ባለውለታዎቻችን ብዙ ናቸው። ውለታ ሠርተው ያለፉ እንዳሉ ሁሉ፤ ውለታ ሲሠሩ ኖረው አሁንም እየሠሩ ያሉት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እየኖሩ የሚያኖሩ፤ እየሠሩ የሚያሠሩ፤ እየተናገሩና ’ጻፉ የሚያስተምሩን ብዛታቸው ጥቂት አይደለም። በመሆኑም፣ እናስታውሳቸዋለን፤ ስለ ውለታቸው ሲባልም እናወድሳቸዋለን!!!
የዛሬው የዓምዳችን እንግዳ ለኢትዮጵያውያን ቀርቶ ለዓለሙም እንግዳ አይደሉም። በሁሉ ነገራቸው ይታወቃሉ። በብዕራቸው ጽፈዋል፤ እየጻፉም ነው። በአንደበታቸው ተናግረዋል፤ እየተናገሩም ነው። በሃይማኖታቸው ስለ እምነትና ሀገራቸው ሰብከዋል፤ እየሰበኩም ነው። ፀብ ይቅር፣ ሰላም ይሰፍን ዘንድ መክረዋል፤ እየመከሩም ነው። ወዘተርፈ …..። እነሆ ዛሬም “ይድረስ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ” ሲሉ ከበር ቆመዋል።
አደም ካሚል ፋሪስ ይባላሉ። በዕድሜያቸው 70ዎቹን ሲያጋምሱ፣ በሥራቸው ሁለ-ገብ ናቸው። በትምህርታቸው (በአካዳሚክ ማዕረጋቸው) እስከ ዩኒቨርስቲ መምህርነት ደረጃ የደረሱ ሲሆን፣ በሥራዎቻቸው የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ደርበዋል። በአስተዋፅዖዋቸው ከዚህ መለስ የሚባሉ አይደሉም። እስካሁን ድረስ 33 የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ያበረከቱ ሲሆን፤ 7ቱ ለሕትመት በቅተዋል በአንባቢያን እጅ ይገኛሉ። ቀሪዎቹ በመሳቢያ ውስጥ ቁጭ ብለው የሕትመት ጊዜያቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የጥናትና ምርምር መስካቸው ሰፊ ቢሆንም፣ በተለይ ትኩረታቸው ኢትዮ-ዓረብ ጉዳይ ላይ ነው።
ዶ/ር አደም በእምነታቸው ፅኑ ሲሆኑ በአተያያቸው ዓለም አቀፍ ናቸው። ሰውየው፣ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በኢትዮጵያዊነታቸውም በሄዱበት ሁሉ ደረታቸውን ነፍተው፤ አንገታቸውን ቀና አድርገው ነው አቋቋማቸው። ተናግረው አሳምነዋል። ተሟግተው ረትተዋል። ቆመው ያስተማሩ ሲሆን፣ ገስፀውም መልሰዋል።
ሰውየው እስልምና ሃይማኖታቸው፤ ሐበሻነት ኩራታቸው፤ ኢትዮጵያዊነት ውስጣቸው ነው። በመሆኑም፣ 15 ክፍሎች ያሉትና ለ11 ዓመታት (የግድቡ መሠረት ድንጋይ መጣሉን ተከትሎ) በዓባይና ግድቡ ጉዳይ ላይ ጥናት አካሂደው ”ይድረስ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ” ለማለታቸውም መነሻቸው ይኸው ነው።
በዓረቡ፣ ስለኢትዮጵያ የሚነገረው 80 በመቶ በዓረቢኛ ነው የሚለት ዶክተሩ ያልሄዱበት የለም። ከአፍሪካና ዓረቡ ዓለም እስከ እስራኤል ዘልቀዋል። ሰላጤውን ጠልቀው ገብተውበታል። የምዕራቡን ዓለም ተንኮሎችንም አንድ ሁለት … በማለት ይቆጥሯቸዋል። ዓባይን ከ—እስከ ፈትሸውታል። ሃይማኖቶችንና የሃይማኖት ጉዳዮችን መርምረዋል። እሚያጣላውን ሳይሆን አንድ የሚያደርገውን አመላክተዋል። መሠረቱን አሳይተዋል። የሐበሻን ሚናና ድርሻ በመረጃና ማስረጃ አስደግፈው ለአደባባይ አብቅተዋል። (ካስፈለገ ”ሐበሻና የሐበሾች ኩራት እና ሞገስ በእስልምና” መጽሐፋቸውን መመልከት ይቻላል።)
ለሚዲያ ቅርብ የሆኑትና አማርኛን፣ አረቢኛን፣ እንግሊዘኛን እያገላበጡ የሚጠቀሙት ዶክተሩ ስለ ሰው ልጅ ሰላም ጮኸዋል፤ አንድነትንና በሰላም አብሮ ስለመኖር ሳይታክቱ ለፍፈዋል። ልዩነትን ኮንነው አንድነትን ”ይበጀናል” ብለዋል። ሃይማኖታዊ ማንነቱን በሚገባው ቋንቋ አስረድተዋል። ብዙ … ብዙ … ሀሳቦችን ሰንዝረዋል፤ ተግባራትንም አከናውነዋል። (ለምሳሌ ያህል፣ በሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት በተዘጋጀው የሰላምና የአንድነት ኮንፈረንስ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክትና የሰጡትን ትምህርት ከዩቲዩብ መመልከት ይቻላል።)
ሰውየው ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሰላም፣ ስለ …. አውርተው የሚጠግቡ፤ ሠርተው የሚደክሙ፤ ጽፈው የሚረኩ አይደሉም። በመሆኑም ዛሬም ”ይድረስ ለኢትዮጵያውያን” በማለት ከበር ሲቆሙ ከላይ ካልናቸው በተጨማሪ አንዱ ምክንያታቸው ይኸው ነው። ስለ ማንነትና ተግባራቸው ማውራቱን እዚሁ ላይ እናቁምና ወደ ”ይድረስ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ” መልዕክታቸው እንሂድ።
ዶ/ር አደም ካሚልን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን አነጋግረናቸዋል። በተሟላ ትህትናና አቀራረብ አስተናግደውናል። በሀሳብ ልውውጣችን ወቅት አብዛኛውን ሰዓት እሳቸው ይጠቀሙበት ዘንድ ፈቅደናል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ የሠሩ እንደ መሆናቸው መጠን ስኬት ፈተናቸውን ያጋሩን ዘንድ መሻት ነውና ዶክተሩ ይናገራሉ።
ይድረስ ለኢትዮጵያውያን
ኢትዮጵያ ሃብታም ሀገር ነች። ኢትዮጵያ ላይ ቁጭ ብሎ ስለድህነት ማሰብና ማውራት ከንቱነት ነው። ተስማሚ የአየር ጸባይ፤ለም መሬት፤ በማዕድን የበለጸገችና በቱሪዝም ረገድም የሰው ልጅ መገኛ የሆነች ሃብታም ሀገር ውስጥ ተቀምጦ ስለድህነት ማውራት ከንቱነት ነው።
የኢትዮጵያን ያህል ተፈጥሮ ያዳላለት ሀገር የለም። የኢትዮጵያን ያህል ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ሃብት ያለው ሀገር የለም። የኢትዮጵያን ያህል በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቁርዓን ተደጋግሞ ስሙ የተነሳ ሀገር የለም። የኢትዮጵያን ያህል ጀግና ሕዝብ የለም። የኢትዮጵያን ያህል ጥንታዊ ሀገር የለም። የኢትዮጵያን ያህል ውብ ሀገር የለም።
እነዚህን ሀብቶች ይዛ ኢትዮጵያ መቸገሯ ሁሉንም የሚያስገርም ነው። ሰው እንዴት ሃብት ላይ ቁጭ ብሎ ይቸግረዋል። ሰው እንዴት የተትረፈረፈ ምግብ ላይ ቁጭ ብሎ ይራባል። ሰው እንዴት አባይን የሚያክል ወንዝ ይዞ ይጠማል። እንቆቅልሽ ነው።
ይህንን እንቆቅልሽ ለመፍታት ጥናትና ምርምር ቢያስፈልገውም በቀላሉ ለሚያስብ ሰው ግን የኢትዮጵያን የሥራ ባህል ደካማ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ይረዳል። ይህንን ደካማ የሥራ ባህል ከስር መሠረቱ ለመፍታትም ኢትዮጵያ እንቆቅልሽዋን ለመፍታት ጉዞ ጀምራለች። ትልቁን ወንዟን አባይን ማልማት በመጀመር ጨለማውን መግፈፍ ጀምራለች። የዓባይን ግድብ በመጀመር ሦስተኛውን የውሃ ሙሌት በማከናወን እንቆቅልሹን መፍታት ተያይዛለች። የስንዴ ልማቱን በማፋፋም ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሀገራት ኤክስፖርት ማድረግ ጀምራለች።
የህዳሴው ግድባችን ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈናል። ብዙ ትግል አካሂደናል። በሂደቱም የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የዓባይ ግድባችንን ለማስተጓጎል ለምን እንደፈለጉ ደርሰንበታል። በዚህ ላይ ተገቢውን ጥናት አድርገናል። ጥናታችንም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ዓባይ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ጥናት 15 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ሁሉንም ሰብሰብ፣ ጨመቅ አድርገን ስናያቸው የሚከተለውን ይመስላሉ።
እነዚህ ሀገራት አፍሪካን በተመለከተ በእውቅ ጸሐፍቶቻቸው የተሰናዱ ከ2ሺህ 226 በላይ፤ ኢትዮጵያን ብቻ በተመለከተ ከ226 በላይ መጻሕፍት በማሳተም አሰራጭተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን የሥራው 80 በመቶ የሚሠራው በአረቢኛ ቋንቋ ሲሆን ዓላማውም የዓረቡን ዓለም ስለኢትዮጵያ የተንሸዋረረ እይታ እንዲኖረው ለማድረግ ነው።
ከእነዚህ ጸሐፊዎቻቸው መካከል መሐመድ አብዱራህማን የሚባለው ግብፃዊ “የኢትዮጵያ ጥያቄ” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃው መጽሐፍ አንዱ ሲሆን፣ የሚያነሳውም የኢትዮጵያና የግብፅ ንትርክ አዲስ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው መሆኑንና በሂደቱም ኢትዮጵያ አሸናፊም ተሸናፊም ሆና እንደነበር፤ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ግብፅን ታስተዳድር ሁሉ እንደ ነበር፤ ሲያስተዳድር የነበረው ንጉሥም ንጉሥ ባንዲ (በ711 አካባቢ) የሚባል እንደሆነ፤ ባስተዳደረባቸውና ወጀል ባህሪ በተባለው አካባቢው ላይ የራሱን ታሪክና ቅርስ ጥሎ እንደሄደ …፤ በኢዛና ዘመን (በ330)ም ኢትዮጵያ ግብፅ ላይ ዘምታ እንደነበር፤ ግብፅን ያስተዳደረው የመጨረሻው የሐበሻ ንጉስም ንጉስ ታሎት አሞ የሚባል ኃይለኛ መሪ የነበረ ሰው መሆኑን የሚያስረዳ ነው።
በወቅቱ ኢትዮጵያውያን እጅግ ጀግኖች ስለ ነበሩ በግብፅና አካባቢው ሀገራት ይፈሩ ነበር፤ ወደ ዓባይም የሄዱት ስልጣኔያቸውን ተከትለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ስልጣኔ የረዥም ጊዜ እድሜ ያለው ነው ሲልም ደራሲው አስፍሯል። እንደዚሁ ደራሲ እምነት ግብፆች ከድሮ ጀምሮ ለኢትዮጵያውያን ጥሩ አመለካከት የላቸውም።
ሌላው ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም የአሁኑ ትውልድ ማወቅ ያለበት አንድ ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር አወለል በድሪ አሊ የሚባሉ እውቅ የግብፅ እንስት ተመራማሪ እኛ (ግብጽ) እና ኢትዮጵያ ከ5ሺህ ዓመት ጀምሮ ፍቅር የለንም። ያለን ግንኙነት የገዥና ተገዥ ነው። ኢትዮጵያውያን ለእኛ ጥሩ አመለካከት የላቸውም። በመሆኑም ነው ወደ ግድብ መገንባቱ ሥራ የገቡት የሚል አቋም ከሚያራምዱት የግብፅ ምሑራን መካከል ፊት መሪ ናቸው። ሌሎችም ተመሳሳይ አመለካከትን የሚያራምዱ ምሑራን መኖራቸውን ኢትዮጵያውያን ሊያውቁት ይገባል። በገዛ ንብረታችን፣ የተፈጥሮ ሀብታችን … መጠቀም እንዳንችል የሚመኙ፣ ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ብዙዎች መሆናቸውን እኛ ኢትዮጵያውያን በውል ልናውቅ ይገባል። አንድ ሆነንም ችግሩን ለመፍታትና ለመቋቋም መትጋት ይኖርብናል።
ወደ ”ዓባይ ማን ነው?” እሚለው ስንሄድ ደግሞ፣ 86 በመቶው ከኢትዮጵያ እንደሚሄድ፣ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን፣ ከ90 ሚሊዮን በላይ ግብፃውያን ሕልውናቸው በዓባይ ላይ የተመሠረተ መሆኑን፤ ግብፃውያንና ሱዳናውያን ዓባይን ከራሳቸው በላይ በደንብ አድርገው የሚያውቁት መሆናቸው፤ ዓባይ ባይኖር ግብፅም ሆነች ሱዳን፤ እንዲሁም ስልጣኔያቸው ሊኖሩ እንደማይችሉ፤ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድም በቁርዓን ውስጥ ”የጀነት ውሃ” ተብሎ የተጠቀሰ መሆኑና በሙስሊሙ ማኅበረሰበም ትልቅ ቦታ እንዳለው መታወቅ አለበት።
ስለ ዓባይም ሆነ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ግብፃውያን በትክክል እውነቱን የፃፉ አሉ። ነገር ግን ግብፆች ኢትዮጵያውያን ለፕሮፖጋንዳ ይጠቀሙበታል በሚል ብቻ ሳያሳትሟቸው በሳጥን ውስጥ አስቀምጠዋቸው ይገኛሉ። እኛ ግን እነዚህን ሥራዎች የመተርጎምም ሆነ የማሳተም መብት ስላለን ማድረግ እንችላለን። ተርጉመን ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ መብታችን ነው።
ለግብፆች ዓባይ ውሃ ብቻ አይደለም፣ በየዓመቱ 110 ሚሊዮን ቶን አፈርም ተሸክሞ ነው የሚሄደው። ግብፆች ይህንን አፈር ቀምመው በመጠቀም በዓመት የሦስት ጊዜ አምራች ለመሆን በቅተዋል። ለውሀና ምግብ እጥረት ለተጋለጠው መካከለኛው ምሥራቅ ኤክስፖርት በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ያገኛሉ። የአሁኑ ስጋታቸው ይህ ሁሉ ይቀርብናል ከሚል የመጣ እንጂ እውነቱ ጠፍቷቸው አይደለም።
ይህ ሁሉ ሆኖ እኛ ተደጋጋሚ ችግርና ረሀብ ባጋጠመን ወቅት አንዲት ዶላር እንኳን የሰጠን የለም።ለዓረቡ ዓለም ከድሮ ጀምሮ በራሱ ቋንቋ ሲቀርብለት የኖረው ኢትዮጵያ የዓረቡ ዓለም ጠላት ተደርጋ ስለሆነ እንደ እውነት የወሰደውና እውቀቱ፣ ንብረቱ ያደረገው ይህንኑ ነበር።
አንድ ኢትዮጵያዊ በአውሮፕላን ወደ’ዛ ሲሄድ እንዴት ቲኬት ቆርጠህ መጣህ፣ ሆቴል ካደረ፣ እንዴት ሆቴል ልታድር ቻልክ … ገንዘብ ከየት አመጣህ፣ ደሀ አይደላችሁም እንዴ? እየተባለ ሁሉ ይጠየቅ ነበር። ይህ እንግዲህ ስለ ኢትዮጵያ ካለማወቅና እኛም በሚፈለገው መልኩ ማስረዳት ስላልቻልን ነው።
የዓረቡ ዓለም ወደ 360 ሚሊዮን ሕዝብ ይደርሳል (አሁን 325 ሚሊዮን ነው) ተብሎ ነው የሚጠበቀው። የእነሱ መሬት ሲቆፈር የሚገኘው ነዳጅ እንጂ ውሃ ባለመሆኑ ይህ ከወዲሁ አሳስቧቸዋል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ትልቁና የሚያሳስባቸው ጉዳይ የውሀ ጉዳይ መሆኑን ነው። በመሆኑም፣ የእኛን፣ የዓባይ የ86 በመቶ ባለመብቶቹን ተጠቃሚነት አሽቀንጥረው በመጣል ”እኔ ብቻ”ን ታቅፈው መኖርን እንደ መርሕ አድርገው ኖረዋል።አሁን አሁን እየተደረጉ ባሉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሁኔታዎች እየተለወጡ ቢመጡም ብዙ መሥራት ግን ይገባል።
የዓረቡ ዓለምም ስጋት የሚመነጨው ከአሁኑ ዘመን ወጪያቸው ሲሆን፣ ያ ማለት የዓረቡ ዓለም የውሀና የምግብ ፍላጎት ይጨምራል ማለት ነው። በአሁኑ ሰዓት እንኳን አጠቃላይ የሰላጤው (ገልፍ) ሀገራት ለ”ፋስት ፉድ” (ብስኩቱ … ምናምኑ) ብቻ በየወሩ 10 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ (ከውጪ ለማስመጣት)። ኩዌቶች በወር 1ሺህ 170 ቢሊዮን ዶላር ወዘተርፈ። የገልፉ ሀገራት ምግብ አምራች አይደሉም። 90 በመቶ ከውጪ ነው የሚያመጡት። በ2050 በዓመት የሚያወጡት ወደ 150 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
ይህ ሁሉ እንግዲህ የሚሸፈነው በእኛ ውሀና አፈር ከሚመረተው ምርት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከጠነከረች የዓረቡን ዓለም በመያዝ የምግብ ዋስትናቸውን በአስተማማኝ መልኩ እንዲረጋገጥ በማድረግ በምትኩ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ትችላለች። በመግቢያው ላይ እንዳሰፈርነው ኢትዮጵያ የምድር ገነት ነችና።
በመሆኑም፣ ግድባችንን ሠርተን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆንነው ሁሉ፣ በሌሎች ሥራዎቻችንም ላይ ተመሳሳይ ትጋትን ማሳየት አለብን። ወዳጅ ጠላቶቻችንን መለየት አለብን። እኛ ከማንም ጋር ፀብ የሌለን መሆኑን መናገርና ማሳየት መቻል አለብን። ከሁሉም ጋር በሰላምና እኩልነት መኖር የምንፈልግ መሆናችንን ሁሉም ሊያውቁት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ላይ ሥራዎችን መሥራት አለብን።
(የዚህን ጽሑፍ ተከታይ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይዘን እንቀርባለን።)
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም