ቃሊቲ በሚገኘው በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ተገኝተናል። ዕለቱ የጥምቀት በዓል ዋዜማ ከተራ ነበርና ሴት ታራሚዎች ለበዓሉ ዝግጅት ሽር ጉድ እያሉ ነው ። ደማቅ ቀይና አዲስ አልባሳት የለበሱት ሴት ታራሚዎች የሚንቀሳቀሱበትና የሚኖሩበት ሥፍራ ፀአዳነት በአግራሞት ያስደምማል። ተደራራቢው አልጋቸው የዩኒቨርሲቲን መኝታ ክፍል ያስታውሳል።
እዛም እዚህም የተፈጨ ሽንኩርት ይበስላል። በማዕከሉ እየተጋገረ ያለው የትኩስ እንጀራ ሽታ ለአፍንጫ ጡዑም ማዕዛ ከመለገስ አልፎ የሰውን ልብ እጅግ አድርጎ ያስደስታል። ለበዓሉ ዋዜማ ከተራ የተሰራውም ገበታ ግርማ ሞገስ ያለው ነበር። በማግስቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል ዕለት ደግሞ ታላቅ የምሳ ግብዣ አላቸው። የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓልም በዚሁ መልኩ ማሳለፋቸውንም ነው የሚናገሩት።
ሁሉም ያነጋገርናቸው ሴት ታራሚዎች በማረሚያ ቤቱ በዕለቱ ታቦታት ይወጣሉ። በዓሉም በድምቀት ይከበራል። በሳቅ በጨዋታ በምግብ መጠጥ፤ ታራሚዎች ቤተሰባቸውን እንዳያስታውሱና ደስተኛ ሆነው እንዲውሉ ይደረጋል። ለአውድ ዓመት ብቻ ሳይሆን ለሰርክ ቀናትም በማረሚያ ቤቱ የሃይማኖት መቻቻል አለ። በየማረፊያቸው ሁሉም ዓይነት ዕምነት ተከታዮች በየዕምነታቸው ፀሎት ያደርጋሉ። በተለይ ለበዓላት በሚደረገው ዝግጅት ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ፤ ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ ጋር በሥራም ሆነ በመዋጮ እኩል ይሳተፋል። እዚህ ጋር በማረሚያ ቤቱ ማረፊያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ተሳትፎም እጅግ የጎላ ነው። እነሱ ለኢትዮጵያዊያኑ በዓል ኢትዮጵያዊያኑ ደግሞ ለውጭ ዜጎቹ በዓላት (ኪሪስማስ) ከመሥራት ጀምሮ ይረዳዳሉ። ማረሚያ ቤቱ ለበዓል ዝግጅት ከወትሮው ለየት ያለ በጀት ይመድባል። በዚህ ላይ ታራሚዎች ከማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር በመቀናጀት ከውጭ ለበዓል መዋያ ድጋፍ ያመጣሉ። አንዳንዶቹም ማረሚያ ቤቱ በሰጣቸው ስልጠና የተለያዩ የእጅ ሙያ ባለቤቶች በመሆናቸው የሰሩትን ለገበያ አቅርበው ከሚያገኙት ገቢ ወይም ከሚያመርቱት ምርት ለበዓል ይቆጥባሉ፤ ያዋጣሉ፤ ስጦታ ይሰጣጣሉ።
በአጠቃላይ እኛ በጥምቀት ዋዜማ አግኝተን ያነጋገርናቸው ታራሚዎች ደስታ የፈነቀለው እንቅስቃሴያቸው በፍፁም ወደ ማዕከሉ ለእርምት የገቡ አላስመሰላቸውም። ዝግጅቱ ማዕከሉ ራሱ ሴቶች ከጥፋታቸው የሚታረሙበት የቅጣት ቦታ መሆኑን የሚያስረሳ ነው። እንዲህ ባለው ዐውድ ዓመት ወቅትና መልካም አያያዝ ወደ ማረሚያና ማረፊያ ማዕከሉ መግባቷን የምታስታውሰው የ20 ዓመት ፍርደኛ የሕግ ታራሚ አስናቀች ጌታቸው በገባችበት ወቅት መልካም አያያዙና ዝግጅቱ ለጥፋት ቅጣት የሚሰጥበት ማረሚያ ቤት መግባቷን ያስረሳት መሆኑን ታወሳለች። “ጓዜን ይዤ ከገባሁ በኋላ ለሰዓታት ቁጭ ብዬም በቅጣት ወደ ማሳልፍበት አስፈሪ ቦታ እስኪወስዱኝ ስጠብቅ ቆይቻለሁ” ስትልም ታስታውሳለች። አስናቀች ወደ እስር ቤት እስክትወሰድ የምትቆይበት ማረፊያ በመሰላት ቦታ ነፃነታቸውን እየተመኘችና እያደነቀች ቆይታለች።
ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ከሰል እያቀጣጠሉ ሁሉ ምግብ ያበስሉና በነፃነት ከወዲያ ወዲህ ሽር ጉድ ይሉ የነበሩት ሴት ታራሚዎች እየመጡ አመጣጧን ከጠየቋት በኋላ ቦታው ታስራ መቆያዋ እንደሆነ የነገሯት መሆኑንም ደስታ በፈነቀለው ፈገግታ ትናገራለች። “ዕውነት ጥፋት አጥፍቼ ነው ወይ የገባሁት?” ብላ ባለማመን ራሷን መጠየቋንም ትገልፃለች። ጥፋት ቢያጠፉ በህግና ደንቡ መሰረት የሚቀጧቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚያሳይዋቸው ትህትና እና ትዕግስት፤ የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። በታራሚዎች ላይ የሚፈጸም የመብት ጥሰት አለመኖሩንም አፏን ሞልታ ታነሳለች።
ይልቁንም ሴት ታራሚዎች የበለጠ ሰርተው በነፃነት እንዲኖሩ በማረሚያ ቤቱ አመራሮች ይበረታታሉ። በመረጡት ሙያ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችላቸው ስልጠናም ይሰጣቸዋል። እሷ በዚህ ዕድል ተጠቅማ በተለያዩ የእጅ ሥራዎች ትሳተፋለች። ሥራዎቿን ለውስጥና ለውጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሸጣ የምትጠቀምበትም ሁኔታ ተመቻችቶላታል። ራሷንም ትደጉማለች። በበዓላት ወቅት ስጦታ ትሰጣለች።
‹‹እንዲህ እንደ ጥምቀት ያሉት ዐውድ ዓመቶች ለእኛ ልዩ ናቸው›› ብላናለችም አስናቀች። ወደ ማረሚያና ማረፊያ ቤቱ የገባችው በ2006 ዓ.ም ነው። በነፍስ ግድያ 20 ዓመት ተፈርዶባት አባሪዋ ከነበረ የ23 ዓመት ፍርደኛ ጋርም ነው የገባችው። በመሆኑም በዚህ ቆይታዋ በርካታ በዓላትን ከቤተሰቦቿ በመለየት በማረሚያና ማረፊያ ቤቱ ውስጥ ለማሳለፍ ተገድዳለች።
ሴት ሆኖ በዓላትን በእስር ቤት ማሳለፍ እጅግ መክበዱንና እሷና ጓደኞቿ በዓላትን ከሌላው ሰው በተለየ ሁኔታ በጉጉት እንደሚጠባበቁም ትናገራለች። በዓላት ለእነሱ ታላቅ ደስታና ተስፋ ይዘው የሚመጡ የዕድል በረከቶች እንደሆኑም ታነሳለች።
ደስታቸው ተትረፍርፎ ከሚቀርበው ምግብና መጠጥ በስተጀርባ ካለው ተስፋ ጋርም በእጅጉ ተሰናስሎ የተቆራኘ እንደሆነ አበክራ ትገልፃለች አስናቀች። እሷ እንደነገረችን ማረሚያ ቤቱ በየዐውድ ዓመቱ በማረፊያ ቤቱ ላሉ ሴት ታራሚዎች ምህረት ያደርጋል። ከምግብ መጠጡ፤ በዚሁ ከታጀበው ሞቅ ደመቅ ያለ ዝግጅትና ሀዘንን ከሚያስረሳው የበዓል ጨዋታና ደስታ በስተጀርባ ያለው ተስፋ በምህረት ወይም በይቅርታ ከስር መለቀቅ ነው።
ሁሉም ሴት ታራሚዎች ይሄን ሁሌ ዐውድ ዓመት በመጣ ቁጥር በጉጉት ይጠብቁታል። ዐውድ ዓመት ሲመጣ ደስ ደስ የሚላቸውና በዝግጅት ተፍ ተፍ የሚሉትም በዋንኛነት ለዚሁ ነው። ይሁንና ይሄ በይቅርታ ወይም በምህረት ከእሥር የመፈታት ተስፋዋ እስከ አሁን ዕውን አልሆነም። በማረሚያ ቤቱ ያሉት ጓደኞቿም እንዲሁ።
ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በማረሚያ ቤቱ በእስር ያሳለፈችው አስናቀች ሁሉንም ዓመታት ያሳለፈቻቸው በተስፋና በበዓሉ ዝግጅት ድምቀት ነው። በተለይ በዘንድሮ የገና እና የጥምቀት በዓል በይቅርታ እፈታለሁ የሚል ተስፋዋ በብርቱ አይሎ ነበር። አንደኛው ምክንያቷ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከተፈረደባት የእስራት ዘመን ሁለት ሦስተኛውን ለመፈፀም መብቃቷ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ወደ ማረሚያ ቤቱ እንድትገባ መንስኤ ከሆናት ሟች ዘመዶች ጋር በገዳ ስርዓት መሰረት ይቅር መባባሏ ነው። እንደምትለው ዘመዶቹ ጉማ ወይም ካሳ በልተናልና ይህችን ልጅ አንፈልጋትም ብለዋል። ሆኖም የገዳ ስርዓት ሕጉ ተጣጥመው የሚሄዱበት ስርዓት ስላልተዘረጋ ይቅርታውን ማግኘት አልቻለችም። ወደፊት ግን እንዲህ ያሉት የፍትህ ስርዓቶች ከህጉ ጋር በሚስማማ መልኩ ተቀባይነት ኖሯቸው ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚልም አስተያየት አላት ። አስናቀችም ሆነች ሌሎቹ ሴት ታራሚዎች ለዚህ ማረሚያ ቤቱን ተጠያቂ ሲያደርጉ አይደመጡም።
‹‹ማረሚያ ቤት ከእግዚአብሔር በታች አባታችንም እናታችንም ቤተሰባችንም ነው›› የምትለው የህግ ታራሚ ሣራ ተሰማ በማረሚያና ማረፊያ ቤቱ በ2007 ዓ.ም ገብታ እስካሁን የቆየችው ሣራ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ኬንያ ላይ ተይዛ ነው በፍርድ ቤቱ ጥፋተኝነቷ ተረጋግጦ ወደ ማረሚያ ቤቱ ልትገባ የቻለችው።
‹‹ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም›› እንደሚሉት ተረት በእርግጥ አጥፍቻለሁ። ሆኖም ስህተቴን አምኜ ተቀብያለሁ። የምትለው ሣራ በየዓመቱ ምህረት ይደረግልኛል ብላ በተስፋ ስትጠባበቅ መቆየቷንም ታወሳለች። ይሄን በየዓመቱ መጠባበቅ የእሷ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሴት ታራሚዎች ብርቱ ፍላጎት መሆኑንም ታነሳለች።
‹‹በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ድሮ የነበረኝ አስተሳሰብ ዛሬ ላይ አለመኖሩን ነው›› የምትለው ሳራ በቆይታዋ ከበቂ በላይ ከስህተቷ በመታረሟ ነገ ከራሷ አልፋ ለቤተሰቧና ለህብረተሰቡ የተሻለ መልካም ነገር የምታደርግ መሆኗንም በራስ በመተማመን መንፈስ ታወሳለች። ስለዚህም በየዓመቱ የሚለጠፈውን የይቅርታ ዝርዝር በጉጉት እንደሚጠብቁ ሴት ታራሚዎች በጉጉት መጠበቋን አላናግር ብሎ የሚተናነቃት እንባ ከዓይኖቿ በመፍለቅ በጉንጯ ላይ እየተዝረከረከ ትገልፃለች።
‹‹ቢሆንም ከዓመት ዓመት ይቅርታ ባለማግኘታችን እናትም አባትም ሆኖ ከነልጆቻችን በቀን ሶስቴ የሚቀልበንን ማረሚያ ቤት ተጠያቂ አናደርግም›› ትላለች። እንደምትለው ማረሚያ ቤቱ የተሰጠውን ሕግ ነው የሚያስፈፅመው። እንደውም የሕግ አማካሪ ቀጥሮ ሁሉ ይቅርታ ይጠይቅላቸዋል። ይግባኝ ሁሉ እንዲጠይቁም ያደርጋል። ሰብዓዊ መብታቸውን በማክበርና በአያያዝ ረገድም እንከን የለሽ ነው።
ሲታመሙ አስታሞ ሲቸገሩ ተቸግሮ፤ ሲያለቅሱ አብሮ አልቅሶ ሲደሰቱ ተደስቶ አውድ ዓመትን በደስታ እንዲያሳልፉ በጀት መድቦ ይንከባከባቸዋል። ለነሱ ይቅርታ በመጠየቁ ጉዳይ ማረሚያ ቤት ምንም ማድረግ አይችልም።
‹‹ሴት ልጅ እንደወንድ አይደለችም ብዙ ችግሮች አሉባት›› የምትለው ሣራ አራት ልጆችና ቤተሰብ እንዳላት ከቅጣቷ አብዛኛውን በመፈፀሟ መንግስት ይሄን ከግንዛቤ በማግባት ከሕግ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለእሷና ለሌሎች ሴት ታራሚዎች ምህረት እንዲያደርግ በዐውድ ዓመት ስም ትጠይቃለች።
የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መጋዘን ቁልፍ በእጇ ሆኖ በመዘረፉ በከባድ ዕምነት ማጉደል ምክንያት ነው ከአንድ ባልደረባዋ ጋር ተፈርዶባት ወደ ማረሚያ ቤቱ የገባችው። ቆይታዋና የዐውድ አመት ክብር ሰው መሆን ምንድነው፤ ሕይወት ምንድነው የሚለውን እንድትማር አስችሏታል።‹‹ ስወጣ አይደለም እኔ ቤተሰቤን መላው ማህበረሰብ ሁሉ ማስተማር እችላለሁ›› የመንግስት ጠበቃ ሲከራከርላት መቆየቱንና ቁልፍ ስለያዘች ተጠያቂ መሆኗን ደጋግማ የምታወሳው ታራሚዋ ለበዓላት እኛ ያየነውን ሞቅ ደመቅ ያለ ዝግጅት ቢያደርጉም እሷን ጨምሮ አብዛኞቹ በተለይም ደግሞ በማረሚያ ቤቱ 3 አራተኛ የእስራት ጊዚያቸውን የፈፀሙ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን ይቅርታ ሲያጡ ደስታቸው በለቅሶ ተለውጦ ዐውድ ዓመቱን በለቅሶ ጭምር የሚያሳልፉበት ጊዜ እንዳለና ሆኖም በየዓመቱ ምህረት ይደረግልናል በሚል በተስፋ እንደሚጠባበቁ አውግታናለች አስናቀች።
የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ቤት አባልና የሴቶችና ህጻናት ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ምክትል ኢንስፔክተር በዛብሽ ማርያም እንደሚሉት በማረሚያ ቤቱ 558 ሴት ታራሚዎች አሉ:: ለአውደ አመት በልዩ በጀት በግና በሬ በማረድ በዓላትን በደስታ እንዲያሳልፉ ይደረጋል ይላሉ።
የሕግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት በማክበርና በማስከበር በኩል የይቅርታ አሰጣጥ ዋና ዓላማ የሕዝብ የመንግስትንና የታራሚዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መንግስት ጥፋተኞች በጥፋታቸው የተፀፀቱና የታረሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ ማድረግ ነው። አመክሮ አንድ የሕግ እስረኛ የእስራት ቅጣት ተወስኖበት ከእስራት ዘመኑ ሁለት ሦስተኛውን እንደፈፀመ የጠባዩ መሻሻል በበቂ ሁኔታ ሲመሰከርለት ከእስር ቤት እንዲፈታ የሚፈቀድበት ሁኔታ ነው። ይህም ሲባል በሕጉ የተወሰነው የአፈፃፀም ጊዜ ሲደርስና ጠቅላላ ሁኔታው ተሟልቶ ሲገኝ ጥፋተኛውን በአመክሮ አስቀድሞ መልቀቅ የሚቻል መሆኑን ያመለክታል። አመክሮ ጠባይ ማሻሻያና ወደ ማህበራዊ ኑሮ መመለሻ መሣሪያ ነው። ከዚህ አኳያ አመክሮ የሚፈቀደው እስረኛው በጠባዩም ሆነ በጠቅላላ ሁኔታው የተሻሻለ መሆኑ ሲታመን ነው። የአመክሮ ጊዜ አንድ የሕግ እስረኛ የተበየነበት ረጅም የእስራት ጊዜ ከማለቁ በፊት ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ከአደገኛ ጥፋትና የወንጀል ድርጊት ተገትቶ የመልካም ስነ ምግባር ተገዢ ሆኖ ይኖር እንደሆነ የሚፈተሽበት ወቅት ነው።
በእስራት የተቀጣን የሕግ እስረኛ በአመክሮ ለመልቀቅ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 207 የሕግ እስረኛው ከተፈረደበት የእስራት ዘመን ሁለት ሦስተኛውን መፈፀሙን፤ እስረኛው በማረሚያ ቤት በነበረበት ጊዜ መልካም ጠባይ ያሳየ በመሆኑ በቂና አጥጋቢ የምስክር ወረቀት ማግኘቱ፤ እስረኛው ከማረሚያ ቤት ሲወጣ ሥራ የሚያስገኝ መሆኑ መረጋገጡ እስረኛው በተቀጣበት የወንጀል ክስ ከባላጋራው ጋር እርቅ መፈፀሙ ይታያል መሰየም ወንጀለኞች ከስር ከተለቀቁ በኋላ መልካም ስማቸውን የሚያስመልሱበት መንገድ ነው።
አንድ ወንጀለኛዋ የቀድሞ መልካም ስሟን የሚያስከብርላትና የጥፋተኛ ስሟ የሚፋቅበት መንገድ ነው። ውጤቶቹም በቀጥታ የነበረችው ሴት ከተሰየመችበት ጊዜ ጀምሮ ተወስኖባት የነበረው የመብት፤ የማዕረግ ወይም የችሎታ ማጣት ቀሪ በማድረግ ሕዝባዊ መብቱን ቤተሰብ የማስተዳደርና የሙያ ሥራ የመሥራት መብቱን እንደገና ለመያዝ ችሎታ የምታገኝበት አግባብ ነው። በተጨማሪም የምትሰየም ሴት ቀድሞ የተላለፈባት ቅጣት ከወንጀለኞች መዝገብ ላይ እንዲፋቅና ወደፊትም እንዳልተፈረደባት እንዲቆጠር ሕጉ ታሳቢ እንደሚያደርግ ይናገራሉ። በመሆኑም በማናቸውም ጊዜ በዚህች ግለሰብ ላይ ያለፈውን ወንጀል አንስቶ መውቀስ ስም ማጥፋትና ሌሎች ድርጊቶችን መፈፀም ክልክል ናቸው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015