ኢትዮ ቴሌኮም ከቅርብ ቀናት ወዲህ ለደንበኞቹ በሚያቀርባቸው የተለያዩ ጥቅል አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ ጉርሻ እንደሚሰጥ ይታወቃል። ለምሳሌ 50 ሜጋባይት የኢንተርኔት ጥቅል የሚገዛ ደንበኛ ተጨማሪ 50 ሜጋባይት ይመረቅለታል። ያም ሆኖ በርካቶች ተጨማሪ ጉርሻው ትክክል እንዳልሆነና የገዙት ጥቅልና ጉርሻው ብዙም ሳይጠቀሙበት እያለቀባቸው መሆኑን ሲያማርሩ ይሰማል። ቅሬታው ትክክል ይሁን አይሁን ጉዳዩን ለኢትዮ ቴሌኮም ልተወውና ይህ የቅናሽ ጉዳይ ወዳስታወሰኝ ትዝብት ልግባ።
ከሰሞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ልጀምር። ባለፈው የካቲት 07/2015 የፍቅረኛሞች ቀን(ቫላንታይን ደይ) በተለያዩ ሀገራት እንደወትሮው መከበሩ ይታወቃል። በኢትዮጵያም ይህ በዓል በተለይም በከተማ ወጣቶች ዘንድ በስፋት መከበር ከጀመረ ቆይቷል። ታዲያ ይህን በዓል አስመልክቶ በየቡቲኮች ለበዓሉ ዋነኛ ድምቀት የሆኑ ቀይ አልባሳት ላይ ታላቅ ቅናሽ በሚል ተለጥፎባቸው ማየት የተለመደ ነው። በዓሉ ከምዕራባውያን የመጣ በመሆኑ በሀገራችን መከበር አለመከበሩ ብዙ ክርክሮችን የሚያስነሳ ጉዳይ በመሆኑ ወደሱ ጉዳይ አልገባም። ግን በርካቶች ይህን በዓል አስመልክቶ ቀይ አልባሳት ላይ ታላቅ ቅናሽ ከሚደረግ ይልቅ እንደ ቀይ ሽንኩርትና ቀይ ጤፍ ላይ ቅናሽ ቢደረግ ለሰፊው ሕዝብ እንደሚጠቅም የሚሰጡት አስተያየት አዝናኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ወደ ቁም ነገሩ ስገባ በዚህ ወቅት በየቡቲኮቹ ታላቅ ቅናሽ ተብሎ የሚቸበቸቡ አልባሳት እውነት ታላቅ ቅናሽ ተደርጎባቸው ነው? ብለን ከጠየቅን መልሱ ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን በዓል ብቻም ሳይሆን በአዘቦት ቀን ታላቅ ቅናሽ ተብለው የሚሸጡ ነገሮች ሁሉ እውነት ታላቅ ቅናሽ ተደርጎባቸው አይደለም። ታላቅ ቅናሽ የምትለው መሪ ቃል ዝም ብላ ገበያ መሳቢያ እንጂ እውነት እንዳልሆነ ዞር ዞር ብሎ ገበያውን መቃኘት ይቻላል።
ታላቅ ቅናሽ የሚል የገበያ ጥሪ አይተን አንድ ቡቲክ ዘው ብለን ገብተን አንድ ሱሪ ለመግዛት ብንፈልግ የሚጠራው ዋጋ ሱሪው ታላቅ ቅናሽ ሳይደረግበት ስንት እንደነበር ስናሰላው ጆሮን ጭው ሊያደርግ ይችላል። ሕዝቡም ታላቅ ቅናሽ የሚለው መሪ ቃል የነጋዴው የታላቅ ሽያጭ የገበያ ስትራቴጂ መሆኑ እየገባው የመጣ ይመስላል። ሆን ብሎ ታላቅ ቅናሽ የሚል ማስታወቂያ አይቶ ብቻ በማመን ወደ መሸጫ ሱቆች የሚሄድ ሰው ያን ያህል ነው። በእርግጥ ታላቅ ቅናሽ ብለው በመጠኑም ቢሆን ቀነስ አድርገው የሚሸጡ ነጋዴዎች የሉም ማለት አይደለም። እንዲህ አይነቶቹ ነጋዴዎች ታላቅ ቅናሽ እያሉ ታላቅ ሽያጭ ከሚያደርጉ ነጋዴዎች ጋር እኩል ላለመወቀስ “እውነተኛ ቅናሽ” ብለው በሌላ መንገድ የሚመጡት ወደው አይመስለኝም። ያው “እውነተኛ ቅናሽ” የሚለው በራሱ እውነት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም።
አንዳንዶቹ ነጋዴዎች ደግሞ አሉ ከዚህም በተለየ ስልት ገበያ ለመሳብ ሌላ መንገድ የሚከተሉ። እነዚህ ነጋዴዎች በተለይም በቡቲኮቻቸው የሚሸጡት እቃ ላይ ዋጋውን በመለጠፍ ታላቅ ቅናሽ ከሚለው ማስታወቂያ በተሻለ ገዢን ለመሳብ የሚጥሩ። እነዚህ በአንፃሩ የተሻሉ ይመስላል። የነዚህ ችግር ግን የለጠፉት ዋጋ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርአን ቃል አይለወጥም። ገዢ ተከራክሮ ዋጋ አስቀንሼ ገዛለሁ ማለት እዚህ አይሠራም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ ሌላ ጉዳይ ላንሳ። በዓላትን ተከትሎ በትልልቅ ከተሞች ኤግዚቢሽንና ባዛሮች የተለመዱ ናቸው። በአነስተኛ ከተሞች ደግሞ ተጓዥ ባዛሮች በስፋት ይታወቃሉ። የበዓል ወቅትን ተከትሎ በየዓመቱ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለመግዛት ከሚያዘወትሯቸው የገበያ ማዕከላትና ዝግጅቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተመራጭ የሆኑት ባዛሮች ይገኙበታል።
አንዳንድ ሰዎች የእቃዎች ዋጋ በባዛር ገበያ እንደሚቀንስ ያስባሉ። ሌሎቹም ደግሞ ውጭ ከሚሸጠው ምንም ዓይነት የዋጋ ልዩነት እንደሌለው ሲናገሩ ይደመጣሉ። የዋጋ ቅናሽ ባይኖርም የተለያዩ እቃዎችን ከባዛር ገበያ ለመሸመት ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚመጣ የሰው ቁጥር ግን ቀላል የሚባል አይደለም።
ያም ሆኖ በነዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ እቃዎች ላይ ይህ ነው የሚባል የዋጋ ቅናሽ እንደሌለ እግር ጥሎት የሄደ ሁሉ ማስተዋሉ አይቀርም። በመደበኛ ሱቅ 1000 ብር የሚገዛው የባህል ቀሚስ በባዛሩ ላይ 1200 ሲሸጥ ልናገኘው እንችላለን። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች በነጋዴዎች በኩል ይቀርባሉ። አንዳንድ አነስተኛ እቃ የሚሸጡ ነጋዴዎች ባዛሩ ላይ ለመሳተፍ የሚከፍሉትን ወጪያቸውን ለመሸፈን ዋጋ ይጨምራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ራሳቸው ነጋዴዎች ሳይሆኑ የሽያጭ ሠራተኛ ሆነው እቃው ከሚሸጥበት ዋጋ ከፍ አድርገው በመሸጥ ትርፉን ወደ ኪሳቸው ለማስገባት ሲሉ እሳት የላሰ ምላሳቸውን ተጠቅመው ሸማቹን ያሳምናሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ የደረሰበት ደረጃ እና ሃገሪቷ ያለችበት የፀጥታ ሁኔታ እንደ ምክንያት ይነሳሉ።
በበዓል ወቅቶች በከተሞች የሚዘጋጁት የባዛር ገበያዎች ዋና ዓላማ በርካታና የተለያዩ እቃዎችንና ሸቀጦችን በቅናሽ ዋጋ በአንድ ስፍራ ለሸማቹ ማቅረብ እንደሆነ ይታሰባል። ነገር ግን አብዛኞቹ ባዛሮች ላይ የዋጋ ቅናሽ አለ በሚለው ላይ ሁሉም ሸማቾች አይስማሙም። ያም ሆነ ይህ ታላቅ ቅናሽ ብሎ የእውነትም ቅናሽ በሌለበት ከንቱ ማስታወቂያ የምንታለል ሰዎች ካለን በቅድሚያ የገበያ ጥናት ማድረግ ለሁላችንም ይበጃል ለማለት ያህል ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም