የኢንቨስትመንት ዘርፍ በባህሪው ከየትኛውም ዘርፍ በበለጠ ሰላምን ይፈልጋል፤ ኮሽታ ጭምር ጸሩ ነው። ባለፉት ሁለት አመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የታየው የጸጥታ መደረፍረስ ይህን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጎድቶታል። በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት አማካይነት በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት ታዲያ ይህን የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደሚታደገው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እያመለከቱ ናቸው።
የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ እንደሚሉትም፤ ሰላም ለኢንቨስትመንት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ዋነኛው ነው። ያለ ሰላም ኢንቨስትመንት የማይታሰብ ነው። በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚሉት፤ ባለፉት ሁለት አመታት በሀገሪቱ በተካሄዱ ጦርነቶች ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች አንዱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው። በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶች አንዱ በኢኮኖሚው ላይ የደረሰ ጉዳት ነው። የጦርነቱ ተሳታፊዎች ሁለት ሀገራት ቢሆኑ በሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ነበር ጦርነቱ ጫና የሚያደርስባቸው። የሁለት ሀገራት ኢኮኖሚ ሲሆን ችግሩን ለመቋቋምም የተሻለ አቅም ይኖረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገው ጦርነት ግን መቶ በመቶ ውድመት የደረሰበት የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ መሆኑን አቶ ፍሬዘር ጠቅሰው፣ በጦርነቱ ከደረሱት ሰብዓዊ ጉዳቶች፣ የንብረት ውድመቶች እና ለጦርነቱ ከወጠው ወጪ ባሻገር ሊኖሩ የሚችሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ሀገሪቱ ያጣችበት መሆኑን ያብራራሉ። ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ ድጋፎች ከመቆማቸውም ባሻገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይም የሚኖረው መቀዛቀዝ ቀላል አለመሆኑን ነው የሚገልጹት።
ለኢንቨስትመንት ከሚያስፈልጉ ዋና ዋና ግብዓች አንዱ ሰላም ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፣ ለኢንቨስትመንት ትልቁ ነገር ሰላምና ጸጥታ ነው። ሰላም በሌለበት፤ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተገታበት፣ ብቃት ያለው የሰው ሃይል በማይገኝበት፣ ሃብት በሚዘረፍበትና በማንኛውም አጋጣሚ ሊወድም በሚችልበት ሁኔታ ማንም ሀብቱን ሊያፈስ አይፈልግም ሲሉ ያብራራሉ። ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት እንደማይኖር፣ መንግስት ለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የሚያደርገው አንዱ ምክንያትም ይሄው ነው ይላሉ።
እንደ አቶ ፍሬዘር ማብራሪያ፤ የስራ እድል ፈጠራ፣ አካባቢያዊ ልማት፣ አጠቃላይ የሃገር ገቢ እድገት፣ ወዘተ የኢንቨስትመንት ቀዳሚ ፋይዳዎች ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት ኢንቨስትመንቱ ከመጎዳቱ ባሻገር ሊፈጠሩ የሚችል የስራ እድሎች አልተፈጠሩም። የስራ እድልን የመፍጠር ግብ ለባለሃብቱ ቀዳሚ ባይሆኑም፣ ለሃገርና ህዝብ ግን ቀዳሚ ናቸው። መንግስታት ትርፍ ፈላጊውን ባለሃብት የሚያበረታቱት፣ የኢንቨስትመንት መደላድል የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ የሚጠበቅባቸውም ለዚህ ነው።
ሌላው አስተያየት የሰጡት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣ ሰላምና ኢንቨስትመንት ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። ሰላም የለም ብሎ በሚያስብበት ቦታ ላይ ኢንቨስት ላድርግ ብሎ የሚያስብ ሰውም ሆነ ሀገር የለም በማለት በሰላም እና ኢንቨስትመንት መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት አይነት ጦርነት ባለበት ሀገር ቀርቶ አነስተኛ አካባቢያዊ ኢ መደበኛ ግጭቶች ባሉባቸው ቦታዎች እንኳ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ሊያፈሱ አይፈልጉም። በአሁኑ ወቅት ብዙ ሀገራት እና ብዙ ባለጻጋዎች ኢንቨስትመንታቸውን ለማፍሰስ ከአዋጭነቱ ጥናቱ ጋር አብሮ ከግምት ውስጥ ከሚያስገባቸው ዋና ዋና ነገሮች መካከል የሰላም ጉዳይ አንዱ ነው። ይህም ለሰላም የሚሰጡት ቦታ ከፍ ያለ መሆኑን ያመላክታል።
እንደ ዶክተር ሞላ ማብራሪያ፤ በእርግጥ ሁሉም ዘርፎች ሰላምን ይፈልጋሉ። ኢንቨስትመንት ግን ከሌሎች ዘርፎች ለየት ባለ መልኩ የሰላም እጦት ሲያጋጥም በቀላሉ ሊቋረጥ እና በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል ነው። የሰላም እጦት፣ አለመረጋጋት የሚስታዋል ከሆነ ኢንቨስትመንታቸውን ቶሎ ነው የሚዘጉት። ሌሎች ዘርፎች ሰላም ባይኖር ለተወሰነ ጊዜ ስራ አቋርጠው ዳግም ወደ ስራ ሊገቡ ይችላሉ። የኢንቨሰትመንት ዘርፍ ግን የሰላም እጥረት ይኖራል ብሎ ካሰበ ሌሎች አማራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን ማማተር ይጀምራል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግስትና ህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው የጠቆሙት ሁለቱ የምጣኔ ሀብት ምሁራን፣ በጦርነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲሳተፍ የነበረው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሁን ደግሞ ለኢንቨስትመንቱ ዳግም መነቃቃት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
እንደ መምህር ፍሬዘር ማብራሪያ፤ በቅርቡ በፌዴራል መንግስት እና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢንቨስትመንቱን የበለጠ ለማነቃቃት ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል። የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ከፍተኛ ፋይዳ አለው። የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችም በነጻነት ሀብታቸውን ስራ ላይ እንዲያውሉ ይጋብዛል። በአጠቃላይ በዚህ የሰላም ስምምነት ምክንያት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ አውንታዊ ውጤቶች ይጠበቃሉ።
አቶ ፍሬዘር የሰላም ስምምነቱ ዘላቂ እና አስተማማኝ እንዲሆን መንግስት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በቅርበት ሊሰሩ እንደሚገባም ይመክራሉ። ሰላሙ ቀጣይነት ያለው መሆን ከቻለ የሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተለይም ኢንቨስትመንቱ እንዲያውም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የተሻለ መነቃቃት የማሳየት እድል ይኖረዋል ሲሉም ይጠቁማሉ።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ፍሬዘር ኢንቨስትመንቱ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የተሻለ እንዲነቃቃ የሚያስችል አስተሳሰብ መፈጠሩንም ነው የጠቆሙት። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ተደራራቢ የውጭ ሀገራት ማዕቀቦች እና እቀባዎች በመጣሉ የውጭ ጫናውን ለመቋቋም ኢኮኖሚውን በሀገር ውስጥ አቅም ማቆም አለብን በሚል “ኢትዮጵያ ታመርታለች” የሚል እንቅስቃሴ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ጥሩ ጅምር መታየቱንም ለእዚህ በአብነት ይጠቅሳሉ። ይህ ሁኔታ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ አምራች ዘርፍ በመግባት ኢንቨስት እንዲያደርጉ በር ከፍቷል ይላሉ። ከውጭ ሀገራት ይገቡ የነበሩ ምርቶችም በሀገር ውስጥ መመረት መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ታመርት እንቅስቃሴ ከሰላም ጋር ሲደመር ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ነው የሚሉት።
ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ጉዳይ እንዳለም ምሁሩ ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ታመርታለች በሚል የተጀመረው መነሳሳት ሰላም መጣ፣ የውጭ እርዳታና ብድር ተገኘ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መጣ ተብሎ መቀዛቀዝ የለበትም ነው የሚሉት። ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ከውጭ ሀገራት ለመሳብ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን እነዚህን የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታት እና ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፣ በተጀመረው ግለት የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶችን መደገፍ ከተቻለ ኢኮኖሚው ከሚጠበቀው በላይ ሊያድግ የሚችልበት እድል እንዳለም ያመለክታሉ።
እንደ አቶ ፍሬዘር ማብራሪያ፤ ሰላሙን ሁሉም የጋራ አድርጎ መውሰድ አለበት። በአንድም በሌላም መንገድ ጦርነቱን ሲደግፍ የነበረው በሙሉ ፊቱን ወደ ልማቱ ማዞር ይኖርበታል። ኢንቨስትመንቱ የበለጠ እንዲያገግም መንግስት ሰላሙን ከማረጋጋጥ ባሻገር መሰረተ ልማቶችን መገንባት እና መጠገን ላይ ትኩረት ካደረገ ኢንቨስትመንቱ ወደነበረበት መነቃቃት ይመለሳል።
ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት፤ የሰላም ስምምነቱ ትሩፋቶች ከአሁኑ መታየት ጀምረዋል። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ሊያነቃቃ የሚችል ሁኔታ እየታየ ነው። በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል የሰላም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ በርካታ ፈንድ ሰጪ ድርጅቶች ብድር ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ነው። ይህም በሀገሪቱ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉት ትልቅ ተስፋ ይሰጣል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ የመንግስት ዋነኛው ስራ የማመቻቸት ሚና መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሞላ፣ የተጀመሩትን ሰላምን የማረጋገጥ ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠል የኢንቨስትመንት ከባቢን የበለጠ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ። ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ ነገሮች በቀላሉ ፍሰት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ዶክተር ሞላ እንደሚሉት፤ ኢንቨስትመንት በሌለበት የአንድ ሀገር እድገትና ልማት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ኢንቨስትመንትና እድገት በጣም የተቆራኘ ስለሆነ በኢንቨስትመንት ላይ የመንግስት አካላት፣ ህዝቡ እና ባለሃብቱ ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ አለባቸው።
የኢንቨስትመንት ከባቢው አመቺ ከሆነ ኢንቨስተሮች በቀላሉ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሳሉ፤ ኢንቨስትመንቱ የተረጋገ ይሆናል። ኢንቨስተሮችም መዋዕለ ንዋያቸውን በተረጋገ አካባቢ በማፍሰሳቸው እፎይታ ይሰማቸዋል። በቀጣይም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ብናፈስ የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
በመሆኑም ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት አማራጫቸው አድርገው እንዲያዩ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት። በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማመቻቸትም ያስፈልጋል ነው የሚሉት ዶክተር ሞላ። በአንዳንድ ኢንቨስተሮች ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ የተያዘውን የተዛባ ግንዛቤ ለመቀየር በተግባር ከሚሰራው ስራ ባሻገር ኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስተዋወቅ እና የፕሮሞሽን ስራዎችን በትኩረት መስራት እንደሚገባም ይመክራሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የአቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ከተደረገው የሰላም ስምምነት ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የኢትዮጵያ ‘ዩሮ ቦንድ’ ገዢ ኢንቨስተሮች ቁጥር በአንዴ በዓለም ደረጃ መጨመሩን አስታወቀዋል። ይህ ሀሳብ የሰላም ስምምነቱ ትሩፋቶች ከአሁኑ መታየት ጀምረዋል ሲሉ ዶክተር ሞላ የጠቀሱትን ሀሳብ ያጠናክረዋል። በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን ለመገንባት የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ በተገቢው ከተተገበረ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አክለው ገልጸዋል።
አቶ ዘመዴነህ በተለይ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የኢንቨስተሮች ፍሰትን ለመጨመር ከዓለም ኢንቨስተሮች የተበደረችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ‘ዩሮ ቦንድ’ በጦርነቱ ምክንያት ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ የመሄድ ፍላጎት በማጣታቸው የቦንዱ ዋጋ በዓለም ገበያ በጣም ወርዶ ከነበረበት ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የሰላም እጦቱ በኢንቨስተሮች ፍሰት ላይ ያስከተለው ጥቁር ጠባሳ እንዳለ ሆኖ በኢንቨተሮች ፍሰት ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ መሰለፍ መቻሏንም አቶ ዘመዴነህ አስታውቀዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ምናልባት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ በቢሊዮን ብር የሚቆጠሩ መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን ጠቅሰው፣ በስምምነቱ ምክንያት በብድርና በእርዳታ መልክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ታስቦ የተያዙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦች ሊለቀቁ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ፤ ይህም አካባቢዎቹን መልሶ ከመገንባት በዘለለ ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ሰሞኑን ከአሜሪካ ባለሀብቶች ጋር በተደረገው ውይይት ባለሀብቶቹ የሀገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት ከተመለሰ የአጎዋን ችግር መፍታት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን አቶ ዘመዴነህ ተናግረዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዚህ በፊት የተጀመረውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማሻሻል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች እንደሚሳዩት፣ የፀጥታ መደፍረሱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ይሰሩ የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ አስገብቷቸዋል። የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሰሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድሮ ቆይቷል። በተጨማሪም ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመስራት ተገድደውም ነበር።
በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ካስከተላቸው ችግሮች መካከል የምርት አገልግሎትና አቅርቦት መቋረጥ፣ የምርት ሽያጭ ገቢ መቀነስ፣ የስነ ልቦና ጫናዎችና ሌሎች ቀጥተኛ ችግሮች ይጠቀሳሉ። የጸጥታ መደፍረሱ ካስከተላቸው ቀጥተኛና ፈጣን ጉዳቶች ባሻገር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2014 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከጦርነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ጠቁሟል። በ2014 በጀት አመት ከሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ቢቻልም፣ ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 64 ነጥብ አራት በመቶ ብቻ ነው። አለመረጋጋቱና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጫና በአፈፃፀሙ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
የጸጥታ መደፍረሱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የአሜሪካ መንግሥት ባሳደረው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ከዚህ ነፃ የንግድ እድል ተጠቃሚነቷ መታገዷ ይታወቃል። ይህም ከ2014 በጀት አመት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
በአጠቃላይ ከምሁራኑ መረዳት የሚቻለው የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ ሰላምን ከምንም በላይ አጥብቆ ለሚፈልገው የኢንቨስትመንት ዘርፍ መነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩ የማምረት ስራዎች አንዲጀመሩ፣ ተቀዛቅዘው የነበሩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስራዎች አንዲያንሰራሩ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
መንግስት በፍጥነት ከባለሀበቶች ጋር በመምከር ኢንቨስትመንቱን ይታደጋሉ የሚባሉ እርምጃዎችን መውሰድም ይኖርበታል፤ ባለሀብቶችም ኢንቨስትመንቶቻቸውን በማነቃቃት፣ አዳዲስ ባለሀብቶችም የተፈጠረውን መደላድል በመጠቀም በዘርፉ በመሰማራት ዘርፉ እንዲያንሰራራና እንዲጎለብት መስራት መጀመር ይኖርባቸዋል።
ይህ የሰላም ስምምነት ለዜጎች የተሻለ ህይወት መሰረት የሆነው ኢንቨስትመንት፣ እድገትና ልማት መደላድል ነው። አሁን የሀገሪቱ ገጽታ መቀየር ጀምሯል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/ 2015 ዓ.ም