ኢትዮጵያ በማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም በሚዳሰሱ የተፈጥሮ ቅርስ፣የስነ ፅሁፍ እና አርኪዮሎጂካል ሃብቶች የታደለች መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህን ሀብቶች ጠብቆና አልምቶ ለትውልድ ማሻገር ይገባል፤ ሀብቶቹን ለዓለም በማስተዋወቅ የገቢ ምንጭ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የማሳደግ ሥራዎችም ጎን ለጎን መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡
ከታህሳስ ወር 2015ዓም መጨረሻ ጀምሮ ማሕበራዊ እሴትን በተላበሰ መንፈሳዊ በዓሉ ጎልተው የሚታዩት የእየሱስ ክርስቶስ የልደት (የገና) እና ጥምቀት ክብረ በዓላት ከቱሪዝም መስህብ ሀብቶች መካከል የሚጠቀሱና የቱሪዝም ኢንደስትሪውን በማነቃቃትም የጎላ ሚና ያላቸው መሆናቸው በሚገባ ይታወቃል፡፡ የዓለም ቱሪስቶችን በመሳብ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍ ያለ ድርሻ ሲወጡም ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሚጠበቀው ልክ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንዳልተቻለ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠውና በከፍተኛ ዝግጅት፣ በደማቅ ስነስርአት በላልይበላ በሚከበረው የገና በአል ከመላው አለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ በስፍራው ይታደማል፡፡ ከመላ ኢትዮጵያም እንዲሁ እጅግ በርካታ ህዝብ ይገኛል፡፡ በየአመቱ ከሚታደመው ቱሪስትም በሚገኘው ገቢም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጀምሮ የሀገር ኢኮኖሚ ይነቃቃል፡፡ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በሀገር ምጣኔ ሀብት ላይም የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ታህሳስ 29ቀን2015ዓም በላልይበላ በተከበረው የገና በአል እስከ አንድ ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝብ ተገኝቷል። ይሄ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ታላቅ ብስራት ነው። ከቀናት በፊት በተከበረው የጥምቀት በአል ደግሞ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ፣ በኢራንቡቲ፣ በዝዋይ (ባቱ) አያሌ የአገር ውስጥና የውጪ አገራት ቱሪስቶች ታድመውበታል።
ከዚህ መረዳት የምንችለው በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በአል ስነስርዓት ጨምሮ መሰል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሃብቶች ላይ ከተሰራ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው።
ዶክተር አያሌው ሲሳይ የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በዩኒስኮ የተመዘገቡ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ ሃብቶችን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማነቃቂያና ለእድገቱ መሰረት መጠቀም ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያው እንደሚያስረዱት፤ የአደባባይ በዓላት ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም አላቸው። የጥምቀት በዓልም ወደ ኢትዮጵያ ቱሪስትን ለመሳብ የምንጠቀምበት አንዱና ዋነኛው የአደባባይ በዓል ነው። ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የጥምቀት በዓል አከባበርን ከመታደም ባለፈ በአካባቢው ያለውን ባህልና ቅርስ እንዲጎበኙ ያደርጋል ብለዋል። ቱሪስቶቹ ለሚጠቀሙበት የተለያዩ አገልግሎቶች የሚፈጽሙት የተለያዩ ክፍያም የሀገር የኢኮኖሚ እድገት እንዲፋጠን እንደሚያስችል አመልክተዋል።እንዲህ ያለውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በየዘርፉ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ትህትናን የተላበሰ አገልግሎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
“በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ከኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ ሆቴሎች ሥራቸው ተቀዛቅዟል፡፡ አየር መንገድ እንግዳ አጥቷል፡፡ በመሆኑም በየአመቱ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣ የነበረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል” ያሉት ዶክተር አያሌው፤ አሁን ኢትዮጵያ ሰላም በመሆኗ ክብረ በዓሉ የቱሪዝም ዘርፉንና የሀገር ኢኮኖሚን እንደሚያሳድግ ተናግረዋል። ቱሪስቶች የጥምቀት በዓልን ለማክበር ሲመጡ አንደኛ የአደባባይ በዓሉ እንደሚታደሙና ሌሎች መስህቦችንም እንደሚጎበኙ ገልፀዋል። በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገኛል ብለዋል። የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል ተብሎ ዝም መባል እንደሌለበትና ለኢኮኖሚ እድገት የማስተዋወቅና ቱሪስቶች በአካባቢው እንዲቆዩ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል።
ዶክተር ደስታ ሎሬንሶ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በዓደባባይ ተከብሮ ያለፈው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ በዋነኝነት እንዳለ ሆኖ “የባህል ቱሪዝም” የሚንፀባረቅበት ዓለም አቀፍ ቅርስ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ማራኪ ትእይንቶች የሚስተዋልበት ትልቅ “ፌስቲቫል” እንደሆነ ይገልፃሉ።
“ጥምቀትን የመሰሉ የአደባባይ ባአሎች የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ ቱሪስቶችን ይስባሉ” የሚሉት ዶክተር ደስታ ሎሬንሶ፤ በተለይ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ፣ ክዋኔው፣ አለባበስ፣ ዝማሬውና ሌሎች መሰል መሰናዶዎች ለጎብኚዎች ማራኪ ገፅታን የሚያላብሱ ከመሆናቸውም በላይ አዲስ እውቀት እና ልምድን እንዲያገኙ እድል እንደሚሰጡ ይናገራሉ።
ከዚያ ባለፈ ይህ ብዝሃ ትእይንት ራሱን ችሎ “ኢትዮጵያዊ መልክ” ሆኖ እንደሚታይ ይገልፃሉ። በተለይ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ይህን መሰል ሃይማኖታዊ ስርዓት፣ ባህል እና ደማቅ የአደባባይ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ እንጂ በሌላ ቦታ እንደማያገኙ ይገልፃሉ። ይህም በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ ከማገዙም በላይ ኢንዱስትሪው እንዲያድግ መሰረት እንደሚሆን ይገልጻሉ።
“ጥምቀትን በመሳሰሉ ክብረ በዓላት ላይ ቱሪስቶች ሲታደሙ ምጣኔ ሃብቱ ይነቃቃል” የሚሉት ዶክተር ደስታ፣ ጎብኚዎች ሆቴሎችን በመጠቀም፣ የባህል አልባሳትና ቁሳቁስን፣ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦችን በመገብየትና ሌሎች ወጪዎችን በማውጣት የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት እንዲነቃቃ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎች፣ የትራንስፖርት ዘርፍ ይህን እድል እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው በሰፊው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ እንደሆነ ያስረዳሉ። የዘንድሮው የጥምቀት በአል በአገሪቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች በድምቀት ተከብሮ ከማለፉ ባሻገር፤ የአፍሪካ መዲና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በድምቀት መከበሩ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ልዩ አስተዋፆ አለው የሚሉት ዶክተር ደስታ፣ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ለሆነው ጥምቀት እንዲሁም ይህንን ለመመልከት ከውጪ አገራት ለሚመጡ ቱሪስቶች ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በነበረው የሰላም መደፍስ የቱሪዝም ዘርፉ ድብታ ወስጥ ግብቶ ነበር። ይህም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ሚና ነበረው። ዶክተር ደስታ አሁን ላይ የሰላም ስምምነት መደረጉና ገናንና ጥምቀትን የመሳሰሉ በዓላት በልዩ ድምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ በተገኘበት ተከብረው ማለፋቸው እንደ ስኬት ሊቆጠር ይገባል ይላሉ።
ምክንያቱም የውጪ አገራት ቱሪስቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰራተኞች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያ ሰላም እንደሆነችና ድንቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሃብት ያለባት አገር እንደሆነች ምስክርነታቸው ይሰጣሉ ይላሉ። ይህ ደግሞ የአገሪቱን መልካም ገፅታ አንደሚገነባና የቱሪዝም ዘርፍ እንደሚያነቃቃ ያስረዳሉ።
ዶክተር ደስታ ከዚህ በኋላ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ጥምቀትን የሃይማኖት፣ የባህልና ፌስቲቫል ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና የከተማዋ ግዙፍ የቱሪዝም ሃብት ምልክት ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። አስጎብኚዎች፣ የሆቴልና መስተንግዶ ዘርፍ ባለሃብቶች የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎችም ጎብኚዎች የሚፈጥሩትን የገበያ እድል ተጠቅመው የስራ እድል ለመፍጠርና ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሙን ለማጉላት በቅንጅት እንዲሚሰራ ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቱሪዝም ሚኒስቴር በሰራው ስራ ባሳለፍነው ዓመት “ገናን በላልበላ” በተመሳሳይ ተከብሮ ነበር። ሆኖም ግን በነበረው የፀጥታ ችግርና ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ ያልነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ተፅእኖን ተከትሎ ብዙ ጎብኚዎችና የሃይማኖቱ ተከታዮች ወደ ስፍራው እንዳይጓዙ አድርጎ ነበር። በዚህ ተፅእኖ ውስጥ ስለነበር ብዙ አመርቂ አልነበረም።
የዘንድሮው ግን በጣም በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። በርካታ ቱሪስቶች፣ ዲያስፖራዎች እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዓሉን ለማክበር በእግር፣ በትራንስፖርትና በአየር ትራንስፖርት ጭምር በመጠቀም በበዓሉ ታድመዋል፡፡የውጪ ቱሪስቶች በዘንድሮው በዓል ላይ በብዛት ተገኝተዋል። የእነዚህ ጎብኚዎች ቁጥር ከ500 በላይ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል። በዘንድሮው በዓል ለየት ባለ መልኩ ጎብኚዎች ከዚህ ቀደም ግማሽ ቀን ብቻ በስነስርዓቱ ላይ ታድመው የሚሄዱበትን ዝግጅት ወደ ሁለት ቀን ከግማሽ እንዲያራዝሙ ማድረጉንም አስታውቋል። በአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲጎበኙና ከገና አንድ ቀን ቀደም ብለው አንዲመጡ የተለያዩ የመስህብ ሰፍራዎችን እንዲመለከቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡በአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰሩ ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች እና ሌሎች ምርቶችን እንዲሸምቱ እድሉ ሰፊ ነበር።
ኢትዮጵያ ከጥምቀትም ሆነ ከገና በተጨማሪ እጅግ ብዙ የሚያስደንቅ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች አሏት። እነዚህን ግን በተገቢው መንገድ ዓለም ሊያውቃቸው ይገባል። ከውጪ አገራት ቱሪስቶች በተጨማሪም የአገር ውስጥ ጎብኚዎች አገራቸውን ማወቅና የመጎብኘት ባህላቸው ሊያድግ ይገባል። ለዚህ ጥሩ ማሳያና ምሳሌ የሚሆኑት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላትን (ጥምቀት ፣ገና፣ኢሬቻ፣ ጫምባላላ እናሌሎችም) የሚያከብሩ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችና ታዳሚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ነው። ይህን መሰል ባህል መዳበሩ ያለንን ሃብት ለራሳችን ከማወቅ ባሻገር ኢትዮጵያን ብለው የሚመጡ የሌላ አገር ዜጎችን በኩራትና በእውቀት አንድናሳውቅ ስለሚያግዘን ነው። የቱሪዝም መስህባቸውን አሳድገው ከዚያ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ የሆኑ አገራት በገነቡት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የኢንዱስትሪው ተቋማት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዜጎቻቸው ነው የመስህብ ሃብቶቻቸውን የሚያስተዋውቁት። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ እውቅናንና ተርፍን አስገኝቶላቸዋል።
ቱሪዝም በበርካታ የበለፀጉ አገራት ቀዳሚ የምጣኔ ሃብት ምንጭ ነው። ይህንን መንግስታቸው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጎች በቅጡ ተገንዝበውታል። ለምሳሌ ያህል ፈረንሳይ (ፓሪስ)፣ ጣሊያን (ሮም)፣ ግብፅ (ካይሮ)፣ ከቱርክ (ኢስታንቡል) እና ሌሎችም አገራት ከቱሪዝም እጅግ ከፍተኛ ሃብት በማጋበስ የስልጣኔ መንገዳቸውን አልጋ በአልጋ ማድረግ ችለዋል።
ይሁን እንጂ በቀደሙት ዘመናት ሃብቶቻቸውን ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ (ለገበያ ምቹ በማድረግ) ሰፊ ትግል አድርገዋል። በተለይ ታሪካቸውን፣ የቀደመ ስልጣኔን፣ የህንፃ ጥበባቸውን፣ የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን ለሰሚውም ሆነ ለተመልካቹ ምቹና አዝናኝ እንዲሆን አድርገው አሰናድተዋል። በቱሪዝም ሃብቶች ጥበቃና ልማት ዙሪያም እጅግ አስደናቂ ስራዎችን ሰርተዋል። አሁንም ድረስ እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ አያሌ ጎብኚዎችን እንዲያስተናግዱ፣ የአገር መልካም ገፅታ እንዲገነቡ (መልካም ስም ከመልካም ማእዛ ይበልጣል እንዲሉ) አስችሏቸዋል። ከምንም በላይ ግን ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ባለቤት ሆነዋል። በጭስ አልባ ኢንዱስትሪው የማይነጥፍና የማይጎድፍ ሃብትና ስምን ገንብተዋል። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ተግባር እና ጠንካራ ስራ ያስፈልጋል። በተለይ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የቱሪዝም ሚኒስትር እና የዘርፉ ባለሙያዎች በአደባባይ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሃብቶች ላይ ጠንካራ የማስተዋወቅ እና የገበያ ልማት ስራ እየሰሩ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ከዚህም በላይ መጠናከር ይኖርበታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም