በአገራችን ታሪክም ሆነ ቱባ ባህል መሰረት የታረዘን ማልበስ፣ የተራበን ማብላት፣ በአጠቃላይ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን “ከጎናችሁ ነን! አለንላችሁ! አይዟችሁ!” ማለት የእኛ፣ የኢትዮጵያዊያን ቱባ እሴት ነው።
ይህን ዓይነቱ ታሪክ፣ ባህል …፣ ባጠቃላይ እሴት ትውልድ በቅብብሎሽ ይዞት እንዲቀጥልና እንዲያስቀጥል የሚጠበቅ ሲሆን፤ ምንም እንኳን መሀል ላይ የተዳከመ መስሎ ብዙዎችን አሳስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የበለጠ ተጠናክሮ በመቀጠል ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን መሬት ለማስያዝ በርካታ ማሳያዎች ያሉ ሲሆን፣ የማዕድ ማጋራት፣ የአልባሳት፣ የገንዘብና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ወዘተ ድጋፍ ማድረግ፤ ከሰራዊቱ ጎን ሳይቀር የመሰለፍና ድጋፍ ማድረግ … እና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በተለይ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” (ይህ መርህ እንደ አንድ ሰብዓዊ መርህ ተወስዶ በመጀመሪያ ሲቀነቀን የሰማሁት በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ነው) የሚለው አስተሳሰብ እየሰረፀ መምጣቱ በራሱ አንድ ትልቅ እርምጃ ነውና የአሁኑም ሆነ መጪዎቹ ትውልዶች ይህ ቋሚ መርሀቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።
በ2001 ዓ.ም የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ኤጀንሲ ሕግ በ2012 ዓ.ም እስኪሻሻል ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ ማህበራት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ፈርሰዋል፤ አልያም በእጅጉ ተዳከመዋል … የተባለበት ወቅት ሲሆን፤ ከህጉ መሻሻልና “የኢፌዴሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ኤጀንሲ” መቋቋም በኋላ በተሻለ ሁኔታ ዘርፉ እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገራል። የሚመለከታቸው ተቋማት መረጃዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው።
በተለይ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የሚለው ሀሳብም ይሁን አስተሳሰብ ምንም የማይወጣለት፤ ፍፁም ሰብዓዊና ሰው ተኮር እንደ መሆኑ መጠን በመርህነት መያዙና በሱም ጥላ ስር መሰባሰቡ በየትኛውም መስፈርት ተገቢነት ስላለው ተጠናክሮ ቢቀጥል እንጂ የሚዳከም ጉዳይ አይደለም። ሜቄዶኒያን የመሳሰሉት ተቋማት መርሀቸው ይኸው በመሆኑም በመርሁ እየተመሩ፤ የበለጠም እየተጠናከሩና ተደራሽ እየሆኑ ዘለቁ እንጂ የተቀዛቀዙበት ጊዜ አልታየምና መርሁ አሰሪም አዋጭም ነው። ዳር ዳርታችን ወደ “በጎ አድራጎት”፤ በተለይም “አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች” ነውና ወደዛው እንሂድ።
እንደሚታወቀው፣ አገር በቀል ተቋማት፣ የማህበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው መጠን፣ ስነልቦናን በመረዳት፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤን በማክበር፣ እንዲሁም በወገንተኝነትና ተቋርቋሪነት ስሜት ሊሰሩ መቻላቸው አገርን ለማሻገርና ማህበረሰብን ለማንቃት የሚኖራቸው ሚናም ሆነ ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡
ዲሞክራሲን ለመተግበር፣ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር እንዲሁም ለሕግ ተገዥ የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር ሕጎችና ፖሊሲዎችን ከማጽደቅና ለመተገበር ከመስራት ባለፈ፣ መርሆቹ የማህበረሰብ ባህልና አስተሳሰብ እንዲሆኑና በየእለት ሕይወት ውስጥ እንዲተገበሩ መስራት ግድ ይላል፡፡ በበርካታ አገራት እንደታየው ይህንን ንቃተ ህሊና መፍጠር ደግሞ በዋነኛነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሚና ከፍተኛና ከዚህ መለስ የሚባል አይደለም፡፡ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ በደል ከመታደግ አኳያም እንደዛው። (ለምሳሌ፣ የዛሬን አያድርገው እንጂ እነ አምነስቲ ከፈጣሪ በታች የሚታመኑም የሚመለኩም ይሆኑ ዘንድ አስችሏቸው የነበረው ይህ ተግባራቸው ነበር።)
እዚህ ላይ አንድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር “ምን አይነት ሰው መፍጠር ነው ከእነዚህ ድርጅቶች የሚጠበቀው?” የሚለው ነው። እንደ ባለሙያዎችም ሆነ ዓለም አቀፍ ጥናቶች አተያይ አንድ ድርጅት ዝም ብሎ ብቻ እርዳታ መስጠትና መቀበል ላይ ማተኮር የለበትም። የተቋማቱ ትኩረት ይህ ከሆነ የተረጂነት መንፈስ ሥር ሰዶ ይንሰራፋል፡፡ እንደ ባህልም ይዳብራል፡፡ ከዳበረና ሥር ከሰደደ በኋላ ደግሞ ለመመለስና ለማስተካከል ፈታኝ ይሆናል፡፡ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ መተካት ሲገባው ሁልጊዜ የዕርዳታ እጅ የሚጠባበቅ ዜጋ ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሆኑም ይህ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋል ማለት ነው።
በአንድ ወቅት የተረጂነትን መንፈስ ለማስወገድ አቅም በፈቀደ መጠን ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት መካከል “ጳጉሜን አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅት” ያከናወናቸው ተግባራት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ገሠሠ እንደገለጹት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ከሚገኙት ችግረኞች መካከል አቅም በፈቀደ መጠን 150 ያህሉን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚናገሩ የሚዲያ ዘገባዎች ስንሰማ እንደነበር እናስታውሳለን።
ስራ አስኪያጁ “የጎዳና ሕይወትን የሚኖሩ፣ ቀን ጨልሞባቸው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ … እነዚህን ወገኖች ከተረጂነት የማላቀቁ ሥራ የሚከናወነው በኮንስትራክሽንና በጨርቃ ጨርቅ (ጋርመንት) ሥራዎች ላይ በማሰማራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንና በሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ላይ ያተኮረ ሥልጠና እንደተሰጣቸው፣ በሥልጠናውም ያገኙትን ዕውቀት የማጠናከር ሥራ ላይ ያተኮረ ሌላ ሥልጠናም በቅርቡ እንደሚሰጣቸው” መናገራቸውም እንደዚሁ በተያያዘ ዜና (ሴፕቴምበር 14 ቀን 2022) መነገሩ አይዘነጋም።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ ያልነውን፣ የተረጅነትና ጠባቂነት መንፈስ እንዳይሰፍን ለማድረግ ከማሰብ የመጣ ነውና ሁሉም ይህንኑ ጉዳይ ሊያስቡበት ይገባል ማለት ይሆናል።
ተቋማቱ ከእርዳታና ድጋፍ፣ ልገሳና ረድኤት ባለፈ ከሰላምና ፀጥታ … አኳያም የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ግጭቶችን በምታስተናግደው ናይጄሪያ፣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ በመንግስት የሚደርገውን ጥረት በማገዝ፣ የተጋጩ ወገኖችን ለንግግር በመጋበዝና በማሸማገል ረገድ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸው፤ አሁንም በመጫወት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከእርስ በርስ ጦርነት፣ ከዘር ማጥፋትና ከዘረኝነት ግጭቶች ተላቀው አገር ለማስቀጠል በቻሉት እንደ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ አገራትም በተለይ አገር በቀል ተቋማት ያደረጉት አስተዋጽኦ ዘርፉን ከማጠናከርና የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ከማስቀጠል አኳያ ተደጋግመው የሚጠቀሱ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ተቋማት፣ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ፣ ከፖለቲካ ነጻ እንደመሆናቸው መጠን፣ የሚኖራቸው ተአማኒነት፣ ተቀባይነትና ማህበረሰብ ጋ የመድረስ፤ ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት ጉልበታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ነው እንግዲህ በአዋጅ ተደግፈው፣ ደንብና መመሪያ ወጥቶላቸው ወደ ስራ እንዲገቡና የአገርና ትውልድ የማስቀጠል ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የተደረገው።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ አገር በቀል የሆኑትም ሆኑ ያልሆኑት፣ ከተቋቋሙበትም አላማም ሆነ ደንብና ስርአት ውጭ በመሆን በተቀራኒው የሚሰሩ አሉ። ይህ ደግሞ ሁሌም የሚታይና የሚሰማ ሮሮና ንቅዘት ስለሆነ እዚህ መድገሙ አያስፈልግም። ምናልባት ስለ ጉዳዩ ሰፋ አድርጎ መመልከት ለፈለገ ግን ከብዙዎቹ አንዱ የሆነውን፤ “ሪፖርተር” ጋዜጣ የካቲት 25 ቀን 2010 ዓ.ም፣ በገጽ 42 ላይ «የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎች የመፍትሔው አካል ይደረጉ፤›› በሚል ርዕስ ያቀረበውን ጽሑፍ፤ እንዲሁም፣ እሱን ተከትለው ለንባብ የበቁ (ለምሳሌ “የበጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኞችም ተመልካች ይሻሉ” በሚል ርእስ የቀረበው) አስተያየቶችን መመልከት የሚቻል ሲሆን፤ እየተነጋገርንበት ላለው ጉዳይም ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ወደ ዛሬው ጽሑፋችን መነሻ ወደ ሆነው “መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር” እንምጣ።
“መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር” በ2012 ዓ.ም በ55 ተማሪዎች አማካኝነት የተመሰረተ፣ ታዳጊ ማህበር ሲሆን የማህበሩ መቀመጫም ከአዲስ አበባ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አምቦ ከተማ ነው።
ከማህበሩ መስራችና ሊቀ መንበር ወጣት ዳግም ገዛኸኝ ጋር ባደረግነው ቆይታ እንዳጫወተን ከሆነ ለማህበሩ መመስረት ዋና ምክንያት የሆነው በአካባቢው አቅመ ደካሞችና ርዳታ ፈላጊ ወገኖች፤ መማር እየተገባቸው መማር ያልቻሉ ህፃናትና ወጣቶች መኖር፤ እንዲሁም ምንም አይነት ገቢና ረዳት የሌላቸውና በከፋ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸውና እነሱን መደገፍ የዜግነት ብቻ ሳይሆን፤ ሰው የመሆን ግዴታም ጭምር መሆኑ ነው።
ከአምቦ አስተዳደር እውቅና አግኝተን፣ ሰርተፊኬትም ተሰጥቶን በመንቀሳቀስ ላይ ነን የሚለው ሊቀመንበር ዳግም ከህብረተሰቡ በኩል በከፍተኛ ደረጃ እነዚህን ወገኖች የመርዳት ፍላጎት እንዳለ፤ በመኖሩም እነሱ በጠየቁ ቁጥር ከግለሰቦች ጀምሮ እስከ ተቋማት ድረስ እንደሚተባበሯቸውና ያላቸውን እንደሚለግሱ፤ “መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር”ም ያሰባሰበውን ሀብት ለሚመለከታቸው ተደጓሚዎች እንደሚያደርስ ይናገራል።
አባላቶቻችን ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመሄዳቸው ምክንያት የአባላቶቹ ቁጥር በጣም ቀንሶ 25 ደርሷል። ይህንን የአባላት ቁጥር ከፍ ለማድረግ እየሰራን ነው ያለን ወጣት ዳግም የአካባቢው ወጣት ተሳትፎ የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑንም ይገልፃል። በወጣቱ ከሚያደርጉት ተሳትፎዎች በተጨማሪ ወደ እነሱ ማህበርም በመምጣት አባል እንደሚሆኑም ተስፋ እንዳለው ይናገራል። በማህበሩ ድረ ገፅም ላይም ይኸው ሰፍሮ ለንባብ በቅቷል።
“ሰው ነንና ሰውን እንርዳ!!!” በሚል መርህ የሚመራው መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር ከዚህ በፊት በተለያዩ ዙሮች ለተቸገሩና አቅም ለሌላቸው አረጋዊያን የቤት አስቤዛ ሲያድል እንደቆየው ሁሉ፣ ባለፈው ፋሲካም 5ኛውን ዙር እርዳታ የማሰባሰብ ተግባር (“ለበዓል ለ16 ቤተሰቦች አስቤዛ ለማስገባት 50ሺህ ብር” እንደሚያስፈልገው በመግለፅ) ፈፅሞ “የወር አስቤዛ (ጤፍ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሽንኩርት) በተለያዩ ጊዜያት ሰጥተናል።” በማለት በማህበራዊ ድረ-ገፁ ለአባላቱና ደጋፊዎቹ ይፋ አድርጓል። በተለያዩ ጊዜያትና በዓላት “የምገባ ፕሮግራም” ማካሄዱንም በፎቶግራፍ አስደግፎ ገፁ ላይ አስፍሯል። ከወጣት ዳግም ገዛኸኝም ይህንኑ አረጋግጦልናል።
ይህ አገር በቀል ድርጅት በወጣቶች የሚመራ ሲሆን የሚያከናውናቸውን አበይት ተግባራትን በተመለከተ የማህበሩ ሊቀመንበር የሆነው ዳግም ገዛኸኝ “የምንሰራቸው ስራዎች – የወር አስቤዛ መሸፈን፤ የአልባሳት ድጋፍ” ማድረግ በማለት የሚገልፃቸው ሲሆን፤ ከገቢ ምንጮቹ ጥቂቶቹን ሲገልፅም “ሊስትሮ በመስራት እንዲሁም ፌስ ማክስ በመሸጥ፤ ኩፖን በመሸጥ፤ ʻstring art’ (በተለያዩ ቁሶች የተለያዩ ሥዕሎችን በመሣል) በማዘጋጀትና በመሸጥ እንደሆነ ይናገራል። “በተለያየ መንገድ እጃችሁን እንድትዘረጉልን በአክብሮት እንጠይቃለን። የእጅ ጌጥ በምትፈልጉትን ስም በማሰራት (በመግዛትም ጭምር) አንድም ይጠቀሙ፤ እግረ መንገድዎትንም የተቸገሩትን ያግዙ ….” ሲልም ጥሪ ያቀርባል። በአብዛኛው ከእርዳታ ሰጪ ግለሰቦች ለድጋፍ የሚሆነውን ገንዘብ እንደሚያገኙ ነግሮናል።” የቤት እድሳት የምናካሄድበት እለትም አለ ሲልም የሚከናወኑ ተግባራትን ፕሮግራሞች በቦታና ጊዜ ለአባላትና ባለድርሻ አካላት እንደሚገለፅ ይናገራል።
ይህ “መልካም እናድርግ መልካምነት ኃይማኖት፣ ብሔር … አይገድበውም። ፈጣሪን መውደዳችንን ሰዎችን በመርዳት አናስመስክር። ሰው ነንና ሰውን እንርዳ!!”ን መርሁ ያደረገው “መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር” የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት በዚህ እንደማይገደብና ወደፊት ሌሎች በርካታ ስራዎችን ለመስራት እቅድ እንዳለው ሊቀመንበሩ የተናገረ ሲሆን፤ ይህንንም “ወደፊት እቅዳችን ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ራሱን እንዲችል ማድረግ ነው። ከአንድ እርዳታ ከሚፈልግ ቤተሰብ ውስጥ በአንድ በሆነ መንገድ፣ ሙያ … ራሱን ችሎ ቤተሰቦቹንም እንዲያግዝ የማድረግ እቅድ ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው” በማለት ይገልጸዋል።” ይህም ይሳካልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲልም ያክላል።
“ከመስተዳድሩ ያገኛችሁት ድጋፍ ካለ?” ብለነውም “የአምቦ ከተማ መስተዳድር ከእውቅና መስጠት ጀምሮ ከጎናችን ነው። ስብሰባ የምናካሂደውም በወጣቶች ማእከል ነው። መስተዳድሩና ሌሎች አካላትም እንዲተባበሩን የጠየቅናቸው ጉዳዮች አሉ። እስካሁን ምላሽ ባናገኝም ወደፊት ምላሽ ይሰጠናል ብለን እንጠብቃለን።” ሲል ነው የገለፀልን።
በመጨረሻም “ለአንተና አንተን መሰል ወጣቶች በአጠቃላይ የምታስተላልፈው መልእክት ካለ?” ብለነውም “በየአካባቢው በጣም የተቸገሩ ሰዎች አሉ። ብዙ ሰው በከፋ ሁኔታ ውስጥ አለ። እያንዳንዳችን አካባቢያችንን ብንቃኝ ይህ ችግር ግልፅ ሆኖ ይታየናል። በመሆኑም ይህ ችግር በመንግስት ትከሻ ብቻ ይፈታል ተብሎ ማሰብ ስለማይቻል፤ ችግሩን ከመፍታትና ለእነዚህ ወገኖች ከመድረስ አኳያ ወጣቱ የራሱ የሆነ ሀላፊነት አለበት። በመሆኑም፣ ይህንን ሀላፊነቱን በውል በመረዳት በራሱ መንገድ፣ በመደራጀትም ይሁን በሌላ ለእነዚህ ወገኖች መድረስ አለበት።” በማለት የ“መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር” የኮሌጅ ትምህርቱን ጨርሶ በግል ስራ ላይ የተሰማራው የ25 አመቱ ወጣትና የማህበሩ ሊቀመንበር ዳግም ገዛኸኝ መልሶልናል።
እኛም እንላለን፤ ቀደም ሲል በመግቢያችን ላይ ሰፋ አድርገን እንደገለፅነው ሁሉ፣ አገር በቀል ድርጅቶች ከአገር ውጭ ከመጡት በብዙ መልኩ የተሻሉና ተመራጭ ናቸው። ርእሳችንን “አገር በቀል ተቋማትና እሴትን የማስቀጠል ተግባራቸው” ብለን ስንነሳ በጎ አድራጊነት (በሌላ ስሙ “አገልጋይነት”) እሴታችን መሆኑን መግለፃችን ነውና ወጣቶችም ሆኑ ሌላው ዜጋ በእንደዚህ አይነቱ በጎ አድራጎት ተግባራ ላይ ቢሰማራ አገርም፤ ወገንም ይጠቀማል፤ ቱባው የመረዳዳት፣ መተጋገዝ … እሴታችንም ይቀጥላል ብለን እናስባለን። የ“መልካምነት የበጎ አድራጎት ማህበር” አባላትንም በርቱ ስንል የሚመለከተው ሁሉ ይተባበራቸዋል ከሚል እምነት ጋር ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም