(«ባህላዊ የፍትህ ስርአት» እንደ ማንፀሪያ)
በዛሬዋ ዘመን ዓለማችን በዴሞክራሲ፣ በሕግ የበላይነት፣ በሰብአዊ መብቶች … ላይ አተኩሮ መሰራት የምርጫ ጉዳይ አይደለም። በዛሬው መልክ አይሁን እንጂ በድሮዋ ዓለምም፣ በጥንታዊቷ ምድርም ያውና ያው ሲሆን፤ በጠቀስናቸው ጉዳዮች ላይ መስራት የህልውና ጉዳይ ነው። እንደውም፣ አንዳንድ አንጋፋ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ከዛሬዋ ዓለማችን በተሻለ በጥንታዊቷ ዓለማችን ይሰራ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሲጠቅሱም፣ የሰው ልጅ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ከዛሬው ይልቅ በጥንቱ ዘመን ይሻል ነበር፤ ሰላም ከዛሬዋ ዓለም ይልቅ በጥንታዊቷ ዓለም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሰፈነ ነበር፤ የሰዎች የእርስ በርስ ተግባቦት ከዛሬዋ ይልቅ በጥንታዊቷ ዓለማችምን የሚያስቀና ነበር።
ዲሞክራሲ ማለት ሕዝባዊ አገዛዝ ማለት ከሆነ ከዛሬው ይልቅ የድሮው ሰብአዊ ነበር፤ እርቅና ሰላምን በተመለከተም ከዛሬዋ ዓለም ጋር በማይገናኝ ሁኔታ የጥንቱ እጅግ የላቀ ነበር፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም፣ ወልዶ መሳምም ሆነ ዘርቶ መቃም … ከዛሬዋ አለማችን ይልቅ በጥንቷ አለማችን … ወዘተርፈ በማለት ይዘረዝራሉ። ዝርዝሩ (መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ መከባበር …ን ጨምሮ) ብዙ ስለሆነ ወደ ተነሳንበት ርእሰ ጉዳያችን እንመለስ። በቅድሚያም፡-
”ሕግ እና ፍትህ በጥብቅ የተቆራኙ ቢሆንም የተለያዩ ጽንሰ-ሀሳቦች ናቸው። ሕግ “ይህንን አድርግ፤ ያንን አታድርግ” የሚል ድንጋጌ ነው። አቅም ያለው ሁሉ የፈለገውን ሕግ አውጥቶ ሊያስፈጽም ይችላል። ፍትህ ግን፣ ሰዎች ተሳስበው እና ተጋግዘው እንዲኖሩ የሚያደርግ፤ አድልዎንና ጥቃትን የሚከላከል፤ በዳይን የሚቀጣ፣ ተጠቂን የሚክስ በጎነት ነው። ፍትህ የማኅበራዊ ተቋማት ቀዳሚ በጎ ውጤት ነው። ሕግ መሣሪያ ሲሆን ፍትህ ደግሞ ሕጉ በተግባር ላይ ሲውል የሚገኘው ውጤት ነው። ጥሩ ሕግ በሥራ ላይ ከዋለ ፍትህን ያስገኛል። ጥሩ ሕግ ኖሮ ሥራ ላይ ካልዋለ ግን ሕጉ መኖሩ ብቻውን ፍትህን አያስገኝም። መጥፎ ሕግ ደግሞ ፍትህን ያጓድላል፤ ኢፍትሃዊነትን ያነግሳል።” የሚለውን የባለሙያዎች ብያኔ ለጠቅላላ እውቀትም ቢሆን እንያዘው። (በብያኔው ላይ ችግር ካለ መወያየት ይቻላል።)
በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ሰለሞን አረዳ (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት) ‹‹በፍርድ ቤት ላይ እምነት ማጣት በመንግስት ላይ እምነት ማጣትን ያስከትላል፡፡ ያለ ጠንካራ ፍርድ ቤት ስለ ሀገር ግንባታ ማሰብ አይቻልም›› በማለት የሰጡትን አስተያየትም እዚሁ ላይ በደጋፊነት ማቅረብ ጉዳዩን ለማስረጽ ይረዳል:: አቶ ሰለሞን በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ወቅት እንዳሉት ”በሀገር ግንባታ ውስጥ ”ሕገመንግስታዊነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ስርዓት ያለው የመንግስት አወቃቀር፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ ዋስትና የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ያለ ዳኝነት አካሉ ሊታሰቡ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ የዳኝነት አካሉ ለዜጎችም ሆነ ለአንድ አገር የማይተካ ሚና ይጫወታል የምንለው፡፡” ያሉትን ከዚሁ ጋር በተያያዥ ጠቅሶና የጉዳዩን ውስብስብነት አቅልሎ ማለፍ ይቻላል።
አሁን ደግሞ ”አገር በቀል እውቀት”ንና መሰረታዊ ፋይዳውን በተመለከተ የጋራ መግባባት የተደረሰበት የሚመስለውን ሀሳብ እንመልከት።
”የአገር በቀል እውቀትንና ትምህርትን ፋይዳ በሚገባ በመረዳት ሞራልና ግብረገብነትን የተላበሰ ኅብረተሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግ፤ እስካሁን በአገሪቱ የተተገበሩት ሥርዓተ ትምህርቶች የአገሪቱን የኋላ ታሪክ ያላካተቱ፤ የወደፊት ጉዞዋን መሠረት ያላደረጉና ከምዕራባውያን የመጣውን በጭፍኑ የተቀበሉ ናቸው” የሚለው መቸም ያልሰለቸው (በተለይ የከተሜው ዜና ተከታታይ) የለም ማለት ይቻላል። ችግሩ የተግባር ጉዳይ እንጂ በአንደበት ተደጋግሞ የተነገረ ነው። ከዚህ ውስጥ ”የአገሪቱ የኋላ ታሪክ ምን ይመስላል?” የሚለውን እንመልከት።
አገር በቀል እውቀታችን ያለበት ይዞታ
እንደ የአንድሮሜዳ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ (ዶክተር ሮዳስ ታደሰ) ኢትዮጵያ በፍልስፍናው፣ በሥነ ፈለክ፣ በሕክምናውና በማዕድን ጥናት ዓለምን የሚያስደምሙ እውቀቶች ያላት አገር ብቻ ሳትሆን የስልጣኔዎች ሁሉ መነሻና ምንጭ ነች። በተለይ ምዕተ ዓመትን ሊደፍን ጥቂት ፈሪ የሆነውን፣ የጥቁር አሜሪካዊቷ ድሩሲላ ጁንዲን ስራዎች ያገላበጠ ይህንን እውነት አንድ፣ ሁለት …. በማለት ቆጥሮ መቀበል ይችላልና ስለ እውነትነቱ መከራከር የመከራከር ፍላጎትን ከማርካት ያለፈ ፋይዳ የለውም። ያ ማለት የእኛ የኋላ ታሪክ በሁለንተናዊ ይዞታው የበለፀገ ነበር ማለት ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ጠና ደዎ እንደሚሉት ከሆነ ”አሁን ካለው አኗኗራችን መረዳት እንደሚቻለው ማህበራዊ እሴቶቻችን እየተዳከሙና እየተሸረሸሩ መጥተዋል”። በመሆኑም ከዚህ አይነቱ ብርቱ ችግር በመውጣት ”እሴቶቹ በአገሪቱ እየተወሰደ ያለውን የለውጥ እርምጃ ሊያግዙ በሚችሉበት መልኩ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።እሴቶቹን ለማጠናከርም የአስተዳደራዊና ፖሊቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞችን ከባዕድ አገሮች ከማምጣት ይልቅ የአገር በቀል ዕውቀቱን ከሳይንሱ ጋር በማስታረቅ ተስማሚውን መቅረፅ አስፈላጊ” ነው። ”እየተሸረሸሩ የመጡትን አገራዊ እሴቶችን ለማበልፀግ በትምህርት ስርዓት ውስጥ አካቶ ማስተማር” ይገባል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ፋካልቲ “አገር በቀል ዕውቀትና ትምህርት በኢትዮጵያ ፤ ፋይዳው፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫው” (2011 ዓ.ም) በሚል ርዕስ ያዘጋጀው አገር አቀፍ ዐውደ ርእይ ላይም የተንፀባረቀው ይሄው መሆኑን ማስታወስና የዚህ ጽሑፍ አንባቢያንን ለተጨማሪ ንባብ መጋበዝም ተገቢ ይሆናል። በአውደ ርዕዩ ላይም ”አገር በቀል ዕውቀትና ትምህርቱን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ባለመካተቱ ፊደላዊና ከ’እኛ’ ይልቅ ’እኔ’ የሚል ማህበረሰብ ተፈጥሯል” የሚለው፤ እንዲሁም ”የአገር በቀል እውቀትና ትምህርትን ፋይዳ በሚገባ በመረዳት ሞራልና ግብረገብነትን የተላበሰ ኅብረተሰብ መፍጠር” ይገባል የሚሉት ሀሳቦች በስፋት መንፀባረቃቸውንም ጠቆም ማድረግ ይገባልና አድርገነዋል።
እየተነጋገርን ያለነው፣ እየተነጋገርንብት ያለነው አገር በቀል እውቀት አካል የሆነውን፣ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓትን በተመለከተ ነውና ወደ’ዛው እናዝግም።
ከሚመለከተው ተቋም የተገኘውና ከርእሰ ጉዳያችን ጋር የሚሄደው መረጃ እንደሚያሳየው ”የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የፍትህ ሥርዓቱን ጠንካራ፣ ውጤታማና ብቁ ለማድረግ እና ኃላፊነትን በብቃት ለመወጣት እንዲቻል አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች እየወሰደ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህም አንጻር የፌዴራል የፍትሕና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ዋና ዋና ተልዕኮዎችና ተግባራት አንዱ ችግር ፈቺ የፍትህና የሕግ ጥናት ማካሄድ ነው፡፡ ይህን ተልዕኮ ለመወጣት የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ተደራጅቷል፡፡
በየዘርፉ ያሉ ነባር ሕጎችን ለማጠቃለል፣ ከወቅቱ የእድገት ደረጃ ጋር ለማጣጣም እና ለአጠቃቀም ምቹ ሆነው እንዲሻሻሉ ለማድረግ፤ የአገሪቱን የሕግ ሥርዓት ለማሟላት የሚያስችሉ አዳዲስ ሕጎችን ለማውጣት፤ የሕግ ትምህርት እና ሥልጠናን ለማጠናከር፤ የፍትህ አካላትን የሰው ሃብት ብቃት ለማሳደግ፣ አደረጃጀታቸውን እና አሰራራቸውን ለማሻሻል፤ እና ከሕግ ብዝሃነት ጋር የተያያዙ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እና ሌሎች ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚረዱ ጥናቶችን ማካሄድ የዚህ ዘርፍ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡” የሚል ሲሆን፤ ”… ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት …” የሚለውን ከስሩ አስምረንበት ብናልፍ ተገቢ ይሆናል።
ዶ/ር ጠና እና ሌሎችም በዚሁ ሀሳብ በመስማማት ”እሴቶቹን ለማጠናከርም የአስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞችን ከባዕድ አገሮች ከማምጣት ይልቅ የአገር በቀል ዕውቀቱን ከሳይንሱ ጋር በማስታረቅ ተስማሚውን መቅረፅ አስፈላጊ” ነው ያሉትን ጉዳዩ ይሰምር ዘንድ እዚህ እንድገመው።
”በኀብረተሰቡ መካከል የነበሩ የመተሳሰብና አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴቶች በመሸርሸራቸውና በመዳከማቸው የችግር መፍቻ መሳሪያ በመሆን እያገለገሉ” አይደሉም። ”በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭቶችና አለመግባባቶች ተበራክተው በየክልሉ ዜጎችን ከቀዬአቸው እያፈናቀለ ያለውን ችግር ለመፍታት አገራዊ እሴቶቹ ጠቃሚ በመሆናቸው”ም ተገቢውን ትኩረት ማግኘትና በተግባር ላይ መዋል አለባቸው ነው የሚሉት ዶክተሩ።
”አገር በቀል እሴቶችን በማደራጀት ጥቅም ላይ ማዋል አለመቻሉ ጉዳት እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ጠና፤ ከውጭ የሚመጡ እሴቶች ለአገሪቱ በሚሆን መልኩ ተቀምረው አለመወሰዳቸው ለተለያዩ ችግሮች መንስኤ” መሆናቸውንም ነው አስቀምጠው ያለፉት ።
ምን ማለት ነው፣ “የመረዳዳት፣ የመከባበር፣ አብሮ የመኖርና የመሳሰሉት አገር በቀል አቅማችን እየተዳከመ መምጣት የማህበራዊ እሴቶቻችን እየተዳከሙ እንጂ እየተጠናከሩ መምጣታቸውን አያሳዩም”። በመሆኑም፣ ”ለአገር በቀል እሴቶች ተገቢውን ዋጋ መሰጠት” የግድ ይሆናል እያልን ነው። ምሁራንም ”በተለያየ የአገሪቷ አካባቢዎች ያሉ እሴቶችን በማጥናት ሁሉም የሚግባባበት እሴት ማጎልበት” አስፈላጊነት፤”ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያግባባ እሴታዊ ስርዓት (ቫልዩ ሲስተም) ሊፈጠር” የሚገባ መሆኑን ነው ደጋግመው የሚመክሩት። ለዚህ ደግሞ ”እሴቶችን የሚያጎለብት ተቋማዊ አደረጃጀት” ያስፈልጋል። ይህ ጸሐፊም በአዲስ ዘመን (ነሐሴ 20 /2014 ዓ.ም) ላይ”አገር በቀል እውቀት እና ወቅታዊ ይዞታው” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍም ይህንን አረጋግጧል።
አቶ ሰለሞን አረዳ እንደሚሉት ”የዳኝነት አካል በኢትዮጵያ ሥነመንግስት ረጅም ታሪክ አለው፡፡ በተለይም ደግሞ በዘመናዊ መንግስት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ወይም በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመናዊ ሕጎች በኢትዮጽያ እንዲወጡ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ከአውሮፓ በመውሰድ ከአገር ሁኔታ ጋር እንዲዛመዱ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡” ያሉትንም ሆነ፣ አብዱልፈታ አብደላህ በ”የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የአስተዳደር፣ የሕግና የፍትህ ሥርአቶች ማውጫ ቅጽ 1” (2010 ዓ.ም) መጽሐፋቸው ላይ ”የሀገራችን የመንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ የሕግና የፍትህ ሥርአት እስከ ሃየኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በሀገር በቀል እውቀቶችና እሴቶች የሚመራ እንደ ነበር አይዘነጋም።” በማለት በ”እንደ መግቢያ” ገፃቸው ላይ ያሰፈሩትን ወስደን ስንመለከት በርካታ ቁም ነገሮችን የምናገኝ ሲሆን፣ አንዱም በጉዳዩ ላይ ቀደምት የመሆናችን ጉዳይ፤ ቀጣዩ ደግሞ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ ስንገለገልበት የኖርነው በቀድሞው፣ በባህላዊው የፍትህ ስርአት ነበር ማለት ነው። በመሆኑም፣ የአገራችን ባህላዊ የፍትህ ስርአት ገና ለገና ”ባህላዊ” ስለተባለ ብቻ አሽቀንጥረን ልንጥለው አይገባም እያሉን ነው።
አብዱልፈታ ”አብዛኛዎቹ የሀገር፣ የሕዝብና የመንግሥት ችግሮቻችን መፍትሄዎች ከሀገር በቀል የአስተዳደር፣ የሕግና የፍትህ ሥርአቶቻችን ውስጥ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም።” ያሉትን፤ እንዲሁም፣ በዚሁ ስራቸው ”ብዙዎቹ ምሁራኖቻችንና የመንግሥት መሪዎቻችን [ለችግሮቻችን] መፍትሄ ፍለጋና ለልምድ ልውውጥ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ሩቅ ምሥራቅና ሩሲያ የሚያንከራትቷቸው ጉዳዮች ሁሉ በእኛው የባህል እሴቶች ውስጥ መኖራቸውን ካወቅንና ከተገነዘብን ቆይቷል።” ሲሉ መታዘባቸውን ስንመለከት ርእሳችንን ”ማን እንደ አገር በቀል …” በማለት ማንነቱን መቀንበባችን ትክክል ሆኖ እናገኘዋለን።
”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ከሚለው ጀምሮ፣ የትም አገር ቢኬድ አገር በቀል እውቀት (IK)ን የሚተካከል መፍትሄም ሆነ አሰሪ መሳሪያ አይገኝም። ናይጄሪያ ከባህላዊ መድሀኒት ጀምሮ ትጠቀምበታለች። ሩዋንዳ ላምን (ይህ አንዱ ምሳሌ ብቻ ነው) የሰላም፣ የብልፅግና፣ የግጭት ማስወገጃ፣ የእናትነት … ተምሳሌት በማድረግ የእለት ተእለት ስራዋን ታከናውናለች። ህንድ፣ ሩሲያ (የቻይናን አንስተን አንጨርሰውም ) እና ሌሎችም አገር በቀል እውቀታቸውን ለመድህናቸው ሲጠቀሙበት እንጂ የራሳቸውን ጥለው የሌላ ፍለጋ ሲኳትኑ አይታዩም። እንግሊዝ (ከ’ኛ የወሰደችውን አስተርጉማ ነው የሚሉ አሉ) አገር በቀል ባህላዊ መድሀኒትን የሚያብራራ ዳጎስ ያለ መጽሐፍን አሳትማ ለሕዝቧ እነሆ ካለች አመታትን ያስቆጠረች መሆኑ ሌላው ለዚህ ጽሑፍ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው።
ባጠቃላይ፣ ያለ አገር በቀል እውቀትና ዘርፎቹ የትም አይደረስምና የሚመለከተው ሁሉ ለአፍታም ቸል ሊለው አይገባም እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም