በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተው የኮይሻ የተቀናጀ ፕሮጀክት፣ ለዳውሮ ሕዝብ አዲስ ዕድልና ተስፋን የሰነቀለት ይመስላል። ለአካባቢው ማኅበረሰብም የማታ ስንቅ እንደቋጠረለት ይታያል። ምክንያቱም በዚህ ፕሮጀክት ሰበብ ዳውሮ ለዘመናት በጉያዋ ደብቃ ይዛ የቆየቻቸውን ሃብቶች ለዓለም ሕዝብ የማሳየት ዕድል ትጎናጸፋለች። የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መስሕቦቿን ሸጣ ትልቅ የገቢ ምንጭ ታገኛለች። ዜጎቿም በሥራ እድል እንዳይሰቃዩ ታደርጋለች። እንዴት ከተባለ መልሱ ቀላል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ቦታውን ጎብኝተውት ከአካባቢው ማኅበረሰብ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ብዙ ሀብት አይተዋልና ታላቁን ሀገራዊ ፕሮጀክት እዚያ ላይ እንዲሠራ ወስነዋል። ከዚህም በላይ ብዙዎች በቴሌቪዥን መስኮት አይተው የዳውሮን ምድር ለመርገጥ እንዲመኟት አስችለዋል።
ምድራዊ ገነት መሆኗንና እምቅ ሀብት እንዳላት አስጎብኝተዋል። እኛም ከሰሞኑ እርሳቸው ረግጠውት የተለያዩ ተግባራትን ሲከውኑበት ያየነውንና የተደመምንበትን ሰው ሠራሽ ሀብት ጀባ ልንላችሁ ወደድን። ይህም የ‹‹ሀላላ ኬላ›› እየተባለ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚጠራው ቅርስ ነው። ለመሆኑ “ሀላላ ኬላ ምንድን ነው? በማን ተሠራ? ለሕዝቡስ ምን ነበር? ለዛሬው ትውልድስ ምን ሰጠ? ካላችሁ በዛሬው ‹‹የሀገርኛ›› መጣጥፋችን እንንገራችሁ ተከተሉን።
ከስሙ አመጣጥ ስንነሳ ‹‹ ሃላላ›› የዳውሮ ንጉሥ መጠሪያ ስም ነው። ‹‹ኬላ›› የሚለው ደግሞ የድንጋይ ካብ (የመከላከያ ካብ) የሚል ትርጉም አለው። ካቡ ባለው ሰባት ረድፍ 1225 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ለግንባታ 350 ዓመታት ያህል ጊዜን ወስዷል። ከ15 እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ዳውሮን ያስተዳድሩ የነበሩ 14 ነገሥታት የተፈራረቁበትና በቅብብሎሽ የገነቡትም ነው። የሦስት ትውልድ አሻራ ያረፈበትም ነው። እናም 14ኛው ንጉስ ካዎ ሀላላ ነበሩና ኬላውን ማስጨረስ ችለዋል። ይህንን እንዲያደርጉ ያስቻላቸው ደግሞ የካቡ መሠረት ሲጣል ጀምሮ ለመጠናቀቁ ዋስትና የሚሆናቸውን ነገሮችን ነገሥታቱ በማስቀመጣቸው ነው። ይህም ቃለ መሐላ ሲሆን፤ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የተሳሰሩበት ነው። ሰባተኛው ትውልድ ላይ የነገሰው “ካዎ ሀላላ”ም ይህንን አድርጓል። የአባቶቻቸውን ስም ይዘው ቅርሱን አስቀምጧል።
ይህ ካብ(ኬላ) የዳውሮ ማኅበረሰብ የብሔሩ ማንነት የተገለጠበት፣ የትውልድ ቅብብሎሽ የታየበት ብቻ ሳይሆን ድንጋይን በድንጋይ ላይ በማነባበር ግዙፍ አለቶችን አያይዞ ዓመታት ያሻገረ ነው። ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ የመንግሥታትን ቅብብሎሽ የሚታይበት መሆኑ ነው።
ይህ ታሪካዊውና ጥንታዊው የኪነ ሕንጻ ግንባታ የዳውሮ ሕዝብ ጥበባዊነቱን ብቻ ሳይሆን ሀገር በቀል እውቀቱን ያሳየበት ነው። ለዚህም ማሳያው አንዱን ረድፍ ጭምር በምን ያህል ርዝመት መሥራት እንዳለበት ተጠቦበታል። እናም አንዱ ረድፍ 175 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ኖሮት እንዲሠራ ነው ያስቻለው። ውፍረቱ ደግሞ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 5 ሜትር ይደርሳል። ቁመቱም እንዲሁ ልኬት አለው። ይህም በአማካይ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ነጥብ 8 ሜትር ይረዝማል።
“ሀላላ ኬላ” ለምን ዓላማ ተገነባ ከተባለ የታሪክ ባለሙያውና በካቡ ዙሪያ ትናንትና ምርምር ያደረገው ዶክተር አድማሱ አበበ ከዳውሮ ቲዩብ ጋር በነበረው ቆይታ እንዳስቀመጠው፤ ዳውሮዎች ዳር ድንበራቸውን ለማስጠበቅና የመሬት መንሸራተት ለማስቀረት ብለው የገነቡት ነው። የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ በጣም ስለሚያሳስባቸው ጠላትን ከመመከቱ ባሻገር ሌላም ሀገራዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው አድርገው ገንብተውታል።
የ480 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ካብ፤ አገነባቡ አንዳች ዘመናዊ መሣሪያዎችን ሳይጠቀሙ ነው። ሲሚንቶና አርማታም አላስገቡበትም። የሀገር በቀል እውቀት ቴክኖሎጂያቸውን ብቻ ተጠቅመው ነው ዘመንን ያሻገሩት። ስለዚህ የሥልጣኔ ሁኔታቸው ምን ድረስ እንደሚዘልቅ ለዛሬ የግንባታ ባለሙያዎች በደንብ የሚያስተምር ነው።
ስለሥነ-ሕንፃ ጥንታዊነቱ ስናወራም በሰባት የጦር በሮች (ኬላዎች) ከፋፍሎ ዘመናትን ያስተሳሰረም እንደሆነ ይነገርለታል። እነዚህ በሮችም በስተምስራቅ በወላይታ ዞን በኩል ሎማ ወረዳ የዚማ ዋሩማ ዳርሚሳ በር (ሚጻ)፣ በስተደቡብ በጎፋ ዞን በኩል ዲሣ ወረዳ የሾታ ማልዶ ካረ ሚጣ እና በየሊ በር /ሚፃ/፣ በኦሮሚያ ጅማ ዞን በኩል ታርጫ ዙሪያ ወረዳ የአባ ኬላ በር /ሚፃ/፣ በሀዲያና ከንባታ ጠንባሮ ዞን በኩል ገና ወረዳ የዳራ በር /ሚፃ/ በወላይታ ዞን በኩል በዛጋዞ ወረዳ ጋራዳ በር /ሚፃ/ እና የዛባ በር /ሚፃ/ እንዲሁም በኮንታ ልዩ ወረዳ በኩል ቃሎ በር /ሚፃ/ ተብሎ በአድራሻዎች ይጠበቃል፡፡
ኬላው የጠላት ጦር ጥበቃ መከላከያን በምን አይነት መልኩ ማስቀመጥ እንደሚቻልም በሚገባ ያሳየ ነው ይባልለታል። የዳውሮ ሕዝብ በጀግንነት የራሱን ዳር ድንበር ከጠላት ወረራና ጥቃት መከላከል እንዴት እንደሚችል ያረጋገጠ ነውና ሕዝቡ ሉዓላዊነቱን ለማስጠበቅ ምን ያህል ዋጋ እንደከፈለ አሳይቶለታል። በቂ ባይሆንም በሀላላው መኖር እስከ ዛሬ ድረስ ያለው ትውልድ ካቡን ይንከባከበዋል፣ ይጎበኘዋል፣ ለጥናታዊና ምርምር ሥራ ተመራማሪዎች እንዲጠቀሙበት ይደረጋል። የዛሬው ትውልድ የአባቶቻችን የጀግንነት አሻራ ያደንቅበታልም።
ከዚያም አለፍ ሲል አልምተው ለቱሪስት መዳረሻ ያደርጉታል። ከዘርፉ አያሌ የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ይጠቀሙበታል። የሕዝብ ተጠቃሚነትንም ያረጋግጡበታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን የመጣውን እድል በአግባቡ ከተጠቀሙና እድሉን ከአሰፉት ለሀገር መልካም ገጽታ ግንባታ ድርሻው ከፍተኛ ነው። ኬላውን በዚህ ባሕሪው ብዙዎች ከቻይናው ‹‹ግሬት ዎል›› እና ከፐርሺያው ‹‹ባቢሎን›› ጋር ያመሳስሉታል። አፍሪካ ውስጥ መኖሩ ደግሞ ለብዙ አጥኚዎች መሠረት እንደሚሆን ይተነብዩለታል። ያው የሚጠቀመው ካለ።
ንጉሥ ሀላላ የድንጋይ ካብ በሰባቱ በሮች በጎጀብና በኦሞ ወንዝ ተከብቦ ያለ አከባቢ ነው። በዚህም በወንዞቹ ኅብረተሰቡ የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ፤ የገበያ ልውውጦችን ከአጎራባች ዞኖች ጋር እንዲያደርጉና ጠንካራ ግንኙነትን እንዲያዳብሩ አስችሏቸዋል። አርቀው በማሰብ ጥቃቶችን በመተንበይ በአንዳንድ ጉዳዮች አለመግባባት ከተከሰተ ተንኳሾች እንዳያገኟቸው ተከላክለውበታልም። የጦረኞች ፈረስ የማይወጣው ድንጋይ ካብ በማስገንባት ከእነዚህ መውጫና መግቢያ በሮች ከጎሳዎች ሹመት በመስጠት ያስጠበቁበትም ነው -ሀላላ ኬላ።
“የድንጋይ ካብ የጠላት መግቢያና መውጫ እንደሚሆኑ በሚገመቱ አካካባቢዎች የጦር በሮች (tooraa miis’aa) በማዘጋጀት በእያንዳንዱ የጦር በር ጠባቂ ሹም (miis’aa iraasha) ሹመት በመስጠት፣ የግዛት ወሰንና የሕዝብ ደህንነትን ያስጠብቁበታልም” ይላሉ የታሪክ ባለሙያው ዶክተር አድማሱ።
የካዎ ሃላላ ድንጋ ካብ (ኬላ) (kawo halaalaa keelaa) መገኛ አሁን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በዳውሮ ዞን ኦሞ ወንዝን ተከትሎ ነው። ኢሳሩ፣ ዲሳ፣ ሎማ፣ ዛባ ጋዞ፣ ጌና፣ ታርጫ ከተማ አስተዳደርና ታርጫ ዙሪያ ወረዳዎችን ያካልላል። ከጋሞ ጎፋ፣ ከወላይታ፣ ከምባታና ጠንባሮ፣ ከጅማ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ጋርም ይዋሰናል።
ይህ ኬላ ይህንን ሁሉ ዓመት ሲያስቆጥር ዝም ብሎ የተጓዘ አይደለም። ታሪካዊ ነገሮችን እያስቀመጠ፤ የማኅበረሰቡን የሥራ ድርሻ እያሳየና ጥበባዊ እውቀቶችን እያስቀመጠ ነው። በዚህም ግንባታው ሲጠናቀቅ መሠረታዊ ነገሮችን እንዲያስተላልፍ ሆኗል። ለአብነት በየወቅቱ ሲያስተዳድሩት የነበሩትን ነገሥታት ይነግረናል፤ ግዛት ላይ የነበረውን አመራር ያስረዳናል። በተመሳሳይ የትውልድ ቅብብሎሽን ጥቅም ያሳየናል። ምክንያቱም ካቡ ሲገነባ ዓላማው የውጭ ወራሪ ኃይል ወደ ዳውሮ ግዛት ገብቶ የዳውሮን ሕዝብ እንዳይረብሽ ለማድረግና ማዕከላዊ መንግሥቱን ለመከላከል ተብሎ ነው።
የሀላላ ኬላ የተደበቁ ባሕሎችና ማንነቶች የሚታይበት ዶሴ ነው። የትውልዱን ተስፋ የሚያለመልም ምንጭም ነው። ምክንያቱም ይህ ካብ የድንጋይ ካብን ታሪካዊ አመጣጥ የሚያሳይ በመሆኑ በሐምሌ 2000 ዓ.ም በብሔራዊ ቅርስነት ተመዝግቧል። ሀላላ ኬላ የድንበር አጠባበቅ ሥርዓቱ በዚያ ወቅት ምን ይመስላል? የሚለውን የሚተነትኑት ዶክተር አድማሱ፤ ኬላው ዝም ብለው ሲያዩት ጫካ ይመስላል። ወደ ውስጥ ሲገባ ግን እንደ ሀገር መከላከያ በተጠንቀቅ የቆመ ሀገራዊ ስሪት ነው። ለአብነት ከዲዛይን ሥራው ብንነሳ ተፈጥሮን መነሻ ያደርጋል።
የጥርስ አይነት መልክ ያለው ነው። በዲዛይን ሥራቸው የተመጣጠነ ክብደት እንዴት ማምጣት ይቻላል በሚል አስበው ገባወጣ ቢያደርጉትም እንደመንጋጋ ጥርስ በሁለት ረድፍ ደርዝ ይዞ ንቅንቅ የማይል አለት አድርገውታል። ይህንን በማድረጋቸው ደግሞ ማኅበረሰቡን ጎርፍ እንዳይጎዳው አስችለውበታል። ምክንያቱም ኬላውን ከመሠረቱ ጀምሮ ሲገነቡት መሬት ነክቶ እንዲነሳ አድርገው ነው። በቀላሉ ግምቡን ንዶ ውሃ እንዳይገባ አንጸውታል።
ዛሬ ታሪኩን የዳውሮ ሕዝብ ሁሉ ያውቃል። ለዚህ ደግሞ ቀደምት ትውልዶች በግንባታው ሥራ ውስጥ መሳተፋቸውና ከትውልድ ወደ ትውልድም በቃል ሲተላለፍ መኖሩ ሁሉም ታሪኩን በቀላሉ እንዲረዳው እንዳደረገው ተመራማሪው ያስረዳሉ። በተለይም በካዎ ሀላላ አስተዳደር ጊዜ በቤት ውስጥ ያለ ወንድ ትልቅ ኃላፊነት ነበረበት። አንድ ወንድ ልጅ ወክሎ ማሠራት ግዴታ ነው። ወንድ ልጅ ከሌለ ደግሞ አባወራው የቤቱን ሥራ ጭምር በመተው መሳተፍ እንዳለበት ተወስኗል። በዚህም ቅድሚያ ለራሴ ሳይል ኃላፊነቱን ተወጥቷል። በዚህ ግንባታ አባት የሚያርፈው ወንድ ልጅ ሲተካ ብቻ እንደሆነም ይነገራል። ስለዚህ የዳውሮ ማኅበረሰብ ለዚህ የጥበብ ሥራ እጅግ ውድ ዋጋ ከፍሎበታል።
ሌላው ከሀላላ ኬላ ጋር ተያይዞ የምናነሳው ነገር በወቅቱ የነበሩት አባቶች ካቡን እንዴት እንደሠሩት የሚነሳበት ነው። ወታደራዊ ጥበብን ተጠቅመው እንደከወኑት ዶክተሩ ማስረጃ ጭምር በማንሳት ያብራራሉ። የቀን የግንባታ ውሏቸው ሲያበቃ ዝም ብለው ተነስተው አይሄዱም። የቦታውን አቀማመጥና የቆመበትን መንገድ አረጋግጠው ነው። በዚህም ብዙ ጊዜ የቀኑ ሥራቸው የሚጠናቀቀው ተራራን ተገን አድርጎ ነው። ምክንያቱም በእነርሱ እምነት ተራራ አንዱ መከላከያ ነው። በተጨማሪም ውሃ፣ ገደልና መሰል መሰናክሎች ሲያጋጥሟቸው ካቡን ወደ አንድ ሰብሰብ አድርገው ይገነቡታል። ይህ ደግሞ ሰባቱን የጦር በሮች እንዲከፍቱ ያስቻላቸው ነው። ካቡ የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት በመሆኑም በተለይ ለፈረሰኛ ጦር ምሽግነት እንዲያገለግልም ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡
የዚህ ታላቅ ታሪካዊ ኬላ አጠናቃቂ ንጉስ ሀላላ ታሪክ አውራሽ ብቻ አይደሉም። ሥልጣንን በግል ጠቅልሎ ከመያዝ ልማድ በመውጣት አዳዲስ የአመራር ስልቶችን ማሳየት የቻሉ መሪ ናቸው። በተለይም ሥልጣንን ለሕዝብ በማካፈልና በየደረጃው በማውረድ ሕዝባዊ አገዛዝን መመሥረቱ ላይ የተዋጣላቸው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። የሕዝብ አንድነትን ከምንም በላይ የሚፈልጉና ዋጋ የሚሰጡም ስለመሆናቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። የታሪክ ቅርሶቹም ቢሆኑ ምስክሮች ናቸው።
ድንጋይ በድንጋይ ላይ በማነባበር ግዙፍ አለቶችን አገናኝተው ታሪክ ያኖሩልንን አባቶች እኛ ማስታወስ የምንችለው ታሪኩንና ጥቅሙን ተረድተን ወደ ልማት ስንቀይረው ነው። ለዚህ ደግሞ ብዙ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውልናል። አንዱ ታሪካዊዎቹ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፤ ኮይሻ ለዚህ ትልቁና ቅርቡ ፕሮጀክት ማድረግ አንዱ ነው። እናም እርሱን ከዳር በማድረስ ከዚያ የሚገኘውን ገጸበረከት ለእነዚህ ሀብቶቻችን እንዲተርፍ ማስቻል የዳዎሮ ሕዝብ ድርሻ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሀገር ወዳድ እንደሆነ ማመን ይገባል።
ይህንን ታላቅ ቅርስ ቀደምት የዳውሮ ነገሥታት ጥለውት ያለፉት ዝምብሎ እንዲቀመጥና ዘመናትን እንዲያስቆጥር አይደለም። ቅርሱ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ሰው እንዲጠቀምበት ነው። ሀገር የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝና እድገቷን እንድታፋጥን በማለም ነው። እናም የዛሬ ሀገር ተረካቢዎች በዚህ ልክ አስበን እንጠቀምበት ማለት እንወዳለን።
በጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ አማካኝነት ከተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ዳርቻ የሚገኝ በመሆኑ ጠቀሜታው ቀላል አይደለም። በተለይ አሁን ከተያዘው ‘ገበታ ለሀገር’ ኮይሻ ኮሪደር ፕሮጀክት ውስጥ ተካቶ የሚለማ እንዲሁም ባሕላዊ ሙዚየሞችና የምርምር ማዕከላት እንደሚቋቋምለት የሚደረግ ስለሆነ ለራሳችን ደስታና የገቢ ምንጭ፣ ለሌሎች እረፍትና የሥራ እድል ማግኛ እናድርገው በማለት ለዛሬ ሀሳባችንን አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም