
በዱር በገደል ተንከራቶ ፣ አጥንቱን ከስክሶ፤ ደሙን አፍስሶና ህይወቱን ሰውቶ ንጹህ አየር እንድንተነፍስ፤ በሰላም ወጥተን እንድንገባ፣ የሀገር ሉዓላዊነት እያስከበረ የሚገኘው ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው።
የመከላከያ ሰራዊቱ የግንባታ አቅጣጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት የሚመጥን፤ በቀጣናው ላለበት ከፍተኛ ኃላፊነት ብቁ የሆነ፣ የሕዝብ አመኔታን የተጎናፀፈ፣ ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎትን የጨበጠ፣ በፈጠረው አስተማማኝ ዝግጁነት ጦርነትን በሩቁ ማስቀረት የሚችል፣ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተገቢውን ሚና የሚጫወት ኃይል የመፍጠርን ራዕይ የሰነቀ ነው። ይህንኑ ራዕዩን እውን እያደረገና በተጨባጭም እያረጋገጠ ይገኛል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብራክ የወጣና ኢትዮጵያን የሚመስል ለሕዝብ ደኅንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የአካልና የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍል ብሔራዊ ኃይል ነው፡፡ ይህ የሕዝብ ልጅ የሆነው ሠራዊታችን ከሕዝቡ ጋር ያለውን ትስስርና አንድነት በማጠናከር የሕዝቡን የባለቤትነት ስሜት ይበልጥ እያጎለበተ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግንባታ ከፍተኛ አቅም ተፈጥሯል፤ ከሩቅ የሚፈራ፣ በብቃቱ የተመሰከረለት ፤ ሳይዋጋ የሚያሸንፍ መከላከያ ሠራዊት ሆኗል። ይህም መከላከያ ሠራዊቱን እንኳን ኢትዮጵያን አፍሪካን ጭምር የሚያኮራ ያደርገዋል።
ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብራክ የተገኘው ሠራዊት ከተቋቋመበት ዓላማ ጎን ለጎን ከበቀለበት ሕዝብ ጎን በመቆም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በተለያየ መልኩም ሲወጣ ቆይቷል። አሁንም እየተወጣ ይገኛል። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ግንባር ቀደም በመሆን፣ የአቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት በመገንባት፣ በእርሻ ወቅት አርሶ አደሩን በአጨዳውና በሰብል ስብሰባ በማገዝ ፤ ሰብል ሊያጠፋ የመጣበትን አንበጣ በማባረር ጭምር የሕዝብ አለኝታ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ አረጋግጧል። የሕዝብ ሃዘን ሃዘኑ፤ የሕዝብ ደስታ ደስታው የሆነው ይሄ ሠራዊት የሕዝብን ችግሮች የራሱ ችግሮች አድርጎ እርሱ እየተራበ ሌላውን እየመገበና እርሱ እየሞተ ሌላውን እያኖረ ኖሯል።
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዓባይ ግድብ በእውቀት፣ በገንዘብ እና በጉልበት ድጋፍ ሲያደርጉ የመከላከያ ሰራዊቱ ግን በበረሀ ላይ ቀን በጸሀይ ሀሩር እየተቃጠለ፤ ሌሊት በውርጭና ቁር እየተጠበሰ ግድቡን ሲጠብቅ ውሎ ያድራል። ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ በላይ ከስድስት እና ሰባት ጊዜ በላይ ደመወዙን በመስጠትና ቦንድ በመግዛትም ጭምር የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን አስመስክሯል።
የመከላከያ ሠራዊቱ በስነምግባሩ አንቱ የተባለ፤ በብቃቱ የተመሰከረለት ጀግና ሠራዊት መሆኑን ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ሀገሮችና የግዳጅ ቀጣናዎች ሁሉ አስመስክሯል። በብቃቱ ፣ በታማኝነቱ ፣ በስነምግባሩ እና በህዝብ አገልጋይነቱ በሰላም አስከባሪነት በተባበሩት መንግስታት ተመራጭ ሆኖ በሰራቸው የሰላም ማስከበር ስራዎች የእውቅና ሽልማት ጭምር ተችሮታል። አሁንም ይሄንኑ ክብሩንና ብቃቱን አስጠብቆ ቀጥሏል።
የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ፤ የሀገራችንን አንድነት ለማስቀጠልና ሀገርን ከመፍረስ አደጋ በመታደግ ሠራዊታችን በተለያዩ ጊዜያት ከውስጥ እና ከውጪ ጠላቶቻችን ጋር ተጋድሎ በማድረግ አኩሪ መስዋእትነት ከፍሏል። አኩሪ ድሎችንም አስመዝግቧል። ለዚህ ታላቅ መስዋዕትነት ዕውቅና መስጠትና በክብር እንዲዘከር ማድረግ ይገባል።
የታሪክ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በ1983 ዓ.ም ጀምሮ እንዲፈርስ ፣ ክብሩና ዝናው ረክሶ እንዲፈረካከስ ተደርጎ መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም። የመከላከያ ሠራዊቱ ቁመናም በአንድ ብሄር አዛዥነትና የበላይነት ላይ የተመሰረተ እንጂ ኅብረ ብሄራዊ አልነበረም። ሀገሪቱ የባህር ኃይልም እንዳይኖራትና ሌላውም የመከላከያ ኃይል ጠንካራ ሆኖ እንዳይቀጥል ተደርጓል። ይሁን እንጂ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የባህር ኃይሉም እንደገና እንዲደራጅ የመከላከያ ሠራዊቱም ኢትዮጵያን በሚመስልና በሚመጥን መልኩ ሆኖ ተደራጅቷል። ይህም በመሆኑ ዛሬ አሸባሪው ትህነግ ሁለት ሶስት ጊዜ ያደረገውን ወረራ በብቃቱ መመከትና መቀልበስ ችሏል።
ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷ በማንም እንደማይሸረፍ በመስዋዕትነት የሚያረጋግጥ ጀግና መከላከያ ሠራዊት ያላት ሀገር ናት። ይህንንም አሸባሪው ትህነግ ከታሪካዊ ጠላቶችና የኢትዮጵያን እድገት ከማይፈልጉ የውጭ ጠላቶች ጋር ሆኖ የተልዕኮ ውጊያ በገጠመበት ወቅት አስመስክሯል።
ቀደም ሲልም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚታወቀውም በዚሁ ጀግንነቱ ነበር። ይሄ ህዝባዊ ሠራዊት አሁንም ለሀገሩ ሉዓላዊነት ህይወቱን ሳይሰስት የሚሰጥ እና የሚያስከብር ሙሉ ብቃትና ዝግጁነት ያለው ነው። ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ ፣ ከሩቅ የሚፈራና የሚከበር ሆኖ በጀግንነቱ ይቀጥላል። ዛሬም አኩሪ ተልዕኮውን በመፈጸም ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ይገኛል። ለዚህ ጀግና ሠራዊት ታላቅ ክብርና ምስጋና ያስፈልገዋል። ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም