ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትነቷን የሚያረጋግጡ የበርካታ ቅርሶች፣ ታሪኮች፣ባህሎችና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት መሆኗ ይታወቃል፤ የሰው ዘር መገኛ “ምድረ ቀደምት” በመባል ትታወቃለች፤ አያሌ ባህሎች፣ ቋንቋዎች መገኛም፣ የውብ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤትም ናት፤ እነዚህ ሁሉ እምቅ ሀብቶች ሀገሪቱን በዓለም ሰፊ የቱሪዝም ሃብት ካላቸው ሀገሮች ተርታ ያሰልፏታል::
ሀገሪቱ ይህን ሁሉ ሃብት በጉያዋ ይዛ ብትገኝም፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በሚፈለገው መንገድ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅና ለገበያ በማቅረብ ፣ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማትና ነባሮቹን ጠብቆ በማቆየት ረገድ በቂ የሚባል ሥራ አልተሰራም፤ በዚህ ሳቢያም ሀገሪቱ ከዚህ እምቅ ሀብት ተጠቃሚ ሳትሆን ኖራለች:: መላው ዓለም “የኛ” የሆኑትን፣ የማንነትና የሉዓላዊነታችን መገለጫዎቻችንን በበቂ ሁኔታ ማወቅ የሚችልበት ሁኔታ ሳይፈጠር ቆይቷል።
ችግሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” እንደሚባለው የአገራችን አባባል በልዩ ልዩ የቱሪዝም መስህቦች (በርቀትም ይሁን በዙሪያችን የሚገኙትን) የቱሪስት መስህቦች የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ተመልክተው በራሳቸው ቅርስ፣ ታሪክ፣ ተፈጥሯዊ ስፍራ እንዲደመሙ ለማድረግ የሚከናወነው ተግባር እጅግ ደካማ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ችግር በዋነኝነት “የኛ” የሆኑት ሃብቶቻችንን እንዳናውቅ ከማድረጉም ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቻቸውን ተረድተን ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ እንዳናደርግላቸው አርጎንም ቆይቷል። በእነዚህና በመሳሰሉት ችግሮች ሳቢያ የቱሪዝም ዘርፉም ክፉኛ ተጎድቶ ኖሯል::
ባለፉት ጥቂት አመታትም ግን በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ጉልህ ለውጦች መታየት ጀምረዋል:: መንግስት በአስር አመቱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅዱ የኢኮኖሚው ምሰሶ ብሎ ከያዛቸው አምስት ግዙፍ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ተደርጓል::
ይህን ተከትሎም መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን ፣ ቴሪዝም ሚኒስቴር ራሱን ችሎ በሚኒስቴር ደረጃ ተደራጅቷል:: የፌዴራል መንግስት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ጉልህ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በአዲስ አበባና በክልሎች እያካሄደ ይገኛል:: በአዲስ አበባ ሶስት ግዙፍ ፕሮጅክቶች ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል:: እነዚህ የቱሪዝም መስህቦች የከተማዋን ገጽታ በወሳኝ መልኩ መቀየር የቻሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎበኙ ይገኛሉ:: በክልሎችም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በጎርጎራ፣ በወንጪና በኮይሻ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ::
ክልሎችም የቱሪዝም መስህቦችን በማስተዋወቅ፣ በማልማትና ለገበያ በማቅረብ በኩል የየራሳቸውን ተግባሮች እያከናወኑ ይገኛሉ:: በዘርፉ አዳዲስ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋትና በዘርፉ ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ እየሰሩ ከሚገኙ ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አንዱ ነው። ክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ከማልማት፣ ከማስተዋወቅና ከመጠበቅ ባሻገር አዳዲስ መዳረሻዎችን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ዓመትም የቱሪዝም ዘርፉ በክልሉ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ስለመሆኑ የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎችንም መመልከት እየተቻለ ነው።
ባሳለፍነው የጥቅምት ወር “ምስራቅ ሃረርጌን የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ማድረግ” የሚል ግብን በመያዝ በአካባቢው የሚገኙትን የቱሪዝም ሃብቶችና መስህቦች ክልሉ ያስተዋወቀበት ሁኔታም ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። በዚሁ ወቅት ክልሉን የጎብኚዎች ምርጫ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል። የኢፕድ ሪፓርተርም በስፍራው ተገኝቶ የቱሪዝም መስህቦችንም የመቃኘት እድል አግኝቷል፤ መድረኮቹንም ተከታትሏል።
‘’አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም ‘’ በሚል መሪ ቃል 43ኛው የአለም ቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ ለ35ኛ ጊዜ መከበሩ ይታወቃል:: የኦሮሚያ ክልልም ይህን ቀን ለ18ኛ ጊዜ ከጥቅምት 27 ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን በመጎብኘት፣ በሀረር ከተማ የፓናል ውይይት በማካሄድ ከባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመምክር ቀኑን በክልል ደረጃ አክብሮታል::
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በክልል ደረጃ በምስራቅ ሀረርጌ በተከበረው አለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በአል ላይ እንደገለጹት ፤ በዓሉ ህብረተሰቡ ባህላዊ እሴቶቹንና የቱሪዝም መስህቦቹን ተገንዝቦ እንዲንከባከብ የሚያደርግ ነው::
እንደ ሀገር የኢኮኖሚ ዘርፉን ለማሳደግ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች አንዱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን በማሳደግ የገቢ ምንጭ ማድረግ የሚለው መሆኑን አቶ ሁሴን ጠቅሰው፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅና በመንከባከብ ህብረተሰቡ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ በዜግነት አገልግሎት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝብዋል::
የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የበዓሉ መከበር ህብረተሰቡ የቱሪዝም ሀብትን በመጠበቅ፣ በማልማት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥና ትልቅ ሚና አለው:: በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ለቱሪዝም መስህብ የሚሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ከመቶ በላይ የዱር እንስሳት ዝርያዎች የሚገኙበት ደን፣ ትክል ድንጋዮች ፣ ከ27 በላይ የሚሆኑ የማዕድን ሀብቶች፣ በአካባቢው ከሚገኙ ቁሳቁስ የተሰራ 250 ዓመት እድሜ ያለዉ መኖሪያ ቤትና 1ሺ416 ዓመት ያስቆጠረ ጥንታዊ መዝጅድ ይገኛሉ::
በዞኑ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች መካካል ሀረማያ ሐይቅ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ መኪያ፤ ሀይቁ ለ17 ዓመታት ደርቆ እንደነበር አሰታውሰዋል:: በዜግነት አገልግሎት ተሳትፎ በተሠራ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ሀይቁ መመለሱን ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅትም በሀይቁ ዙሪያ ለሚገኙ እንስሳት የተለመደውን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት፤ የአካባቢው ወጣቶችም በሀይቁ አካባቢ ተደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል:: ሀይቁን በላቀ ደረጃ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል::
ከአፍሪካ በኢትዮጵያና በታንዛኒያ ብቻ የሚገኝ የዝሆን ዝርያ በባቢሌ ዝሆን መጠለያ እንደሚገኝም አስተዳዳሪዋ ተናግረው፣ ይህም የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኝዎችን ትኩረት በመሳብ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው ያመለከቱት:: ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶቹን እንዲንከባከብም ጥሪ አቅርበዋል ::
ከቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቀውን ገቢ ለማሳደግ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ 321 ዋሻዎችን ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል የሚያስችል ጥናት ይፋ ተደርጓል:: በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የዋሻ ጥናት ባለሙያ ናስር አህመድ ለቱሪዝም ሀብት የሚውሉ ዋሻዎች ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ ከዉጭ ሀገራት ዋሻ ጥናት ባለሙያዎች ጋር የ321 ዋሻዎች መረጃ መሰብሰቡን ገልጸዋል ::
እንደ አቶ ናስር ገለጻ፤ በጥናቱ መሰረት ለ200 ዋሻዎች ካርታና ፕላን ተሰርቶላቸዋል:: አብዛኞቹ በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ነው የሚገኙት:: ሌሎቹ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ መልከ ቁንጡሬ አካባቢ ፣ ሰሜን ሸዋ ፣ ወለጋ፣ ግምቢ ደምቢዶሎ እንደሚገኙ ጥናቱ አመላክቷል::
ኢትዮጵያ በዋሻ ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት ያሉት አቶ ናስር፤ አሁን ጥናት ከተደረገባቸው አካባቢዎች በምስራቅ ሀረርጌ አንድ ወረዳ ብቻ 55 ዋሻዎች መኖራቸውን ተናግረዋል:: በክልሉ ይህን ያህል ዋሻዎች መገኘታቸው ክልሉ በዋሻ ሀብት ቀዳሚ መሆኑን ያሳያል ብለዋል:: ከዚህም በተጨማሪ ከክርስትና እምነት ጋር ተያይዞ በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ በሚገኙ 80 ሰው ሰራሽ ዋሻዎች ላይ ጥናት መካሄዱን ገልጸው፣ እስከ አሁን ድረስ ለ53ቱ ዋሻዎች ካርታና ፕላን ተሰርቶ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል ::
እንደ ባለሙያው ገለጻ ፤ ክልሉ ከተፈጥሮዋዊና ሰው ሰራሽ ዋሻዎች በተጨማሪ በዋሻ ዉስጥ የተጻፉ፣ የተቀረጹ ቅርሶችና ጥንታዊ ታሪኮች (prehistoric painting and rock art ) ሀብት መኖራቸውን በጥናቱ ተረጋግጧል :: ምስራቅ ሀረርጌ በዋሻ ውስጥ በተጻፉ ጥንታዊ ታሪኮች ትታወቃለች:: በክልሉ ከሚገኙ የተቀረጹ ቅርሶችና ጥንታዊ ታሪኮች በ126ቱ ላይ ጥናት በማካሄድ ለ60ዎች ካርታና ፕላን ተሰርቶላቸው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ::
ቀይ፣ ነጭና ጥቁር ቀለማት ያላቸው የፀሀይ ፣ ከዋክብት፣ ጨረቃ ፣ ፍየል ፣ ዝሆን ፣ ቀጭኔ፣ ግመል ስእሎች በተለያዩ ቦታዎች መገኘታቸው ቦረና እና በሬንቱማ ጎሳ አኗኗር ዘይቤያቸው ወንድማማቾች መሆናቸው ከማሳየቱም በላይ አካባቢው በደን ተሸፍኖ እንደነበር አመላካች ነው:: በኦሮሚያ ለቱሪስት መስህብ ሊውሉ ከሚችሉ ዋሻዎች በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ፣ ለማዕድን ምርት፣ ለመድሃኒትነትና ለፊዚዮትራፒ አገልግሎት የሚዉሉ የተፈጥሮ ሀብቶችም ይገኛሉ::
ጥናቱ በመሬት ዉስጥ የሚገኙ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች መገኛ ቦታዎችን በማሳየት ለጎብኝዎች ተጨባጭ መረጃ ለማቅረብ፣ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካም ትልቅ ጠቀሜታ አለው :: በዋሻና ከዋሻ ጋር በተያያዙ ሀብቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ጥናቱ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል ::
በምሥራቅ ሀረርጌ ከሚገኙ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በተጨማሪ በክልሉ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴም ሌላኛው የቱሪዝም ዘርፉ ትሩፋት ነው:: የአካባቢውን ባህልና እሴቶች ለማልማት በተከናወኑ ሥራዎች ህብረተሰቡ ጊዜውንና ሀብቱን ሳያባክን ለግጭቶች ወይም ለውዝግቦች መፍትሄ እንዲያገኝ እየተደረገ ይገኛል :: በክልሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ህብረተሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሊደርስበት የሚችለውን የጊዜና የሀብት ብክነት በማስቀረት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነው::
የምዕራብ ሸዋ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሸንኮሬ እንዳለ እንደገለጹት፤ ቢሮው በአዲስ እሳቤ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ የህብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች በማሳደግ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ለማዋል እየሰራ ነው:: ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ተስፋ ሰጪ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ወይዘሮ ሽንኮሬም ይናገራሉ:: ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በማቋቋም ህብረተሰቡ በአካባቢው ፍትህ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው፤ ፍትህ ለማግኘት በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚያባክነውን ጊዜና ሀብት ለመታደግ እያስቻለ ነው::
ባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ የህብረተሰቡን መሰረታዊ እሴቶች መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዳኝነቱ ከሀሰተኛ ምስክርነቶች የጸዳ እንዲሆን ለማደረግ እንደሚያስችልና በህበረተሰቡ ዘንድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ትልቅ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል:: ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ጫና እንደሚቀንስም ነው የጽህፈት ቤት ሃላፊዋ ያመለከቱት:: ሰላም ከሰፈነ ለልማት አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ገልጸው፣ እስከ አሁን በተከናወነው ተግባር ዞኑ ካሉት 590 ቀበሌዎች በ557ቱ ቀበሌዎች የመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ፍርድቤት ማቋቋም ተችሏል ብለዋል::
በባህላዊ ፍርድ ቤቶች ችግሮችን በእርቅ መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፣ ይህም የህብረተሰቡን ማህበራዊ ኑሮ በማጠናከር በኢኮኖሚው ዉስጥ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አንደሚያደርግ ተናግረዋል:: ጽህፈት ቤቱ ከፍትህ ተቋማት ጋር በመሆን ስራውን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል::
“የህበረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች በማሳደግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፉ ድጋፍ ይፈልጋል” ያሉት ሃላፊዋ፣ ስራውን መሬት ለማስያዝ ሚዲያው የህበረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች ለህብረተሰቡና ለሌላው ለማስተዋወቅ ለመንከባከብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል ::
የብሻን ጉራቻ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የኔነሽ ኢደዓ በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ በከተማው ከሚገኙ ሶሰት ቀበሌዎች አንድ መጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ፍርድ ቤትና አንድ ደበርሳ (ይግባኝ የሚባልበት) ፍርድ ቤት በማቋቋም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ :: ፍርድ ቤቱ ህብረተሰቡ ፍትህ ፍለጋ ወደ ሻሸመኔ ሲመላለስ ጊዜና ሀብት እንዳያባክን አድርጓል ነው የሚሉት:: ከዚህም በተጨማሪ ወጣቱ ትውልድ ባህላዊ እሴቶቹንና ታሪኩን ተረድቶ እንዲያድግ በዜግነት አገልግሎት መጻህፍት በመሰብሰብ የንባብ ባህል በማዳበር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የኦሮሞ ህዝብ እሴት በሆነው የእሬቻ ስነስርዓትም ህብረተሰቡ ባህላዊ እሴቶቹን የሚያስተዋውቅበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል:: ባህላዊ ስርአቱ በከተማው ከሚኖሩ ህብረተሰቦች ጋር ያለው ትስስርና አቃፊነት የታየበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል :: በከተማዋ ያሉት የቱሪዝም ሀብቶች በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከተማዋን ምቹ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል::
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ህዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም