ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሃብት፣ ምቹ የአየር ጸባይና በቂ የሰው ኃይል ምክንያት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኗ ይታወቃል። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቱን መሳብ የሚችሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮቿ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ናቸው። መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ለመሳብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑም ለዚሁ ነው። ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ወዲህ ከአሁን በፊት ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ያልሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ጭምር ክፍት በማድረግ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረች እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
የውጭ ባለሀብቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጠሩ የተለያዩ አስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር መዋለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ኢንቨስት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ለዚህም መንግሥት ለባለሃብቶቹ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን በመፍጠር ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከባለሀብቶች በማሰባሰብ እንዲሁም ጊዜ ሰጥቶ በማዳመጥ ምላሽ ለመስጠት ያለው ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ ከሆኑ ምቹ ሁኔታዎች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው ሰላም እንደመሆኑ በአሁን ወቅት በአገሪቱ እየመጣ ያለው ሰላም ለኢንቨስትመንት ጥሩ አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ ብዙዎች ያነሳሉ። ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከገባችበት ጦርነት ተላቃ ወደ ሰላማዊ ድርድርና ውይይት እየመጣች ነው። ይህ ጦርነት የማቆም ስምምነትና ድርድር በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚፈጥረው አጋጣሚ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
መንግሥት ከጦርነት የሚገኝ ኪሳራ ብቻ እንደሆነና ትርፍ የሌለው መሆኑን በማመን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ከሰላም የምታተርፈው ኢትዮጵያ እንደሆነች ተናግረዋል። ከሰላም የሚጎዳ ኢትዮጵያዊ የለም ባይባልም፤ እንደ አገር ሲታይ ሰላም ትርፋማ እንደሆነ ተናግረው ሰላም የሚያስከፋቸው ኃይሎች የጦርነት ነጋዴዎች ናቸው ብለዋል። “ውሃ በወንፊት ዘግኖ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ መውሰድ እንደማይቻለው ሁሉ ሰላምና ብልጽግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነት ማቆም በእጅጉ ያስፈልጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሰላማችንና ለብልጽግናችን ስንል ጦርነት ማቆምን ቀዳሚ ምርጫችን አድርገናልም ብለዋል።
በአሁን ወቅትም ቀዳሚ ምርጫ የሆነውን ሰላም ለማረጋገጥ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የነበረውን ጦርነት ገታ ማድረግ ተችሏል። ጦርነቱን ለማቆም በተደረሰው የሰላም ስምምነትም በርካታ ትርፎች የሚገኙ እንደሆነ ይታመናል። በተለይም የኢትዮጵያን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ በኩል ሰላም የሚኖረው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባደረገው የምክክር መድረክ አመላክቷል። ኮሚሽኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የኢንቨስትመንት አስፈጻሚ አካላት ጋራ በጎንደር ከተማ ባደረገው የምክክር መድረክ ላይ አሁን እየታየ ያለው የሰላም ሂደት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱን ለመሳብ ያለው ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈጠረው የሰላም ስምምነት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶችን በብዛት ለመሳብ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከምንም በላይ ሰላም የሚያሻው ጉዳይ እንደመሆኑ በአገሪቱ ሰላምን ማረጋገጥ የግድ ነው። በተለይም የውጭ ባለሀብቶች በአንድ አገር ኢንቨስት ለማድረግ ሲነሱ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው የሚሆነው የሰላም ጉዳይ ነው። ሰላምና መረጋጋት ካለ ኢንቨስተሩን ማቆየት የሚያስችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
የሰላም ስምምነቱ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ በኮቪድና በጦርነቱ የተቀዛቀዘውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በቀጣይ ለማካካስ የሚያስችል አመቺ እድል እንደሚፈጥር ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ባለፈው አመት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ጠቁመዋል። ይህንንም ዘንድሮ ወደ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
እቅዱ ተግቶ መሥራትን የሚጠይቅና የሰላም ስምምነቱንም እንደ አንድ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ በትኩረት ለመፈጸም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የሆኑ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ነው የጠቀሱት። በአገሪቱ ከሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች መካከልም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የአይሲቲ ዘርፍ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ አብዲ በበኩላቸው፤ ክልሉ በችግሮች ውስጥ ቢሆንም የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት አልተቋረጠም በማለት ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አንስተዋል። በክልሉ በዘንድሮ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 131 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አንድ ሺህ 180 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በአሁን ወቅትም በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት በቀጣይም ለክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተው፤ በተለይም ክልሉ በጦርነት የቆየ እንደመሆኑ የተጀመረው የሰላም ውይይት ለዘር መነቃቃት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጉደታ አበበ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ያለ ስጋት እንዲሰማሩ እድል የሚፈጥር እንደሆነ በማስረዳት ለኢንቨስትመንት ቀዳሚ ጉዳይ ሰላም ነው ብለዋል። በክልሉ በበጀት አመቱ 400 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸውን ባለሀብቶች ለማስተናገድ እቅድ መያዙን ጠቁመው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 42 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከአንድ ሺ 700 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ማስተናገድ እንደተቻለ ነው ያስረዱት። ክልሎቹ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳለጥ በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ ማስቀመጥ ችለዋል።
ኢትዮጵያ ባሏት የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚሳቡ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ስለመኖራቸው ያነሱት የጊዜ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ወይዘሮ ጊዜሽወርቅ ተሰማ ናቸው። እንደሳቸው ገለጻ፤ ማንኛውም ሰው አገር በጦርነት ውስጥ ስትሆን የሚሰማው ጭንቀት እንዳለ ሁሉ የቢዝነስ ሰዎችም ሰላም ከሌለ የበዛ ጭንቀት የሚገጥማቸው መሆኑን አንስተዋል። በተለይም የውጭ ባለሃብቶች ከፍተኛ መጠን ያለውን መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ኢንቨስት የሚደርጉ እንደመሆናቸው የሰላም ጉዳይ በእጅጉ የሚያስጨንቃቸው ነው በማለት የአገር ሰላም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ዋናው ቁልፍ እንደሆነ አስረድተዋል።
በቅርቡም በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የነበረውን ጦርነት ለማቆም ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የተደረገውን የሰላም ውይይት መነሻ በማድረግ በአገር ውስጥ ያሉ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች ደስታቸውን እንደገለጹ አስታውሰዋል። በሥራ ባህሪያቸውና ባላቸው አገራዊ ተሳትፎ አማካኝነት ከተለያዩ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ጋር በየጊዜው የሚገናኙት ወይዘሮ ጊዜሽወርቅ፤ አሁን እየታየ ያለው የሰላም ስምምነት ጅማሮ የውጭ ባለሃብቱን የበለጠ የሚያስደስት እንደሆነ ገልጸው፤ የተጀመረው የሰላም ስምምነት በትክክል መሬት ወርዶ ተግባራዊ መሆን ሲችል ደግሞ በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይበልጥ የሚሰፋ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
በአገር ውስጥ ለሚገኙ የውጭ ኢንቨስተሮችም የተጀመረው የሰላም ሂደት መስመር እየያዘ እንደሆነ እያስረዳን ነው የሚሉት ወይዘሮ ጊዜሽወርቅ፤ ይህን የምናደርገው የገቡት እንዳይወጡ ነው። ከዚህ ባለፈ የተጀመረው የሰላም ስምምነት ዘላቂነቱ ከተረጋጋጠ በአገር ውስጥ ካሉት የውጭ ኢንቨስተሮች በተጨማሪ ሰፊ የኢንቨስትመንት ፍሰት ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያ ገና ብዙ ያልተነኩ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ተናግረዋል።
ለምጣኔ ሃብት ወሳኝ የሆነው ኢንቨስትመንት በተለያየ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠር የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ሲቀዛቀዝና ሲጎዳ ይስተዋላል። እንደሚታወቀው ሰላምና መረጋጋት ለኢንቨስትመንት በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለምጣኔ ሃብቱ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ያለው ነው። ይሁንና የውጭ ባለሃብቶችን ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ እንዲሁም በአገር ውስጥ ያሉትን ባለሃብቶች ለማቆየት የውስጥ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋትን ማስጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል።
በተለያዩ ምክንያቶች መንገራገጭ የሚታይበት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በኢንቨስትመንቱ በይበልጥ የሚደገፍ ቢሆንም የሰላም ዕጦቱ ጋሬጣ ሆኖበት ቆይቷል። ይሁንና አሁን በአገሪቱ እየመጣ ባለው የሰላም ውይይት መነሻነት ዘርፉ ከገባበት ችግር ሊላቀቅ የግድ የሚለውና ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ይታመናል።
በዋናነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን በተለይም የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ በኩል ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም ከሰሞኑ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ የተለያዩ አገራት ከመጡ ባለሃብቶች ጋር የጋራ ስምምነት ማድረጉን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ አገር ውስጥ ከገቡት የውጭ አገር ባለሃብቶች መካከልም የባንግላዲሽ ባለሃብቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ባለሀብቶቹ በሶላር ሃይል፣ በሞባይል ባንኪንግ እንዲሁም በአይሲቲ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቬስት በማድረግ የሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲዳብር እየተሰራ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ፕሮጀክቱንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት የሚደረግ መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2015