ባለፉት ዓመታት መንግስት ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ተከትሎ የፍጥነት መንገዶችን ጨምሮ የተለያዩ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፤ የተገነቡት መሰረተ ልማቶች በየዘርፉ ለተመዘገቡ ለውጦች የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ናቸው።
መሰረተ ልማቶቹ የተለያዩ ፈተናዎችን በማለፍ የተካሄዱ ሲሆን፣ ከፈተናዎቹ አንዱ ደግሞ በዘርፉ ስር ሰዶ የቆየውና ዛሬም አነጋጋሪ የሆነው የቅንጅት አለመኖር ነው። የመሰረተ ልማት ቅንጅት እና ትብብር ጉዳይ ዛሬ የግንባታውን ያህል በቂ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት አይደለም።
የመሰረተ ልማት ግንባታ ቅንጅት አልባ አሰራር በየአካባቢው የሚታይ እና እንደ ሀገር መፍታት ያልተቻለ ችግር መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችም ይመስክራሉ። ግንባታቸው ከተጠናቀቀ ዓመት ያልሞላቸውና ከፍተኛ መዋለ-ንዋይ የፈሰሰባቸው መንገዶችን በመቆፈር የውሃ፣ የቴሌ -ኮም እንዲሁም የመብራት ተቋማት መሰረተ ልማት ለመዘርጋት በሚደረግ ጥረት በርካታ የሀገር ሃብት እየወደመ ነው። ይህ ሥር የሰደደ ችግር የሃገሪቱ አቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ፣ የተጠናቀቁትም ጉዳት እንዲደርስባቸው ሲያደርግ ቆይቷል።
የ2014 ዓ.ም የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሪፖርትም ይህንኑ ጠቁሟል። ሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ አንዱ የመሰረተ ልማት ተቋም የገነባውን ሌላው የማፍረስ፣ የፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ያለመጠናቀቅ አሁንም ቀጥሏል። አመታትን እየተሻገረ እዚህ የደረሰው የተቋማት ተቀናጅቶ የመስራት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈታ ቢመጣም፣ በሚፈለገው መልኩ ተናቦ የመስራት ባህል አሁንም አልዳበረም፤ በዚህ የተነሳም ሃገሪቱ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባትን እንድታጣ አድርጓታል፤ ችግሩ በራሱ ለተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ በመሆን ህብረተሰቡን ለምሬት እየዳረገ ይገኛል።
በቅርቡ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በአዳማ ከተማ በተዘጋጀውና የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈው መድረክ ላይ እንደተገለፀው፤ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ በቅንጅት ማነስ ሳቢያ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተጓተቱ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከተያዘላቸው በጀት በላይ ወጪ እየጠየቁም ናቸው።
በሚኒስቴሩ የሃገራዊ የተቀናጀ መሰረተ ልምት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ተገኝ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተቀናጀ መሰረተ ልማት ሥራችዎችን ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ለማሳደግ ሲባል በመንግስት ከተለዩ ቁልፍ ችግሮች ዋነኛው ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደነበር አስታውሰዋል፤ በተለይም በቅንጅት አሰራር እጦት ምክንያት እየደረሰ ያለውን የወጪና የጊዜ ብክነት፤ የነጠላ ዋጋ ዝግጅት፤ የውጭ ደንበኞች የእርካታ መጠንን ለማወቅና የመሰረተ ልማት የመረጃ ደህንነት እና ስርጭትን ለማሳደግ መሬት የወረዱና ነባራዊ ሁኔታውን በተጨባጭ የሚያመላክቱ ጥናቶች መካሄዳቸውን ይጠቁማሉ።
ከዚህ በመነሳትም ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ያሉ ባለድርሻ ተቋማት በጋራ የሚሰሩበትን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ያመለከቱት ሃላፊው፤ ‹‹በዋናነትም የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የቅንጅት፤ የክትትልና የማስተባበር ስራን ለመስራት በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ ከዲዛይን ጀምሮ በጋራ በቅንጅት እንዲሰራ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል›› ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በየሩብ ዓመቱ የጋራ ዕቅድ አፈጻጸም ለመገምገም በአዲሱ የተቋማት ሪፎርም ምክንያት ለመገምገም አዳጋች ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ እንዲያም ሆኖ ሁለት ጊዜ ማስገምገም ተችሏል። ለነባርና አዲስ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ጋር በመሆን የካሳ፣ የዲዛይንና የወሰን ማስከበር ጉዳያቸው እንዲፈታ ጥረት ተደርጓል። አለመግባባቶቹ ከተፈቱ በኋላም በቀጥታ ወደ ተግባር እንዲገቡ የክትትልና የማስተባበር ስራ ተሰርቷል። ይህም 95 ፕሮጀክቶች በቅንጅት፣ በካሳ ክፍያ፣ በዲዛይን እና በወሰን ማስከበር ዙሪያ የነበሩባቸውን ችግሮች ለማቃለል ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመስክ ምልከታ በማድረግ በ72 ፕሮጀክቶች ላይ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በማከናወን ችግሮቻቸውን ለማቃለል ተችሏል።
ከቅንጅት ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎችን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ከታቀደው አንጻር ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም፣ በበጀት ዓመቱ በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸውን አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀዋል። በሰሜንና በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍሎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ መቀዛቀዙን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ ከዕቅድ አንጻር መፈጸም እንዳልተቻለ ተናግረዋል። በተቋማት ሪፎርም ምክንያት ስራዎች በሚፈለገው ልክ አለመሄዳቸው፤ አስፈፃሚ ተቋማት ለቅንጅት ስራው ትኩረት አለመስጠታቸውና ችግሮች ሲፈጠሩ በጋራ ለመፍታት ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑም ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን ያብራራሉ።
እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አኳያ ሚኒስቴሩ የተለያዩ የድጋፍ ስራዎችን ማከናወኑን የጠቆሙት ሃላፊው ፤ ‹‹የጸጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች የፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ ተደርጓል፤ ሃገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን በሚቀጠሉት ዓመታት ለማዘጋጀት የሚረዳ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ስራና መረጃዎችን የማሰባሰብና የማጠናከር ስራም ተሰርቷል›› ብለዋል።
አቶ ቴዎድሮስ የቅንጅት ችግሩን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊፈቱ የሚችሉ ሁለት ሃገራዊ ስታንዳርዶች ተዘጋጅተው መጽደቃቸውም ይጠቁማሉ። በተለይም አንድ ወጥና ተመሳሳይ የካሳ ክፍያ ስርዓት እንዲኖር የካሳ ክፍያ ቀመር መዘጋጀቱ በዘርፉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ነው ያስረዱት።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫሉቱ ሳኒ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት በሃገር ደረጃ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ትልቅ ትኩረት በመስጠቱ ሀገሪቱ አመርቂ እድገት እያስመዘገበች ነው። ይሁንና በተመሳሳይ መልኩ ለመሰረተ ልማት ሥራ ቅንጅትና ትብብር የግንባታውን ያህል በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ሀገሪቱ ከዘርፉ መጠቀም ባለባት መጠን መጠቀም ሳትችል ቆይታለች።
በተመሳሳይም ባለፈው በጀት ዓመት ለመሰረተ ልማት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረው፣ ተቋማት ተቀናጅተውና ተናበው የመስራት ባህላቸውን አሁንም በሚገባው ልክ ማሳደግ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል። በዚህ የተነሳም በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት። ‹‹ የመሰረተ ልማት ተቋማት አሁንም ተቀናጅተው ባለመሰራታቸው ምክንያት ዘርፉ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍለቂያ መሆኑ ቀጥሏል ›› በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አፅኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ መሰረተ ልማት የአንድ አገር እድገት ወሳኝ ግብዓትና ውጤት ነው። ለዚህም ነው ሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እና የጥገና ስራዎችን እያካሄደች የምትገኘው። ይሁንና በግንባታና ጥገና ወቅት እየታየ ባለው የቅንጅትና መናበብ ጉድለት ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው የሀገር ሃብትና የጊዜ ብክነት ይታይበታል። የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የመሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት የሚታየውን የቅንጅት ክፍተት ማረም ይገባቸዋል። ተቋማቱ በተናበበ መልኩ ወደ ተሻለ አሰራር በመግባት ዘርፉ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ እንዳይሆን በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
እንደ ሚኒስሯ ገለፃ፤ ቅንጅቱን ለማረጋገጥ የሕግ ማዕቀፍ እና መዋቅር የመፍጠር ሥራ የተሰራ ቢሆንም፣ የሚናበብ የተቀናጀ ፕላንና ስታንዳርድ አለመኖር ፣ የመሰረተ ልማት መረጃ አለመደራጀት ፣ የተቋማዊ አቅም ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በህግና አሰራር ስርዓቱ በበቂ ሁኔታ አለመሟላት ሳቢያ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም።
በመሆኑም የመሠረተ ልማት ስራዎችን ለማቀናጀትና ለማስተባበር ሃገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ፣ ወጥ የሆነ የካሳ አሰራር እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባም ወይዘሮ ጫልቱ ያስገነዝባሉ። በተለይም የየአካባቢውን የነጠላ ዋጋ ሰነድ ማዘጋጀት ፣ የመሰረተ ልማት ስራዎች በሚተገበበሩበት ወቅት አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመቀነስ ፣ ኮድና ስታንዳርድ በማዘጋጀትና በመተግበር እንዲሁም የተሟላና የተደራጀ መረጃ ማዕከል እንዲኖር መስራት ይጠበቃልም ሲሉ አስገንዝበዋል።
‹‹ለእድገት አስፈላጊ መሰረተ ልማትና አገልግሎት በተለይ መብራት ሃይል፣ መንገድና ውሃና ፍሳሽ እንዲሁም ትራንስፖርት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ ማስቻል ይገባል›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለዚህም የሁሉንም ሚና በማጎልበትና የፋይናስ አቅርቦት አማራጮችን በማስፋት የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ወሰን ዳይሬክተር አቶ ደረጃ አየለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የመንገድ መሰረተ ልማት በሚከናወንበት ወቅት ፕሮጀክቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው ግለሰቦች አንስቶ በርካታ ባለድርሻ አካላት በመንገድ ወሰን ማስከበር ሥራ ላይ ይሳተፋሉ፤ የየራሳቸው የሆነ ተጽዕኖም ያሳድራሉ። በመሆኑም የመንገድ ወሰን ማስከበር ሥራ በታቀደና በተቀናጀ መንገድ ካልተመራና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ድጋፍ ካላደረጉ በመንገድ ግንባታው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው።
‹‹መንገዱ በቀጥታ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው የህብረተብ ክፍሎች፣ በመንገድ ግንባታው ንብረታቸው ከሚነካ የመሰረተ ልማት ተቋማት፣ ከመንግስት አካላት፣ ወዘተ. ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ በጋራ መሥራት በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል›› በማለት ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሚያስገነባቸው መንገዶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዳይጠናቀቁ ትልቁን ድርሻ ከሚይዙት ተግዳሮቶች መካከል ከመንገድ ወሰን ማስከበር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች ዋነኛዎቹ መሆናቸውን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሪፖርቶችን ጠቅሰው ዳይሬክተሩ ያብራራሉ።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የችግሮቹ ምንጮች በርካታ፣ ውስብሰብ እና ፈርጀ ብዙ ናቸው። ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስት መዋዕለ ንዋይ ወጥቶባቸውና ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያመጣሉ ተብለው የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች፣ የመሰረተ ልማቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ከሚታሰበው ማህበረሰብ ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ላይ በሚገኙ አስፈጻሚ እና ባለድርሻ አካለት የትብብር መንፈስ እና ቅንጅት ማነስ የተነሳ በስፋት ሲቸገሩ ይስተዋላል። ግላዊ ጥቅም ለማግኘት ከሚደረግ ፍላጎት በመነጨ ግንባታዎች በታቀደላቸው አግባብ ሊሰሩ አለመቻላቸው በሀገር ሀብት ላይ እያደረሱ ያለው ጉዳት እየጨመረ መጥቷል።
ሃላፊነትን በሚገባ ተገንዝቦ ከተቋማት ጋር ተናባቦ የመስራቱ ችግር በተለይም በከተማና ወረዳ አስተዳደሮች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ዳይሬክተሩ ያመለክታሉ። ‹‹የከተማና ወረዳ አስዳደሮች ገማች ኮሚቴ የማቋቋም፣ ነጠላ ዋጋ የማዘጋጀት፣ ካሳ የተከፈለባቸውን ንብረቶች የማስነሳት፣ ይዞታ የማረጋገጥ ስልጣን በአዋጅ የተሰጣቸው መሆናቸውንም አስታውቀው፣ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው የመንገድ ወሰን በማስከበር ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
በህብረተሰቡ በኩልም የሚሰራውን የልማት ስራ በባለቤትነት ወስዶ ስራው እንዲከናወን ተባባሪ ያለመሆን ችግር በስፋት እንደሚስተዋል የጠቀሱት አቶ ደረጀ፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም ህብረተሰቡ የመንገድ ግንባታውን በማስተጓጓጎል አሉታዊ ሚና ሲጫወት እንደሚታይ ነው የጠቆሙት። እነዚህ አካላት የሥራ ተቋራጮች ሊመልሷቸው የማይችሏቸውን ልዩ ልዩ ጥያቄዎች እንደሚያቀርቡም ጠቅሰው፣ ምላሽ ሲያጡ ጥያቄቸውን በጉልበት ለማስፈጸም በሚያደርጉት ሙከራ የፕሮጄክቶቹ ግንባታ ሲስተጓጎል ይስተዋላል ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በመንግስት ታቅደው የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም፣ በተለይ በመንገድ ልማት ዘርፍ ክልል ውስጥ ያሉ ንብረቶቻቸውን ለማንሳት እጅግ የተራዘመ ጊዜ ሲወስድባቸው ይታያል፤ በዚህ የተነሳም ንብረቶቻቸው ለመንገድ ግንባታው እንቅፋት ሆነው ይገኛሉ። መንገዶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላም በመንገድ ክልል ወሰን ውስጥ የስልክ መስመር፣ የውሃ ፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመር፣ የመስኖ ውሃ መስመር፣ ወዘተ. ለማሳለፍ መንገዱን የመቆፈር እና መስመር የመዘርጋት ችግር በበጀት ዓመቱ በተደጋጋሚ ከታዩ ችግሮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
በመድረኩ የተሳተፉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፤ በሀገራዊ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዝግጅት ዙሪያ አስፈጻሚ ተቋማት በራሳቸውና በቅንጅት ስራው ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የማድረጉ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። የአካባቢያዊ ነጠላ ዋጋ ስርዓት መዘርጋት፣ ተገቢውን የተደራጀ መረጃ መስጠትና በየደረጃው ያለ አመራር ፕሮጄክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ ቁርጠኝነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
እንደ ታሳታፊዎቹ ገለፃ፤ አስፈጻሚ ተቀማት የመረጃ አያያዝ ስርዓትን የማዘመኑ፤ ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተዘጋጀ ስታንዳርድ እንዲተገበሩ የማድረጉ፣ የተቋማትን የአቅም ውስንነት የመፍታቱ እና ህገ ወጥ ግንባታዎች እንዳይኖሩ የማድረጉ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። በዚሁ ልክም ለማስተር ፕላኑ ተገዢ ያልሆኑና ሃገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉ ባሉ ተቋማት ላይ በየደረጃው ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል።
የመሰረተ ልማት ስራዎች ሲከናወኑ በተለይ አንዱ ግንባታ በሌላው ላይ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት የአገልግሎቶች መቆራረጥ፤ ተጨማሪ የወጪና የጊዜ ብክነት፤ በህብረተሰቡና በትራንስፓርት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ይፈጠራል፤ የአካባቢ ብክለት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁ፤ ይህ ችግር እንዳይከሰት በመሰረተ ልማት ቅንጅት ላይ የሚሰሩ አመራሮች ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደመሆኑ በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በማሳሰብ የዛሬውን የመሰረተ ልማት ጥንቅራችን እንቋጭ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015