በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚጾመው የዐቢይ (ሁዳዴ) ጾም ባለፈው ሰኞ ተጀምሯል፤ የእምነቱ ተከታዮች ለሚቀጥሉት 55 ቀናት የእንስሳት ተዋፅዖ (ፍስክ) ከሆኑ ምግቦች ይቆጠባሉ። ይህን ምክንያት በማድረግ የሁዳዴ ጾም ከሚገባበት ቀደም ብሎ ያለው ቀን ቅበላ ይባላል። ጾሙን መቀበል ማለት ነው።
አንዳንድ አባቶች ሲያወሩ እንደሰማሁት ቅበላ ልማዳዊ ሆኖ እንጂ የእምነቱ አባቶች የሚያዙት አይደለም፤ ትንሳኤው እንጂ ቅበላው ያን ያህል ትልቅ ሥነ ሥርዓት የሚደረግበት አይደለም። እንደ ልማድ ሆኖ ግን የማይጾመው ሁሉ ሳይቀር የቅበላ ዕለት ሰልፍ ይዞ ሥጋ ይመገባል፤ ሥጋ ቤቶችም ይጨናነቃሉ፤ ይህ የተለመደ ሆኗል።
የዕለቱ ትዝብቴ ግን ከጾም ሥነ ሥርዓቱ ጋር የተያያዘ አይደለም። ይልቁንም በሁዳዴ ጾም መግቢያ ዋዜማ ያየኋቸው ተደጋጋሚ አስተያየቶች ናቸው። ይሄውም፤ በጾም መግቢያ ዋዜማ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ማድረግና አዳዲስ ሙዚቃዎችን ማስተዋወቅን የሚያወግዙ አስተያየቶች ናቸው። ጾም ጸሎት ብቻ እንጂ የአሸሼ ገዳሜና የፌሽታ ሥራዎችን በሃይማኖታዊ በዓላት ሰሞን ማስተዋወቅ ይቅር የሚል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶች፤ በጾም መግቢያ ዋዜማ ቅጥ ያጣ የቅንጦት ሥጋ አመጋገብ፣ ስካርና ዝሙት… መቅረት አለባቸው የሚል ነው። ይህ ማንንም የሚያስማማ ሀሳብ ነው። በሃይማኖታዊ በዓላት ምክንያት ስካርና ዝሙት ከሃይማኖታዊ ትዕዛዝ ውጭ ነው። እነዚህን ነገሮች እንኳን መንፈሳዊ ሰው ዓለማዊ ሰው ሁሉ ሊኮንናቸው የሚገባ ድርጊቶች ናቸው። ምክንያቱም ከሃይማኖት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሳይንስ ጋር ራሱ የተጣሉ ናቸው። ቅጥ ያጣ አመጋገብ፣ ስካር፣ ከትዳር ውጭ የሚደረግ ዝሙት… የጤና ጠንቅ መሆናቸውን ማንም ያውቃል።
የኔ ትዝብት፤ ባህላዊና ልማዳዊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ከሃይማት ማላቀቅ አይቻልም የሚል ነው። ለምሳሌ ዘፈንን ሙሉ በሙሉ ከሃይማኖት ውጭ ማድረግ አይቻልም። በሃይማኖታዊ በዓላት ሰሞን አዳዲስ ሙዚቃዎችን ማስተዋወቅና ኮንሰርቶችን ማዘጋጀት አግባብ ነው አግባብ አይደለም የሚለውን እንተወውና፤ ዘፈን ግን ከሃይማኖት ጋር ፍፁም ተቃራኒ ነው ማለት አግባብ አይደለም።
ከዓመታት በፊት ‹‹ቤት ያጣው ቤተኛ›› በተሰኘው የዮናስ ጎርፌ መጽሐፍ ላይ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጄንሲ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነበር። መጽሐፉ በሙዚቃ ላይ የሚያትት መጽሐፍ ነው። ደራሲው በመጽሐፉ ላይ በሰፊው ከተነተነውና በውይይቱ ላይ ከመለሰው መልስ ይቺኛዋን ሀሳብ ብቻ ልውሰድ።
ሙዚቃ ኃጢአት ወይም ወንጀል የሆነው ምኑ ነው? መሳሪያው? ግጥሙ? ድምጹ? ወይስ ምኑ ነው? ብሎ ይጠይቃል።
እነዚህ የጠቀስናቸው ሁሉ በዕለት ከዕለት ክዋኔዎቻችን ውስጥ ሁሉ አሉ። መሳሪያው ከሆነ፤ መሰንቆ፣ ክራር፣ ከበሮ፣ ዋሽንትም ሆነ የትኛውም ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ መነሻው ቤተ ክርስቲያን ናት። ዛሬም ለተለያዩ ሃይማኖታዊ አግልግሎቶች (ፈጣሪን ለማመስገን) እያገለገሉ ነው። የምስጋና መዝሙሮች እየተሰሩበት ነው። ዘመናዊ መሳሪያዎችም እንደዚያው። ስለዚህ የሙዚቃ መሳሪያ በራሱ ኃጢአት አይሆንም ማለት ነው።
የድምጹ ተስረቅራቂነት? የድምጹ ማማርና ተወዳጅ መሆን? ይህም በተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ያለ ነው። ከቅዳሴ ጀምሮ ለመንፈሳዊ መዝሙሮችና ለአገር ፍቅር መዝሙሮች የድምጽ ማማር ተፈላጊ ነው። ስለዚህ ለዘፈን ሲሆን የተለየ የሚያደርገው ምኑ ነው?
እንግዲህ አከራካሪ የሚሆነው ግጥሙ ነው ማለት ነው። ግጥም ማለት ደግሞ ሀሳብ ነው። ያንን ሀሳብ በሻይ ቡና፣ በትራንስፖርት ውስጥ… በየትኛውም ማህበራዊ እንቅስዋሴዎች ውስጥ የምናወራው ሀሳብ ነው። እንኳን ሌላ ሃይማኖታዊ በሆነው በፅዋ ማህበር ውስጥ ሳይቀር የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ይነሳሉ። በዘፈን ግጥም ውስጥ ያሉት እነዚህ ሀሳቦች ናቸው።
የሃይማኖት አባቶች ሲሉ እንደምንሰማው፤ ዘፈን እንደ ኃጢአት የሚቆጠርበት ምክንያት ወደ አልባሌ ነገሮች ይገፋፋል በሚል ነው። ምናልባትም ዝሙት ለመፈፀም፣ መንፈሳዊ ነገሮችን በመርሳት ዓለማዊ መደሰትን ብቻ ወደማሰብ ይገፋፋል በሚል ነው።
ይህ ግን የዘፈኑ አይነት ይወስነዋል። ለአገር ፍቅር የተዘፈነ ዘፈን ሁሉ ኃጢአት ሊባል ይችላል ወይ? ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መተባበርንና አብሮነትን የሚሰብክ ዘፈን ስነ ምግባርን አይቀርጽም ወይ? ስለዚህ ዘፈን ኃጢአት ነው ሲባል ለወንጀል የሚገፋፉትን ነው ወይስ ሁሉንም ዘፈን የሚያጠቃልል ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል።
ዘፈን የባህል ውጤት ነው፤ ባህል ደግሞ ከሃይማኖት ይቀዳል። ብዙ ልማዳዊ ድርጊቶቻችን ከሃይማኖት የተቀዱ ናቸው። በትክክል ባይታወቅ እንኳን ቢያንስ ሃይማኖታዊ አፈ ታሪክና ሃይማኖታዊ ሐተታ ተፈጥሮ ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ፤ በቅሎ የማትወልደው እግሯን አንስታ ስትራገጥ ሰማዩን መታችው፤ በዚያው ፈጣሪ ተቆጥቶ ቅርብ የነበረውን ሰማይ አራቀው፤ በቅሎንም እንዳትወልድ አደረጋት የሚባል ሐተታ ተፈጥሮ አለ። ስለዚህ ባህልና ልማድን ከሃይማኖት ማላቀቅ አይቻልም።
‹‹ባህላዊ›› የምንላቸው ብዙ ትርዒቶች፣ ጨዋታዎች፣ ክዋኔዎች ሃይማኖታዊ መሰረት ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በነሐሴ ወር የሚከወኑት አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ከሴ አጨዳ እና የመሳሰሉት የልጅ አገረዶች ጨዋታዎች ሃይማኖታዊ መነሻ ያላቸው ናቸው። ለጥምቀት የሚደረጉ ባህላዊ ጨዋታዎች ሃይማኖታዊ መነሻ ያላቸው ነው። በየትኛውም የአገራችን ክፍል የሚገኙ ልማዳዊ ድርጊቶች ሃይማኖታዊ መነሻ አላቸው። ዝርዝር ሃይማኖታዊ ምክንያቶችን መጥቀሱ ለዚህ ጽሑፍ አግባብ ባይሆንም በብዙ ባህሎቻችን ውስጥ ግን ሃይማኖታዊ መነሻ አለ።
በነገራችን ላይ ይህ እንቅስቃሴ የመጣው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተጀመረ ፖለቲካ መር ሃይማኖታዊ ብሽሽቅ ነው። የእናንተ ሃይማኖት እንዲህ ነው፣ የእናንተ የጭፈራ ነው፣ የእናንተ ማጭበርበሪያ ነው፣ የእናንተ የዝሙት ነው፣ የእናንተ የስካር ነው… ከሚሉ ብሽሽቆች የመጣ ነው። ይህን ብሽሽቅ ለመከላከል ይመስላል በሃይማኖታዊ በዓላት ሰሞን ኮንሰርትን እና አዳዲስ ሙዚቃዎችን ማስተዋወቅ ማውገዝ የተጀመረው።
ከዚያ በፊት እንደምናውቀው አዳዲስ ሙዚቃዎች የሚለቀቁት በዓላትን ጠብቀው ነው። ኃጢአት ነው ኃጢአት አይደለም የሚለውን ራሱ ዘፋኙ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤ ዳሩ ግን ዘፈን ለምን ተዋወቀ ማለት ልክ አይመስለኝም። ምክንያቱም ማህበራዊ ሕይወት ከሃይማኖት ጋር የተሳሰረ ነው።
ከዚያ ይልቅ በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ የሚደረገውን ቅጥ ያጣ አመጋገብና መጠጥ፣ የዝሙት ወከባና ሌሎች ፀያፍ ነገሮች እንዳይደረጉ ክልከላ ማድረግ ኃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ ድጋፍም አለው። በሙዚቃ ባህልና ታሪክን ማስተዋወቅ ወንጀልና ኃጢአት የሚሆንበት ምክንያት አይገባኝም። ስለዚህ ልማዳዊና ባህላዊ ከዋኔዎችን ከሃይማኖት ማላቀቅ አይቻልምና ቢታሰብበት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም