በጥንታዊት ግሪክ አሥር ዓመት ጦርነት ተካሂደ። በግሪክ እና ትሮይ መካከል ። ግሪኮች ጦርነቱ ሰለቻቸው ፤ እጅ መስጠት አልፈለጉም። እናም መላ ዘየዱ። ግዙፍ የጣውላ ፈረስ ሠርተው ውስጡ ምርጥ ወታደሮችን አስቀምጠው ሸሹ። ግሪኮች ሲሸሹ ትሮዮች በድል ሰከሩ። ትሮዮች ለድላቸው መታሰቢያ እንዲሆን ፈረሱን ጎትተው ከተማቸው መሐል አቆሙ። በውድቅት ሌሊት፣ ፈረሱ ውስጥ የተደበቁት ግሪኮች ወጥተው የትሮይ ከተማን በማውደም በጦርነቱ አሸናፊነት ተቀዳጁ። እናም ባልተጨበጠ ድል የሰከሩ ትሮዮች በተሸናፊነት ከሰሩ። የትሮይን ፈረስ ያነሳነው ነገርን ነገር ያነሳዋን ብለን ነው። ስለኢትዮጵያ ፈረሶችና ፈረሰኞች ልናወጋችሁ ሽተን ።
የሰው ልጅ ፈረስን ለማዳ አድርጎ መጠቀም የለመደው በ3 ሺ ዓ.ዓ መሆኑ ን ሰነዶች ያሳያሉ። የፈረስ የእድሜ ጣሪያ ከ25 እስከ 30 ዓመት ሲሆን በዓለም ከ3 መቶ በላይ ዝርያዎች ለልዩ ልዩ አገልግሎት ይረባሉ። በኢትዮጵያ ስምንት የፈረስ ዝርያዎች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። በዋናነት የሚጠቀሱት የፈረስ ዝርዎች የሰላሌና (በጋላቢነታቸው) የቦረና ፣ እንዲሁም የሶማሌ ጅግጅጋ አለፍ ብሎ የሚገኝ ዋልዌል የዐረብ ዝርያ ያላቸው ፈረሶች ናቸው። የባለሥልጣናት ጉብኝት በገጠር አካባቢዎች ሲኖር ገበሬዎች በብዛት በባህላዊ ጭፈራና ኮርቻ ባጌጠ ፈረስ አቀባበል ማድረግ በኢትዮጵያ የተለመደ ነው። ይህ አሁንም ይታያል። ፈረሶች በአገራችን በወይና ደጋ፣ ደጋና ቆላና ሥፍራዎች ይኖራሉ።
ፈረስ ከጋማ ከብቶች አንዱ ነው። በጀርባው ኮርቻ ጭኖ ሰው የሚቀመጥበት ። የሚወልዱ ፈረሶች ባዝራ ፤ወንዱ ደግሞ ድንጉላ ይባላል። ፈረሰኞች በፈረስ የሚጋልቡ ፤ ግልቢያ አዋቂዎች ማለት ነው። ፈረስ ዘበኛ ማለትም ፈረስ የሚጠብቅ ፤ ባልዳራስ ጭፍራ ፤የንጉሥ ፈረስ ጠባቂ ማለት ነው። ሰዎች ፈረስ እየጋለቡ ሩቅ ቦታ መሄድ ሲፈልጉ ኮርቻ ይጠቀማሉ። ኮርቻ በበቅሎ፣ በፈረስ ጀርባ ላይ ተደርጎ የሚታሠርና ሰው የሚቀመጥበት ከእንጨትና ከቆዳ የሚሠራ ዕቃ ነው። በቅሎ እና ፈረስ በብዛት የኮርቻ ከብት ይባላሉ። ይህም ለኮርቻ ጭነት ብቻ የተመደበ፣ በብዛት ሰው የሚጓጓዝበት በመሆኑ ነው።
ኮርቻ ከላይ እንደተገለፀው መቀመጫ ሆኖ ከፊት መያዣ ያለው ቀዳማይ ሲባል፤ የኋላ መደገፊያው ደኀራይ ይባላል። መወጣጫው እግር የሚጠልቅበት ብረት ርካብ ፤ ከጅራቱ ሥር የሚገባው የጨርቅ ትልታይ ወይም በለስላሳ ቆዳ የተሸፈነ ጠፈር ወዴላ ይባላል። ፈረሱን አቅጣጫ ለመምራት ፍጥነቱን ለመቀነስ የሚረዳው ከቆዳ የሚሠራው ልጓም ነው። ልጓም የመሪ ዓይነት ሚና አለው። ፈረሰኛው አለንጋንም ይጠቀማል።
ኢትዮጵያ በፈረሰኞች በዓለም ትታወቃለች። ነፃነቷን አስከብራ፣ የነጮችን ወራራ አሳፍራ የኖረችው በዘመኑ በነበራት ፈረሶችና ፈረሰኞች ነው። ንግሥት ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ከኢትዮጵያ ለማየት የሄደችው በፈረስና በግመል ነበር። አሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳም የሆነው በእስራኤል የዴር ሱልጣን ገዳም በዘመኑ የንግሥት ሳባ ፈረሶች ማረፊያና ማሰሪያ እንደነበር ይነገራል።
በኢትዮጵያ ጀግኖች መሳፍንት መኳንንት ነገሥታት ዜጋው ሁሉ በፈረስ የመቀመጥ ልምድና ባህል ነበራቸው። በዘመኑም በጨዋ ልጅ አስተዳደግ አንደኛ ደረጃ ክብርና ማዕረግ የሚያሰጥ እንደነበር የሰዋስው ድረገፅ ያስረዳል።
በጎንደር በፋሲል ግቢ የሚገኝ በዐፄ በካፋ የተሠራ የፈረሶች መኖሪያ ህንጻ ነበር። የዞብል ፈረስ መቃብርም አለ። መቃብሩ ከፋሲል መዋኛ አጠገብ ይገኛል። ዞብል በአንዳንዶች ዘንድ ተወዳጁ የዐፄ ፋሲለደስ ፈረስ መሆኑ ይታመናል። ሌሎች ግን የልጃቸው የቀዳማዊ ዮሐንስ ፈረስ ነው ይላሉ። ሆነም ቀረም የዞብል መቃብር በክብ ቅርጽ የተሠራ መታሰቢያ ነው። በግሌ ቦታውን ባላየውም ከቆይታ ብዛት ጉዳት እየደረሰበትና ዛፎች በመካከሉ እየበቀሉበት እየፈረሰ ያለ ምናልባት ብቸኛው የኢትዮጵያ ፈረስ መዘክር የሚሆን ነው። ያም ሆነ ይህ የፈረሱን መቃብር የሠሩለት ፈረስ በዘመኑ ክብር የሚሰጠው መሆኑን የሚያመላክት ነው።
በኢትዮጵያ ካሏት ግዙፍ የባህል ሀብቶች መካከል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዘንድ የሚታወቀው የሚዘወተረው የፈረስ ጉግስ ነው። የቆየ ታሪክ ያለውና ትልቅ ባህላዊ እሴት የሆነ በፈረስ የሚደረግ ውድድር ወይም ጨዋታ ነው። ጉግሥ ሁለት ዓይነት ሲሆን፣ አንደኛው ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግ ሽምጥ ግልቢያ ነው።
ሁለተኛው ጋሻና ጦር በመያዝ ሽምጥ እየጋለቡ አባራሪና ተባራሪ እየሆኑ ተወዳዳሪውን ጋሻ አልፎ ለመውጋት ወይም ለመማረክ የሚደረግ የጨዋታ ፍልሚያ ነው። ጦር የሚባለው በጦር ምትክ የሚያዝ ዘንግ ነው። ይህም በክፉ ጊዜ አገርን ከጠላት ወረራ ለመከላከል ጭምር የረዳ ነው። የፈረስ ጉግስ ወታደራዊ ብቃትና ጀግንነት የሚለካበት ነበር። በፈረስ ጉግሥ ተወዳድሮ ያሸነፈ ‹‹ፈረሰኛ›› የሚል ማዕረግና የፈረሰኛ መሬት በሽልማት ይሰጠው ነበር። በዘመናችን ፈረሰኛ የሚባለው አውዳሚው ነው። (በክረምት ወንዝ ድንገት ሲሞላ ፈረሰኛ ይባላል፤ ተሻጋሪውን ይወስደዋል።) በጥንቱ ኢትዮጵያዊ ባህል ዜጋው የፈረስ ጉግሥ ጨዋታና የግልቢያ ችሎታ ማወቅ ግድ ነበር። በአገራችን ፈረስ የአሸናፊነት ምልክት የክብር መገለጫ ነገሥታቱ ጀግኖቹ ዜጎቹ እንደ ልጅ ይጠሩባቸው ነበር።
በአገራችን ባህል ለሰዎች የሚሰጠው የፈረስ ስም የሰውየውን ጠባይ ሁኔታ ምኞትን ጭምር አጠቃሎ የሚይዝ ሠፊ ትርጉምና መግለጫ የያዘ ነው። ቅጽሉ ስሙ የሚሰጠው ለፈረሱ ቢሆንም፤ የባለቤቱን ሙያ የሚገልጽና የሚያሞግስ ሰውየውንም የሚያኮራ ነው። በሰላም፣ በአስተዳደር ፣በዳኝነት፣ በምክር፣ በጦርነት ጊዜ በጀግንነትና በዘዴ የሚያሳየውን ደግነትና ርህራሄ ኃይልና ቅልጥፍና ከባልደረቦቹ ወይም ከሌሎች የሚሰጠው መታወቂያ ነው።
ከፈረስ ስም መካከል አስተዳደርንና ዳኝነትና የሚያመለክቱ ኣባ ዳኘው፣ መቻል፣ ይርጋ ፤ ለጋስነትንና ችሮታን የሚያመለክቱ አባ ባህር፣ ለጋስ፣ ሙላት፣ ቁጡነትን ጀግንነትን የሚያመለክቱ አባ ቃኘው፣ ደፋር ፣ መብረቅ የፈረሶቹን ቀለም የሚያመለክቱ አባ ጉራች ፣ ሻንቆ፣ ዳማ ትክክለኛነትን የሚያመለክቱ አባ ሚዛን ፣መልዐክ ፤መስፋፋትንና ዕድገትን የሚያሳዩ አባ ይትረፍ፣ ደርብ ወዘተ ይጠቀሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ዓለም የእርሻ ድርጅት በፈረንጆቹ በ2017 ባወጣው የስታትስቲክስ መረጃ ፤ ኢትዮጵያን ፈረስ ከሚያረቡ አገሮች ስምንተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። ይህም ከዓለም አስር ቀዳሚ ሀገሮች ተርታ ይመድባታል። በፈረስ ብዛት አገራችንን ፤ዩናትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ ሞንጎልያ፣ አርጀንቲናና ካዛኪስታን በቅደም ተከተል ይመሩዋታል። ሩሲያና ኮሎምቢያ ደግሞ ኢትዮጵያን ይከተልዋታል። የዊኪፒዲያ ድረገፅ የተባበሩት መንግሥታት ምግብና እርሻ ድርጅት በ2016 ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ እንዳሠፈረው በአፍሪካ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ፈረስ በማርባት ቻድና ግብፅ በሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ይከተላሉ። በኢትዮጵያ ያሉት ፈረሶች ብዛት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሲገመት ይህም የአፍሪካን ፈረሶች ሩብ (1/4 ኛ) ያህል ነው።
ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን ስናስብ ኢሬቻ፣ ፊቼ ፣ጨምበላላ፣ የጥምቀት ከተራና የመስቀል ደመራ የቃና ዘገሊላ በዓል የሚያምሩት የሚደምቁት በፈረሶችና ፈረሰኞች ሲታጀቡ ነው። ከ80 ዓመት በላይ የዘለለ ምሥረታ ያለው የአገው ፈረሰኞች ማኅበርም በየዓመቱ ጥር 23 ቀን ፈረሳቸውን በኮርቻ አጊያጊጠው የፈረስ ፌስቲቫል ያከብራሉ። ፈረሰኛ የማህበሩ አባል ለመሆን፣ ለፈረሱ ኮርቻ፣ ፉርጌሳ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ውስጠ ምቹ እና ግላስ የተባሉ መሉ መሣሪያዎች ማሟላት ሲኖርበት፣ ለራሱ ደግሞ አለንጋ፣ ዘንግ ገምባሌ፣ ባት ተሁለት ሱሪ፣ ሳሪያን ኮት እና ጀበርና ማሟላት ይጠበቅበታል። የፈረስ በዓሉ የሚዲያ ሽፋን ካገኘ ወደፊት የቱሪስት መስህብ ይሆናል። በተባበሩት መንግሥታት የባህልና የሳይንስ ድርጅት የመመዝገቡ ዕድሉም ሠፊ ይመስለኛል።
በፈረሰኝነት የሚታወቁት ኦሮሞዎችም በመሀል አገሪቱ ይሄን ሸጋ ባህል ለማሻገር መጣር አለባቸው። ባለፈው ጥር ወር በኦሮሚያ ክልል ሰንዳፋ ከተማ ‹‹ባሕላዊ የፈረስ ፌስቲቫል ለቱሪዝም ልማት›› በሚል መሪ ቃል የፈረስ ስፖርት ፌስቲቫል መካሄዱን አስታውሳለሁ። በወቅቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የኦሮሞ ፈረሰኞች በአገር ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተወስቷል። በዝግጅቱ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች የተውጣጡ ፈረሰኞች የፈረስ ጉግስ፣ ሽምጥ ግልቢያ እና ባሕላዊ ጭፈራዎችን አቅርበዋል። በተጨማሪም በፌስቲቫሉ ላይ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ያጸኑ የኦሮሞ ጀግና ፈረሰኞች ተዘክረው ነበር።
ፈረስ ጉግሥ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለመደና የሚዘወተር ባህላዊና ጥንታዊ ጨዋታ ነው። በማንኛውም ጊዜ የሚከናወን ጨዋታ ቢሆንም በውድድርና በትርዒት መልክ የሚቀርበው በዓላትን ተንተርሶ ነው። በመስቀል ደመራ በጥምቀት ከተራ በገና በልዩ ድምቀት ይከናወናል። በመስቀል ልጃገረዶች አንድ ላይ ሆነው ሲዘፍኑ ወጣት ወንዶች በበኩላቸው ለዚህ ብለው ሲቀልቡዋቸው እና ሲገሩዋቸው የከረሙትን ፈረሶቻቸውን ይዘው በመምጣት ለጉግሥ ውድድር ይሰለፋሉ። በጥምቀት በተለይ በቃናዘገሊላ እለት ታቦት ካስገቡ በኋላ የፈረስ ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ። በልደትም በየመስኩ የጉግሥ ጨዋታ የተለመደ ነው ።
ተሽከርካሪ ከመጣ በኋላ ፈረሶች በከተሞች ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ መጣ። ሆኖም በከተሞች አልፎ አልፎ ፈረስን የመጠቀም ልምድ አለ። በአነስተኛ ከተሞችና በአዲስ አበባ ከተማ ዳርቻዎች የጋሪ ፈረስን መጠቀም ተጀመረ። የጋሪ ፈረሶች ግራና ቀኝ የሚያየው ዓይናቸው በቆዳ ነገር ተከልሎ በአንድ አቅጣጫ እንዲያይና እግራቸው ወይም ኮቴያቸው ላይ ብረት እንደጫማ ተመቶ እንዲያለግሉ ይደረጋል። ለጋሪ ፈረስ ግንባሩ ላይና አፍንጫው ላይ የሚደረገው ቆዳ ፉሎ ፤የሰዎች መቀመጫው ኮርቻ፣ መደገፊያ ጀርባው ሌቤቻ፣ ደረቱ ላይ የሚወጠረው ቅናት፣ ከተሽከርካሪ ጎማው እስከ ደረቱ የሚደረሰው ግራና ቀኝ ያለው እንጨት ስታንጋ፣ ጎማዎቹን የሚያይዘውና የሚደግፈው ባሌስትራ ይባላል።
በዓለም ለማዳ ያልሆኑ ፈረሶች (feral horses) በተወሰኑ አገሮች ይገኛሉ። በአሜሪካ አትላንቲክ ጠረፍ፣ በአውስትራሊያ ፣ በፖርቱጋልና ስኮትላንድ ይገኛሉ። የአውሬነት ፀባይ ስላለባቸው የዱር ፈረሶች ይባላሉ። በአፍሪካ በናሚቢያ ብቻ ይገኛሉ ቢባልም በኢትዮጵያም በምሥራቅ ሐረርጌ የዱር ፈረሶች ተገኝተዋል።
ዶ/ር ከፈና ኢፋ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው። ከአዲስ አበባ 565 ኪሎ ሜትር ርቆ በምሥራቅ ሐረርጌ በጃርሶና ጉርሱም ወረዳ መካከል በሚገኘው በቁንዱዶ ተራራ በተገኙ ዱር ፈረሶች ላይ ጥናት አድርገዋል።
የቁንዱዶ ተራራ ሰንሰላታማና ከ3 ሺ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ነው። ለፈረሶቹ ተራራውን መውጣት አስቸጋሪ ነው። ፈረሶቹ በተራራው ከመቶ ዓመታት በላይ እንደኖሩበት ጠቁመዋል። ከአስር ዓመት ወዲህ ባደረጉት ጥናት ሰባት የሚደርሱ ፈረሶች ብቻ ቀርተው ነበር። በሥፍራው ያለ ጫካ በሰው እየተመነጠረ አውሬው (ጅብ፣ አነርና ነብር) እየሸሸ ፈረሶቹንም እያደነ ሲበላ፤ ሰውም ለቤት እንስሳነት ለማደን ሲጠቀም ነበር። የኢትዮጵያ ብዙሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ፣ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲና የኦሮምያ አካባቢ ደን ባለሥልጣን የመግባቢያ ስምምነት አድርገው ለአስር ዓመታት በሠሩት ሥራ ሰባት ብቻ ሆነው ዝርያቸው እየጠፉ የነበሩት የዱር ፈረሶች 35 ደርሰዋል።
የቁንዱዶ ፈረሶች እየተራቡ (ሲባዙ) ሲሄዱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቸኛው የዱር ፈረስ መገኛ እንደሚያደርጋት ዶ/ር ከፈና ኢፋ የሰጡት መረጃ ያስረዳል። ይህም እንደ ዋልያ፣ ኒያላ፣ ቀይ ቀበሮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የዱር ፈረስ ያደርጋታል ሲሉ ይገልፃሉ። በናሚቢያ ይገኛል የተባለው የዱር ፈረስ በ 17ኛው ክፍለ ዘመን በቅኝ ወራሪዎች ትተውት የሄዱት እንደሆነም ያስረዳሉ። የቁንዱዶ የዱር ፈረሶች ለማዳ ፈረሶች በማይገኙበት በምሥራቅ ሐረርጌ መገኘታቸው ፤ተራራው ቀዝቃዛማና አስቸጋሪ መሆኑና እንዴት ሊወጡ እንደቻሉም ትንግርት መሆኑን ጠቁመዋል። ቀስ በቀስ ቦታው የቱሪስት መስህብ የሚሆን ነው።
ፈረሶች አገልግሎታቸው ዘርፈ ብዙ ነው። ፈረስና አህያ አገልግለው እርጅና ሕመም ሲያጋጥመው እንደ አሮጌ ቁና ሜዳ ላይ የመጣል ልምድ በሀገራችን አለ። የግብርና ምርምርና የሚመለከታቸው አካላት መላ ቢፈልጉለትና የሕክምና ማዕከላት ቢኖሩ ጥሩ ነው። ባህላዊ የፈረስ ኮርቻ እየተረሳ እንዳይመጣም በፖሊስ ፈረሶች በቤተመንግሥት ፈረሶች ጭምር ብሔራዊ በዓል ሲሆን በኮርቻው ደምቀው አጊጠው ሲገለገሉ ቢታዩ ሸጋ ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም