ከብዙ ስኬቶች ጀርባ ከፍ ያሉ ጥረቶችና ትጋቶች ይስተዋላሉ። የለፋ የጣረ ደግሞ የልፋቱን ዋጋ ማግኘቱ አለያም ያሰበበት መድረሱ አይቀርም። በተለይ ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ካላቸው ቦታ እንዲሁም ተፈጥሮ የተነሳ ስኬታማ ለመባል ብዙ ትግልና ውጣ ውረደን ሊያልፉ ግድ ይሆናል። የልፋትና የውጤት ተምሳሌት የሆኑት ወይዘሮ ይመኙሻል ወርቃለማሁ ደግሞ የዚህ በጥረት የታጀበ ስኬት ማሳያ ናቸው።
ወይዘሮ ይመኙሻል ወርቃለማሁ ተወልደው ያደጉት አዳማ ከተማ ሲሆን፤ ከልጅነታቸው ጀምሮ ታታሪና ኃላፊነት የሚሰማቸው እንስት ናቸው። በዚህ ሁኔታቸው ደግሞ ብዙ ሰዎች ያደንቋቸዋል። በተለይም እናቱ ጋር እንዳለ ልጅ ትምህርት እየተማረች ያገኘቸውን እየበላች ቤተሰቧ ላይ መኖርን አለመምረጣቸው ለብዙዎች አርአያ የሆኑበት ነው። ልጅ ሆነው አባታቸውን በሞት በማጣታቸው ቤተሰቡን የማስተዳደር ሃላፊነትን ከእናታቸው ባልተናነሰ መልኩ ሲከውኑት ኖረዋል። የማገዝ ሀላፊነቱንም ተወጥተዋል። ገና በለጋነት እድሜያቸውም ነው እየሰሩ መማርን የጀመሩት።
ከአሰላ የተለያዩ የእህል ዘሮችን በማምጣት ተወልደው ባደጉበት አዳማ ከተማ ላይ ይሸጣሉ። ገቢውም ጥሩ ስለነበር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የቤተሰቡ አባላት እንዲሁም ለዘመድ አዝማዶቻቸው መድረስ ችለዋል።
“…በወቅቱ አባቴ በሞት ተለይቶን ስለነበር እናቴ ብቻዋን ናት። እሷንም እራሴንም እንዲሁም ሌሎች የቤተሰቡን አባላት መደገፍ ደግሞ በጣም እፈልግ ነበር። እነሱን መደገፍ ማስደሰት ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር፤ ለራሴ የምለው አንድም ነገር አልነበረም። ስለዚህም መስራትን ምርጫዬ አደረኩት። ” በማለት የሥራ ጉዟቸው ምን እንደሚመስል የሚናገሩት ወይዘሮ ይመኙሻል፤ አዳማ ከተማ ላይ ሥራና ትምህርትን እያስኬዱ በርከት ያሉ ዓመታትን አሳልፈዋል። የእህል ንግዱን አዋጭነት ሲመለከቱም ሥራውን ከአዳማ ሻገር ብለው ለማስኬድ አሰቡ። ይህም ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ማስፋት ሲሆን፤ እህል እየጫኑም ቀን በቀን መመላለስን ዋና ተግባራቸው አደረጉ። ትምህርታቸውን ወደማታው ክፍለ ጊዜ በማዞርም ነበር ይህንን ሁሉ ተግባራቸውን የሚያከናውኑት። ስለዚህም የእርሳቸው የውሎ ሁኔታ ማታንም ያጠቃልላል።
ይህ ታታሪነታቸው እንዳለ ሆኖ ከሥራና ትምህርት ባሻገር ትዳር መመስረትን አለሙ፤ አደረጉትም። ምክንያቱም ይህም ሌላ ተጨማሪ ኃላፊነት አለበት። ሁኔታውን ሲያስረዱም እንዲህ ነበር ያሉት “…በወቅቱ ከፍ ያለ የሥራ ፍቅር ነበረኝ። ብዙ እሰራለሁ፤ ትልቅ አልማለሁ፤ አስባለሁም። እዛ ላይ ለመድረስ ቀን ከሌሊት እለፋለሁ፤ ደከመኝ አልልም። ሁሉ ነገር ስኬታማ እንዲሆን ደግሞ በእውቀት መደገፍ አለበትና ትምህርቴንም በአግባቡ እከታተላለሁ። ይህ ሁሉ መስመር የሚይዘውና የሚቀጥለው ደግሞ በተባረከ ትዳር እንደሆነ አሰብኩ። በዚህም ገባሁበት።”
ትዳርና ሥራን ጎን ለጎን ለመምራት ኑሮዋቸውን አዲስ አበባ አደረጉ። ይህ እድል ደግሞ ሌላ የሥራ አማራጭን አመላከታቸው። ይህም የምግብ ቤት ሥራ ነው። እናም ሀሳባቸውን መሬት ለማስያዝ የንግድ ቤት ከባለቤታቸው ጋር ሆነው ማፈላለግ ጀመሩ። ይህ ቤት የመፈለግ ስራ አድካሚ ቢሆንም ወይዘሮ ይመኙሻል አልችልም፣ አጣሁ በቃ የሚለውን ነገር አይቀበሉትምና ስኬታቸው ላይ እስኪደርሱ ፈለጉ። አገኙትም።
“…አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ የእህል ንግድ ስራውን ትቼ ወደ ምግብ ቤት ስራ ተሳብኩ። ለስራው የሚሆን ቦታ ሳፈላልግ ደግሞ ያገኘሁት የአፍሪካ ህብረት ቀበሌ የንግድ ቤት በጨረታ አውጥቶ ለማስተላለፍ ያወጣውን ማስታወቂያ ነው። ጊዜ ሳላጠፋ ጨረታውን በማስገባት እድሌን መጠባበቅ ጀመርኩ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጨረታውን በማሸነፌ የምግብ ቤት ስራዬን አሀዱ አልኩ። ›› በማለትም የስራ አጀማመራቸውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ይመኙሻል ምንም እንኳን በትምህርታቸው የመግፋት ህልም ቢኖራቸውም በወቅቱ ግን የስራ ቦታቸው፣ የምትሰሩት ሥራ፣ ትዳርና ቤተሰብ መደገፉ በአንድ ላይ የሚሄዱላቸው አልሆኑም። ስለዚህም ትምህርታቸውን ማቋረጥ ግድ ሆነባቸው። ከስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የማቋረጣቸው ምስጢርም ይህ ነበር። የጀመሩትን የምግብ ቤት ሥራ እየተሯሯጡ በማስቀጠል ቤተሰብንና የራሴ የሚሏቸውን ልጆች ወደ ማሳደጉ ገቡ። የወጣትነት ጉልበታቸውን በአግባቡ እንደተጠቀሙበት ይሰማቸዋል። ይህ ትጋታቸውም ከእለት እለት ፍሬ እያፈራ ውጤት እያመጣ የሄደም ሆኖላቸዋል።
ወይዘሮ ይመኙሻል ምግብ ቤት ሲከፍቱ እንደተለመደው አይነት እንዲሆን አልፈለጉም። ይልቁንም ስጋ ቤት ያለውና ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በውስጡ ማካተት እቅዳቸው ነበር። አሳክተውታልም። “…ምግብ ቤቱ ስጋ ቤትም ያለው እንዲሆን ነው ያደረኩት። የስጋ ስራ ደግሞ አንዳንዴ በብሔር (የጉራጌ የሌሎችም) ይባላል። በዚያ ላይ ደግሞ በጾታ ሳይቀር ይለያል። እናም ይህ ሥራ ለሴት ያልተፈቀደ ያህል ተደርጎ ይታመናል። እኔ ግን ሁሉንም እችላለሁ የሚል አቋም አለኝና ገባሁበት” ይላሉ አላስፈላጊ ልዩነቶች በሀገርኛ ባህል ውስት ቢኖሩም እነዚህን ተጋፍጠው እንዴት እንደጀመሩት ሲያስረዱ።
ወይዘሮ ይመኙሻል ምንም እንኳን ለሥራው ልዩ ፍቅርና የእችላለሁ ስሜትን አዳብረው ወደ ሥራው ቢገቡም ሥጋ እንዲቆርጡላቸው ከሚቀጥሯቸው ሰራተኞች ጋር ግን በቀላሉ መስማማት አልቻሉም። ከደንበኞች ጋር ያላቸውን ግንኙነትም አልወደዱትም። እናም ይህንን ጉዳይ እልባት መስጠት እንዳለባቸው ወሰኑ። መላ ያሉትም እራሳቸው ሥጋ ቤቱን መያዝ እንዳለባቸው ነው። ስለዚህም የሥራ ልብሳቸውን (ጋዎኑን ) ለብሰው ለደንበኞቻቸው ሥጋ ወደ መቁረጡ ገቡ።
“…ጋዎኔን ለብሼ እራሴ ሥጋ መቁረጥ ጀመርኩ። የሚያዩኝ አንዳንድ ደምበኞቼ እንዴ ሴት ይላሉ። ግን ደግሞ ሴት ምንድናት፣ የታረደን ብትቆርጥ ምን ችግር አለው፣ ስራ ነው በማለት ጆሮ ሳልሰጥ ስራዬን አጠናክሬ መስራቴን ቀጠልኩ። በዚህም በርካታ ደንበኞችን መያዝ ቻልኩ” ይላሉ የምግብ ቤት ውሏቸው ምን ያህል በተለየ የመፍትሄ ሀሳብ እየታገዘ እንደሚጓዝ ሲያወሱ።
ይህ ሥራቸው ለአንዳንዶች ደስታ ባፈጥርም ለብዙዎች ግን ሀሴትን ያጎናጸፈ ነበር። በተለይም ለሴቶች የማንችለው ነገር የለም እንዲሉ ያስችላቸዋል። አብዛኞቹ ደንበኞቻቸውም የሚሳቡት በዚህ ትጋታቸው ነው። ሥራቸውን ከ3እስከ 4መቶ ብር በመያዝ የጀመሩት ወይዘሮ ይመኙሻል፤ የስጋ ቤት ንግድ ብዙ ደንበኞችን ቢያፈራላቸውም፤ ብዙ ደንበኞችን ቢያገኙበትም ሥራው ከባድ በመሆኑ በተጨማሪም ባለቤታቸው በቃ ምግብ ቤቱን ብቻ አጠናክረሽ ቀጥይ በማለታቸው የስጋ ንግዱን ትተው ሙሉ በሙሉ የምግብ ቤቱ ላይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሆነዋል።
ወይዘሮ ይመኙሻል ስለሰራተኞቻቸው ሲናገሩ ‹‹ከስሬ ያሉ ሰራተኞችን ልባዊ በሆነ የጓደኝነት የእናትነት ፍቅር ነው የምይዛቸው፤ ይህንን ማድረጌ ደግሞ ስራው እኔ ብኖርም ባልኖርም እንዲሰራ አድርጎታል። ወልጄ ስተኛ እንኳን ምንም ችግር ሳይኖር በአግባቡና በስርዓቱ ይሰራ ነበር። በዚሀም የቤቱ ባለቤቶች ራሳቸው ናቸው። ከሰሩ ደመወዝ ያገኛሉ ካልሰሩ ደግሞ በቃ እኔም እነሱም ችግር ውስጥ እንገባለን። ይህንን ደግሞ በደንብ ስለሚያውቁና ስለተረዱ ቤቱን በባለቤትነት ስሜት ያስተዳድሩታል›› ይላሉ።
“…በመጀመሪያ ሰው የሚያሰራውን ማንኛውንም ሰራተኛ ማክበር አለበት፤ እኔ ቀጣሪዋ እሱም ተቀጣሪው ለስራ እኩል ነን ብሎ ማመን ያስፈልጋል፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ እኔ የምፈልገው ነገር በሙሉ እሱም ያስፈልገዋል፤ በዚህም መብላት፣ መከበር፣ ደመወዙን በወቅቱ ማግኘት፣ ችግር ሲገጥመው፣ ሲያመው ፍቃድ ማግኘት ይገባዋል። እነዚህን ሁሉ ካሟላ በኋላ ደግሞ እኔ ከእነሱ የምፈልገው ነገር አለ። ይህ ደግሞ ለስራው ብቻ ሳይሆን ለእነሱም የነገ ሕይወት መለወጥ መስራት አለበት። መጠጣት ማጨስ መቃም ለእኔ ሰራተኞች አይፈቀድም። ጨዋ መሆን ደግሞ በሕይወትም በክብርም እንደሚያኖር ልምዴን እየተጠቀምኩ ባገኘሁት አጋጣሚ እነግራቸዋለሁ፤” በማለት በሰራተኛ አያያዝ በኩል የምትሄዱበትን ርቀት ያስረዳሉ።
ይህ የወይዘሮ ይመኙሻል የሰራተኞች አያያዝ ደግሞ ድርጅታቸውን ከምዝበራ ከማዳኑም በላይ ለብዙዎች ማደግ ምክንያት ሆኗል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ “…ሰራተኛ እኔ ስለቀጠርኩት ብቻ ገዝቼዋለሁ ማለት አይደለም፤ ያሳለፈው ወደፊት የሚመኘው ሕይወት ያለው ነው። ይህንን ህልሙን ለማሳካት ደግሞ ብዙ ነገሮችን ሊያስብ ይችላል። ያንን ቀረብ ብሎ እንደሰሪና አሰሪ መረዳት ጥሩ ነው። የሚገርምሽ እኔ አንዲት ሰራተኛ ነበረችኝ። ሁልጊዜ ሳያት ታዝናለች፤ ታለቅሳለችም ፤ ትጮሃለች። እኔም ይህች ልጅ ሰው ያልተረዳላት አንድ ችግርማ አለባት ብዬ አስቤ ብቻችንን ቁጭ ብለን እንድናወራ አደረኳት። የነገረችኝ ነገር በጣም ልብ የሚነካ ነበር። ደግሞም ለሰው የሚወራ አይደለም፤ በጣም አዝኜ አሁን ምን ትፈልጊያለሽ? ስላት በቃ ልትረጂኝ ካሰብሽ “ገንዘብ አበድሪኝና አረብ አገር ላኪኝ ” አለች። እኔም እሺ ብዬ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ወጪ አድርጌ ላኳት። ሰርታ መጣች ፤ ማረፊያዋንም እኔ ጋር አደረገች። አሁን የራሷን ስራ እየሰራች ትዳር መስርታ ልጅ ወልዳ በሰላም ትኖራለች። ከእኔ ጋርም እናትና ልጅ ሆነናል።” በማለት ይናገራሉም።
ወይዘሮ ይመኙሻል የምግብ ቤት ሥራቸውን እየሰሩ ጎን ለጎን ተጨማሪ ሥራዎችን በመስራት በኩልም ባለራዕይ ናቸው፤ የመከላከያ ሚኒስቴር ሰልጣኞችን ለመቀለብ በአወጣው ጨረታ ተሳትፈው የምግብ ባለሙያ በመሆን ” ሁርሶ” ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ ለሶስት ወራት፣ አዋሽ አርባ፣ ጎሬ፣ ሆለታ በመንቀሳቀስ ምልምል ሰልጣኞችን የመቀለብ ሥራን ሰርተዋል። በ1997 ዓ.ም ግን ስራው ሊቋረጥ ችሏል። ሆኖም እርሳቸው ግን ከመሥራት አልተቆጠቡም። የሥራ ዘርፋቸውን በመቀየር የጊቤ 3 ሀይል ማመንጫ ግንባታ ላይ የነበሩትን “የሳሊኒ ኮንስትራክሽን” ሰራተኞችን ምግብ እየሰሩ ወደ ማብላት ገቡ። በዚህ በቀን ለስምንት ሺህ ህዝብ የሚበቃ ምግብን ማዘጋጀት ይችሉ ነበር። ይህ ሥራቸው ደግሞ የበለጠ ጥንካሬን ሰጣቸውና ዳግመኛ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የምግብ ቤት ሥራውን እንዲጀምሩ አደረጋቸው።
ሴትነት፣ እናትነት፣ ሚስትነትን ከስራ ጋር አጣምረው የያዙት ወይዘሮ ይመኙሻል፤ በዚህ ሁሉ የስራ ሂደት ውስጥ አራት ልጆችን ወልደው አሳድገዋል። ባለቤታቸውም ቢሆኑ ልጆቹንም ሥራቸውንም በማገዙ በኩል ደከመኝ አላሏቸውም። ትናንት የተተው ስጋ ቤት ዛሬ ላይ በሰፊው እየሰራ ይገኛል። ሥራው ግን የቀጠለው በእርሳቸው አይደለም። የእናቱን ፈለግ በተከተለው ትልቁ ወንድ ልጃቸው አማካኝነት ነው። በዚህ የስራ ቦታ ላይም ከ35 እስከ 40 የሚደርሱ ሰራተኞች አሉ።
የወንድ የሴት ስራ ብሎ ነገር የማይገባቸው ወይዘሮ ይመኙሻልም አጉል አስተሳሰብን ወደጎን በመተው ሁሌም በስራቸው ስኬታማ ለመሆን ይተጋሉ። ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ኃላፊነት የመሸከም ብቃት አላቸው። በሥራም ውጤታማ ለመሆን እድል እንጂ ሌላ ደጋፊ አያስፈልጋቸውም የሚል እምነት አላቸውናም ያንን እውን አድርገው ለሌሎች አርኣያ ለመሆን ይታትራሉ።
“…ሰዎች በተለይ የንግድ ስራን የሚጀምሩ አተርፋለሁ ብቻ የሚል እምነትን ይዘው መግባት የለባቸውም፤ ልከስርም እችላለሁ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ትርፍ ብቻ የሚታሰብ ከሆነ በትንሽ በትልቁ ስራው ራሱ ያስጠላል፤ እኔ መስራትና መልፋቴን ወጥቼ መግባቴን እንደ ትርፍ እቆጥረዋለሁ፤ ከነገ ዛሬ ይሻሻላል በሚልም ተስፋ አደርጋለሁ። አንድ ስራ ጀምሬ ካላዋጣኝ ትንሽ ታግሼ ሌላ ስራ አጠናለሁ፤ በመሆኑም ሰዎች ስራቸው ላይ ብቻ በትክክል ትኩረት ማድረግ ከዚያ ደግሞ ታጋሽ መሆን ይገባቸዋል” በማለት ይመክራሉ።
ምስክርነት
“….ይመኙሻል በጣም ጎበዝ ታታሪ ብሎም ውጤታማ ሴት ናት። አብረዋት ለሚሰሩ ሰራተኞች ደግሞ እጅግ አዛኝና የእሷ የስራ ስኬታማነት ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆን ነው። ወደፊትም በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ እንድምትደርስ ጅማሬዋ ያሳየናል” በማለት ስለ ወይዘሮ ይመኙሻል የሚናገሩት ከወይዘሮዋ ጋር ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በስራ አጋርነት የቆዩት ወይዘሮ መሰረት እንግዳጌጥ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይመኙሻል ማለት ከትንሽ ስራ ተነስታ ራሷን ለማሳደግ ሰፋ ያለ ጥረትን ያደረገች ናት፤ ይህም ጥረቷ ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ላይ የድካሟን ውጤት እያየችው ትገኛለች። አብሬያት ስራ ስጀምር ስራ ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን በስራ ሂደት የምሰራውን እንድወድ፣ ጠንካራ እንድሆን፣ በራሴ የተማመንኩ ሴት እንድሆን አግዛኛለች። በገንዘብም ደረጃ ቢሆን አሁን ላይ ጥሩ ደረጃ ላይ እገኛለሁ። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። እርሷንም አመሰግናታለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም