ለመሆኑ በመንግሥት አቅጣጫ፣ በግብርና ሚኒስቴር ፊት መሪነት ወደ ተግባር የገባው ”የሌማት ትሩፋት” መኖርና መሰረታዊ ፋይዳው፤ አጠቃላይ ግቡ ምንድን ነው? የሚለውን በአጭሩ እንመልከት።
ከሚመለከታቸው፣ በተለይም የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑት የግብርና የቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሌማት ትሩፋት መርሓ-ግብር ሕብረተሰቡ የተመጣጠነና ጤናማ ይዘት ያለው ምግብ እንዲያገኝና የጥምር ግብርና ተግባርን የሚያበረታታ፤ የተመጣጠነ ምግብ በበቂና እና በጥራት በማምረት እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ለዜጎች በማድረስ ሂደት የተሻለ ዕድል የሚፈጥር፤ በተለይም በአገሪቱ የወተት፣ የማር፣ ፍራፍሬ፣ የእንቁላልና ቀይ ስጋ በስፋት እንዲቀርብ በማስቻልም ትልቅ ጠቀሜታ ያለው፤ ተጨማሪ ገቢና የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የህብረተሰቡን የአመጋገብ ስርዓት የሚያሻሽል ነው።
የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎች እንደሚሉት፤ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚያረጋግጡትም ሆነ እኛም እንደምናውቀው አገሪቱ የበለፀገ ሀብት ባለቤት ነች።
ይህ በበኩሉ ለማር ምርት፣ ለከብት ማድለብ እና ለዶሮ እርባታ አመቺ በመሆኑ የሌማት ትሩፉት ፕሮጀክትን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላል። በመሆኑም፣ በሰብል ልማት ያስመዘገብነውን ስኬት በሌማት ትሩፋት መርሐግብር አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይኖርብናል የሚል አቋም በሁሉም ወገን ተይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጥቅምት ወር በአርባ ምንጭ ከተማ በይፋ ያስጀመሩት ‘የሌማት ትሩፋት’ የልማት ዘመቻ መርሐ ግብሩ ዋና አለማውም ”ሥጋ፣ እንቁላል፣ ማርና ወተት የቅንጦት ምግቦች ሳይሆኑ በቀላሉ የሚገኙ አማራጮች እንዲሆኑ ማስቻል ነው።” በሚል ሰፍሮ ይገኛል። በድረ-ገፃቸው የሰፈረው የዶ/ር ዐቢይ ሙሉ ሀሳብም፡—
“ዛሬ በዐርባ ምንጭ ከተማ ‘የሌማት ትሩፋት’ የልማት ዘመቻን አስጀምረናል። ሌማት አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው። በቂ እና አመርቂ ምግብ ማግኘት ነው። በቂ የመጠን፣ አመርቂ የይዘት ጉዳይ ነው። በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። የሌማት ትሩፋት ዘመቻው በቤተሰብ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት ያፋጥንልናል።” የሚል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመርሀ-ግብሩን መጀመር አስመልክተው በማህበራዊ ድረ ገፃቸው ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን፣ ”ሌማት÷ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ … በቂ እና አመርቂ ምግብ ለማግኘት እንዲቻል ያለመ” እንደ ሆነ አስፍረዋል። ”በቂ የመጠን፣ አመርቂ የይዘት ጉዳይ ነው፤ በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። የሌማት ትሩፋት ዘመቻ በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት ያፋጥናል። መርሐ ግብሩ ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፣ ዋና ግቡም የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የምግብ ስርዓትን ማሻሻል ነው። … የሥራ ዕድል ፈጠራንና የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ እንዲሁም ከውጭ የሚገባ የእንስሳት ተዋጽኦን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያለመ ነው፡፡” ሲሉም አስረድተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተገኝተው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ባስጀመሩበት ወቅትም የተናገሩት ከዚሁ የተለየ ስላልሆነ፤ ከተሰራበት አዋጪ ነው ማለት ነውና መርሀ ግብሩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ሊለወጥ፤ ለዚህም፣ ”ሥጋ፣ እንቁላል፣ ማርና ወተት የቅንጦት ምግቦች … አይደሉምና ሁሉም ሊተባበር ይገባል ማለት ነው።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የሌማት ትሩፋት መርሓ ግብርን በዞኑ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የገለፁ ሲሆን፣ 2 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩቶች ለማህበራት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የሌማት ትሩፋትን የሚያጠናክሩ ሌሎች የግብርና ስራዎችም የሚከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፤ ”ዞኑ ለማር ምርት፣ ለከብት ማድለብ እና እርባታ እንዲሁም ለዶሮ እርባታ አመቺ በመሆኑ የሌማት ትሩፉት ፕሮጀክትን በተሻለ ሁኔታ እንተገብረዋለን” ሲሉም አረጋግጠዋል።
የጅማ ዞን የግብርና ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ጣሀ አባፊጣ በበኩላቸው መርሓ ግብሩን ለማጠናከር በግብርና ዘርፍ ማሕበር የተደራጁ ወጣቶች በዶሮ እርባታ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚሁ በያዝነው ወር በሲዳማ ክልል፣ በሸበዲኖ ወረዳ፣ በፉራ ቀበሌ ”የሌማት ትሩፋት”ን የማስተዋወቅ መርሐ-ግብር የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተካሂዶ እንደ ነበር ይታወሳል።
መርሐ-ግብሩ እንደሀገር የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ለማሳካት የተያዘውን ውጥን ከግብ ለማድረስ ያለመ መሆኑ፤ ሁለንተናዊ የቤተሰብ ብልጽግና ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደ ሆነ … በመርሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
ይህ ”የሌማት ትሩፋት” ፕሮግራም በእንስሳትና አሳ ሀብት፣ በአቮካዶ ምርት፣ በንብ ማነብ፣ በወተት፣ በቡና ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎች ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑም ተነግሯል። የማር፣ የዶሮ፣ የወተትና ሌሎች ምርቶችን ለማምረትም ምቹ በመሆኑ አምራች ሀይሉ በሙሉ አቅም መሥራት የሚገባው መሆኑም እንደዛው። ወደ ኦሮሚያ እንሂድ።
በኦሮሚያም የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ይፋ የተደረገው በዚሁ ወር ነው። በስነስርአቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የተመጣጠነ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አምራች ዜጎችን ለማፍራት አጋዥ በመሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
”የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሶማሌ ክልል የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴን ማስጀመሪያ ሥነስርዓት ላይ ተገኝተዋል፡፡” የሚል ዜና መታወጁንም እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ሲሆን፣ ”የከተማ አስተዳደሩም ለክልሉ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ 110 የውሃ ፓምፖችን ድጋፍ አድርጓል፡፡” የሚለውን፤ እንዲሁም” እንደ ሀገር የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ በሁሉም አካባቢ ወደ ተግባር መለወጡን የሚያሳይ ነው፡፡
”የሌማት ትሩፋት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚሆን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ።” ከሚለው ጋር ለአየር በቅቶ የነበረው ”የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የሌማት ትሩፋት የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በቻግኒ ከተማ” ተካሄደ የሚለው ሲሆን፤ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ”የሌማት ትሩፋት” ፕሮግራም ልዩ ትኩረትን ያገኘ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ ተደርጎበት ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበ ፕሮጀክት መሆኑን ነውና ጉዳዩ የዋዛ አይደለም ማለት ነው።
በስነስርአቱ ላይ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ፀጋ ቢኖራትም እስካሁን በምግብ እራስን አለመቻሏ ያስቆጫል። ችግሩን ለመቅረፍ አዲስ አሠራር መዘርጋት አለበት። ከእነዚህ አሠራሮች ውስጥ አንዱ የሌማት ትሩፋት ትግበራ ሲሆን፣ የሌማት ትሩፋትን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትና ትግልን ይጠይቃል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የአሠራርና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ተገቢ ነው። በክልሉ የሌማት ትሩፋት ስኬታማ እንዲሆን በተለይ አመራሩና ባለሙያው በትኩረት ሊሠሩ የግድ ሲሆን፤ አርሶአደሮች የእንስሳት አረባብ ዘዴን ማሻሻል፤ መላው የክልሉ ሕዝብም ተባባሪ ሊሆን ይገባል።
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ፣ ሲግናል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ እናት (ወይዘሮ አበራሽ ዋቅጅራ) በመኖሪያ ግቢያቸው በአትክልት ልማትና በእንስሳት እርባታ እያከናወኑት ያለውን ሥራ (አትክልት፣ የዶሮና ከብት እርባታ፣ የንብ ማነብና ሌሎችም ስራዎችን) በጎበኙበት ወቅት ”በአረንጓዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት ይገባል” በማለት ከተናገሩበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮጀክቱ ልዩ ትኩረትን ያገኘ ሲሆን፣ በመላው አገሪቱ የማስፋፋት ስራውም ተጠናክሮ ስለ መቀጠሉ ምክንያት ሆኗል።
በምግብ ራስን ለመቻል እንደ አገር ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ ልማት የተከናወኑ የልማት ሥራዎችንና በቅርቡ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት ጠቅሰዋል። በመኖሪያ ግቢያቸው ከጓሮ አትክልት ልማት ባለፈ በእንስሳት እርባታ የወተት፣ እንቁላልና ማር ምርቶች እያከናወኑ ያሉት እናት ለበርካቶች አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን፤ በሁሉም አካባቢዎች የራስን ምግብ የማምረት ሥራዎች ባህል ሆነው ከቀጠሉ በቤተሰብ፣ በአካባቢ አልፎም በአገር ደረጃ የምግብ ፍጆታን ለማሟላት እንደሚጠቅምም ገልጸዋል።
በርካታ ፍላጎቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ በምግብ ራሳችንን ካልቻልን ተጎጂዎች እንሆናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት እንዳለብን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት በአረንጓዴ ልማት፣ በስንዴ፣ ሩዝና ሌሎችም የግብርና ምርቶች ስኬታማ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
”ስለ መርሀ-ግብሩ ምሁራኑስ ምን ይላሉ?” የሚለውን እንደ መውጫ እንጠቀምበትና ጽሑፋችንን እናጠቃልል።
የዘርፉ ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ረጋሳ (በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት አማካሪ ናቸው) በማህበራዊ ገፃቸው ላይ ”ጥቂት ስለ የሌማት ትሩፋት” በሚል ርእስ የሚከተለውን አስፍረዋል፤
ሀገራችን ሰፊ የእንስሳት ሃብት ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ለዘመናት የእንስሳት ሀብታችንን ከአህጉራችንና ከዓለም ሀገራት ጋር በቁጥር ደረጃ ብቻ እያወዳደርን ደረጃችንን ስንገልፅ ቆይተናል፡፡ ምርትና ምርታማነቱን ስንመለከት ግን ከምንም የማይገባና እጅግ ብዙ ሥራዎችን ገና መስራት እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ሴክተር የሚገኘው የወተት፣ ስጋ፣ እንቁላል እና ማር ምርት ከህዝብ ብዛት ፍላጎት አንጻር በጣም ዝቅተኛና ዋጋውም በየጊዜው እየናረ በመምጣቱ መመገብ ሣይሆን መቅመስ እያዳገተ መጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን የውጪ ምንዛሪ መጠቀም አልተቻለም። እንደ ባለሙያ በተለያዩ ጊዜያት የዚህ ዘርፍ መድከምና ምርታማነት መቀነስ ምክንያት “የእንስሳት ዘርፉ በቂ ትኩረት አለማግኘት ነው” የሚባለውን ንግግር ስንሰማና ስንናገር ቆይተናል፡፡
አሁን ግን መንግስት ይሄንን እምቅ የእንስሳት ሀብታችንን ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ “የሌማት ትሩፋት” የሚል ሀገራዊ መርሀ-ግብር በመቅረፅ ያስጀመረ ሲሆን መርሀ-ግብሩ የሚያተኩረውም (prioritized commodities) በወተት ልማት፣ የዶሮ እርባታ እና የማር ልማት (Dairy, Poultry & Honey) ላይ ነው፡፡ ይህም ተያያዥነት ያላቸውን የመኖ፣ የእርባታ፣ የጤና እና የመሳሰሉትን ስራዎች ያካተተ ምሉዕ የሆነ መርሀ-ግብር ነው፡፡
“ሁሉንም እየሰራን የተወሰኑ ጉዳዮችን ቅድሚያ በመስጠት በትኩረት እንሰራልን” በሚል መርህ መሠረት ወተት፣ ዶሮ እና ማር በዚህ መርሀ-ግብር ትኩረት ያገኙ ቢሆንም የተቀሩትን ጉዳዮች በታቀደው መደበኛ የስራ ሂደት የማከናወኑ ተግባር ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ክንውኑን በተመለከተ ከመንደርና ቀበሌ ልየታ ጀምሮ እስከ ፌደራል መስሪያ ቤቶች ድረስ የተቀናጀና የተናበበ አሰራር የተዘረጋለት በመሆኑ ሂደቱ ይበልጥ ግልፅ እየሆነ ይሄዳል፡፡
ስለዚህ ይህ የመንግሰት ትኩረት የሆነው መርሀ-ግብር፤ እኛን የዘርፉ ባለሙያዎችን የድርሻችንን ለመወጣት፤ ማለትም፣ ዘርፉን ከዘገምተኛ እድገት በፍጥነት ለውጥ እንዲመጣበት ለማድረግና በቁጥር ብቻ ሳይሆን በጠቀሜታውም የላቀ ደረጃ በማድረስ የአርብቶና አርሶአደሩን ሕይወት የምንለውጥበት፤ እንዲሁም፣ መላውን ህዝብና ሀገርን ተጠቃሚ የሚናደርግበት መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
እኛም እንላለን፤
ሰላም አይለየን!!!
ያሰብነውን ያሳካልን!!!
ገበታችን በሥጋ፣ በእንቁላል፣ በማርና ወተት ግጥም ይበል!!!
ሌማታችን ሙሉ ይሁን!!!
አሜን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም