውም በዚህ ጊዜ እንግሊዝኛ ለመማር በትጋት ይጣጣሩ ጀመር።
ከአንድ ዓመት በኋላ ጽፈው ያቀረቡዋት “በአዲስ ሥርዓት የተሰናዳ የአማርኛ ሰዋስው” በማጥኛ ደብተር እየተገለበጠ ወዲያው የተማሪዎች መማሪያ ሆኖ በአገልግሎት ላይ ዋለ። ይህ ሰዋስው ከጠላት ወረራ በኋላ በ1935 ዓ.ም ታትሞ የወጣ ሲሆን ለግማሽ ምዕተ ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የሰዋስው ማስተማሪያ ሆኖ አገልግሏል። እንዲሁም ደግሞ የትምህርት ቤቱ ሹም ሐኪም ወርቅነህ በአማርኛ አስተርጉመውት የነበረውን “የዓለም ጅኦግራፊ” እንደገና ሲያርሙትና ለኅትመት ሲያዘጋጁት ሳሉ መርስዔ ኀዘን የሥራ አለቃቸውንና ልባዊ ወዳጃቸውን ለመርዳት በቅንነት አገልግለዋል።
በ1920 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው የዚሁ ጅኦግራፊ መፅሐፍ የመጽሐፉ ባለቤት ሐኪም ወርቅነህም በመጽሐፋቸው መቅድም ላይ በጻፉት ቃል፤ “ይህንም ለማረም ምሁር የሆነ ወዳጄ አቶ መርስዔ ኀዘን በትዕግሥትና በልበ ፈቃድ ከእኔ ጋር በማረም ረዳኝ፤ ቀጥሎ መጽሐፉ ሲታተም ግድፈቱን እያረመ አሳተመልኝ፤ ይህን የመሰለ እርዳታ ባላገኝ ኖሮ ይህ የጅኦግራፊ ትርጉም ወደ ፍጻሜ ባልደረሰም ነበር” ሲሉ ምስጋና ሰጥተዋቸዋል።
መርስዔ ኀዘን በ1922 ዓ.ም ወደ ጅጅጋ ከተማ ተዛውረው ከዚያ ለቆመው ለልዑል ራስ መኰንን ትምህርት ቤት ዋና ሹም በመሆን አምስት ዓመት አገልግለዋል። በዚሁም ጊዜ በተጨማሪነት ከተሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በወሰን ክልል ሥራ ላይ መሳተፍ አንዱ ሲሆን በ1924 ዓ.ም. በታኅሣሥ ወር የተጀመረው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሱማሌላንድ የወሰን ክልል ኮሚሽን ሥራውን እስካበቃበት እስከ 1927 ዓ.ም ድረስ በዋና ጸሐፊነት ሦስት ዓመት ከሁለት ወር አገልግለዋል። የክልሉ ሥራ ከደርኬንጌኞ አንስቶ እስከ ጃሌሎ ድረስ የተዘረጋው ርዝመቱ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ በሆነው የወሰን መስመር ላይ ሲሆን ሐበር አወልንና ገደቡርሲን ኢሳን በመርገጥ የተሠራ ነበር።
በመጨረሻም ጣልያኖች በኡጋዴን ውስጥ ወልወል ላይ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም እለተ ረቡዕ አደጋ በጣሉ ጊዜ መርስዔ ኀዘን በስፍራው ላይ ተገኝተው ከወሰን ተከላካዮቹ ጋር ሆነው አደጋውን ተከላክለዋል። በ1927 ዓ.ም ሰኔ 10 ቀን የትልቁ ወህኒ ቤት ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። ከአንድ ዓመት በኋላ በተከተለውም በጠላት ወረራ ዘመን በጅሩና በዓድአ በሌላም ስፍራ እየተዘዋወሩ ሕይወታቸውን ማትረፍ መቻላቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።
ከጠላት ወረራ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት ሥራ ላይ ሲያገለገሉ የቆዩት እኚሁ ሰው ከእነዚህም መካከል የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ የታሪክና የቤተ መንግሥት ዜና ማሰናጃ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ሆነው መስራታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ የብላታ ማዕረግ 1936 ዓ.ም ካገኙ በኋላም የፍርድ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዓቃቤ ጉባዔ፣ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባልና የሕግ ኮሚቴ ሊቀ መንበር፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ፕሬዝዳንት፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡
መርስዔ ኀዘን ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በመደበኛ ሥራቸው ላይ ደርበው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሹም ሆነው ለ14 ዓመታት፤ የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ተጠባባቂ ሹም ሆነው ለአንድ ዓመት ሠርተዋል። እንዲሁም በርካታ ቦርዶች በአባልነትና በሊቀ መንበርነት የመሩ መሆናቸውን በእሳቸው ዙሪያ የተፃፉ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር በመንግስት ልዩ ትዕዛዝ የፈጸሟቸው አገልግሎቶች፤ ከመደበኛ ሥራቸው ደርበው ልዩ ልዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። ከእነኚህም መካከል የኢትዮጵያና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ድርድር ላይ የመሪነት ሚና መጫወት ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ1940 ዓ.ም የራሷን ፓትሪያርክ እንድትሾም በኢትዮጵያና በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያናት መካከል በሚደረገው ድርድር ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ የተመረጡት ብላታ መርስዔ ኀዘን እስከ ድርድሩ ፍጻሜና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትሪያርክ፣ የአቡነ ባስልዮስ ሢመት እስኪፈጸም ድረስ ተሳታፊ ሆነው አገልግለዋል። ዝርዝር ታሪኩንም «ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ» እና «የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትሪያርክ» በሚል ርእስ ባዘጋጇቸው መጻሕፍት ጽፈውታል።
ለሀገር ሲባል ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁት እኚህ የሀገር ባለውለታ ከመንግስታዊ ስራ ባሻገር በመንፈሳዊ ስራም በተጠሩበት ሁሉ ቅን የሆነ ምላሻቸውን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ ለአብነት ያህልም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማረም ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሆነው ያበረከቱት አስተዋፅኦ ጎልቶ የሚነሳ ሲሆን የተሻሻለው የአማርኛ ሐዲስ ኪዳን እንዲሁም ጠቅላላው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለህትመት እንዲበቃ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር ይነሳል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ የፍትሐ ነገሥት ኮሚሲዮን (የኮዲፊኬሽን ኮሚሲዮን) በ1946 ዓ.ም ሲቋቋም የኮሚሲዮኑ ሊቀ መንበር የፍርድ ምክትል ሚኒስትሩ ብላታ መርስዔ ኀዘን ነበሩ። በፍትሐ ነገሥትና በኢትዮጵያ የነበሩትን ልማዶችና ባህሎችን መሠረት በማድረግ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር፣ የንግድና የባሕር ሕጎችን እንዲዘጋጅ በማድረግ ታሪካዊ ሚና ነበራቸው።
የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዳሚ )ሰኔ 20 ቀን 1964 ዓ.ም ሲቋቋም ብላታ መርስዔ ኀዘን አባል ሆነው የተመረጡ ሲሆን የመርሐ ልሳኑ ዓላማ የመንግሥቱን ቋንቋ አማርኛን ማዳበርና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እንዲስፋፋ ማበረታታት ነበር። ጡረታ እስከወጡበት ዘመን ድረስም በመርሐ ልሳኑ አባልነት አገልግለዋል። የመርሐ ልሳኑ አባል የነበሩት ዶክተር በላቸው አሥራት ስለ ብላታ መርስዔ ኀዘን ‹‹ክቡር ብላታ በኮሚሽኑ ዘንድ የተከበሩ ሊቅ ነበሩ። በተለመደው ጠባያቸው ንግግራቸው የተቆጠበ፤ ሲያስፈልግ አስተያየት የሚሰጡ፤ በተረፈ ግን “ንግግራችሁን አደንቃለሁ›› በማለት ሌሎቻችንን የሚያበረታቱ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
በበርካታ ዘርፎች ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉት እኚህ ሰው ታዲያ በ1964 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆነው ነበር። በ1966 ዓ.ም ጡረታ የወጡት ብላታ መርስዔ ኀዘን ለ49 ዓመት በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውንና መንግሥታቸውን አገልግለው በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ታሪክ በሀገር ባለውለታነታቸው ሲያነሳቸው ይኖራል። ለሀገርና ለህዝብ ያበረከቱዋቸው ስራዎች ትውልድም ሆነ ዘመን ሲሻገር ይቆያል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም