የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናችንን ለመጠበቅ ከሚሰጠን ጥቅም በተጨማሪ ሥነልቦናዊ የሆኑ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ባለሙያዎች ደጋግመው ነግረውናል። ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝን አንድ ጽሑፍ በጥቂቱ ልጥቀስ። ጽሑፉ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ አንጻር የሰው ልጆችን ዕድሜ በሁለት መክፈል ይቻላል ይላል። እነሱም ትክክለኛው ዕድሜ እና ፊዚዮሎጂካል ዕድሜ ናቸው።
ፊዚዮሎጂካል ዕድሜ የሚባለው ዕድሜያችን ስንትም ይሁን ስንት ሰውነታችን ላይ የሆነ ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝን ሰው የአካል ብቃት እንዲታይብን ያደርጋል ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ የ20 አመት ጎረምሳ ፊዚዮሎጂካል ዕድሜው 40 ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የአንድ የ60 አመት አዛውንት ፊዚዮሎጂካል ዕድሜ 40 ሊሆን ይችላል። የአንድ ሰው ፊዚዮሎጂካል ዕድሜ ከትክክለኛ ዕድሜው ከበለጠ ያሰው ያለ ዕድሜው እያረጀ ነው እንደማለት ነው:: ፊዚዮሎጂካል ዕድሜን ትልቅ ወይም ትንሽ ከማድረግ አንጻር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ከዚህ መገንዘብ የምንችለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናን መጠበቅ ብቻም ሳይሆን ፊዚዮሎጂካል ዕድሜያችንን ዝቅ ማድረግ እንደምንችል ነው። ይህ ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ነገር ግን በተግባር ካልተደገፈ ፍላጎት ብቻ ዋጋ የለውም። እንደኛ ዓይነት ማህበረሰብ ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ የማድረግ ፍላጎቱ እንጂ ተግባሩ ላይ እንደሌለበት ግልጽ ነው። ፍላጎቱ እንዳለን የሚያሳይ አንድ ጥሩ አባባል አለ መቀመጥ…. የሚል። ግን ከአባባል አልፎ እንደ ጥሩ ባህል አዳብረነው አንገኝም።
የዛሬው ትዝብቴ ማጠንጠኛ ሃሳብም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች በመንግሥትም ይሁን በግል የቢሮ ሥራ ላይ ተሰማርተን የምንገኝ በርካታ ዜጎች ጉዳይ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጥናት ቢደረግብን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መገኘታችን አይቀርም። ያው የከተማ ኑሮ በብዙ ነገሮች የተወጠረና ብዙ የሚያሳስቡ ጉዳዮች ያሉበት እንደመሆኑ ብዙዎች ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትኩረት ባንሰጥ አይገርምም። ነገር ግን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ጊዜና ትኩረት ሰጥቶ ማከናወን ባይቻል እንኳን ተመጣጣኝ ባይሆንም አማራጭ አለ። ይህ አማራጭ ቢያንስ በእግር መንቀሳቀስ የምንችልበትን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ነው። ብዙዎቻችን ግን ይህን ዕድል እንደማንጠቀምበት የዕለት ከዕለት ውሏችንን መለስ ብለን እናስተውል።
ብዙዎቻችን ጠዋት ተነስተን ወደ ሥራ ቦታ የምንሄደው በታክሲ ወይም በተለያየ የትራንስፖርት አማራጭ ነው። በርካቶቻችን ከሥራው ባህሪ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል ቢሮ ገብተን ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለን ስንሠራ እንውላለን። ምናልባት ምሳ ሰዓት ላይ(የምሳ ዕቃ ካልቋጠርን) እዚያው በሥራችን አቅራቢያ ከቢሮ ወጣ ብለን እንመገባለን። በዚህች ጥቂት የምሳ ሰዓት ራቅ ወዳለ ቦታ በእግር ተጉዞ ለመመገብ የሥራው ባህሪና ያለችን ሰዓትም አትፈቅድልንም። ማታ ከሥራ መልስም ወደ እቤት ለመሄድ እዚያው በአቅራቢያችን የሚገኝ ትራንስፖርት ተጠቅመን ካልሆነ በእግር የተወሰነ መንገድ የመጓዝ ልምዱ የለንም። ቀጥሎም እቤት ገብተን በሥራ የደከመ አካላችንን አሳርፈን ለነገ ሥራ ራሳችንን ማዘጋጀት ነው። በነጋታውም የዕለት እንቅስቃሴያችን የተለየ አይደለም። ይህ ድግግሞሽ በብዙዎቻችን ዘንድ ቢያንስ በሳምንቱ የሥራ ቀናት ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል።
ቢሮ በሥራ ተጠምደው ቁጭ ብለው የሚውሉትን ለምሳሌ ያህል አነሳሁ እንጂ እንደ ማኅበረሰብም ለዚህ ችግር ተጋላጭ መሆናችን አከራካሪ አይደለም። በአሁኑ ወቅት በኅብረተሰቡ ዘንድ የጤና እና የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድ እየተሻሻለ መምጣቱ ቢነገርም በጥናት ቢደገፍ ብዙ ርቀት እንዳልተጓዝን መታወቁ አይቀርም። ለዚህ አንዱ ማሳያ በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚሞተው ሰው 52 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን በቅርብ የተሠሩ ጥናቶችን መመልከት ይቻላል። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሁሉ መንስኤያቸው እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ብቻ ባይያያዝም መቀነስ የሚቻለው በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው።
ከፈረንጆች ልንወስዳቸው ከሚገቡ ጥሩ ባህሎች ውስጥ አንዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በየዕለቱ ማድረግን ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ግዴታ ጂም መሄድ ወይም የተመቻቸ ነገር ማግኘት አይጠበቅብንም። ባለንበት ቦታ ሆነን በቀን የተወሰነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ባህሉ እና ቁርጠኝነቱ ቢኖረን ፈርጀ ብዙ የሆኑ ጥቅሞችን ማግኘት እንችላለን። ብዙዎቻችን ጋር ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። የ1ብር ከ50 ሳንቲም መንገድ እንኳን በእግራችን ለመሄድ የምንፈልግ ስንቶቻችን ነን? አንድ ኪሎ ሜትር የማይሞላ መንገድ በእግር ላለመጓዝ ታክሲ አንድ ሰዓት ተሰልፈን የምንጠብቅ ሰዎች ቁጥራችን ጥቂት አይደለም። ምናልባት አንድ ሰዓት ተሰልፈን በታክሲ ለመጓዝ የምንፈልገው መንገድ ቢበዛ በእግር ሰላሳ ደቂቃ ቢፈጅብን ነው። ይህንን መንገድ በእግር መጓዛችን ግን ጥቅሙ ሰዓት መቆጠባችን ብቻ ሳይሆን ከዚያም የዘለለ ነው። ሌላው ይቅርና ሙሉ ጤና ይዘን ሁለት ፎቅ በእግር ላለመውጣትና ላለመውረድ አካልጉዳተኞችና አቅመ ደካሞችን አሳንስር (ሊፍት) የምንጋፋ ጥቂት አይደለንም።
በዚህ ረገድ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች እንቅስቃሴ የማድረግ ባህላችንን ለመቀየር በእረፍት ቀናት መንገዶች ከተሽከርካሪ ነፃ ሆነው ነዋሪዎች የእግር ጉዞና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ የተጀመሩ ጥረቶች ወረት ሆነው መቅረት የለባቸውም። በብስክሌት የመንቀሳቀስን ጉዳይም መንግሥት ጀምሮት የነበረውን ሃሳብ ከግብ ሳያደርሰው ሊዘነጋው አይገባም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም