ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በአጭር ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል:: እንደ ኢትዮጵያም ካየን በአሁኑ ጊዜ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ ተከታይ አላቸው:: እንዲያውም ከመደበኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ቀድመው እየታዩም ነው:: ከእነዚህ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ውስጥ በስፋት የወጣቱን ቀልብ የተቆጣጠረው ፌስቡክ ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ‹‹ቲክቶክ›› የሚባለው ተጨምሯል::
ፌስቡክ በጣም ብዙ ተብሎለታል:: በመድረክም ይሁን በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ስለፌስቡክ ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን ብዙ ተብሏል:: ክርክሮችም ነበሩበት:: ክርክሮቹ ግን የተለያዩ አይነት ናቸው:: መጀመሪያ ፋሽን በነበረበት ጊዜ የነበረው ክርክር ‹‹ጊዜን ያባክናል እንጂ ምንም አይጠቅምም›› የሚሉ እና ‹‹በራሱ ማንበብ ስለሆነ ጊዜን ማባከን አይደለም›› የሚሉ ነበሩ:: በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ‹‹ውሸትና አሉባልታ የሚነዛበት ነው፣ ብሔርን ከብሔር እያጋጨ ነው›› የሚሉ እና ‹‹መደበኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን በጣም ይዘገያሉ፣ እውነቱን አያሳውቁም፤ ስለዚህ ፌስቡክ አማራጭ ነው›› የሚሉ ናቸው::
ለሁሉም ክርክሮች እንደ አስታራቂ የሚወሰደው ሀሳብ ‹‹እንደ አጠቃቀሙ ነው›› የሚለው ነው:: እርግጥ ነው እንዳጠቃቀሙ ነው፤ ግን የሚያጠፋው ከበለጠ ደግሞ ችግር ነው:: እንደ አጠቃቀሙ ነው የሚባለው ለግለሰብ ነው:: ለምሳሌ እኔ ጥሩ ጥሩ ነገር ብቻ እየፈለኩ የማነብበት ከሆነ፣ ጊዜዬን በአግባቡ የምጠቀምበት ከሆነ ጠቀሜታው ለእኔ ብቻ ነው:: እንደ አገር እያስከተለ ያለውን ችግር ማስቀረት የሚቻለው ግን ሁሉም ባይሆን እንኳን ቢያንስ አብዛኛው በአግባቡ ቢጠቀም ነበር::
ለማንኛውም ፌስቡክም ሆነ ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እያስከተሉ ካለው አሉታዊ ችግር ውስጥ እኔ መታዘብ የፈለኩት የቋንቋ አጠቃቀምን ነው:: ይሄ ነገር ብዙም ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም:: ዳሩ ግን ቋንቋን በጣም እያበላሹ ነው:: ውሸት እየተደጋገመ ሲሄድ እውነት መምሰሉ ግልጽ ነው:: በተመሳሳይ ስህተት በጣም በተደጋገመ ቁጥር ልክ ሊመስል ይችላል::
ነገሩ ቀላል አለመሆኑን ለማረጋገጥ ይህን ልብ እንበል! ፌስቡክ ላይ ያለውን የተሳሳተ የቋንቋ አጠቃቀም በጋዜጦች፣ መጽሔት፣ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ላይ ያሉ ጋዜጠኞች መጠቀም ጀምረዋል:: በዚህ አሥራ አምስት ዓመት እንኳን ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ፌስቡክ ይህን ያህል ጥፋት ማድረስ ከቻለ በአርባና ሃምሳ ዓመታት ውስጥ አንድን ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ላለማውደሙ እርግጠኞች አይደለንም::
ስህተቱ እኮ እዚያው ፌስቡክ ላይ ብቻ ቢቀር ባልከፋ ነበር:: ዛሬ ላይ ጋዜጠኛውም፣ ባለሥልጣኑም፣ ምሁሩም የፌስቡክ ተጠቃሚ ቢሆንም በብዛት የሚጠቀሙት ግን ወጣቶች ናቸው:: እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ለቋንቋ አጠቃቀም ግዴለሽ እየሆኑ ነው:: ጋዜጠኛው ይህን ነገር ማስተካከል ሲገባው ጭራሽ በመገናኛ ብዙኃንም ፌስቡክ ላይ በለመደው እየተጠቀመ ለሚሊዮን ህዝብ ያዳርሳል:: አሁን ላይ እኮ ጋዜጦችና መጽሔት ላይ፣ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ጸያፍ የቃላት አጠቃቀም እያየን ነው::
ለምሳሌ ‹‹መጣህ›› ለማለት ‹‹መጣክ›› ‹‹በላህ›› ለማለት ‹‹በላክ›› እያሉ መጠቀም እየተለመደ መጥቷል:: በሌላ በኩል አግባብ ያልሆኑ አብዢ ቅጥያዎችን ማየትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፌስቡክ ያስፋፋው ስህተት ነው:: ‹‹መጣችሁ›› ለማለት ‹‹መጣቹ›› ወይም ደግሞ ‹‹መጣችው›› የሚባልም አለ:: ምናለ ስህተቱ እንኳን አንድ አይነት ቢሆን? ‹‹እመጣለሁ›› ለማለት ‹‹እመጣለው›› እያሉ መጻፍ አሁን አሁን እየተለመደ ነው::
እነዚህ ነገሮች እየተለመዱ ሲሄዱ መደበኞቹ አጠቃቀሞች ስህተት ሊመስሉ ይችላሉ ማለት ነው:: ለምሳሌ አንድ ታዳጊ በተደጋጋሚ ‹‹እመጣለው›› የሚል ቃል ከሆነ የሚያነብና የሚሰማ ‹‹እመጣለሁ›› የሚል ቃል ቢያገኝ ስህተት ሊመስለው ይችላል ማለት ነው:: ‹‹ምን ችግር አለው ይሄኛው ቢለመድና መግባቢያ ቢሆን?›› ይባል ይሆናል:: በጣም ችግር አለው:: አንደኛ ቀደም ያሉ መጻሕፍትን ማንበብ ላይቻል ነው:: ሁለተኛ ደግሞ በጣም ስህተት ስለሆኑ የትርጉም ለውጥ ሁሉ ያመጣሉ:: በቋንቋ ምሁራን ከተጠናው የሰዋሰው ህግ ውጭ ይሆናል ማለት ነው::
ለምሳሌ፡- ‹‹በላችሁ›› በሚለው ዓረፍተ ነገር(ቃል) ውስጥ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ‹‹እናንተ›› የሚለው ነው:: አሁን ፌስቡክ ባበላሸው የቋንቋ አጠቃቀም ስንሄድ ግን ‹‹በላችሁ›› ለማለት ‹‹በላችው›› ተብሎ ይጻፋል? እዚህ ላይ እንግዲህ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ማነው? ‹‹እናንተ›› ወይስ ‹‹እሷ››? ተመልከቱ እንግዲህ የተፈጠረውን ስህተት! ‹‹እናንተ›› የሚለውና ‹‹እሷ›› የሚለው ተውላጠ ስም ተምታት ማለት ነው:: ሁለቱ ተውላጠ ስሞች ምንም የማይገናኙ ናቸው:: ‹‹እናንተ›› ሁለተኛ መደብ ብዙ ቁጥር ሲሆን ‹‹እሷ›› የሚለው ደግሞ ሦስተኛ መደብ ነጠላ ቁጥር ነው::
እነዚህ ነገሮች ለጊዜው እንደ ቀላል ይመስሉን ይሆናል፤ ዳሩ ግን ቀስበቀስ ብዙ ጥፋት እያመጡ ነው:: ደጋግሜ እንዳልኩት በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃንም እንደ ትክክል ተወስደው አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው:: ይሄ ጋዜጠኛ መጽሐፍ እንኳን ቢጽፍ በዚህ ቋንቋ ነው ማለት ነው የሚጠቀመው::
ሌላው ፌስቡክ በቋንቋ ላይ እያደረሰው ያለው ጥፋት ደግሞ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ነው:: ሥርዓተ ነጥብ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ግልጽ ነው:: የትኛውም ቋንቋ የራሱ የሆነ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ሥርዓት አለው:: ብዙ ቋንቋዎች በጋራ የሚጠቀሟቸው የሥርዓተ ነጥብ አይነቶች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ደግሞ የራሳቸው ሥርዓተ ነጥብ የላቸውም አሉ:: በመገናኛ ብዙኃን በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለው የአማርኛ ቋንቋ የራሱ የፊደል ገበታ ያለውና በአፍሪካ ብቸኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ነው:: ይህ ቋንቋችን የራሱ የሆነ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀምም ያለው ነው:: አማርኛ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር በጋራ የሚጠቀማቸው የሥርዓተ ነጥብ አይነቶች ቢኖሩም የራሱ ብቻ የሆኑም አሉ::
ፌስቡክ ላይ የሚታየው ግን እንኳንስ የራሱን የሚጠቀሙበትን ቋንቋ የየትኛውንም ቋንቋ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ህግ ያልተከተለ ነው:: ሥርዓተ ነጥብን ያለ አግባብ መጠቀም ደግሞ የትርጉም ለውጥ ሁሉ ያመጣል:: በአሁኑ ጊዜ ታዳጊዎች ሁሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሆነዋል:: ያለምንም አገልግሎት በቃላት መካከል ውስጥ የተደረተን ሥርዓተ ነጥብ ሲያዩ ትክክለኛ አገልግሎቱ እንደዚያው ሊመስላቸው ይችላል:: አንዳንዴ ደግሞ ጭራሽ መሆን የማይገባውን ሥርዓተ ነጥብ ሁሉ ሊጠቀሙ ይችላሉ:: በሌላ በኩልም አገልግሎት ላይ ካለመዋላቸው የተነሳ የሌሉ የሚመስሉ ሥርዓተ ነጥቦችን ይረሷቸው ይሆናል::
ለምሳሌ፡- እንደ ድርብ ሰረዝ(፤)፣ ነጠላ ሰረዝ(፣) ሁለት ነጥብ ከሰረዝ(፡-) አቆልቋይ ወይም እዝባር(/)፣ ሁለት ነጥብ(፡) እና የመሳሰሉት ፌስቡክ ላይ አገልግሎት ላይ ሲውሉ አይታይም:: የእነዚህን ሥርዓተ ነጥቦች አገልግሎት ቢጠየቅ ብዙ ሰው ግራ ሊጋባ ይችላል::
ለቋንቋና ባህል መበረዝ ብዙ ጊዜ ቴክኖሎጂ ተጠያቂ ሲደረግ ይሰማል:: አንድ የቋንቋና ስነ ጽሑፍ ተመራማሪ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር:: እርሳቸው የነገሩኝ እንዲያውም ቴክኖሎጂ የበለጠ እንዲተዋወቅ የሚያደርግ፣ ለማስተካከል የሚያግዝና የበለጠ አመቺ እንደሆነ ነበር የነገሩኝ:: የእርሳቸው ሀሳብ ልክ መሆኑን ደግሞ ጥፋት ቢኖርባቸውም የማህበራዊ ገጾች አሳይተውናል:: ብዙ አባባሎችን፣ የፈጠራ ሥራዎችን፣ ቀልዶችን፣… አይተንበታል::
የጽሑፍ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች(ለምሳሌ ፌስቡክ) የጽሑፍ ቋንቋ ላይ ከላይ ያየነውን የአጻጻፍ ስህተቶች አስከተሉ:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጡት እንደ ቲክቶክ ያሉ የቪዲዮ መተግበሪያዎች ደግሞ የንግግር የቋንቋ አብዮት ፈጠሩ:: ጎልማሶችና አዛውንቶች ሊረዱት የማይችሉት የአነጋገር ቅላጼ ጀመሩ:: አዛውንቶች ቲክቶች ስለማያዩ ችግር አልነበረውም፤ የሚያሳዝነው ግን ቲክቶክ ሲከታተሉ የሚውሉ ጋዜጠኞች ሬዲዮ ላይ ወጥተው በዚያው መንገድ እያወሩ ነው:: የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ያሉትን ለመታዘብ ባይቻል እንኳን ቢያንስ መደበኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያሉት ግን ለሁሉም በሚገባ ቋንቋ ቢያወሩ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም