ኢትዮጵያ ከ5 ነጥብ 8 እስከ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር የሚሆን መሬቷ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ባለፈው ዓመት ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በመስኖ ሊለማ ከሚችለው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታሩ ብቻ ነው በመስኖ እየለማ ያለው። ይህም ማለት በሀገሪቱ ውስጥ በመስኖ ሊለማ ከሚችል መሬት ውስጥ ጥቂቱን ብቻ እያለማች ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
የመስኖ ልማት መሰራት ባለበት ልክ ባለመሰራቱ በርካታ አርሶ አደሮች የዝናብ ወቅትን እየጠበቁ የግብርና ስራቸውን ይሰራሉ። በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ ጊዜ ማምረት የሚችሉ አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ትኩረት ያላገኘ በመሆኑ ምክንያት የዝናብ ውሃ በመጠበቅ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እያመረቱ ነው። ይህም ሀገሪቱ በምግብ ራሷን እንዳትችል ካደረጓት ምክንያቶቹ አንዱ ሊባል ይችላል።
ለበርካታ ዓመታት በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ የግብርና ምርቶችን ከውጭ ሀገራት ስታስገባ ኖራለች። የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ አቅም ማሟላት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ የግብርና ምርቶች ጭምር ከውጭ ሀገራት ስታስገባ ነው የኖረችው። ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር ቆይቷል።
መንግስት ይህንን ሁኔታ ለመቀየር በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የአስር አመት መሪ እቅድ ላይ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱ ለመስኖ ልማት ከፍተኛ በጀት መድባ እየተንቀሳቀሰች ነው። በተለይም በቆላማ አካባቢዎች ለመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል። በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እና የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ ጥረቱ ቀጥሏል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ግንባታቸው ከተጀመሩት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በስልጤ ዞን በዳሎቻ ወረዳ በካሊድ ዲጆ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የካሊድ- ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው። ይህ ፕሮጀክት በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚያብራሩት፤ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ የሚገኘው የካሊድ- ዲጆ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ለግንባታው በወርሃ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም ስምምነት የተደረገ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ነው ግንባታው የተጀመረው። ፕሮጀክቱን የ2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ ግብ ተቀምጦለታል።
ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ አንድ ሺህ 800 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም አለው። ከስድስት ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑት ውቅሮች መካከል የግድቡ ርዝመት 1ሺ828 ነጥብ 25 ሜትር፣ የግድቡ ከፍታ 26 ነጥብ 4 ሜትር ሲሆን ስምንት ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ በመያዝ 1ሺ800 ሄክታር መሬት ያለማል። ግድቡ የሚይዘው ውኃ 64 ሄክታር ላይ ወደ ኋላ እንደሚተኛም ነው ያብራሩት።
ፕሮጀክቱን መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በባለቤትነት እያስገነባው ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ተቋራጭ ደግሞ የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው። የፕሮጀክቱ በአለትና በውስጥ በኩል በሸክላ አፈር እንደሚገነባም አቶ ብዙነህ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ እየተገነባ ያለበት አካባቢ አየር ንብረት እና አፈር ለምርታማነት እጅግ አመቺ ነው፤ በአካባቢው የመስኖ ልማት ስራ ባለመሰራቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከምቹ የአየር ንብረትና ለእርሻ አመቺ ከሆነው አፈር በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል። አርሶ አደሮቹ በአካባቢው ለመስኖ ልማት አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ በዓመት አንድ ጊዜ ነው ሰብሎችን እያመረቱ የሚገኙ ሲሆን፣ በቂ ውሃ ካገኙ ከደጋ ሰብሎች በስተቀር ሁሉንም አይነት አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ሰብል ማምረት ይችላሉ።
በተለይም በአካባቢው በብዛት በምርት የሚታወቀውን በርበሬ በስፋት ለማምረት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ፕሮጀክቱ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና በዘመናዊ ዘዴ በአመት ሁለት ጊዜ እና ከሁለት ጊዜ በላይ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ያስችላል። የቆላ ስንዴ፣ አቮካዶ፣ ፓፓዬ እና ቲማቲምም በአካባቢው በስፋት ሊመረቱ ከሚችሉ ምርቶች መካከል ናቸው። በዚህም የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ያስችላል።
ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ለአሳ እርባታም ሊውል እንደሚችል አቶ ብዙነህ ጠቁመዋል። ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው አሳ እያረቡ ለከተማውም ዓሳ ማቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፤ በዚህ ሁሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር የስራ እድል ይፈጥራል ይላሉ። ከዚያ ባሻገር የሚፈጠረው ሀይቅ አካባቢው የአረንጓዴ እጽዋት እንዲላበስም ያደርጋል። ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ከማገዙ ባሻገር የአካባቢውን ውበት ይጨምራል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ የካሊድ- ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ከወራቤ ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ በመገንባት ላይ ያለ መሆኑም ፕሮጀክቱን በሀገራችን ውስጥ ከተገነቡት እና እየተገነቡ ካሉት ከሌሎች የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ለየት ያደርገዋል። የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ ከከተሞች ቢያንስ የ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገነቡት።
የካሊድ- ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግን ከወራቤ ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ ነው። ከተማው እያደገ ሲሄድ በፕሮጀክቱ እና በከተማው መካከል ያለው ርቀት ከ10 ኪሎ ሜትርም ያጠረ ይሆናል። የመስኖ ፕሮጀክቱ በከተማው አቅራቢያ መገንባት ለከተማው እና አካባቢው በርካታ እድሎችን ይዞ ይመጣል። በመሆኑም ግድቡ ለመዝናኛነት ሊውልም ይችላል። ሪዞርቶችን እና ሆቴሎችን መገንባት ከተቻለ በአካባቢው የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር የሚያስችል ነው።
ከወራቤ ዩኒቨርሲቲም በቅርብ ርቀት ላይ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ለዩኒቨርሲቲው ብዙ ፋይዳ ሊኖረው ይችላል፤ የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ላይ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች ስለሚኖሩ ዩኒቨርሲቲው በነዚያ የዓሳ ዝርያዎች ላይ ምርምር ሊያካሂድ ይችላል። የተለያዩ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች ላይ ጥናት በማድረግ እና ዝርያዎችን በማሻሻል ለማህበረሰቡ እንዲያቀርብ ያስችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠሩን የጠቆሙት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ በ2014 በጀት ዓመት ለአካባቢው ነዋሪዎች ለ85 ወንዶች፣ ለ52 ሴቶች በድምሩ ለ137 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። በቀጣይም ለተጨማሪ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችል አመልክተዋል።
የካሊድ-ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የግድብ እና ተያያዥ ስራዎች እንዲሁም የመስኖ አውታር ግንባታን በ2014 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት የ14 ነጥብ 53 በመቶ አፈጻጸም በ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ ወደ 56 ነጥብ 55በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ፕሮጀክቱ በ2016 ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም፣ በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ፕሮጀክቱ መዘግየት እንደሚታይበት ይጠቁማሉ። ከፕሮጀክቱ ተግዳሮቶች መካከል የካሳ ክፍያ መዘግየት፣ በባለድርሻ አካላት በኩል የሚደረግ እገዛ እና ድጋፍ በቂ ያለመሆን ፣የሥራ ተቋራጭ ድርጅቱ የአቅም ውስንነት፣ የማሽነሪ አቅርቦት አነስተኛ መሆን ተጠቃሽ መሆናቸው ጠቅሰው፣ ተቋራጩ ባሳየው ዝቅተኛ አፈጻጸም ምክንያት ማስጠንቀቂያ እንደተጻፈበትም ያመለከቱት። ተቋራጭ ድርጅቱ አስፈላጊ የሆኑ የግንባታ ማሽነሪዎችን በአፋጣኝ ወደ ፕሮጀክቱ እንዲያስገባ የሥራ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል ይላሉ። የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ካደረገ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ይችላል ብለዋል።
ተቋራጩ አቅሙን ማሻሻል፣ አዳዲስ ማሽነሪዎችን ማስገባት፣ የሰው ሀይል መጨመር ካልቻለ በ2016 መጨረሻ ለማጠናቀቅ አዳጋች እንደሚሆን ጠቅሰው። የማሽነሪዎችን ቁጥር ከጨመረ፣ እና በቂ የሰው ሀይል ካስገባ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ሲሉ ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን፣ ከተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል የካሳ ግመታው በአስቸኳይ ተሰርቶ ገንዘቡ ወደ ወረዳ ተልኮ እንዲከፈል መደረጉ፤ እንዲሁም ከሚመለከታቸው የክልል፣ ዞን እና ወረዳ መስተዳደሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ ለፕሮጀክቱ የሚፈለገው ድጋፍ እና እገዛ እንዲደረግ ግፊት መደረጉ ተጠቃሽ ናቸው ፤ ሆኖም አሁንም ያሉ ክፍተቶችን በትኩረት ለይቶ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በተጀመረበት እለት ንግግር ያደረጉት የዞኑ፣ የወረዳው እና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሀላፊዎች ፤ ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት የህዝብ የልማት ጥያቄ ሆኖ ቆይቶ በጉጉት ሲጠበቅ እንደነበረ ጠቁመው ነበር። ዞኑ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የነበረውን ልምድ እንደ እርሾ በመጠቀም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ቃል ግብቶም ነበር። ግድቡ ለኢኮ ቱሪዝም፣ ለመስኖ ልማት ሁለንተናዊ ፋይዳው የጎላ በመሆን ለግድቡ ስኬት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ከተቋራጩ ተቀራርበው እንደሚሰሩም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቄ ወደ ስራ ለማስገባት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በተፋሰሱ ውስጥ በርካታ ስራዎችን መስራትም ያስፈልጋል። የተፋሰስ እንክብካቤ እና የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ በስፋት መስራት የሚፈጠረው ሀይቅ በደለል እንዳይሞላ አስፈላጊ ተግባር ነው። በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በመተባበር የተፋሰስ እንክብካቤ እና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በስፋት ሊሰሩ ይገባል:: በተለይም የዞኑ እና የወረዳው መዋቅር በዚህ ረገድ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም