ኢትዮጵያ በብዙ ጅረቶችና በትላልቅ ወንዞች የተከበበ በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አላት፡፡ በግብርናው ዘርፍ ለሚታየው ተጨባጭ ለውጥ የመስኖ ልማት መስፋፋት እጅግ መሠረታዊ ከመሆኑ አንጻር ይህን የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል የአርሶ አደሩን ሕይወት የበለጠ ለማሻሻል እና ግብርና በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋጽዖ ይበልጥ ለማሳደግ በእጅጉ ይረዳል፡፡ በአፍሪካ ሊታረስ ከሚችለው ጠቅላላ መሬት ስድስት በመቶ የሚሆነው ብቻ እስካሁን ድረስ በመስኖ የለማ ሲሆን የተቀረው መሬት ግን የመልማት ከፍተኛ አቅም ያለው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ የልማት ሬሾ ውስጥ የተሻለ እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው ሀገራት መካከል ብትሆንም ሀገሪቱ ካላት የውሃ ሃብት እና ለመስኖ ምቹ ከሆነው የመሬት ሀብት አንጻር እስካሁን የለማው የመሬት መጠን የሚያኩራራ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በመስኖ ሊለማ ከሚችለው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው፡፡
እ.አ.አ. በ2018 የማላቦ ሞንትፔለር ፓናል ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከ1994 አንስቶ የመስኖ ልማት እድገቱ በ52 በመቶ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን በ2007 ብቻ ለመስኖ ዝግጁ የሆነው የሚታረስ መሬት በሄክታር 848 ሺህ 340 ሄክታር ደርሶ እንደነበር በሪፖርቱ ተመዝግቧል፡፡ ከዚያ በኋላ የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ለመስኖ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የአስር ዓመት እቅድ ላይ ለመስኖ ፕሮጀክቶች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ ሀገሪቱ ለመስኖ ልማት ከፍተኛ በጀት መድባ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፤ በተለይም በቆላማ አካባቢዎች ለመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ
ይገኛል፡፡ በተለይም መንግሥት በወሰደው ተነሳሽነት የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሚደረገው ከፍተኛ ጥረትም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ግብ ተቀምጦ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል፡፡
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ካሉ አነስተኛ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች መካከል ትሪድል ፓምፕ፣ ዋሸር ፓምፕ፣ ሮፕ ፓምፕ እና የመሳሰሉት ቴክኖሎጂዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደ መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በሀገራችን በመጠኑም ቢሆን አገልግሎት መስጠት እየጀመሩ ነው፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎችን ለማዳረስ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚሉት፤ አንዳንድ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች በሀገሪቱ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፤ ሀገሪቱ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች መካከል የወለል መስኖ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡ የወለል መስኖ በአገራችን በአንፃራዊነት ለረዥም ዓመታት የተለመደና እየተተገበረ ያለ የመስኖ ቴክኖሎጂ ሲሆን ለጥጥ፣ ለበቆሎ፣ ለሸንኮራ አገዳ ወዘተ እና ሰፋፊ ሄክታር ለሚሸፍኑ ሰብሎች ተስማሚ ቴክኖሎጂ ነው።
ተፋሰስን መሠረት በማድረግ የፈሮው (የቦይ) መስኖን በማቀናጀት የሚተገበር ሲሆን የውሃ ፍሰቱ ጥሩ በመሆኑ አፈር ውስጥ ሰርጎ ለመግባት
አይቸገርም፡፡ በአብዛኛው ሜዳማ በሆኑ ማሳዎች ጥቅም ላይ
ይውላል፡፡ የወለል መስኖ አካል የሆነው ተፋሰስ መስኖ ጎርፉን በትንንሽ ቦዮች በመጥለፍ ተፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ይህም ለሜካናይዝድ ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች እንደሚያገለግል አብራርተዋል፡፡
የወለል መስኖ አካል የሆነው የፈሮው (ቦይ) መስኖ በሰፋፊ ማሳዎች ላይ ትናንሽ ሰርጦችን በመፍጠር ጥቅም ላይ እንደሚውል ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ ውሃው በእያንዳንዱ ጉድጓድ አናት ጫፍ ላይ በስበት ኃይል የሚፈስ ሲሆን ይህም በተዘጋ ቧንቧና በሳይፈን አማካኝነት ውሃውን ይረጫል፡፡ የፈሮ መስኖ በተለይ ለጥጥ፣ ለበቆሎ ለሸንኮራ አገዳና መሰል ሰፋፊ ሄክታር ለሚሸፍኑ ሰብሎች ተስማሚ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ በስፋትም ባይሆን የርጭት ስፕሪን ኪለር የሚባለው በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሞክሯል፡፡ በአማራ ክልል ራያ ቆቦ አካባቢ፣ በትግራይ ክልል ራያ አዘቦ አካባቢ ስፕሪን ኪለር ጥቅም ላይ ሲውል ነበር፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም ስፕሪን ኪለር የሚባለው የመስኖ ዘዴ ተሞክሯል፡፡
የሀገሪቱን የመስኖ ልማት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እስካሁን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም፡፡ የመሐል ምሰሶ መስኖ ቴክኖሎጂ እና የግፊት ተንቀሳቃሽ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች ለሀገራችን የመስኖ ዘርፍ ሽግግር ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ናቸው፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ የመሐል ምሰሶ መስኖ (Center Pivot Irrigation) ቋሚ ምሰሶ ላይ በተሠራ የብረትና የአሉሚኒየም ቧንቧ ተሽከርካሪ ማማዎች ላይ በተገጠሙ የውኃ መስመሮች የውሃ ማጠጫ መስኖ ዘዴ ነው። ውሃ ተሸካሚው ማሽን 360 ዲግሪ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በክቡ መሐል ካለው ምሰሶ ውኃውን በሁሉም ቅርንጫፎች ይረጫል።
ለመሐል ምሰሶ አቀማመጥ ምቹነት ሲባል መሬቱ በተመጣጣኝ ሁኔታ ለጥ ያለ ሜዳ ይፈልጋል፡፡ ሰለሆነም ይህ ቴክኖሎጂ ለቆላማና ሜዳማ አካባቢዎች በጣም ተስማሚ ነው፡፡ መሐል ምሰሶ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የመስኖ እርሻ ልማትና የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ እንዲጨምር አድርጓል።
በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውስትራሊያ፣ በኒውዝላንድና ብራዚል እንዲሁም ከሰሃራ በረሃ በታች ባሉ ሀገራትና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የመሐል ምሰሶ መስኖ ልማት በሀገራችን ኢትዮጵያ በተወሰኑ አካባቢዎች የተጀመረ ሲሆን በተለይም ራያ፣ ሑመራ፣ አፋርና ሶማሌን በመሳሰሉ ሞቃታማና ቆላማ አካባቢዎች ላይ ቢተገበር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡
የመሐል ምሰሶዎች በተለምዶ ከ500 ሜትር ርዝመት ክብ ራዲየስ ያነሱ ሲሆኑ በመደበኛነት የተለመደው መጠንም 400 ሜትር ርዝመት ያለው ራዲየስ ማሽን ነው። የተለመደው 400 ሜትር ራዲየስ የሰብል ማሳ 125 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡ ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂው ውድና በቅርብ የማይገኝ በመሆኑ እንዲሁም በሜዳማ አካባቢዎች ብቻ የሚያገለግል ሆኖ የራሱ ውስንነት እንዳለበት ይነሳል፡፡
በሀገራችን በስፋት ጥቅም ላይ ቢውል ከፍተኛ ጠቃሜታ የሚያስገኘው እና እስካሁን ድረስ ብዙም ጥቅም ላይ ያልዋለው የግፊት ተንቀሳቃሽ የመስኖ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የግፊት ተንቀሳቃሽ የመስኖ ቴክኖሎጂ በሚባለው የቴክኖሎጂ ዓይነት ቴክኖሎጂው በፓይፕ ወይም በቱቦ አማካኝነት ውሃውን በበርካታ ቀዳዳዎቹ እንዲረጭ በማድረግ ማሳውን በቂ ውሃ
ያጠጣል፡፡ መሳሪያው እየተሽከረከረ ሌሎች ስፍራዎችን ውሃው በርጭት እንዲያዳርስ ያደረጋል።
ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የግፊት ተንቀሳቃሽ መስኖ በእርሻው መካከል ረጅም የውሃ ምሰሶ በመትከል ውኃውን በቋሚ የገመድ ቱቦ በማፍሰስ የሚተገበር ሲሆን ከ100-130 ሚሊ ሜትር ወይም ከአራት እስከ አምስት ኢንች ዲያሜትር የአሉሚኒየም ቧንቧ ለዚህ አገልግሎት ይውላል። ቴክኖሎጂው በውኃው መጠንና በሚለማው ሰብል ቁመት ላይ የተመረኮዘ ነው። የግፊት ተንቀሳቃሽ መስኖ ለአሠራር ምቹ በመሆን፣ ተለዋዋጭ ባህሪ ባለመኖሩ፣ በብዛት በመርጨት፣ ትንሽ ቦታ በመያዝ፣ ወጭን በመቀነስ፣ ዝቅተኛ ኃይል በመጠቀምና የውሃ ጥራትን በማሳደግ ለመስኖ ልማት አስተዋፅዖው ከፍተኛ ነው፡፡
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ አብዛኞቹ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች በሀገራችን ውስጥ ገና በጅምር ደረጃ ላይ ያለ ከመሆኑ አኳያ እንዲሁም እንደ ሀገር በቂ ውሃ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ እነዚህን ቴክኖሎጂዎችን ከማስፋፋት ይልቅ የመስኖ ግድቦችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማስፋቱ ሥራ የበለጠ ትኩረት አግኝቷል፡፡
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በመጪው ዘመን በሀገራችን ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የመዋል እድል እንዳላቸው የሚያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ የውሃ እጥረት ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ እነዚህን ዘዴዎች መጠቀም ይቻላል፡፡ በተለይም እንደ ሀገር የከርሰ ምድር ውሃን በስፋት መጠቀም የሚጀመርበት ደረጃ ላይ ሲደረስ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ አብዛኞቹ የዘመናዊ መስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎች ንጹሕ ውሃ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በተለይም ደለል የሌለው ውሃ
ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጅምር ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የማስፋፋት ሥራው በትኩረት የሚሠራ ይሆናል፡፡
መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዙ የሚችሉ የመስኖ የፈጠራ ሥራዎች እና ቴክኖሎጂዎች ግብይት ዙሪያ መዋቅራዊ አደረጃጀት ያላቸው የማምረቻ ድርጅቶች የሚሳተፉበትን ሁኔታ መፍጠር ቢችል ድርጅቶችና በተጠቃሚው መካከል ያለውን ልዩነት ከማጥበብ አንጻር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ይህም የቴክኖሎጂዎቹን የግብይት ዋጋ ከአርሶ አደሮቹ አቅም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን የአምራች ድርጅቶቹን የመሸጫ ዋጋ ቋሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል ይሆናል፡፡
ሀገሪቱ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንጻር በዝናብ እየጠበቁ በዓመት አንድ ጊዜ በማምረት ብቻ የሀገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ ቀርቶ የሀገሪቱን ሕዝብ መመገብ የማይታሰብ ነው፡፡ በመሆኑም የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይም ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሮች ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርቱ በር የሚከፍቱላቸው ናቸው፡፡ ይህም አርሶ አደሮቹ የተሻለ ገቢ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡ ለዚህም ነው በዓለማችን ያሉ ሀገራት እነዚህ ቴክኖሎጂዎችን አነስተኛ መሬት ላላቸው ለአርሶ አደሮቻቸው ለማድረስ ርብርብ በማድረግ ላይ የሚገኙት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም እነዚህን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለአርሶ አደሮች እንዲዳረሱ ማድረግ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ወደ አርሶ አደሮቹ እንዲደርሱ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ለመንግሥት ብቻ የሚተው
አይደለም፡፡ በትብብር መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመንግሥት መዋቅር ስር በየደረጃው ካሉ የመንግሥት መዋቅሮች በተጨማሪ የሀገር ውስጥና ውጭ ሀገራት ባለሃብቶች ከፍ ያለ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ በተለይም በአነስተኛ ዋጋ የሚገዙ የመስኖ የፈጠራ ውጤቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት በዘርፉ ከተሠማሩት የውጭ ሀገራት እና የሀገር ውስጥ የግል ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም