የትምህርት ነገር በሀገራችን ኢትዮጵያ በብርቱ ሕመምና ሥቃይ ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል። ነገረ ጉዳዬን ፈር ለማስያዝ ያግዝኝ ዘንድ ጥቂት ገጠመኞቼን ላስቀድም።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንዲት የሥራ ባልደረባዬ የሆነች ጓደኛዬ ስልክ ደውላልኝ- “እባክህ አንድ ጉዳይ ላማክርህ ፈልጌ ነበር፤” አለችኝ። የእኔን ዕርዳታና የምክር እገዛ የሚሻ ምን ጉዳይ አጋጥሟት ይሆን ይህች ወዳጄ በሚል ሥጋትና ፍርሃት ውስጥ ሆኜ – ምንድን ይሆን ጉዳዩ አልኳት። እንዲህ ስትል ጉዳዩዋን አጫወተችኝ።
“… ይኸውልህ ታናሽ እህቴ የሁለተኛ ዲግሪዋን በአንድ የግል ኮሌጅ እየተማረች ነው። እናም ለማስተርስ ዲግሪዋ ማሟያ የሚሆናትን የጥናት ወረቀት የሚሠራላት ሰው ትፈልጋለች። አንድ ሁለት ሰዎችን ጠይቃ ነበር ግን ከ 15 እስከ 20 ሺህ ብር ዋጋ ጠየቋት። መቼም የመንግሥት ቤት የደመወዝ ነገር ታውቃዋለህ… ዋጋው ተወደደባት እናም ቀነስ ባለ ዋጋ የሚሠራ አንተ የምታውቀው ተባባሪ ሰው ካለ እንድትጠቁመኝ ብዬ ነው፤” አለችኝ።
እኔም፤ እንዴ!? ለምን ይህን ያህል የዋጋ ድርድር ውስጥ ከምትገባ የሚከብዳትን ነገር ካለ እያገዝናት በራሷ ጥረት/ችሎታ የመመረቂያ ወረቀቷን ለመስራት አትሞክርም አልኳት። “አይ! ወንድሜ እሷ ከፕሮፖዛል ጀምሮ የመመረቂያ ወረቀቱን ሙሉውን ሠርቶ የሚያስረክባት ሰው ነው የምትፈልገው፤” አለችኝ። ደግሞስ አናውቅምና ነው እንዴ… ለመሆኑ ከጥቂት ተማሪዎች በቀር አብዛኛው ሰው የሌላ ሰው የመመረቂያ ወረቀት ርእሱን ብቻ እየቀየረ እያሰገባ አይደል እንዴ የሚመረቀው… ሲጀመርስ እዚህ አገር ወረቀት ይኑርህ እንጂ እውቀት ቦታና ስፍራ አለው እንዴ?! ወንድም ዓለም እህቴ አሁን የምትፈልገው ትንሽም ብትሆን የደረጃና የደመወዝ የዕድገት ምክንያት የሚሆን የዲግሪ ሰርተፊኬት በእጇ ላይ እንዲገባላት ብቻ ነው፤ ሌላው ሁሉ ትርፍ ነው፤” አለችኝ በምሬት ፈርጠም ብላ።
እህቴ ይቅርታ ይህ ሌላ ጉዳይ ነው.. እኔ ግን የዲግሪና የማስተርስ ወረቀት ንግድ ጉዳይ ውስጥ መግባት አልፈልግም፤ በየኮሌጁና በየዩኒቨርሲቲው ደጃፍ ያለ ምንም ሃፍረትና መሳቀቅ “የመመረቂያ ወረቀት በተመጣጣኝ ዋጋ እንሠራለን!” የሚሉ ማስታወቂያን የለጠፉ ብዙዎች አሉና እነሱኑ ብትደራደር/ብትለማመጥ ይሻላታል፤ ብያት ተለያየን። ከጥቂት ሳምንት በኋላ ይህችን የሥራ ባልደረባዬን አገኘኋትና እህቷ እንዴት እንደሆነች ጠየቅኳት።
“እባክህ ምን ይደረግ ብለህ ነው?! እንደምንም ተደራድረን በ 12 ሺህ ብር የማስተርስ ዲግሪ የመመረቂያ ወረቀቷን ሠርተው እንዳስረከቧት፤” ነገረችኝ። አሁን ደግሞ ይኸውልህ ለዲፌንስ የ Powerpoint ገለጻዋን በአማርኛ ተርጉሞ የሚያስረዳት ሰው እየፈለግን ነው፤ ብቻ እንደ ምንም ብላ በተገላገለች እኔንም ግራ አጋባችኝ እኮ…፤” ብላኝ እርፍ አለች።
እንግዲህ በሀገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ምን ያህል ማጣጣርና በጽኑ ሥቃይ ውስጥ እንዳለ ይህ አንድ ማሳያ ነው። በተመሳሳይም በዚሁ ዓመት በግሌ የማውቃቸው ከሌላ የግል ዩኒቨርሲቲ በሌላ ተማሪ የተሠራ/የተገለበጠ የጥናት ድርሳንን እንደገና እነርሱም ገልብጠው አቅርበው የተመረቁ ተማሪዎችን አውቃለሁ። የመመረቂያ ወረቀቶችን መሥራት ለነገሩ መሥራት ሳይሆን የአንዱን ከአንዱ እየገለበጡ መስጠት የጦፈና የሚያዋጣ ቢዝነስ ሆኗል። ሌላ መራር ገጠመኜን ላክል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰነ ጊዜያት በሥራ በቆየሁበት አጋጣሚ በግል ኮሌጆች የሚማሩ ጥቂት የማይባሉ የኢሕአዴግ ሹመኞችና ካድሬዎች ከዩኒቨርሲቲው ቤተ-መጻሕፍት በተማሪዎች የተሠሩ የመመረቂያ ወረቀቶችን እያስወጡ የራሳቸው እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ይመረቁ እንደነበር እነርሱም ያውቃሉ፤ እኛም እናውቃለን።
እንግዲህ በዚህ ዓይነት የወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፉ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች ምን ዓይነት ተማሪዎችንና ዜጋን ሊያፈሩ እንደሚችሉ ማሰብ ነው… ለነገሩማ የነገረ-ገዳዩን አንዱን ስር ስንመዝ መንግሥት እንደ ጠበል በየክልሉ ካዳረሳቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጀምሮ በየመንደሩ የተከፈቱ የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን- የመምህራኑን የእውቀት ደረጃ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-ሙከራዎች ጥራት፣ ዘመናዊነትና ተደራሽነት ብንገመግም ተቋማቶቻችን ብዙ የሚያስደነግጡ ጉዶችን ተሸክመው ነው ያሉት።
ሌላው ትምህርትን እንደ አንድ በአቋራጭ የመክበሪያ/የቢዝነስ መንገድ አድርገው የዲግሪና የማስተርስ ወረቀቶችን የሚቸርችሩ ጥቂት የማይባሉ የግል ኮሌጆች ለመጀመሪያ ዲግሪም ሆነ የሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር የሚያበቃቸውን የጥራት ማረጋገጫ በእንዴት ባለ ማታለል፣ እጅ መንሻና ሙስና እንደሚያገኙት ብትሰሙና ብታዩ ትደነግጣላችሁ። አሳዛኙና አስደንጋጩ እውነታ ደግሞ እነዚህን የትምህርት ተቋማት በማቋቋም፣ ባለቤትነትም ሆነ በመምራት ረገድ ጥቂት የማይባሉ “ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች” መኖራቸው ብቻ ሳይሆን በዚህ ትውልድን የሚያመክን ሥራ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ስትታዘቡ ድንጋጤያችሁንና ኀዘናችሁን ያከፋዋል።
ለመውጫ ያህልም፤ ሰለሞን በላይ ፋሪስ (ዶ/ር)፤ ለሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ መመረቂያ የሆነውን የፒ.ኤቺ.ዲ የጥናትና ምርምር ድርሳናቸውን፤ “ከዶክተርነት ደብተራ እና ወልይነት” በሚል አርእስት ለንባብ አብቅተዋል። ዶክተር ሰለሞን በዚሁ ወደ አማርኛ ቋንቋ በተረጎሙት የዶክትሬት መመረቂያ ድርሳን/መጽሐፋቸው ውስጥ – ከሀገሩም ከውጭውም ሳይሆን ግራ ተጋብቶ ስላለው የትምህርት ሥርዓታችን ጉዳይ ለጥናት ሥራቸው መረጃ ለማሰባሰብ ከሀገረ ካናዳ መጥተው ያጋጠማቸውን እንዲህ በማለት በቁጭትና በኀዘን ይገልጹታል።
“… በመንግሥት ስር ያሉም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ያሉ የትምህርት ባለሙያዎች ሙያቸውን የተመለከተ ቃለ-መጠይቅ ማድረግ አስቸጋሪና በጣሙን ፈታኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አንድም ከመጀመሪያውኑ ሥርዓተ-ትምህርቱ አርቆና አሰላስሎ አሳቢ ስላላደረጋቸውና በሚናገሩበት ጉዳይ ላይም በቂ ሥልጠና/ችሎታ ስለሌላቸው መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ችግሩን የሚያከብደውና የሚያከፋው ደግሞ አጣምሞ ያሳደገን ትምህርት መጣመማችንን (መንገድ መሳታችንን) እንድናውቅ አለማድረጉና መጣመማችንን ደግሞ ልናቃናው ያለመቻላችን መርገምት ነው። የሀገራችንን/የዛሬውንና የነገውን ትውልድ ዕጣ ፈንታችንን የምንወስንበትን ትምህርትን የመሰለ ነገር ሥርዓቱን ማሻሻልና መመርመር ካልተጋን ውጤቱ ከዛሬውም በጣሙን የባሰና የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነው…፤” ይሉናል ትዝብት አከል በሆነ መጽሐፋቸው።
እንግዲህ የዛሬው ከመቶ ሺዎች ተፈታኞች ሃያ ሺዎቹ ብቻ የማለፊያ ለውጤት የማግኘታቸው ብዙዎቻችንን ያስደነገጠ ዜና እንዲሁ የአንድ ጀምበር ክሥተት አይደለም። ከታች ጀምሮ እስከ ላይ የተበላሸው የትምህርት ሥርዓታችን የተንጋደደ አካሄድ ውጤት ነው፤ ብሎ መደምደም ይቻላል።
በአጠቃላይ የትምህርት ጉዳይ በጽኑ ሕመም እና በብርቱ ሥቃይ ውስጥ ነው ያለው፤ እናም እስከወዲያኛው ከማሸለቡ በፊት መንግሥት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እና ምሁራን ቅድሚያ ትኩረት ሊቸሩት ይገባል። አፋጣኝ የሆኑ ተከታታይ ርምጃዎችም ሊወሰዱ ይገባል። በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩትን የለውጥና የማሻሻል ሥራዎችንም አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።
እንደ መቆዘሚያ ያለ የውይይት ማጫሪያ ሐሳብ፤
እንደ ሕዝብ ችግራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ መሄዱ የሚከተለውን መሠረታዊ ጥያቄ እንድንጠይቅ ያስገድደናል፤ “ዘመናዊ ትምህርታችን ድህነትን የምንቀርፍበትን ክህሎት፣ እውቀትና ስብእና ሊሰጠን አሊያም ሊያጎናጽፈን ለምን አልቻለም?!”
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም