
አዲስ አበባ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት የደረሰበት የወልዲያ–አላማጣ የባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ጥገና መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የመስመሩ መጠገን ከዓመት በላይ ኃይል ተቋርጦባቸው የቆዩ የላሊበላና ሰቆጣ ከተሞች እንዲሁም ሌሎች የዋግኸምራ ዞን አካባቢዎች የመብራት ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
ከወልዲያ ዶሮ ግብር ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ በተደረገ ፍተሻ 50 ቦታዎች ላይ የኮንዳክተር ጉዳትና መበጣጠስ መድረሱ ተገልጿል።
አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ቀደም ሲል ከባህርዳር፣ አሸጎዳ እና ኮምቦልቻ ከተዘረጉ መስመሮች ኃይል ያገኝ የነበረ ሲሆን ከባህርዳር–አላማጣ የተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር እስከሚጠገን ከኮምቦልቻ – አላማጣ ያለውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት መሥመር የመጠገን ሥራ ተጀምሯል።
ጥገናው ሲጠናቀቅ ከአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ በ66 ኪሎ ቮልት ኃይል ሲያገኙ የነበሩት የላሊበላ፣ ሰቆጣና ማይጨው መስመሮች ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።
የመሠረተ ልማት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀደም ብሎ መግለጹ ይታወሳል።
አሸባሪው ሕወሓት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በፈፀመው ጥቃት የትግራይና የተወሰኑ የአማራ አካባቢዎች እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አልቻሉም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም