መንግሥት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። እነዚህ ተልዕኮዎቻቸውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ስራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም ርካሽ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል።
በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች እየተገኘበት ነው። በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል።
ለአብነት ያህል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በተጠናቀረ መረጃ መሰረት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በቀጥታ በምርት ተግባራት ላይ የተሰማሩ 81ሺ ሰራተኞች ነበሩ። ይህ ቁጥር ከፓርኮቹ ውጭ ያሉና ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች አይጨምርም። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ከፓርኮቹ ውጭ ካሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የስራ ትስስር ስላላቸው በዚህ ሂደትም በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ቀርበዋል። በሌላ በኩል ፓርኮቹ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ፣ ለውጭ ገበያ የቀረበውና በተተኪ ምርቶች የተገኘው ዋጋ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ከዚህ ውስጥ፣ 930 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው በተተኪ ምርቶችን የማምረት ተግባርም (Import Substitution) ጥሩ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይም የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች የግብይት ሰንሰለቱን ቀላል በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ። ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። መንግሥት አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እስካሁን ድረስ 30 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንና ይህ ወጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ገብተው በምርት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኘው የ‹‹ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በሀገሪቱ ከተገነቡ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች (Integrated Agro-Industry Parks) መካከል አንዱ ነው። የፓርኩ ግንባታ በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በጥር 2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመረቀ ሲሆን፣ የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች ይሰማሩበታል።
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ260 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው። ከዚህ ውስጥ 168 ሄክታር የሚሆነው ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ዝግጁ የተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅት 60 ሄክታር መሬት ለ23 ፕሮጀክቶች የተላለፈ ሲሆን ቀሪው 108 ሄክታር መሬት ደግሞ ባለሀብቶችን እየጠበቀ ነው። ለመጀመሪያ ዙር ግንባታው ከአራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፓርኩ፣ ከ25ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል።
ወደ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገቡ አምራቾች የግብርና ምርትን በግብዓትነት የሚጠቀሙና የሚያቀነባብሩ፣ ምርታቸውን በጋራ ወይም በተናጠል ወደ ውጭ የሚልኩ፣ ለግብርናው ምርት መዘመን መሰረት የሚሆኑ፣ የተሻሻለ ቴክኖሎጅ የሚያስተዋውቁ እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ይሆናሉ። የብዕርና የጥራጥሬ እህል፣ የሰሊጥ፣ የአትክልት፣ የማርና ሰም፣ የዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ እንዲሁም ስጋና የስጋ ውጤቶች ማቀነባበሪያዎች ወደ ፓርኩ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከአካባቢው ግብአቶችን የሚያቀርቡ ሰባት መጋቢ የገጠር የሽግግር ማዕከላት እየተገነቡ ይገኛሉ። ማዕከላቱ በሞጣ፣ አማኑኤል፣ ዳንግላ፣ ፍኖተ-ሰላም፣ እንጂባራ፣ ቻግኒ እና መራዊ ከተሞች የሚገኙ ሲሆኑ፤ ግብዓቶችን የመቀበል፣ የማጣራትና ደረጃዎችን የማውጣት እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ስልጠና የመስጠት ተግባራትን ያከናውናሉ። ስለሆነም ማዕከላቱ ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር በመፍጠር ለአርሶ አደሩ የላቀ ተጠቃሚነት እንዲሰሩ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በፓርኩ ምርቃት ወቅት ‹‹በቡሬና አካባቢው ከፍተኛ ምርት ቢመረትም ፍራፍሬ እየላክን ጭማቂ ስናስመጣ ቆይተናል። ፍራፍሬ ወደ ውጭ እየላክን ጭማቂ ወደ ሀገር ውስጥ ማስመጣት ተገቢ አይደለም። ይህ ሁኔታ እንዲቀየር ምርቶቻችን ሀገር ውስጥ ተቀነባብረው መመረት አለባቸው። ግዙፉ የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይህን ለማሳካት ያስችላል። ስለሆነም ባለሀብቶች በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል›› በማለት ተናግረው ነበር።
በሀገሪቱ በኦሮሚያ ክልል የቡልቡላ አግሮ እንዱስትሪ ፓርክ በሲዳማ ክልል የይርጋአለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአማራ ክልል ደግሞ የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ መግባታቸው ይታወቃል። በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ባለሀብቶች ገብተው እያለሙ ይገኛሉ።
ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ካላቸው እምቅ አቅም አኳያ በርካታ ባለሀብቶችን መቀበል ይችላሉ። ፓርኮቹ የሚገኙባቸው ክልሎች ለባለሀብቶች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ። የቡልቡላ እንዲሁም የይርጋ አለም የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀደም ሲል በየተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በፓርኮቹና በአካባቢያቸው ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች በመጥቀስ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይም ባለሀብቶች በቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያካሂዱ የአማራ ክልል ጥሪ አቅርቧል።
ባለሀብቶች ወደ ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው እንዲያለሙ ለማድረግ የተዘጋጀ ፎረም ኅዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል። መድረኩ የፓርኩ አቅም፣ ምቹ እድሎችና፣ የገጠር ሽግግር ማዕከላት ምርታቸው የተዋወቀበት ሲሆን፣ ከ103 በላይ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው በኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ስምምነታቸውን ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፤ የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሰብል ልማት ብቻ ሳይሆን በአትክልትና ፍራፍሬ እና በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፎችም ያሉ እድሎችን ለመጠቀም ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር የልማት ማሳለጫ እንደሆነ ተናግረዋል። ፓርኩ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆኑን ጠቁመው፤ በግብርናው ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል። ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በመግባት በአጭር ጊዜ ወደ ምርት በመሸጋገር ራሳቸውን ጠቅመው በአገሪቱ ብልጽግና ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ጣዕምአለው፤ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በውስጡ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ማካተቱን ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ፓርኩ የገበያ ማዕከል፣ የአስተዳደር ሕንፃ፣ ክሊኒክ፣ የሕፃናት ማቆያ፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው። የፓርኩ መገንባት ከዚህ ቀደም በተበታተነ መልኩ ሲቀርቡ የነበሩ የመሬት ጥያቄዎችን በአንድ አካባቢ ለማግኘትና ለማስተናገድ ያስችላል። እስካሁን 23 ፕሮጀክቶች መሬት ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፤ ፓርኩ የተገነባበት አካባቢ ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለሀብቶች የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር እንደማይገጥማቸው ያስረዳሉ። ‹‹አካባቢው ምርታማ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኩ ይህን የምርት አቅም በመጠቀም የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።
አቶ እንድሪስ እንደሚሉት፤ የክልሉ መንግሥት በክልሉ ያለውን ሀብት ለማልማት እና ለክልሉ የኢኮኖሚ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሳደግ የኢንቨስትመንት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ እየሰራ ይገኛል። በክልሉ ከ3ሺ200 ሄክታር በላይ መሬት እና 3ሺ444 ኢንዱትሪዎችን የያዙ 28 የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚገኙ ሲሆን፣ 755 ኢንዱስትሪዎች የግብርና ምርቶችን በጥሬ እቃነት የሚጠቀሙ ናቸው።
ባለሃብቶች በሚፈለገው መጠን ወደ ፓርኩ እንዳይገቡና የገቡትም በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት ከሆኑ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት ችግር እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት እጥረት መሆኑን አስታውሰው፤ ይህን ችግር ለመፍታት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከመብራት ኃይል ቦርድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተከናወኑ ተግባራት ችግሩ በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ ተናግረዋል።
ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል የተባለውና በአንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ የሚገነባው የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤሌክትሪክ ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው ባለፈው ወር ተጀምሯል። ማከፋፈያ ጣቢያው በዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ግንባታውን በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ሥራው በሁለት ሥራ ተቋራጮች እንደሚከናወን ተገልጿል። የግንባታ ሥራው የኤሌክትሪክ ኃይልን ከዋናው መስመር ወደ ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ለማድረስ የሚያስችል የ90 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታን ያካትታል። የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ በፓርኩ ውስጥ ሥራ ለጀመሩና አዲስ ለሚገቡ ኢንዱስትሪዎች በቂ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ይጠበቃል።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል።
የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል። ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሰረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም