ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ስብጥር፤ በእምቅ የሀገረሰብ እውቀት ክምችትና ተያያዥ ጠቀሜታ ባላቸው መድኃኒታማ እጽዋት ብዛት በዓለም ከታወቁ አገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለዩት ከ50 ሺ ለመድኃኒትነት የሚውሉ እጽዋቶች መካከልም ስድስት ሺ ያህሉ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ከዚህ ውስጥም አንድ ሺ የሚሆኑት ለመድኃኒትነት የሚውሉ የእጽዋት ዓይነቶች ሲሆኑ፤ 240ዎቹ አገር በቀል መሆናቸውን ነው የዘርፉ ተመራማሪዎች የሚያስረዱት።
ሀገሪቱ እነዚህን ሀገር በቀል እፅዋቶችን ለመድሃኒትነት ጥቅም ላይ በማዋል ረገድም ረጅም ዘመናትን ማስቆጠሯን ሰነዶች ያመለክታሉ። በተለይም የሀገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኑሯቸውና የጤና አጠባበቃቸው በባህላዊ ሕክምና እና መድኃኒት ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆኑ ከዕፅዋቶቹ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ያመለክታል።
ይሁንና በተለይም የዘመናዊ ህክምና መስፋፋት ጋር ተያይዞ እፅዋቶችን ለህክምና የመጠቀሙ ባህል እየተዳከመ ስለመምጣቱ ይነሳል። በዚህ ረገድ በአውሮፓ እንደጀርመን፤ በኢዢያ ደግሞ ቻይና እና ህንድ የመሳሳሉት ሀገራት ያላቸውን የእፅዋት ሀብትም ሆነ ባህላዊ ህክምና ከማሳደግ ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀሙ ካሉ የዓለም ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይም በቻይና ዘርፉ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በመተሳሰሩና ለተጠቃሚዎች ምቹ በመደረጉና ወደ ተለያዩ ዓለም ሃገራት ጭምር በመላክ ለሀገራቸው ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ነው የሚገኘው። ቻይና በባህላዊ ህክምና እጅግ እየተራመደች ያለች ሀገር በመሆንዋም የባህል ህክምና ኢንስቲትዩት፤ በጣም የተደራጀ የባህል ህክምና እና መድሀኒት ፣ ኢንሳይክሎፒዲያ (የባህል መዝገባ ቃላት)፤ በሙያው በየጊዜው የሰለጥኑ እና እውቅና የተሰጣቸው ዶክተሮችና የመታከሚያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆናለች።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የበርካታ እፅዋቶች ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አይለም። ይልቁንም ከዘመናዊ ህክምና መስፋፋት ጋር ተያይዞ የምዕራብውያኑ እውቀትና ተሞክሮ በማምጣት ያላትን እምቅ ሀብትም ሆነ እውቀት እየጣለች እንደምትገኝ ነው በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የሚናገሩት። ይህ ሁኔታ በእጅጉ ከሚያስቆጫቸው ሰዎች መካከል የሚና ባህል ህክምና ማዕከል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኡስታዝ ኑሩ ጀማል አንዱ ናቸው። የባህል ህክምናውንም ሆነ በዕፅዋት ላይ ያላቸውን ጥልቅ እውቀት ያገኙት ከአባታቸው መሆኑት የሚናገሩት እኚሁ ሰው ‹‹ያለንን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት አለማወቃችን ብቻ ሳይሆን ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠታችን የምዕራባውያኑ ሸቀጥ ማራገፊያ መሆናችንን ሳስብ ያንገበግበኛል›› በማለት ይገልፃሉ።
ባለፉት ሁለት አስርተ -ዓመታት ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ ድረስ በባህላዊ ህክምና ዘርፍ የሰሩት ኡስታዝ ኑሩ ከባህላዊ ህክምናው ባሻገር ዘመናዊ ሳይንስንም ጭምር በማጥናት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙ ሰው ናቸው። ግለሰቡ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ቡሬ ግብርና ኮሌጅ በመግባት እፅዋት ሳይንስ ያጠኑ ሲሆን ከአባታቸው የተረከቡትን በአረብኛ ቋንቋ የተፃፉ የእፅዋትና ባህላዊ ህክምና መጻህፍትን በማንበብ አቅማቸውን አጎልብተዋል። ከዚህም ባሻገር እነዚህን መጻህፍትን ወደ አማርኛ በመተርጎም በማህራዊ መተግበሪያዎች አማካኝነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ አድርገዋል።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ከአባታቸው እግር ስር እየተከተሉ የባህል ህክምና እውቀት እየቀሰሙ ያደጉት ኡስታዝ ኑሩ በተለይም ባህላዊ እውቀቱን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማጣመር በተለያዩ ህመም ውስጥ ያሉ ለአካባቢያቸው ነዋሪዎች አገልግሎት በመስጠት ፤ በባህል ህክምናም ሆነ በሃኪሞቹ ዙሪያ ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቀየር፤ በመድሃቶቹ ፈዋሽነት ላይ ያሉ ጥርጣሬዎችን በማጥራት ረገድ ከፍተኛ የሆነ ስራ እያከናወኑ ነው ያሉት።
እንደ ኡስታዝ ኑሩ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የባህል ህክምና የጀመረበት ጊዜ በውል ባይታወቅም የሺ ዘመናት ታሪክ እንዳለው በዘርፉ የተፃፉ ጥንታዊ መጻህፍት ያስረዳሉ። ባህላዊ ህክምና የሕረተሰቡን ብቻ ሳይሆን የከብቶችንም ጤና በመጠበቅ ትልቅ ባለውለታ የሆነ ዘርፍ ነው። ከአፄ ኃይለስላሴ ጀምሮ የባህል ህክምና በሕግ እንዲመራ ተሞክሮ ነበር። ይሁንና ዘርፉ ካለው ፋይዳ አንፃር የሚገባውን ትኩረት አልተሰጠውም። በተለይ የደርግ መንግሥት መምጣቱን ተከትሎ የባህል ህክምና የሚሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና ማሳደርና የመሳሰሉት ችግሮች ነበሩበት።
ከዚሁ በላይ ግን ጊዜው እየሰለጠነ በመጣ ቁጥር አብዛኛው ማህበረሰብ የአባቶችን የቀደመ እውቀት በመተው ወደ ምዕራባውያኑ እውቀትና ህክምና ላይ ማተኮር መጀመሩ የዘርፉ እድገት እንዲያሽቆለቁል ምክንያት እንደሆነ ኡስታዝ ኑሩ ያስረዳሉ። ‹‹በዚህ ትልቅ እሴታችን ዙሪያ አባቶቻችን ሰንደው ያዘጋጇቸው በርካታ መጻህፍት አሉ፤ ነገር ግን እነዚህን መጻህፍት አዋራቸውን አራግፈን እንዳንጠቀም ብዙ መሰናክሎች አሉብን›› ይላሉ።
እንደኡስታዝ ኑሩ ማብራሪያ፤ ጀርመን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እፅዋቶችን በመውሰድና ባህላዊ እውቀት በመቀመር ከፍተኛ ደረጃ ደርሳለች። ጀርመን በቅርቡ 3ሺ 500 የሚደርሱ ባህላዊ መድሃኒቶችን ገበያ ላይ አውላለች። የዘመናዊ ህክምና ባለቤት የምትባለው አሜሪካም 1 ሺ800 የሚሆኑ የዕፅዋት መድሃኒቶችን ለገበያ አቅርባለች። ኢትዮጵያ ከዚያ በላይ ሀብት ቢኖራትም ያሏትን መጻህፍቶች በህገመጥ መንገድ ወደውጭ በመውጣታቸውና ለዘርፉ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ከዘርፉ ከሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል።
ቻይናም የራሷ ባህል እና ጥንታዊ እውቀት ለማሳደግ በጣም ብዙ ጥረት ማድረጓን ያነሳሉ። ‹‹ቻይና በባህል ህክምና ዘርፉ ዩኒቨርሲቲ እስከማቋቋም ደርሳለች። በዩኒቨርሲቲው 60 በመቶ ባህላዊ፤ 40 ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ነው የሚሰጠው› ይላሉ። ጀርመንም በተመሳሳይ ለባህላዊ ህክምና ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጥ አንስተው፤ ‹‹በጀርመን ማንኛው ዶክተር የስራ ፈቃድ የሚሰጠው በባህል ህክምና ዘርፍ ፈተና ወስዶ ፈተናው ማለፍ ሲችል ብቻ ነው›› ሲሉ ይጠቅሳሉ።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የተለያየ የአየር ፀባይ እና እንደየአካባቢው የሚበቅሉ በርካታ መድሃኒትነት ያላቸው እፅዋቶች ቢኖሯትም ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ከመጠቀም ወደኋላ ቀርታለች። ‹‹ሱዳን ብትሄጂ ግን እንደሁኔታው የሚመች የአየር ፀባይ የለም። እኛ ደግሞ በተቃራኒው የአየር ፀባይም ሆነ መድሃኒታማ እፅዋቶች ባለሀብቶች ነን። ግን ደግሞ ፈጣሪ አሟልቶ የሰጠንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም›› ይላሉ።
ለዚህ ደግሞ በዋናነት በኢትዮጵያ የምዕራብውያኑ ተፅዕኖ በመዋጥ የራስን እወቅት፤ ታሪክ ቅርስና ማንነት በመተው የሌሎችን ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የመጠቀም ልምዱ በመጎልበቱ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹ይህ ደግሞ አሁንም በሌሎች ሀገራት ላይ ጥገኛ እንድሆን ከማድረጉም ባሻገር በእጃችን ያለውን አቅም እያጣነው ነው ያለነው›› ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ከመካከለኛ ገቢ ካላቸው ጋርም ተርታ መሰለፍ ያለመቻሏንና ዛሬም በሌሎች ሀገራት ጥገኛ በመሆን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬም እየተዳረገች መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ለዘርፉ እድገት ማነቆ ከሆኑት ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ በዘርፉ ላይ ያለው የተዛባ አመለካከት መሆኑንም ኡስታዝ ኑሩ ይናገራሉ። ‹‹ህብረተሰባችን የባህል ህክምና ሲባል በብዛት ከጥንቆላና ከባዕድ አምልኮ ጋር ያያይዙታል። ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም፤ ከጥንት አባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ፤ ለሺ ዘመናት ጥልቅ ምርምር የተደረገበት፤ ብዙዎቹ ፈዋሽነታቸውን በራሳቸው ያረጋገጡበት ነው›› ሲሉ ይናገራሉ። ይህ ሲባል ግን ሁሉም የባህል ሃኪም በዘርፉ ጥልቅ እውቀት ኖሮት ይሰራል፤ ከባዕድ አምልኮ የፀዳ ነው አማለታቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ለዚህ ደግሞ በዋናነነት በዘርፉ ዙሪያ ያለውን የተሳሳተ አስተሳብ በመቀየር ሀገራዊ እሴቶቻችንን አጉልቶ ማውጣት ይገባል የሚል እምነት ያላቸው የባህል ሃኪሙ በዚህ ረገድ እሳቸው ስራ በጀመሩበት ዘመን ይህ በሙያውና በባለሙያዎች ላይ መጥፎ እሳቤ ጎልቶ የወጣበት ጊዜ መሆኑ ስራቸውን ፈታኝ አድርጎባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹ከእምነቱ ባሻገር የመድሃኒቶቹ ጥራትና መጠን እዲሁም ፈዋሽነታቸው ላይ ያለው የተጠቃሚዎች ጥርጣሬን እያለ ይህንን ተጋፍጦ መስራት በጣም ከባድ ነበር›› ይላሉ።
ያንን እውነታን መሰረት ያላደረገ ግንዛቤ ለመስበርም በማሰብ እፅዋት ሳይንስ ማጥናታቸውን ያስረዳሉ። ‹‹ይህ ለዘመናት ከአባቶቻንን ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ የወረስነው ጥልቅ እውቀት በአጉል እምነት መሸፈን የለበትም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ›› ይላሉ። ይህ እውቀት የኢትዮጵያ ቅርስ በመሆኑ ይህንን ሀብት ከትውልድ ለማሻገርና ለሀገር በሚበጅ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ብዙ ምርምሮችን ማድረጋቸውን ያነሳሉ። ‹‹በተለይ የራሴን ማህበራዊ ሚዲያ ገፅ በመክፈት በዘርፉ ጥያቄ ላለባቸው ማህበረሰቦች ምላሽ በመስጠትና እውቀት እንዲያገኙ በማድረግ የራሴን ጥረት አድርጌያለሁ። በዚህም የህብረተሰቡን አመለካከት መለወጥ ችያለሁ›› በማለት ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል የባህል መድሃኒት ፈዋሽነት ጋር ተያይዞ ያለውን ጥርጣሬ ለራስ እሴት ዋጋ ካለመስጠትና ካለማክበር የመነጨ እንደሆነ ያነሳሉ። ለዚህም አብነት አድርገው ‹‹ካልሰየምና ሌሎች ማዕድናት ተብለው ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚመጡትን መድሃኒቶች ከአጥንት ተፈጥጭተው ነው። እኛ ሃገር ግን ያንን ሊተካ የሚችል እፅዋት አለ፤ ይህንን ግን ብዙ ሰው አያውቅም፤ ቢያውቅም ለመጠቀም እምነት የለውም›› በማለት ይጠቅሳሉ።
አክለውም ‹‹ዘመናዊ መድሃኒት ለአንድ በሽታ ነው የሚታዘዘው የእኛ እፅዋቶች ለምሳሌ ዳማካሴን ብንወስድ ከሆድ ቁርጠት ባሻገር ለራስምታትና ለሌሎች በሽታዎች በአንድ ጊዜ ፈውስ ይሆናል›› ይላሉ። እንዳውም ተጓዳኝ ችግር በማምጣት ረገድ ከተፈጥሮ ከሚገኘው የባህል መድሃኒት ይልቅ በዘመናዊ መንገድ የሚመረተው ላይ እንደሚያመዝን ያስረዳሉ። ከዚያ ይልቅም እንደቻይና ካሉ ሀገራት በገፍ በውጭ ምንዛሬ እየመጣ ሀገሪቱን ለተጨማሪ ኪሰራ እየዳረጋት መሆኑን ነው የሚያመለክቱት። ሌሎች የቅመማ ቅመም እፅዋቶችንና የጫካ ዛፎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ሀብቶች መኖራቸውን ጠቁመው እነዚህን መድሃኒቶች እንደየሰው ሁኔታ፤ በሳይንሳዊ ቀመር በመለካት ብንጠቀምባቸው ብዙ ከውጭ የምናስመጣቸውንም መድሃኒቶች ማስቀረት እንደሚቻል ነው የተናገሩት።
ዘርፉ ለሀገር እድገት ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ ድጋፍ በማድረግ የተሰራው ስራ እምብዛም መሆኑን ኡስታዝ ኑሩ ይናገራሉ። ‹‹እርግጥ ነው በመንግሥት በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ። በተለይ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የባህል ህክምና ራሱን የቻለ ቢሮ ተቋቁሞለት ከዘመናዊ ህክምና ጋር ጎን ለጎን አገልግሎት እንዲሰጥ ጅምር ስራዎች አሉ። ይሁንና አሁንም ቢሆን ድጋፉ በሚፈለገው ደረጃ ነው ማለት አይቻልም›› ይላሉ።
በዋናነትም ልክ እንደሌሎች የልማት መስኮች በዘርፉ ምርምር ለሚያደርጉ አካላት በመንግሥት በኩል የሚበጀት የፋይናንስ ድጋፍ አለመኖሩ የባህል ህክምናው አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማድረግ ያለመቻሉን ያስረዳሉ። ‹‹በአውሮፓና ቻይና ራሱን የቻለ በጀት ይመደባል። እኛ ሀገር ግን እንኳን በጀት ሊመደብለት ይቅርና በራሳችን ጥረት ስራውን እንዳንሰራ እንቅፋቱ ብዙ ነው›› ይላሉ።
አክለውም ‹‹እኔ ካለችኝ ቀንሼ ነው የምሰራው ግን ይህንን የምርምር ስራ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ መንግሥት ልክ እንደሌሎች የልማት ዘርፎች ማበረታቻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ቢያደርግልኝ፤ ካልሆነም ገንዘብ በብድር የምናገኝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ባይ ነኝ›› በማለት ተናግረዋል።
ኡስታዝ ኑሩ አሁን ከሚያከናወኑት የምርምር ስራ ባሻገር ከአንድ በዘርፉ ከሰለጠነ ሰው ጋር በመተባበር በተወሰኑ በሽታዎች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ እቅድ እንዳላቸው ያመለክታሉ። ‹‹ከጉበት ካንሰር ፤ ከፀጉር፤ ከማዲያትና ከውፍረት ጋር ተያይዞ የጀመርኳቸው የጥናት ስራዎች አሉ። በተጨማሪም ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችሉ ተጓዳኝ ስራዎችም እያከናወንኩ ነው ያለሁት›› ይላሉ። በተጨማሪም ሚና የባህል ህክምና ማዕከልን በማስፋት ወደፊት በተመረጡ ችግሮች ላይ ማህበረሰቡን ይጠቅማሉ፤ ያገለግላሉ የሚባሉ ሰፋፊ ጥናቶችን በማድረግ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ የማሳደግ ህልም ሰንቀው እየሰሩ መሆናቸውን ያስረዱት።
ይሁንና ይህንን ህልማቸውን ለማሳደግ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያሻቸው ይናገራሉ። ‹‹እኔ በግሌ የተወሰነ ጥረት ባደርግም የመንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ያስፈልገኛል። በተለይም በመንግሥት በኩል ምርምር የማደርግበትና እፅዋቶችን የምተክልበት የማባዛትና የምንከባከብበት መሬት ያስፈልገኛል›› ይላሉ። አሁን ባለው ሁኔታ በዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች በተለይ በከተማ የሚተክልበት ቦታ ስለሌለ ልጆቻችን ዳማከሴንና ጤናዳምን እንኳን እየረሱ በመሆናቸው ሙያውንም ሆነ እፅዋቶቹን ከነጭራሹ እንዳይጠፉ ስጋት እንዳላቸው ያነሳሉ።
በሌላ በኩልም ሀገር በቀል እፅዋቶችን በመጠበቅ ረገድ በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶታል የሚል እምነት አላቸው። ያም ቢሆን በይበልጥ እየተተከሉ ያሉት ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች መሆኑን ጠቁመው ይህ በራሱ በምግብ እህል ራሳችንን ለማዋል ጥቅም እንዳለው ግልፅ ቢሆንም በተጓዳኝ ለመድሃኒትነት የሚውሉ የጫካ ዛፎችም ሊተከሉ ይገባል ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህ ስራ ሲሰራ ደግሞ የባህል ሃኪሞችም ቢሳተፍበትና የእነሱን እውቀት የሚያካፍሉበት እድል ቢመቻች የተሻለ እንደሆነም ነው ያመለከቱት። በአጠቃላይ መንግሥት ዘርፉ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በመረዳት የዘርፉን አንቀሳቃሾች ቀርቦ እንዲያወያይ ነው ሃጂ ኑሩ ጥሪ ያቀረቡት።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም