ታላቅ ሥራ የሚከወንባት ታላቅ ጥበብ
የሰው ልጅ መፈንቅለ ፈጣሪ ለማድረግና በምድር ላይ ስሙን ለዘላለም ለማስጠራት አስቦ ሰማይ ጠቀስ ሳይሆን እስከሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመገንባት ክተት አዋጅ ጠርቶ በባቢሎን ተሰባሰበ። በዚህ የተነሳ በፈጣሪ ቁጣ ቋንቋው ከመደባለቁ በፊት ምድር ሁሉ የምትግባባው በአንድ ቋንቋ ነበር።
የሰው ልጅ አጉል ላይሳካለት የማይሆን ነገር አስቦ፤ የቆጡን አወርድ ብሎ የጉያውን ካጣ፣ የሰው ልጆች አንዱን ልሳናቸውን በሺህ ከለወጡ በኋላ የጋራ ቋንቋ ይሉት ነገር አከተመ። እናም ምድርን በቅጡ ሳይኖርባት ሰማይ ቤት እሄዳለሁ ብሎ በአልጠግብ ባይነቱ፣ በገዛ ቅሌቱ አንድነቱን ተቀምቶ፣ እርስ በእርሱ አልስማማ ብሎ፣ የናቃት ምድር ላይ በየፊናው ተበትኖ የቀረው የሰው ልጅ ከጋራ ቋንቋው መደበላለቅ በኋላ በተሻለ መንገድ እርስ በእርስ የሚግባባበትን ቋንቋ ፈጠረ። ይችንም ቋንቋ ስሟን ሙዚቃ ብሎ የሰየማት ሲሆን በሰው ልጆች ዘንድ “የዓለም ቋንቋ” እየተባለች ትሞካሻለች።
በእርግጥም ሙዚቃ እንዲህ መሞገሷ ያንስባት እንደሆነ እንጂ አይበዛባትም። እርሷ በሥርዓት በተቀመሩ፣ ጥልቅ ትርጉምን አምቀው በያዙ ኃይለኛ ቃላት ስምረት እና በፍቅር ፈልቀው በውበት በሚፈሱ ጥዑም ዜማ ታጅባ፣ የላይኛውን አካላዊ ዓለም አልፋ፣ ውስጥ ድረስ ዘልቆ፣ መንፈስን የምታድስ፣ ልብን በደስታ የምታረሰርስ ሰዎች ከራሳቸውና ከላይኛው ምንጫቸው ጋር የሚግባቡባት የዓለም ቋንቋ ብቻ ሳትሆን የነፍስ ቋንቋም ናት። ከዚህም ባሻገር ሙዚቃ ተራ የጭፈራ ማድመቂያ ብቻ አይደለችም፤ ትልልቅ ሃሳቦች የሚፈልቁባትና የሚተላለፉበት፣ ለዓለምና ለዘላለም የሚጠቅሙ ወሳኝ ድርጊቶች የሚከወኑባት ዓለማዊውንና መለኮታዊውን ህላዌ አዋህዳ የያዘች ታላቅ ጥበብም ናት። በመሆኑም ከታላቁ የእስራኤል ንጉስ ቅዱስ ዳዊት እስከ ኢትዮጵያዊው ታላቁ የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ ከማርያ ማኬቫ እስከ ቦብ ማርሌ፣ ከማይክል ጃክሰን እስከ ጥላሁን ገሰሰ… የሙዚቃ ጥበብ የታደላቸው ዜመኞች፣ ዘማሪዎች፣ ድምጻውያን በሏቸው ዘፋኞች ሙዚቃን በመጠቀም እንደየ ተሰጥኦዋቸው ዘመን የማይሽራቸው ታላላቅ ገድሎችንና ጀብዶችን ፈጽመውበታል።
በድል መዝሙር የተጀመረ ታላቅ የሙዚቃ ጉዞ “ፋሺስት ኢጣሊያ፣ ኢትዮጵያን ወርራ የቆየችባቸው ዓመታት እና የ1932 ክረምት አልፈው፣ የነጻነት ብሥራት በተሰማበት ዓመት፣ በወሊሶ አውራጃ፣ ጎሮ ወረዳ፣ ሶየማ ቀበሌ፣ “መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ወይዘሮ ጌጤነሽ ጉርሙ ኢተኣ ወንድ ልጅ ተገላገለች” ይላል በአቶ ፈይሣ ኃይሌ ሐሰና ቤኛ ከ1934 ጀምሮ የተከተበው የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ” ይለናል አንጋፋው ጋዜጠኛና “ጥላሁን ገሠሠ፡- የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር” የተሰኘና የታላቁን ሰው የሕይወት ታሪክ በጥልቀት የዳሰሰ ተነባቢ መጽሐፍ ያበረከተልን ዘከርያ መሀመድ።
የታላቁ ሰው የጥላሁን ገሰሰ የሙዚቃ አጀማመርን በተመለከተም እንደሚከተለው ይተርክልናል። “በ1939 ዓ.ም ጥላሁን በቀኛዝማች መኮንን ጥያቄ እና በአቶ ፈይሣ ምክር፣ ወሊሶ ከተማ በሚገኘው ራስ ጎበና ዳጨው ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ። አያቱ ወይዘሮ ነገዬም፣ ለእርሱ ሲሉ በወሊሶ ቤት ተከራይተው መኖር ጀመሩ። …የወላጆቹ እርሱን ጥለው መጥፋት ሳይፈጥርበት እንዳልቀረ ከሚገመተው የመተው፣ ትኩረት የመነፈግ አልያም የብቸኝነት ስሜት ጋር ሲታገል ከመቆዘም ይልቅ ወደ እንጉርጉሮ ያደላ ነበር።
….በራስ ጎበና ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ፣ “ሆያ ሆዬ የሚሉትን በማየት” እና “ጠላታችን ወደቀ፣ ፍፁም ጠፋ ሙሶሎኒ” የምትለዋን መዝሙር በማዳመጥ አጥንቶ ይዘምር ነበር። ይህን ያዩት የትምህርት ቤቱ ዳሬክተር (ሱዳናዊው) ሚስተር ሸዳድ በአድናቆት አበረታቱት። ወንድማቸው ማህሙድ ሳንሁሪም ቤቱ እየወሰደ በሸክላ የተቀረፁ ዘፈኖችን አስደመጠው። የሰማውን በቃሉ ይዞ ማንጎራጎር ሥራው ሆነ። ከሙዚቃ ጋር ተዋወቀ።
ጥላሁን የአምስት ዓመት ሕጻን ሳለ ድንገት የጠፋችው ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ጌጤነሽ ከአምስት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ በመገኘቷ ከእናቱ ጋር ለመገናኘት በ1943 ዓ.ም በአሥር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣም ታሪኩ ያስረዳል። ከእናቱ ጋር ከተገናኘ በኋላ ትምህርቱን ይቀጥል ዘንድ ወሊሶ እንዲመለስ ቢደረግም፣ ልቡ ወደ አዲስ አበባ የሸፈተበት ጥላሁን ከሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ፣ በ1944 ዓ.ም አዲስ አበባ ጠቅልሎ ሊገባ ችሏል።
አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በ1947 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ማኅበር በመቀጠርና የድምጻዊነት ሕይወቱን በይፋ መጀመሩንና በዚያ በቆየባቸው የሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ቆይታው፤ “ጥላ ከለላዬ”፣ “ጽጌረዳ ነሽ”፣ “ደጉ ንጉሥ” እና “ፍቅሬ ሰውነቴ” የተሰኙ ዘፈኖችን በመዝፈን ከሕዝብ ጋር እንደተዋወቀም የሕይወት ታሪኩን በተመለከተ የተጻፉ መዛግብት ያመላክታሉ። የሆነ ሆኖ ሠሪው ሳይኖር ሥራዎቹ ሊኖሩ አይችሉምና ሠሪውን በዚህ መንገድ ካስታወስን የጽሑፋችን ዋነኛ ትኩረት ወደሆኑት የእናት ሀገር ኢትዮጵያ ፍቅርን፣ ክብርንና በልጆቿ ታላቅ ተጋድሎና ጀግንነት በደምና በአጥንት የተገነባ ታላቅ ማንነትን የሚገልጹ የሙዚቃው ንጉስ ህያው ሥራዎች ከብዙ በጥቂቱ፣ ከረጅሙ በአጭሩ በጨረፍታ ወደማስቃኘት እናልፋለን።
ሲጀምር በሀገር፡- ጥላ ከለላየ
ከላይ ስለ ሕይወቱና ሙዚቃ አጀማመሩ ባነሳንበት ላይ እንደገለጽነው ጋሽ ጥላሁን ሕይወቱም ሙዚቃውም የጀመሩት ከሀገር ፍቅርና ህልውና ጋር ተያይዘው ነው። በእብሪት ተነሳስቶ ታላቋን ሀገር ኢትዮጵያን ለመግዛት የመጣው በጀግኖች ኢትዮጵያን ዓድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ፣ አይዋረዱ ውርደት ተዋርዶ፣ ኢትዮጵያን ይበልጥ ዓለም ላይ ከፍ አድርጎ የተመለሰው ፋሺስት ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ለወረራ መጥቶ ክንዳቸው በማይዝለው በአይበገሬዎቹ አባቶቻችን አስደናቂ ተጋድሎ በድጋሚ ድል ተነስቶ የነጻነት ብሥራት ሲሰማ ጥላሁን ተወለደ። የድል ዜማዎችን እየዘመረ አደገ። የሙዚቀኝነት ሥራውን ደግሞ በአዲስ አበባ ከነ ስሙም በሀገር ፍቅር ማህበር በይፋ ጀመረ። እናም በሀገር ፍቅር ማህበር በቆየባቸው የሁለት ዓመት ተኩል ገደማ የመጀመሪያ የሙዚቃ ሥራዎች መካከል “ጥላ ከለላዬ” በሚል ስለ ሀገሩ ያዜመው ዜማ ዘመን ከማይሽራቸው የንጉሱ ሥራዎች መካከል አንዱ ሆነለት።
“ለውዲቷ ለእናት ኢትዮጵያ ታጥቄ ጠንክሬ
የምሰዋላት ነኝ እኔስ ለሀገሬ
ጠላቶቿን እቃወማለሁ አጥብቄ በብርቱ
ስለ ሀገር ፍቅር ገባኝ በእውነቱ
አያት ቅድመ አያቴ ተወለዱብሽ
እምዬ እናት አገር ለእኔም ሀገሬ ነሽ
ኑሬ በነጻነት ኮርተሽ” አላት።
በሀገር ፍቅር ማኅበር “ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ”ን በመጫወት በይፋ የተጀመረው የጥላሁን ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ ሆኖ በሕዝብ ውስጥ የኖረው ጥላሁን፣ ሀገሩ ኢትዮጵያን የወላጆቹ ምትክ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ደግሞ ወንድምና እህቶቹ አድርጎ የሚያስብ፣ “የእኔ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” የሚል ልባዊ እምነቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚናገር ሰው ነበር። የጥበብ ሕይወቱን ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ አሟሽቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ ኖሮ፣ ስለ ኢትዮጵያ የዘመረ ውብ ድምፁን፣ ጣፋጭ ቅላፄውን፣ አቻ ያልተገኘለት የመድረክ አቀራረብ ጥበቡን አሻራ፣ እንዲሁም ልዩ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅሩን አውርሶ የሄደው ጥላሁን ገሠሠ፣ በድምፁ ሐውልቱን የተከለ ታላቅ ከያኒ ነበር።
የሀገር ጠላትን ከወታደር እኩል የሚዋጉት የንጉሱ ዘፈኖች
መቼም ይች ታላቅና ባለ ብዙ አኩሪ ታሪክ አገር አልሆንለት እያለ እንጂ ከከፍታዋ ሊያወርዳት ክብሯን ሊያዋርዳት ያልሞከረ የለም። ከእነዚህ ልክ አያውቄ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች አንዱ ደግሞ አላዋቂነትና ትዕቢት ልቡን አሳብጦት በከ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ የፈጸመው፤ የዚያድ ባሬ ወራሪ በማያስደፍሩት የእሳት አጥሮቹ የኢትዮጵያ ጀግኖች ልኩን ቀምሶ አፍሮ ተመልሷል። ታዲያ በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን የጥላሁን ድምጾች በመከራ፣ በጦርነት ጊዜም ይዘፍናሉ። ዜማና ግጥሞቹ የሚዘፈኑት ታዲያ በመከራ ጊዜ ስለሆነ “እንደ ማሽላ ሳር እስቃለሁ” እያሉ አይደለም፤ እሳት ነበልባል ሆነው ጠላትን እያቃጠሉ፣ ጠላትን እያሳረሩ፣ የወገንን ልብ ደግሞ በፍቅር እያቃጠሉ ሞራልና ጀግንነቱን እያቀጣጠሉ ነው የሚዘፈኑት። እስኪ በዚያድባሬ ወራሪ ላይ ተተኩሰው፣ ከጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆችና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተባብረው የጠላትን ጦርና ሥነ ልቦና እስከወዲያኛው ካንኮታኮቱ የጥላሁን እሳተ ነበልባል ኃያል ስንኞች መካከል “ዘማች ነኝ እኔም ለሀገሬ” ከሚለው ዜማ ላይ የተወሰዱትን እንመልከት፡-
የመጣው ቢመጣ ምን ጦር ቢነቀነቅ
ከሀገሬ ድንበር ላይ ነኝ የማልል ንቅንቅ
ምንም ስለሌለኝ የሚበልጥ ከሀገሬ
ቢሰጥ ደስ ይለኛል ሥጋዬ እንኳን ላውሬ
ዘማች ነኝ ቆራጥ እኔም ለሀገሬ
አልሻም ተደፍራ ለማየት ድንበሬ…
ዳገት ቁልቁለቱን ወጥቼ ወርጄ
የመደብ ጠላቴን አጋድሜ አርጄ
የእናቴን ነጻነት ስሟን አስጠርቼ
ብሞት ደስ ይለኛል እኔም ለሀገሬ
ታዲያ ይሄ የጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች የእሳት ክንድ ሲጨመርበት በእርግጥስ ጠላትን አቃጥሎ አመድ አድርጎ የእናት ኢትዮጵያን ክብር ከፍ ከማድረግ በቀር ሌላ ያስመኛልን? የሆነውም እንደዛ ነው! በዚህ መንፈስ የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ከተጫወታቸው ሀገራዊ ዘፈኖች ውስጥ በ1969 የተጫወተው “አጥንቴም ይከስከስ” እንዲሁም በ1979 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርፆ ለሕዝብ የቀረበው “ቃል ኪዳን” የተሰኘው ግጥሙ በሻምበል ክፍሌ አቦቸር የተጻፉ ዘፈኖችም ሁሌም የማይረሱ የሀገር ዘብ የሆኑ የጥበብ ውጤቶች ናቸው። “ቃል ኪዳን” የተሰኘው የታላቁ የሙዚቃ ጥበበኛ ዜማ ከሀገር ቤት አልፎም ዘፈኑ ባሕር ማዶ ለሚኖሩ ወገኖች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ “የእናት ሀገር ጥሪ” የቀረበበት ህያው ሥራ እንደሆነም ይነገራል።
ዛሬም እነዚህ ህያው የጥበብ ጥይቶች ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት በገጠማት ፈተና ወቅት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለመላ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የስነልቦና ስንቅ ሆነው ታይተዋል። በኢትዮጵያ ፍቅር ሕይወትን በፍቅርና በድል፣ የሙዚቃን ጥበብም በሀገሩ ፍቅር “ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ” ብሎ የጀመረው ታላቁ ጥላሁን ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረውን ረጅሙን የሙዚቃ ሕይወቱን የደመደመውም “ቆሜ ልመርቅሽ” በተሰኘ በግሩም ሁኔታ ኢትዮጵያ የገጠማትን የፈተና ጊዜ ቀድሞ የተነበየና የኢትዮጵያን ትንሳኤ በሚመኝ የፍቅር አልበም ነው።
ትንቢትሽ ሲፈጸም ከመሬት ጠብ አይበል
ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ገድልሽ ይነበልበል
ሰንደቅሽ ከፍ ይበል ይቁም ለዘላለም
ሰላም ፍቅር ደስታ
ይታይብሽ በዓለም
ሴራው ይክሸፍበት
የመጣብሽ አድማ
እጁን ሳር ያድርገው
ጉልበቱን ቄጤማ
ካቀባበለብሽ
ብረት ከደገነ
አምላክ ያግዝልሽ
ላንች እየወገነ
አሜን እማማ!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም