በኢትዮጵያ የባለሀብቶችን ትኩረት ከሳቡ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች መካከል አንዷ መሆን የቻለችው ደብረ ብርሃን ከተማ፣ የኢንቨስትመንት ስኬቷ ለሌሎች አካባቢዎችም አርዓያ መሆን እየቻለ መጥቷል። ከተማዋ ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ፣ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት መሆኗ፣ የአካባቢዋ ምቹ የአየር ንብረት እንዲሁም ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለአገልግሎት ዘርፎች ልማት የሚሆን እምቅ አቅም ያላት መሆኑ ደብረ ብርሃን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ካስቻሏት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ለቀጣይ 50 ዓመታት የሚያገለግል መዋቅራዊ የከተማ ፕላን እየተዘጋጀላት መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። በቀጣይ ዓመታትም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዋ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
በከተማዋ በ2014 በጀት አመት ለ300 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ 39 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ ለ310 ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል። እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ሲገቡ ከ35ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ናቸው። በ2015 በጀት አመት ደግሞ ለ350 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት የታቀደ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከ100 ለሚበልጡ ባለሀብቶች ፈቃድ መስጠት ተችሏል።
ደብረ ብርሃን ከዚህ የተሻገረ እቅድም አላት። አሁን ያለውን የኢንቨስትመንት አቅሟን በማሳደግ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እምብርት (Investment Hub) ለመሆን አልማ እየተጋች ነው። ይህን እቅዷን ለማሳካትም በአካባቢው እየተበራከተ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ማገዝና ማበረታት፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አቅሞችን በማስተዋወቅና ምቹ አሰራሮችን በመዘርጋት ተጨማሪ ባለሀብቶችን መሳብ፣ አዳዲስ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ማገዝ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የንግድ፣ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ግብዓቶች መሆናቸውን በመገንዘብ እነዚህን ግብዓቶች ለማሟላት እገዛ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች ነው።
በዚህ መሰረት ከእነዚህ የኢንቨስትመንት አቅም ማሳደጊያ ግብዓቶች መካከል አንዱ ይሆናል የተባለው ‹‹የደብረ ብርሃን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የፋይናንስ ኤክስፖ›› ከጥር አራት እስከ 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ ይካሄዳል። ኤክስፖው ከዚህ ቀደም መሰል የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የፋይናንስ ኤክስፖ ላልተካሄደባት ለደብረ ብርሃን ከተማ አዲስና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ትልቅ ኹነት ነው። ይህም ኢንቨስትመንት ለሰመረላት ደብረ ብርሃን ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላት ይታመናል።
‹‹የደብረ ብርሃን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የፋይናንስ ኤክስፖ›› በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር በማድረግ፣ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰርና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ እንዲነቃቃ ለማድረግ አጋዥ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
መቀዛቀዝና ውደመት የገጠመውን ምጣኔ ሀብት ማነቃቃት፤ ትርፍ አምራቾችና ለማንኛውም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምቹ ለሆኑት የሰሜን ሸዋ ዞን እና አጎራባች አካባቢዎች ከዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ ጋር የተሳሳረ የምጣኔ ሀብት ስርዓት መዘርጋት፤ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ተቋማት የጋራ የትስስር መድረክ መፍጠር፤ የኢንቨስትመንት ቅስቀሳ በማካሄድ የደብረ ብርሃን ሪጂዮፖሊታን ከተማን የኢንቨስትመንት እምብርትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ እንዲሁም የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሏቸውን የኢንቨስትመንት አቅሞች እንዲያስተዋውቁ እድል መፍጠር ማስፈለጉ ኤክስፖውን ለማዘጋጀት መነሻ የሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
በኤክስፖው ላይ ከ800 እስከ አንድ ሺ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች፣ አከፋፋዮችና በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ የምርምርና ፈጠራ ተቋማት፣ የፋይናንስ ድርጅቶች (ባንኮች፣ የብድርና ቁጠባ እንዲሁም የኢንሹራንስ ተቋማት)፣ የወጣት ስራ ፈጣሪ ማኅበራት እና ክልሎች፣ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች በኹነቱ ላይ ይሳተፋሉ። በተሳትፏቸውም አቅሞቻቸውን ያስተዋውቃሉ፤ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ። ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና አምባሳደሮችም እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ኤክስፖው የኢንቨስትመንት አቅምን ከማስተዋቂያነቱና ከልምድ ልውውጥ መድረክነቱ ባሻገር በደብረ ብርሃን የኢንቨስትመንት እድገት ተስፋ፣ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችም ይካሄዱበታል።
‹‹ተጉለት ሚዲያና ፕሮሞሽን››፣ ‹‹ዠማ ፕሮሞሽንና ኹነቶች›› እና ‹‹ናብሊስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ፣ ማርኬቲንግና ኤቨንትስ›› ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር፣ ከአማራ ክልልና ከፌደራል መንግሥት ጋር በትብብር ለሚያዘጋጁት ለዚህ ኹነት፣ ከጥቅምት 15 እስከ ታኅሳሥ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ምዝገባ የሚከናወን ሲሆን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከ10 በላይ ከተሞች ምዝገባው በይፋ እንደተጀመረ ተጠቁሟል።
የኤክስፖው ዓላማዎችና ፋይዳዎች
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሣሁን እምቢአለ፤ ኤክስፖው ደብረ ብርሃንን ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነና የደብረ ብርሃን መልማት ከአማራ ክልል አልፎ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ እድገት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ከግምት ውስጥ ያስገባ ኹነት እንደሆነ ያስረዳሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የፋይናንስ ኤክስፖው የአማራ ክልል በኢንቨስትመንት ልማትና ፕሮሞሽን ተግባራት ረገድ ቀዳሚ ትኩረት በሚፈልጉ ዘርፎች ላይ አተኩሮ የመስራት አቅጣጫዎችን፣ የኢንቨስትመንትን ዓለም አቀፋዊነትና እና ተወዳዳሪነትን እንዲሁም የተቀዛቀዘውን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ማነቃቃትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከናወን ተግባር ነው።
እንደ አቶ ካሳሁን ማብራሪያ፣ በደብረ ብርሃንና አካባቢው እየተበራከተ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ፣ ማገዝና ማበረታታት፤ አዋጭ በሆኑ ዘርፎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ አዳዲስ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች (Youth Entrepreneurs and Start-Ups) ከትልልቅ ኩባንያዎች ጋር ትስስር እንዲኖራቸው እድል መፍጠር፤ የዓለም አቀፍ ንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ተቋማትን የትብብር ማዕቀፍና ትስስር ማጠናከር፤ የደብረ ብርሃንን የኢንቨስትመንት መዳረሻ እምብርትነት ማሳደግ፤ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ዞኖች የኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውን ለኢንቨስተሮች ማስተዋወቅ እንዲችሉ መድረክ መፍጠር የኤክስፖው ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው። በኢንቨስትመንትና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ያተኮረ ኤክስፖ ተዘጋጅቶ የማያውቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣ መድረኩ በዘርፉ አዲስ ልምድ እንዲገኝ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹የአማራ ክልል ዋና ዋና የኢንቨስትመንት የትኩረት ዘርፎችንና አካባቢዎችን በመለየት ዘርፉን ለማሳደግ እንዲሁም ክልሉ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት ለማካካስና የኢንቨስትመንት ተግባራትን ለማነቃቃት እየሰራ ነው›› የሚሉት አቶ ካሣሁን፣ ከኢንቨስትመንት መዳረሻዎች መካከል አንዷ የሆነችውን የደብረ ብርሃን ከተማን የኢንቨስትመንት አቅምና እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ከተማዋ ያገኘችውን የኢንቨስትመንት እድል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ደብረ ብርሃን ለአማራ ክልል ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት አስተዋፅኦ እንድታበረክት እንፈልጋለን ያሉት አቶ ከሳሁን፣ በኢንቨስትመንት የተገኙ ልምዶችን ለማስፋትና ለማጠናከር የሚያግዝ አቅም ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው ኤክስፖው በዚህ መነሻ የተቃኘ መሆኑን ይገልፃሉ።
የደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት በበኩላቸው፣ ኤክስፖው የደብረ ብርሃን ከተማን የኢንቨስትመንት አቅም በማስተዋወቅ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚያግዝ ጠቁመው፣ ኤክስፖው የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ያግዛሉ ተብለው የተለዩ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ እንደሚከናወን ያብራራሉ።
ትልልቅ የካፒታል አቅም ያላቸውንና ብዙ የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉ ባለሀብቶችን መሳብ፣ የአካባቢውን ጥሬ እቃ የሚጠቀሙ አምራቾችንና የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ማበረታታት፣ ኤክስፖርት መር የሆነ የኢንቨስትመንት ስራን ማሳካት፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ ያላቸው ፕሮጀክቶች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ማገዝ እና የስራ እድል ፈጠራን በማሳደግ ድህነትን መቅረፍ የኢንቨስትመንት ዘርፉ የትኩረት አቅጣጫዎችና መመሪያዎች ናቸው ይላሉ። ኤክስፖውም እነዚህን የትኩረት አቅጣጫዎች ታሳቢ በማድረግ የደብረ ብርሃን የኢንቨስትመንት አቅም የሚተዋወቅበትና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ ከተማዋና አካባቢው እንዲመጣ የሚደረግበት መድረክ እንደሚሆን ይጠቁማሉ።
‹‹በኤክስፖው ላይ እንደሚሳተፉ ከሚጠበቁት ኢንቨስተሮች መካከል በማምረቻ፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ሽግግር ያደረጉ ኢንተርፕራይዞች፣ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችና የምርምር ተቋማት ይገኙበታል። ተጨማሪ ባለሀብቶች ወደ አካባቢ እንዲመጡ፣ በተለያዩ ሙያዎች ተመርቀው ወደ ስራ ያልገቡ ወጣቶች ከስራ ፈጣሪዎቹ ልምድ እንዲያገኙ፣ የጥሬ እቃ መገኛዎች ከአምራች ፋብሪካዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያግዙ የልምድ ልውጦችና ውይይቶች ይደረጋሉ›› ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ዝግጅት
ይህን መሰል ትልቅ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የፋይናንስ ኤክስፖ ለማዘጋጀት ሲታሰብ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማትና የቢሮክራሲ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚገባ የታወቀ ነው። ከዚህ አንፃር ደብረ ብርሃን ‹‹ደብረ ብርሃን ኤክስፖ 2023››ን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችሏትን ዝግጅቶች እያደረገች እንደምትገኝ ተገልጿል።
አቶ ካሣሁን፣ ለኤክስፖው እስካሁን ከተደረጉት ዝግጅቶች በተጨማሪ፣ በቀጣይ ጊዜያትም በከተማዋም ሆነ በክልሉ አቅም የሚሟሉ የመሰረተ ልማት እጥረቶችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል። ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ በሚከናወኑ ተግባሮች ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ለዚህ ኤክስፖ እንቅፋት የሚሆኑ የመሰረተ ልማት እጥረቶች አሉ ብለን አናምንም›› በማለት ደብረ ብርሃን ትልቁን ኹነት ለማስተናገድ ያላትን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
አቶ ብርሃን ገብረሕይወትም፣ ኤክስፖውን ለማስተናገድ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ። ‹‹ኤክስፖውን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተን ስንሰራ ቆይተናል። በከተማ ጽዳት፣ በሆቴል አገልግሎትና በሌሎች የመሰረተ ልማቶች ዝግጅቶች ተጨማሪ የመሰረተ ልማት ክፍተቶች በሚታዩባቸው አካባቢዎችና ዘርፎች ያሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል እየተሰራ ነው ሲሉ ያብራራሉ። ‹‹በአጠቃላይ ኤክስፖውን ውጤታማ በሆነ መልኩ በማከናወን ባለሀብቶች ወደ ደብረ ብርሃን እንዲመጡ፣ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆንና ሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ እንዲነቃቃ የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ትልቅ ጥረት ይደረጋል›› በማለት ደብረ ብርሃን ለኤክስፖው እያደረገችው ያለውን ዝግጅት ያስረዳሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015