በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ታሪክ ትልቅ አበርክቶ ትተው ካለፉ ሰዎች መካከል ታደሰ ሙሉነህ ዋነኛው ነው:: በሙያው ስርነቀል ለውጥ እንዳመጣ የሚመሰከርለት ይህ ታላቅ ጋዜጠኛ ትውልዱም ሆነ ዕድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነው:: ታደሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን የተከታተለ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንና ከፍተኛ ትምህርቱን ደግሞ በልዑል በዕደ-ማርያም ትምህርት ቤት እና በቀድሞው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተከታትሏል:: ጋዜጠኛ ታደሰ በልጅነቱ ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የአንደኛ ክፍለጦር የቲያትርና ሙዚቃ ክፍል ሠራተኞች ወደቤት ሲገቡ እና ሲወጡ በጥንቃቄ ይከታተል ነበር:: በተለይ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን የመሳሰሉትን አንጋፋ አርቲስቶችን በቅርበት ለማየት መታደሉና የበርካታ አርቲስቶች መኖሪያ እሱ ከተወለደበት አቅራቢያ በመሆኑ የተነሳ ልቡ ተዋናይ የመሆን ፍላጎት ሞልቶት ነበር::
ይሁን እንጂ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ቋንቋ ተማሪ ሳለ ሕይወቱን እስከወዲኛው ሊቀይረው የቻለ ነገር ተፈጠረ:: በአንጋፋው ተዋናይ ተስፋዬ ገሠሠ አማካኝነት የሚመራው የዩኒቨርሲቲው የባሕል ማዕከልን የሚያዘወትረው ታደሰ ሙሉነህ ለኪነ-ጥበብ ይውል ዘንድ ዕድል ተሰጠው፤ የያኔው አፍላ ወጣት ከወጋየሁ ንጋቱ፤ ኃይሌ ገሪማ እና አባተ መኩሪያን ከመሳሰሉት ታላላቅ ሰዎች ጋር መማሩ ከፈጠረለት የደስታ ስሜት ባሻገር የተለየ ነገር አልጠበቀም ነበር:: ሆኖም ያቺ አጋጣሚ ትክክለኛ መክሊቱ ጋዜጠኝነት መሆንዋን አበሰረችለት::
በሙያቸው ምትክ ሊገኝላቸው ከማይችሉ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ታደሰ ሙሉነህ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በ1960 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በዜና አንባቢነት የጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቀለ፡፡ በመቀጠልም የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራምንና በዓይነቱ ልዩ በነበረው የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም በማዘጋጀትና በመምራት ለተቋሙም ሆነ ለሙያው እድገት አብዮታዊ ለውጥ አምጥቷል:: በዋናነትም የመጽሔት ፎርማት የመጀመሪያ ፕሮግራም ‹‹እሁድ ጠዋት›› የተሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም እሱን በመላው የሬዲዮ አድማጮች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋወቀው ሲሆን በሙያው የመዝናኛ ጋዜጠኛ አባት የሚል መጠሪያ እስከማግኘት ደርሷል::
ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ አድማጮች የሚቆዝሙበትን በርካታ አዳዲስ ፕሮግራሞች ለሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በማስተዋወቅ ስኬታማ መሆን የቻለው እውቁ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ በሃገሪቱ የሬዲዮ ታሪክ ፋና ወጊ ተብለው የሚታወሱትን ፕሮግራሞች በመቅረፅና በማዘጋጀትም ሙያው አንድ እርምጃ ከፍ በማድረጉ ዛሬም ስሙ ይነሳል:: ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ መዝናኛና እርሶም ይሞክሩት የተሰኙትን ተወዳጅ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ሲወሱና ለዘመናት ሲታወሱ የነበሩ ፕሮግራሞች አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን አይረሴ ታሪክ መሥራት መቻሉ ተጠቃሽ ነው::
በባለ አስገምጋሚ ድምፁ ታደሰ ሙሉነህ በተለይም 1973 ዓ.ም በኢትዮጵያ የእሁድ ጠዋቱ የመዝናኛ ዝግጅት ማዘጋጀት ከጀመረ ወዲህ ነበር ስሙ በአየር ላይ መናኘቱን ‹‹የነበረ ይናገር…›› እንደሚባለው ሁሉ በቅርብ የሚያውቁትና የፕሮግራሙ ተከታታዮች የነበሩ የሚመሰክሩለት ሐቅ ነው:: በጊዜው በነበሩ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አድማጮች በእለተ ሰንበት ጠዋት በጉጉት ከሚጠበቀው በዚህ ፕሮግራም ብዙዎች ተምረውበታልም፤ ተዝናንተውበታልም:: ለዚያ ዘመን ትውልድ እሁድ ልዩ ትዝታ ነበራት፤ ቀኗ ደርሳ ጠዋት የመዝናኛ ፕሮግራሙን ለመስማት የነበራቸው ጉጉት ዛሬ በሕይወት ያሉት በትዝታ የሚያስታውሱት ሁነት ነው::
አስቀድሞ በነበረው ልማድ መሠረት የኢትዮጵያ ሬዲዮ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ ከሚገኘው ስቱዲዮ በጥንቃቄ የተዘጋጁ ፕሮግራሞችን ሠርቶ ከማሰራጨት በተጨማሪ ሕዝቡን በንቃት ባሳተፈ መልኩ ከስቱዲዮ ውጪ ፕሮግራሞችን የመሥራት ምንም አይነት ልምድ አልነበረውም:: ታደሰ ሙሉነህ የፈጠራ ችሎታውና ለትምህርት ውጭ ሃገር በሄደበት ወቅት ያገኘውን ልምድ በማሰባሰብ አዳዲስ አሠራሮች በማምጣትም የበኩሉን አሻራ ማሳረፍ ችሏል:: በዚያ ጊዜ ሊያውም በተደራጀ መልኩ የሬዲዮ ፕሮግራምን ከስቱዲዮ ለማውጣት በመቻል ሌላ ታሪክ በመሥራቱም ይታወቃል::
ታደሰ ሙሉነህ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ወቅቱ የቀጥታ ስርጭት ያልተለመደበት ጊዜ ነበር፤ እኔ የማስታውሰው አቶ አሳምነው በቀጥታ ከቤተመንግሥትና የጥምቀት በዓል ጃንሜዳ ሲካሄድ የነበረውን ዝግጅት ተክቼ የገባሁት እኔ ነኝ፤ ያንጊዜ ልጅ ነኝ እሱ ግን ድምፄን ሲሰማ በጣም ነው የገረመው:: ያንጊዜ ደግሞ ማዕረግ ማወቅ አለብህ፤ አለባበስ ማወቅ አለብህ ….. በጣም ጥሩ ጊዜ ነበረን፤ የመማማሪያ ጊዜ ነበረ፤ እኔም ብዙ ነገሮች ለማድረግ ጥሬያለሁ ›› በማለት ስለራሱ ሥራዎች ተናግሯል::
አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር ወደኋላ የማይለው ታደሰ ሙሉነህ አዲስ ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ፣ ‹‹እርሶም ይሞክሩት›› የሚል ፕሮግራም ሠርቼ ማቅረብ እንደሚፈልግ ለአለቆቹ ይናገራል:: ፕሮግራሙን በምን አይነት መልኩ እንደሚያቀርብ በአለቆቹ ሲጠየቅ ‹‹በየቀበሌው አዳራሽ እየዞርን፤ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ እየገባን አድማጮችን በጥያቄና መልስ በማወዳደር ፕሮግራሙን እናቀርባለን›› የሚለው የታደሰ አጭርና ቀጥተኛ ምላሽ በአለቆቹ ዘንድ ጥርጣሬ ማጫሩ አልቀረም:: አለቆቹ ፍላጎቱን አይተው እንደነገሩ ‹‹ጀምር›› ብለው ፍቃዳቸውን ገለጹለት:: ይሁን እንጂ ፕሮግራሙ ተወዳጅ ስለመሆኑ ሰፊ ጥርጣሬ ነበራቸው:: ሆኖም ፕሮግራሙን በሬዲዮ ማቅረብ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ተወዳጅነት በማግኝቱ ለጣቢያው መደመጥ የራሱን ጉልህ ሚና ተጫውቷል:: ፕሮግራሙ ሲጀመር ስኬታማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ነበር፤ ነገር ግን ፕሮግራሙ በሁሉ ዘንድ ተወዳጅ ሲሆን ከአለቆቹ ምስጋናን አግኝቷል::
የእሁድ መዝናኛ የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞች በስፋት የሚቀርቡበት እንደነበር ይታወሳል:: ምንአልባትም በኢትዮጵያ የሬዲዮ ታሪክ ትልቅ የፕሮግራም አብዮት ማስነሳት የቻለ ነበር ማለት ይቻላል:: የሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤትና የፕሮግራም አዘጋጅ የሆነችው መዓዛ ብሩንና ተፈሪ ዓለሙን የመሳሰሉትን ወጣት ጋዜጠኞችን በመያዝ ዳግሞ አዲስ ነገር ይዞ ብቅ አለ:: ይሄ እያዝናና ቁምነገርን የሚያስጨብጠው ፕሮግራም የተለያዩ ንዑስ ፕሮግራሞችን በውስጡ ያካተተ በመሆኑ የተነሳ አለቆቹ ይህ ፕሮግራም እውን ስለመሆኑ ለእሱ ያልደበቁት ስጋት በውስጣቸው አድሮባቸው ነበር:: ይሁን እንጂ ምስጋና ለእሱ ጥረትና ለመዓዛና ተፈሪ ዓለሙ እንዲሁም ለሌሎቹ ወጣት ጋዜጠኞች ይሁንና የእሁድ መዝናኛ ዘወትር እንደተናፈቀ ዓመታትን በስኬት ማሳለፍ የቻለ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ታላቅ ፕሮግራም መሆኑ ዛሬም ድረስ ይታወሳል ::
የደርግ ዘመን አክትሞ ኢሕአዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት የቆየው ታደሰ ሙሉነህ ጡረታ በመጠየቅ ራሱን ከመንግሥትና ከሚዲያ ሥራ ካገለለ በኋላ የማስታወቂያ ድርጅት በመክፈት በግሉ በመንቀሳቀስ ላይ ነበር:: የታደሰ ሙሉነህ የጋዜጠኝነት ሕይወት ከሞላ ጎደል በስኬት የተሞላ ሲሆን ብዙዎች ከሚያውቁት ከጋዜጠኝነቱ ባለፈ የአዲስ አበባ የዳት ስፖርት ሻምፒዮን ሲሆን ነው:: በሌላ በኩልም ታደሰን በቅርብ የሚያውቁት ጓደኞቹ አንባቢነቱን ይመሰክሩለታል:: በተጨማሪም በሃገሪቱ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ ሬዲዮን ለመጀመሪያ ጊዜ ከስቱዲዮ ያወጣ ሁለገብ ጋዜጠኛ ስለመሆኑ ሁሉም አብነት አድርገው የሚጠቅሱት ጉምቱ ጋዜጠኛ ነው:: በተለይም በወቅቱ አንድ ለእናቱ ለነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ የአድማጮቹን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር በማድረግ ሌላ ደማቅ ታሪክ በመፃፉም ለሃገር የማይዘነጋ ውለታን አሳርፎ ያለፈ ሰው ነው::
ሁለገቡ ጋዜጠኛ የአዳዲስ ሃሳብ አመንጪ፤ የማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ታደሰ ሙሉነህ ከዜና አንባቢነት እስከ ዋና ክፍል ኃላፊነት በሬዲዮ ጣቢያ ያገለገለ ሲሆን አዲስ ቻምበር ድምጽ መሥራችና የፕሮግራም መሪ በመሆን አገልግሏል:: ለሰባት ዓመታትም የሞሐ ሳምንታዊ ፕሮግራሞችን እንዲሁም ደግሞ ‹‹እሁድን እንደገና›› በተሰኙት ፕሮግራሞች በሸገር ኤፍ ኤም ያቀርብ ነበር:: ብዙዎች የማያውቁትና የሚገርመው ነገር ግን ታደሰ የሬዲዮ ብቻ ሳይሆን የቴሌቪዥን ስፖርት ጋዜጠኛ ሆኖ ጭምር መሥራቱን ነው:: ከዚህ ባሻገር በሞሐ ሕዝብ ግንኙነት ውስጥም የሠራው ታደሰ በጡረታ ዘመኑ ሳይቀር በርካታ ሥራዎችን አበርክቷል:: ይህን አንጋፋ ጋዜጠኛ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ከማበርከት ባለፈ እንደመዓዛ ብሩና ተፈሪ ዓለሙን የመሰሉ ብርቱና ምርጥ ጋዜጠኞችን በማፍራትም ያበረከተው አስተዋፅኦ የማይዘነጋ ነው::
በግል ሕይወቱ ታደሰ የሕዝብን አድናቆትን እና ክብር ካገኘበት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ የእንግሊዘኛ ክፍል ባልደረባ ከነበረችው የሕይወት አጋሩ ጋር በመጣመር ሕይወቴ ታደሰ ሲል የሰየማትን ብቸኛ ሴት ልጁን አግኝቷል:: በቤተሰቡም ደስተኛ የነበረ ሲሆን በግሉ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሦስት አይነስውራን ወጣቶችም በዲግሪ ተመርቀውለታል:: ከአስር በላይ በሚሆኑት ሃገራት ያሰባሰበውን እውቀት ለአዲሱ ትውልድ በማካፈሉ ቤቱ ይቁጠራቸው የሚባሉ በርካታ የሙያ ልጆችንም አፍርቷል:: ታደሰ አንድ ወቅት ላይ ‹‹የተቻለኝን የሙያው ባለቤት እንዲሆኑ ጥረት አድርጌያለሁ:: አሁን የምትሰሟቸው ልጆች ሁሉ ጥሩ ቦታ ደርሰው ሳያቸው የሚሰማኝ የመንፈስ ደስታ ትልቅ ነው›› ሲልም ተናግሯል::
ጋዜጠኛ ታደሰ ጡረታ ከወጣም በኋላ ከሙያው ሳይለይ በርካታ ሥራዎችን በመሥራቱ ከፍተኛ እውቅና ከተለያዩ አካላት ተሰጥቶታል:: በሙያው ካገኛቸው በርካታ ሽልማቶች መካከልም ከኢትዮጵያ የሥነ- ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት ድርጅት ያገኘው በዋናነት ይጠቀሳል::
ታላቁ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ ከአራት አስርተ- ዓመታት በላይ ከዜና አንባቢነት ጀምሮ በፕሮግራም አዘጋጅነት፣ በፕሮዳክሽን ኃላፊነት፣ በዋና ክፍል ኃላፊነትና በተጠባባቂ የመምሪያ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ብቻ ፕሮግራሞች አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ጡረታ እስከወጣበት ጥቅምት 1986 ዓ.ም ድረስ ለ26 ዓመታት አገልግሏል:: ከጡረታ በኋላም ለሕይወቱ ማለፍ ምክንያት የሆነው ሕመም እስካደናቀፈው ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይይል ለሙያው እድገት ዋጋ ከፍሏል:: ጋዜጠኛ ታደሰ ባደረበት ሕመም በአዲስ አበባ፣ በጆሐንስበርግ (ደቡብ አፍሪካ) እና ባንኮክ (ታይላንድ) ሕክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በ66 ዓመት ዕድሜው ከሚወደው ሙያና ሕዝብ በሞት ተለይቷል:: ይሁንና በሙያው ውስጥ ላሉ የዘርፉ ተዋናዮችም ሆነ ለሃገር ትቶት ያለፈው አሻራ ዛሬም ደማቅ ሆኖ እያበራ ይኖራል::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015