‹‹በሕግ ፊት አላወቅኩም ማለት ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ በእርግጥ እኔም ወደ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀለኝነት የገባሁት ሳላስበውና ጎጂነቱን ሳላውቀው ነበር›› ይሄን ያለችን በቃሊቲ የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ቤት የቅጣት ጊዜዋን እየፈፀመች የምትገኘው የሕግ ታራሚ ሣራ ተሰማ ናት።
ሣራ እንደነገረችን ከአገር የወጣችው ለሥራ አመች በሆነና ጥሩ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ለመሰማራት ነው። ሆኖም ባላሰበቸው መንገድ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት ጠልፎ ጣላትና ለወንጀል ዳረጋት፡፡ መጨረሻዋም ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነ፡፡
‹‹ይሄን እህቶቼ ለስቃይ የሚዳረጉበትን ተግባር በመፈፀም ገቢ እያገኘሁ ራሴን አስተዳድርና ለዘለቄታውም እኖራለሁ የሚል ሀሳብ በእውኔ ቀርቶ በህልሜም አስቤውና አይቼው አላውቅም›› ስትል በፈጣሪ ስም እየማለች በተግባሩ ሆን ብላ አለመሰማራቷን ትገልፃለች ታራሚዋ፡፡
የሕግ ታራሚዋ ወደ አስከፊው ተግባር አገባቧን እንዳጫወተችንም ለሥራ ከአገር ከወጣች በኋላ ከብዙ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል አግኝታ ነበር። በናይሮቢ ያለው ሆቴሏ በዚህ በኩል ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላታል፡፡ ወደ ሆቴሏ ከሚመጡት ደንበኞች አብዛኞቹ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ነበሩ። እነዚህ ሕገወጥ ደላላዎች በኢትዮጵያ ካሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ የገጠሩ የአገራችን ክፍል ሴት ወጣትና ታዳጊዎችን በሥራና በሕይወታችሁ ለውጥ ታገኛላችሁ በሚልና በተለያየ ማግባባትና ማታለል እያመጡ ወደ አረብና ወደ ተለያዩ አገራት ይልካሉ።
ተግባሩ በብዙ ሰዎች ቅብብሎሽ የሚፈፀም ነው። ከኢትዮጵያ ታች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ወረዳና ክልል እንዲሁም ክፍለ ከተማ ብሎም እንደ ዋና መዲናችን አዲስ አበባ ባሉ አካባቢዎች ሁሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ይከናወናል፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ እንደሸቀጥ ሁሉ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ በውጭ አገር ተቀምጠው ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የሚያሸጋግሩ ሕገወጥ ደላሎች ቃሉ ካነሳቸውም ደግሞ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ሰዎች በብርቱ ይታገዛል፡፡
ታራሚዋ የፀፀት እንባ ያቆረዘዙት ዓይኖቿ ያዘሉትን የቁጭት እንባ እያረገፉ እንደነገረችን ወደ ተግባሩ ከገባች በኋላ እንደተገነዘበችው በተለይ ምንም የማያውቁትና ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ የሌላቸው በገጠር ያለው አርሶ አደር ልጆች የነዚህ ሕገወጥ ደላሎች ሰለባ ናቸው፡፡ በእርሻ፤ በጉልጓሎ፤ በአረማ፤ በትምህርት ገበታቸው፤ በገበያና በተለያዩ ሥፍራዎች ሁሉ እነዚህ ደላሎች እያንጃበቡ ይመለምሏቸዋል፡፡
የተሻለ ደመወዝ፤ የተሻለ ኑሮ፤ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙና በአጭር ጊዜም እንደሚለወጡ፤ ከእነሱ አልፈው የቤተሰባቸውን አኗኗርና ሕይወት በብርቱ እንደሚለውጡና ለሌሎች ጓደኞቻቸው ሳይቀር እንደሚተርፉ ይነግሯቸዋል፡፡ ሆኖም ይሄ በአብዛኛው ወይም 99 በመቶ ውሸትና ማታለል ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ አቀባባይ ናቸው፡፡ ከነሱ በአንድ ደረጃ ከፍ ላለው ሕገወጥ ደላላ አሳልፈው እስኪሰጧቸው ድረስ ብቻ ነው ይሄን የሚሏቸው፡፡ አሳልፈው ከሰጡና ክፍያ ካገኙ በኋላ ዞር ብለው አያይዋቸውም፡፡ ልያቸው ቢሉም የገቡበትን ሥፍራ አያውቁም፡፡ ወይም ማወቅ አይችሉም።
እነዚህ ታችኛው ክፍል ያሉትም ሆኑ በየደረጃው እስከላይኛው ያሉት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ደላሎች የሚያስጨንቃቸው ገቢያቸው ነውና ስለነዚህ ነፍሶች ብዙም አይጨነቁም፡፡ ነፍሶቹ ከመነሻው እስከ መድረሻው ከአካል ጉዳትና ከነፃ ጉልበት ብዝበዛ እስከ ሞት ድረስ ስለሚገጥማቸውም ችግርም ግድ አይሰጣቸውም፡፡ በጉዞ ላይ በተለይ በእግር ከሆነ ከአገር የሚወጡት በመንገድ ለሚደርስባቸው ብዙ ስቃይና መከራ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ እራሳቸውን ተጠያቂ አያደርጉም፡፡ በባህርም ሆነ በመኪናም በነፍሶቹ ላይ ለሚደርሰውም እንዲሁ በተመሳሳይ ያገባናል የሚሉ አይደሉም፡፡
ሌላው ቀርቶ ነፍሶቹ በለስ ቀንቷቸው በመንገዳቸው ላይ ክፉ ሳይገጥማቸው ከመካከለኛው ምሥራቅ ወይም ከአፍሪካ በአንዱ አገር ቢደርሱና ተቀባዩ ያለ ደመወዝ ቢያሰራቸውና እንደ ባርያ ቢገዛቸው የሚደርስላቸው የለም፡፡ ፓስፖርታቸውም በአሰሪዎቻቸው እጅ ነው የሚሆነው፡፡ መኖሪያም ፈቃድ ቢሆን የሚያገኙበት ዕድል የላቸውም፡፤ በየትኞቹም አገር ቢሆን ከአሰሪዎቼ አምልጬ እሄዳለሁ የሚሉ በፖሊስ እጅ ወድቀው ለባስ ችግር ነው የሚዳረጉት፡፡ ዕውቀቱ የሌላቸው ለማምለጥ ሲሞክሩ ለእስርና እንግልት ይዳረጋሉ፡፡ ዕውቀቱ ያላቸው ቢሆኑ አማራጭ ስለሚያጡ እንደ ባርያ ለአሰሪዎቻቸው በነፃ ለማገልገል ይገደዳሉ፡፡
እነዚህ ሕገወጥ አዟዟሪዎች ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ያልበሰሉ ሴቶችን ጭምር ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍል ይልካሉ፡፡ ከአፍሪካ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጎረቤት ጅቡቲ፣ ከሚልኩባቸው ይጠቀሳሉ። ከመካከለኛ ምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ፤ የመን፣ ሊባኖስ ሌሎችም አገራት እንዲሁ ይገኙበታል። ዳጎስ ባለ ገንዘብ ወደ አሜሪካም እና አውሮፓ የሚያሻግሩ ደላሎችም አሉ፡፡
በእነዚህ ሕገወጥ አስተላላፊዎች ምክንያት ከሞቀ ኑሮና ከትምህርት ገበታ ሳይቀር ተፈናቅለዋል። በተለይ በሕገወጥ ተግባሩ ብዙዎች ነፍሶቹ አድራሻቸው አለመታወቁን አንዳንድ ቤተሰቦች ሲያነሱ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ የሚሉበት እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡ እናም በሆቴሏ አማካኝነት የተዋወቋት ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ቅልጥፍናዋንና ዕውቀቷን አስተውለው ሣራን ቀስ በቀስ የሥራቸው ተባባሪ አደረጓት። የአራት ልጆች እናት የሆነችው የሕግ ታራሚዋ ሣራ በዚህ ዓለም አቀፍ የወንጀል ተግባር ላይ በዚህ መልኩ ተሰማርታም በመገኘቷ ከኬንያ በኢንተር ፖል አማካኝነት ተይዛ ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡
ታራሚዋ እንደምትለው በሕገወጥ ወንጀሉ ተሰማርታ በመገኘቷ ብዙ መብቶቿን አጥታለች፡፡ ከልጆቿ ተለያይታለች፡፡ ሁለቱን ልጆቿ እዚያው ኬንያ ሆና ነው ከእሷ በመነጠል አንዳቸው አሜሪካ ሌላኛቸው ለንደን የሄዱት፡፡ ሁለቱ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ከእሷ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡም ወንጀለኛ መሆኗን ሲያዩ አንዷን ልጇን የአባቷ ቤተሰቦች ሊያሳድጓት ተረከቧት፡፡ ሌላዋ ደግሞ ተረካቢ አልነበራትምና ባላጠፋችው ጥፋት ገና በ14 ዓመቷ አብራት ዘብጥያ ወረደች፡፡ በተለይም ጥፍር ይነቀልበት ነበር በምትለው ማዕከላዊ ጦሷ ለታዳጊ ልጇ እስኪተርፍ ለስምንት ወራት ብዙ ስቃይና መከራን ስትቀበል ቆየች፡፡
‹‹ታራሚዋ ሁኔታውን ለሠራሁት ሥራ ሲያንሰኝ ነው›› ስትል በፀፀት ታስታውሰዋለች፡፡ ከራሷ አልፎ የልጇን ሕይወት መስረቋ በብርቱ እንደሚፀፅታትም ታወሳለች፡፡ በተግባሩ የተሰማሩ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የልጆቻቸውን፤ የቤተሰባቸውንና በአጠቃላይ የብዙ ማህበረሰብና ሕዝቦችን ሕይወት እንደሚጎዱ በልጇ ላይ ጭምር የደረሰውን ስቃይና መከራ በማሳያነት ታነሳለች፡፡
ታራሚዋ ሣራ ከስምንት ወር የማዕከላዊ ቅጣት በኋላ በ2007 ዓ.ም ወንጀለኛነቷ በፍርድ ቤት ተረጋግጦ ወደ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ተዘዋወረች፡፡ አሁን ላይ ቅጣቷን ለመፈፀም ሁለት ዓመታት ከጥቂት ወራት ይቀራታል፡፡
ሳራ በወንጀሉ ስትያዝ የ14 ዓመት ታዳጊ የነበረችው ልጇም ሆነች እሷ የተለያዩ ሙያ ባለቤቶች የሚሆኑበት ስልጠና ተሰጥቷቸው በዚያው በማረሚያ ቤቱ በሥራ ተሰማርተዋል፡፡ ልጇ የተለያዩ ሙያዎች ስልጠና አግኝታ የራሷን ሥራ እየሠራች መገኘቷ እንደተጠበቀ ሆኖ እሷ በበኩሏ አሁን ላይ ከሌሎች ሴት የሕግ ታራሚዎች ጋር ‹‹ማራኪ የልብስ ጥበብ ሙያ›› የሚል ስያሜ ባለው ማህበር ተደራጅታ የእርምት ጊዜዋን ከመፈፀም ጎን ለጎን ገቢ በማግኘት ላይ ትኛለች፡፡
‹‹ማረሚያ ቤት ጥሩ ነው ብለሽ የምትናገሪበት ቦታም አይደለም›› የምትለው ታራሚዋ ሆኖም ማረሚያ ቤት ሰው ውጭ ሆኖ እንደሚያየውና እንደሚያስበው የስቃይና የመከራ ብሎም የሰው ልጆች ሰብአዊ መብት የሚረገጥበት ቦታ አይደለም፡፡ ማረሚያ ቤት መማር ከፈለጉ የሚማሩበት መታረም፤ የዕውነት መታረም ከፈለጉ የሚታረሙበት፤ መሥራት ከፈለጉም የሚሠሩበት፤ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብሎ መዋልም ከፈለጉ ቁጭ ብለው መዋል የሚችሉበትና የታራሚው ፍላጎትና ሰብዓዊ መብት የሚከበርበት ነው›› ትላለች፡፡ በተለይ ቀድሞ የነበረው የማረሚያ ቤቶች ሰብአዊ አያያዝ መሻሻሉን ታስረዳለች፡፡
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ‹‹አሰቃቂ ሥራ ነው›› ስትልም ከልቧ ትናገራለች፡፡ በቅርብ ወደ ሞት መንገድ የሚለውን መጽሐፍ ካነበበች በኋላ ‹‹እኔም ስሠራ የነበረው ነገር ይሄን ነው እንዴ›› በማለት ራሷን በፀፀትና በአግራሞት መጠየቋን ትጠቅሳለች፡፡
‹‹የማይሳሳተው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ እኔ ተሳስቻለሁ›› ስትልም በተግባሩ መፀፀቷን በቁጭት ትናገራለች፡፡ እንደምትለው በሰዎች መከራና ስቃይ የሚበላ ምግብም ሆነ የሚገኙ ጥቅሞች ሁሉ ጥሩ አይደሉም፡፡ ይህ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ወንጀል ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የሚጎዱት ምንም የማያውቁ ንጹሃንን ሕይወት ነውና ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ስትል ምክሯን ትለግሳለች።
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ ወንጀል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በዓለም አገራትም ሆነ ሕዝቦች በብርቱ የሚወገዙ ናቸው፡፡ በአብዛኛው እንዲህ ባሉ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎች የቅጣት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ በአመክሮም ሆነ በምህረት ከስር የሚፈቱበት ዕድል ሊኖር አይችልም ሲሉ በየፊናቸው አስተያየታቸውን የሰጡን በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አለም ጥላሁንና የማረሚያ ቤቱና ማረፊያ ቤቱ አባልና የሴቶችና ሕፃናት ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር በዛብሽ ማርያም ናቸው፡፡
ኃላፊዎቹ በማረሚያና ማረፊያ ቤቱ ከሚገኙት 558 ታራሚ ሴቶች መካከል በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የገቡ እንዳሉ ያነሳሉ፡፡ ሆኖም የሰብአዊ መብቶቻቸው ተከብሮ በመልካም አያያዝ እንደሚገኙና በቆይታቸው የእነሱን ፈቃድ ብቻ መሠረት በማድረግ የተለያየ ሙያ ስልጠና እንዲወስዱና የእርምት ጊዜያቸውን ከመፈፀም ጎን ለጎን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ቅጣታቸውን ፈፅመው በሚወጡበት ጊዜ በሥራ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ገቢ እንዲያገኙ እንደሚደረግም ገልፀውልናል፡፡
አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙትና ለረጅም ጊዜ በዳኝነትና በሕግ ጉዳዮች ላይ ሲሠሩ የቆዩት የሕግ ባለሙያ ተሾመ እሸቱን በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ጠይቀናቸው የሰጡንን አስተያየት ለሌሎች በወንጀሉ ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ ትምህርት ይሆናል በሚል እንደሚከተለው በጽሑፉ ውስጥ አካተነዋል፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ታዲያ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በዓለምም ሆነ በአገራችን ‹‹የባርያ ዘመን›› ተብሎ በአሳፋሪና በአፀያፊነቱ በመታወቅ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያለው እንጂ አዲስ አይደለም።
በታሪክ ስናነሳውም በዚህ ተግባር ተሳትፎ መገኘት የሚያሳፍርና የሚያፀይፍ በከባድ ዓለም አቀፍ ወንጀልም የሚያስጠይቅ ሕገወጥ ተግባር ነው ብለው የዓለም አገራት በሙሉ ያወገዙት ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት በፊት ያወገዘችውና አሁንም በብርቱ እያወገዘችው ያለ እኩይ ተግባር ነው፡፡
የሰው ልጅ በከፍተኛ ደረጃ ሰልጥኗል በሚባልበት ጊዜ ሰውን ሸጦ እንጀራ መብላት በጣም አፀያፊና ነውረኛ ሥራ ነው፡፡ ‹‹ያላመረትከውንና እንድትሸጠው ፈቃድ የሌለህንና ደረጃውን ያልጠበቀ ዕቃ መሸጥ የለብህም›› እያለ ባለበት ሰዓት ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ መሸጥ ሴትም ያድርገው ወንድም ያድርገው፤የተማረም ሰው ያድርገው ፤ያልተማረም ሰው ያድርገው ነውር ነው፡፡ ምክንያቱም ተግባሩን ማንም ሰው ሊያደርገው አይገባም፡፡ የዚህ ድርጊት መንስኤው ስግብግብነት ነው፡፡ ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች አብልጠው ለመኖርና ለመጠቀም የሚያደርጉት ሩጫ ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል፡፡ አዲስ ባለመሆኑ ሲወገዝም የኖረ ነው፡፡ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ፈፃሚዎች በተለይም ሣራ በኢንተር ፖል ተፈልጋ ልትመጣ የቻለችው የዓለም ሕዝብ ያወገዘው ዓለም አቀፍ ወንጀል ስለሆነም ነው ባይ ናቸው የሕግ ባለሙያው፡፡
ወንጀልነቱን የከፍ የሚያደርገው የሰው ልጅ በሰው ላይ ለምንድነው የሚጨክነው የሚለው ሲመዘን ወንጀሉን ከባድ ያደርገዋልም ባይ ናቸው። በዚህ ምክንያት ወንድም ሆነ ሴት ድርጊቱን ሲፈጽሙ የተገኙ ሰዎች ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያጋጥማቸው በሕግና ደንቡ በግልፅ የተቀመጠ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ ይሄን ወንጀል ፈጽመው በእስር ጊዜ ለሚደርስባቸው ማንኛውም ጉዳት ተጠያቂዎቹ ራሳቸው እንጂ ሌላ አካል ሊሆን አይችልም የሚልም አቋም አላቸው፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም