እመጫት ናት፤ ለያውም አንድ ሳምንት ላይ ያለች። ሆኖም የምትሰራው ካገኘች ወደ ኋላ አትልም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ያጠራቀመችው ቤሳ ቤስቲን የሌላት መሆኑ፤ የሚያርሳትና ጎዶሎዋን የሚሞላላት ወገን፤ ዘመድ አለመኖሩ ነው። ስለዚህም መታረስን እያማራትም ቢሆን ጥላው ወደ ስራ ማቅናት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የእለት ጉርሷ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው።
ዮርዲኖስ አሰፋ እንደዛሬው ወልዳ በቤት ሳትቀመጥ ሰው ቤት በተመላላሽ ሰራተኛነት ታገለግል ነበር። በዚህም ለእርሷም ሆነ ለልጇ ጉሮሮ አንሳ አታውቅም። ባለቤቷ ትቷት ሲሄድ ግን ነገሮች ለጊዜው ጨለሙባት። የምታደርገውም ግራ ገባት። ብዙ ነገሮችም ከበዷት። ሆኖም ዝም ብላ ግን አልተቀመጠችም። ህመሟን ቻል አድርጋ ጎንበስ ቀና ማለቱን ተያያዘችው እንጂ። ለመብላት መሥራት፣ ልጇንና እርሷን ለማኖር መፍጋት ግድ ነውና ያለምንም ምርጫ ያገኘችውን ትሰራም ነበር።
ነብሰጡር ሆኖ፣ ማልዶ ወጥቶ ምሽት ላይ ወደቤት መመለስ እጅግ ፈታኝ የሆነባት ዮርዲኖስ፤ ልጇን አዝላ ጭምር ነበር ሥራ የምትሄደውም፤ የምትሰራውም። አንዳንዴ ልብስ እያጠበች በምትቆይበት ጊዜ ከጀርባዋ አውርዳው እንዲጫወት ታደርገዋለች። ይህ ግን የባሰውን መከራ የሚያበላት ነበር። ምክንያቱም ሳታስበው ከስሯ ጠፍቶ ይሄዳል። እናም እርሱን በመፈለግ ጊዜዋን ታጠፋለች። የዚህን ጊዜ አሰሪዎቿም ይናደዱባታል።
‹‹ኑሮው ጠብ ሳይል በዚህ አይነት ፈተና ውስጥ ራስን ማኖር እጅግ ከባድ ነው። ነገር ግን ምርጫ ሳይኖር ምን ማድረግ ይቻላል›› የምትለው ዮርዲኖስ፤ ፈተና ቢኖረውም ትናንትን ታግላ አሸንፈዋለች። ዛሬን ግን ልትቋቋመው በምትችለው ደረጃ ላይ አይደለችም። የብዙዎች እጅ ካልተዘረጋላት ጊዜውን ማለፍ ከብዷታል። ምክንያቱም ዛሬ ከእርሷና ከልጇ ሌላ አዲስ ነፍስ ተጨምሯል። ለያውም ብዙ ነገር የሚያስፈልገው። እንደ አገራችን ባህል፣ ወግና ልማድ መሰረት እስካሁን ለአራሷ የተደረገላት እንክብካቤ ባይኖርም የምታጠባ ነችና እንክብካቤ ሊደረግላት ግድ ነው። ግን ማን ያድርገው ነው ጥያቄው? መተጋገዝን ሀሳባቸው ያደረጉ ባህላችንን ዳግመኛ ለማለምለም የተነሱት ድንቅ የኢትዮጵያ ልጆች ይህንን ከሚያደርጉት መካከል ናቸው። ስማቸው “የኢትዮጵያ ልጆች የእርስ በእርስ መተጋገዝ ማህበር” ይባላል። ቀደምት እናቶቻችንና አባቶቻችንን ያስታውሱናል። “በምን?” ከተባለ፣ በʿርስ በʾርስ መተጋገዝ ሲሆን፤ ወደ ጎዳና ለመውጣት ጫፍ የደረሱ ሰዎችን በማገዝ ይታወቃሉ። እንዴት ከተባለ ደግሞ ፈቃደኞችን በመሰብሰብና ድጋፋቸውን በቀጥታ ለችግረኞች እንዲሰጡ በማድረግ ነው። ለአብነት “አምስት ዳቦ ለአንድ ቤተሰብ” በሚል የጀመሩት ፕሮጀክት ከ75 ቤተሰብ በላይ ተጠቃሚ ያደርጋሉ። ይህ ሲሆንም ወረዳው የመለመለላቸውን ሰው ከዳቦ ቤት ባለቤቶች ጋር በማስተሳሰር በቀን አምስት ዳቦ እንዲወስዱ በማድረግ ነው።
ከዚህ ዳቦ ጠቀሜታ አንጻር ባለታሪካችን ዮርዲኖስ የምትለው ነገር አላት። ‹‹ልጄ ሦስት ዓመት የሞላው በቅርቡ ነው። እናም ትምህርት ቤት አልገባም። ስለዚህም ከእግሬ ስር ስለማይጠፋ በራበው ቁጥር ዳቦ ይለኛል። እናም ብዙ ጊዜ አስር ብር ይዤ ሸገር ዳቦ እሰለፋለሁ። ይሁንና ሳላገኝ የምመለስበት ቀን ብዙ ነው። የዚህን ጊዜ ለልጄ ምን መመለስ እንዳለብኝ ግራ ይገባኛል። ልጄ ሲያለቅስ እንባውን መጥረግ እንኳን አልችልም። ስለዚህም ሁልጊዜ እድሌን አማርረዋለሁ፤ አለቅስም ነበር።
”ፍሰጡር ስሆን ደግሞ ብዙ ልብስ በአጠብኩ ጊዜ በጣም ይርበኛል። ማንንም ስጡኝ ስለማልል እየራበኝ ሥራውን አጠናቅቃለሁ። ከዚያም የሚብሰው ቤት ልግባ እንጂ የምቀምሰው ነገር ስለማይኖር በድካሜ የተነሳ ምግብ ማዘጋጀት አልችልም። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ አቅቶኝ እንድወድቅ አድርጎኛል። እናም የነበርኩበት ስቃይ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። አሁን ግን ሁሉ ነገር ተቀይሯል። በእነርሱ እገዛ ልጄም ማልቀስ አቁሟል። እኔም ብሆን ረሀቤን አስታግሼ እንደልቤ ቤቴ ገብቼ ምግብ በማዘጋጀት ልጄንም እኔንም ስመግብ ቆይቻለሁ። ዳቦውን በመስጠታቸው መጀመሪያ የልጄን እንባ ጠረግሁ። በመቀጠል ደግሞ መንገድ ላይ ሲርበኝ እየተመገብሁ ረሀቤን ገታሁ። ቤት ስገባም ብርታት ስለሚሰጠኝ ድካሜን እንድረሳ ሆንኩ።›› ትላለች የበጎ አድራጎት ማህበሩን ሥራ ሰብዓዊነት ስታስረዳ።
ዮርዲኖስ ቀጣይ ሕልሟ በቅርቡ ተነስታ ሥራዋን መጀመር ሲሆን፤ የተሻለ ሥራ ሰርታ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መትረፍ ነው። በተለይም በጎ አድራጎት ማህበሩ ሌሎችን ሲያግዝ በተለያየ መልኩ ስለሆነ እንደ እነርሱ ከእርሷ ላነሱ ሰዎች መድረስ ትፈልጋለች። ከእነርሱ እርዳታ እራሷን አውጥታ በምትችለው ሁሉ እነርሱን ለመምሰልም ታልማለች። ምክንያቱም በእርሷ እምነት ሰው ሰውን የሚያግዘው ስላለው ብቻ አይደለም። ʻከአለው ነገር ሲያካፍልና እርስ በእርስ ሲተጋገዝ ተረዳዳ እንለዋለን’ የሚል አቋም አላት።
ሌላው ባለታሪካችን አይነስውሩ አቶ ሸዋንግዛው በሻህውረድ ሲሆኑ፤ አራት ልጆቻቸውን ያለ እናት የሚያሳድጉና የሚያስተምሩ ናቸው። ቀደም ብሎ እንደዛሬው አይነስውር ሳይሆኑ የሬሳ ሳጥን በመስራትና በመሸጥ ይተዳደሩ ነበር። የአበባ ሥራም በእጅጉ ይችላሉ። እናም ደስተኛ ሆነው ዓመታትን አሳልፈዋል። ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ግን አንድ ትልቅ አሳዛኝ ነገር ገጠማቸው። መከታና ተንከባካቢ፣ ጧሪና ቀባሪ ትሆነኛለች የሚሏትን የበኩር ልጃቸውን በሞት ተነጠቁ። በዚህም እጅጉን አዘኑ። ጠዋት ማታም እዬዬ ሆነ ሥራቸው። ነገሮች ሁሉ ተስፋ እያስቆረጧቸው ሥራቸውን በአግባቡ እማያከናውኑበት ደረጃ ላይ ደረሱ።
ይህ ከባድ ሀዘን ደግሞ ተደራራቢ መዘዝ ይዞባቸው መጣ። “መሥሪያዬ …” የሚሉትን መሪና የፈለጉት ቦታ ላይ የሚያደርሳቸውን ዓይናቸውን አሳጣቸው። በአጠራቀሙት ገንዘብ ያልሞከሩት ህክምና አልነበረም። ዓይንዎት ጉዳት ደርሶበታል ተብለው ከዓይን ባንክ ወጥቶ ሌላ ዓይን እስኪተከል ድረስ ደርሰዋል። ነገር ግን ይህም ሆኖ የጠበቁት አልተገኘም። የተተከለው ዓይን ለተወሰነ ጊዜ ብርሃን ሆናቸው እንጂ አልዘለቀም። የባሰ ትንሹን ብርሃን ጨምሮ አጠፋው። በእርግጥ እዚህ ላይ አንድ ነገር ያነሳሉ። ከብራቸውም፤ ከዓይናቸውም እንዳይሆኑ ያደረጋቸው የሐኪሙ ሁኔታ እንደሆነ ያምናሉ። ምክንያቱም ሌሎች ዓይናቸው የተቀየረላቸው ሰዎች ዛሬ ድረስ እያዩ ነው። እናም በእድላቸው እንጂ በህክምናው አያማርሩም።
አቶ ሸዋንግዛው በደረሰባቸው የጤና ችግር ምክንያት ልጆቻቸውን ሰርተው መመገብ እንዳይችሉ ሆነዋል። አሁን በዳበሳ ነው ሁሉን ነገር የሚያከናውኑት። ከሰል ለማቀጣጠል እንኳን ጎረቤት ለምነው ነው። ከዚያ የልጆቻቸውን ዓይን ዓይናቸው አድርገው ምግብ ያበስላሉ። ጠዋት ቀስቅሰው ትምህርት ቤት ከላኳቸው በኋላም ማታም እንደተለመደው ይቀበሏቸዋል። እንደውም መንግስት ጠዋትና ማታ ባይመግብላቸው ኖሮ ሁሉ ነገር እንደሚጨልምባቸው ያነሳሉ። እርሳቸው ማታ ለእራት ብቻ ያበስላሉ። የኢትዮጵያ ልጆች የእርስ በእርስ መተጋገዝ በጎ አድራጎት ማህበር እጅ ባይታከልበት ደግሞ ይህም አይሳካም ነበር።
ማህበሩ ከችግሮቻቸው ቅድሚያ የሰጠው ለቤታቸው ጉዳይ ሲሆን፤ ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ጋር በማስተሳሰር ቤታቸው እንዲሰራላቸው አድርጓል። ከዚያ ደግሞ የቤት ውስጥ አስቤዛ ያቀርብላቸዋል። በዚህም ‹‹የልጆቼ እናት ነው›› ይሉታል የማህበሩን ሥራ ሲያስረዱ። በተለይም ከቤታቸው መታደስ ጋር ተያይዞ ‹‹ቤቱ ጎርፍ ነበር፤ አራቱም ልጆቼ በአንድ ላይ ተኝተው ሁልጊዜ ያበሰብሳቸዋል። በዳበሳ ሳያቸው እንደረጠቡ ነው። ብዙ ጊዜ ቅዝቃዜው የበረታ ስለሚሆን ሳል አያስተኛቸውም። እናም በአይነስውርነት አቅሜ ጸድቷል፣ አልጸዳም ሳልል አጥቤ አደርቃለሁ። አንዳንዴ ዝናቡ ሲበረታና ልብሱ መድረቅ እንደማይችል ሳምን ጨምቄ አለብሳቸዋለሁ። በተለይ ክረምት ለእኔም ሆነ ለልጆቼ የፈተና ጊዜ ሆኖ ያልፋል። ማህበሩ ከሰራልኝ በኋላ ግን ሁለት ሁለት ሆነው ዝናብ ጠብ ሳይልባቸው እንቅልፋቸውን ይተኛሉ። አሁን ደስተኛ ሆነው፣ እኔንም ወደ ማገዝ ገብተውልኛል። ስለዚህም እነዚህን በጎ ሰሪዎች አምላክ ያብዛልን እያልኩ ሁሌ እመርቃለሁ።›› ይላሉ።
አቶ ነፃነት ጣሰው የኢትዮጵያ ልጆች የእርስ በርስ መተጋገዝ በጎ አድራጎት ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው። ማህበሩ በከፋ የድህነት ችግር ውስጥ ያሉ ወላጆችን ለልመና ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት ተረባርቦ ማገዝ የኢትዮጵያዊያን ባህል ነው። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ይህን ባህል የሚሸረሽሩ በርካታ ነገሮች በመታየት ላይ ናቸው። ማገዝ በበዓል ብቻ እስኪመስል ድረስ ብዙዎች ተግባራቸውን ወደዚያ አዙረዋል። ይህ ደግሞ እየጨመረ ያለውን የከፋ የድህነት ችግር በቀላሉ መቅረፍ አያስችልም። እናም “ማህበሩ የሰው ልጅ የሚመገበው ቀን በቀን በመሆኑ እገዛውም ቀን በቀን መሆን አለበት” የሚለውን አላማው አድርጎ እንደተነሳ ይናገራሉ።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወደ ጎዳና ለልመና እየወጣ ያለው የወላጆች፣ የአረጋዊያንና የሕፃናት ቁጥር እንደ አገር አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል። ነገር ግን ከዚህ ችግራቸው ሊያወጣ የሚችል ሥራ በተለያዩ አካላት እየተሰራ ቢሆንም ለውጡ ግን እጅግ አዝጋሚ ነው። ምክንያቱም ጎዳና የወጡ ሰዎች ልምዳቸውን በቀላሉ አይተውምና መደላደሎች ቢኖሩም ተመልሰው ይወጣሉ። ስለሆነም ማህበሩ የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት አምኖ ወደ ተግባር ገብቷል። ከተግባራቱም አንዱ በሕግ የተመራ የጎዳና ልመናን ክልከላ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው በከፋ ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ጎዳና ሳይወጡ በአሉበት ማገዝና እንዲለወጡ ማስቻል ነው። የእርስ በእርስ መተጋገዙ ደግሞ ይህንን በብዙ መንገድ ውጤታማ ያደርገዋል።
የእርስ በእርስ መተጋገዝ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ አይደለም። ባህልም፣ ሃይማኖትም፣ እሴትም ነው። ስለዚህም ለዘመናት ሲከውኑትና ሲኖሩት የቆዩት ነገር ነው። ያ ነገራቸው ደግሞ ዛሬ ድረስ መኖሩን የሚያሳዩን በርካታ ተግባራት ያሉ ሲሆን፣ አንዱም አግዙ፣ እርዱ ሲባሉ ካላቸው ላይ መስጠታቸው ነው። ይሁንና አስተዋሽ ግን እንዲፈልጉ ሆነዋል። ምክንያቱም የእኛ ያልሆኑ ባህሎች ተቀላቅለውናልና ነው። ዛሬ “የ(ለ)እኔ ብቻ” በሚል አስተሳሰብ ውስጥ ያለ ሰው ተበራክቷል። ሆኖም “… ጭራሽ ጠፍቷል” ማለት አይቻልምና ማህበሩ አስተዋሽ፣ አስተሳሳሪ በመሆን ተግባሩን ለመከወን ወስኗል። እያደረገውም ይገኛል ብለውናል።
የማህበሩ ሥራ ድርጅቶችን፣ አከፋፋዮችንና ባለሀብቶችን ከችግርተኞቹ ጋር በማስተሳሰር ሕይወታቸውን በዘላቂነት መለወጥ ነው። ምንም አይነት የውጪ ድጋፍን አያስተናግድም። ‹‹የአገር ልጅ የማር ጠጅ›› የሚለው መርህ ይከተላል። ዋና አላማውም ለወገኖቹ ደራሽ ወገን መሆኑን ማሳየት ነው። በተለይም የእርስ በእርስ መተጋገዝ ባህልን ማጠናከርና የአገራችንን ችግር በጋራ መፍታትን ላይ ያተኩራል። ለዚህ ደግሞ በእየለቱ የሚሰራ ሥራ መኖር አለበት። ሥራው ደግሞ ከተናጠል ይልቅ በጋራ ቢተገበር ይጠቅማልና ማህበሩ ይህንን እየተገበረ ነው።
ወላጆች፣ አረጋዊያንና ህፃናት ለጎዳና ላይ ልመና ሲዳረጉ አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ፆታዊ ጥቃት ይዳረጋሉ። ይህንን ማህበራዊ ችግር በጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ ድጋፍና እገዛ ማድረግ ካልቻልን አደጋው እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም የከፋ ይሆናል። በመሆኑም ህብረታችን በእርስ በእርስ መተጋገዛችን መታየት አለበት የሚሉት አቶ ነጻነት፤ ማህበሩ ዓመት እንኳን ያልሞላው መሆኑንም ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ሰዓት በ“አምስት ዳቦ ለአንድ ቤተሰብ” ፕሮጀክት ክፍለ ከተማው መልምሎ በሰጣቸው መሰረት ማህበሩ 75 የቤተሰብ አባላትን ያግዛል። ከዚህም ባሻገር 10 የክልል ከተሞች ላይ ‹‹የጎዳና ላይ ልመና ይቁም፤ የሕግ ክልከላ ይኑረው፤ የማህበራዊ ኤጀንሲ ፈንድ ተቋቁሞ የተቸገሩ ሰዎች በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ይግቡ›› በሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በህብረት በመስራትም ጥናቱ በደንብ እንዲዳብር የተለያዩ ሀሳቦችን እያሰባሰበ ይገኛሉ። በቅርቡም የጥናቱን ውጤት ይፋ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ልጆች የእርስ በርስ መተጋገዝ በጎ አድራጎት ማህበር በ15 ሰዎች የተጀመረ ሲሆን፤ አሁን የተለያዩ የእምነት አባቶችን፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላትን በበላይ ጠባቂነት አስቀምጦ ከአራት ሺህ የሚበልጡ አባላትን አሳትፎ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ በኋላም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አባሉ አድርጎ እንደሚቀጥል ተገልጿል። ምክንያቱም የእርስ በእርስ መተጋገዝ ገንዘብን ብቻ ሳይሆን እውቀትንና ጉልበትን ያካትታል። በመሆኑም፣ በጎነትን የሚፈልግ ሁሉ ለተቸገሩ እንዲደርስበት የሚደረግበት አሰራር ነው መዘርጋት ያለበት። ማህበሩ በምንም መልኩ ከአንድ ሰው ተቀብሎ ወደ ሌላ ሰው ምግቡን እንዲያስተላልፍ አይፈልግም። ይህ የእሱ ስራ ይሆን ዘንድም አይሻም። ስለሆነም ዋና እቅዱ ሰዎችን ከሰዎች ጋር በማገናኘት እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ ማድረግ ነው። በሌላ በኩል ማህበሩ ጎዳና ላይ ያሉትን አይደግፍም። ምክንያቱም እዚያ እያሉ ማገዝ “ጎዳና ላይ መሆናችሁ ትክክል ነው፤ እዛው ጎዳና ላይ ቆዩ” ከማለት አይተናነስም። እናም የማህበሩ ዋና አላማ ከቤት ሳይወጡ የሚታገዙበትን ስርዓት መፍጠርና ለውጣቸውን እያዩ በእነርሱ ምትክ ሌላ ችግረኛ ሰው እንዲደገፍ ማድረግ ነው።
ማህበሩ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን፣ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበርን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ (አብቹ ካንፓስ)ን ይዞ እየሰራ ያለ እንደሆነ ያጫወቱን አቶ ነጻነት፤ በእነርሱና መሰል አጋሮች እገዛ በሕግ ክልከላው መሰረት የአምስት ዓመት እቅዱን፤ ማለትም በኢትዮጵያ ውስጥ የጎዳና ላይ ልመናን ማስቆምን እውን እንደሚያደርግ ያምናል። ይህንን እውን ካደረገ በኋላ ደግሞ ራሱን ወደ ትምህርት ተቋምነት ለመቀየርም አስቧል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዋና ግቡ መሰረቱን በመተጋገዝ ላይ ማጽናት ስለሆነ ነው። ከዚያ ማህበሩ ሥራውን ለማህበረሰቡ አስረክቦ፤ የትምህርት ማዕከል ሆኖ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባሩን ይቀጥላል።
ማህበሩ አገርኛ ባህላችንን ይዞ ብቅ ማለቱና ለአብነት ያነሳናቸውን ባለታሪኮቻችንን እየፈጠረ በመሆኑ ይበል አሰኝቶናል። ይዟቸው እየተጓዘ ያሉት ሀሳቦች፤ ማለትም ‹‹ወላጆች በችግር ምክንያት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ኃላፊነቴን እወጣለሁ፤ የተቸገሩ ጎረቤቶቼን በማገዝ ወደ ልመና እንዳይወጡ ኃላፊነቴን እወጣለሁ፤ በጎዳና ልመና ለተሰማሩ ወገኖቼ የመፍትሔ ባለቤት እሆናለሁ።›› የሚሉት የሁላችንም የቤት ስራዎች ናቸውና ልዩ ትኩረትን በመስጠት ሀላፊነታችንን እንወጣ ዘንድ በማሳሰብ ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም